‹‹ያላዩት ሀገር ይናፍቃል›› ሆኖብን የሌሎችን ባህር ማዶ ሀገራት እንናፍቃለን እንጂ ሀገራችን የትም የሌለ የአየር ንብረት፣ውሃ፣ለም መሬት ውብና አስደማሚ የተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ናት። ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው ዜጎች የሚፈልቁባት ሀገር ናት። ያለንን በአግባቡ መጠቀም ሳንችል ድህነትን እንድንኖረው ተገደናል። ስደትን እናማትራለን። ቁጭ ብለን ከሰማይ መና እንዲወርድልን እንጠብቃለን ወይም ደግሞ በአንድ ጊዜ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆንልን እንመኛልን።
ሌሎች የበለፀጉ መስራት ያለባቸውን ሰርተው መክፈል የሚገባቸውን መስዕዋትነት ከፍለው ዛሬ መድረሳቸውን እንዘነጋዋለን። ሁልጊዜ የሚያምረን የምንናፍቀው የውጪ የሚባሉ ማንኛውንም ነገር ነው። የውጪ አልባሳት፣ የውጪ ጫማ፣ የውጪ መዋቢያ፣ የውጪ ቁሳቁስ… ነው ፍላጎታችን። በአጠቃላይ የውጪ ነገር ይማርከናል፤ በዚህ አስተሳሰብ ጥገኛ ሆነናል። በሀገራችን ምንም የተሻለ ነገር ቢኖር የሀገር ውስጥ ምርት መሆኑን ካወቅን የምንሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። በሀገራችን እጅግ ውብ የሆነ የባህል ጥበብ አልባሳት እያለ ተመሳስሎ በሌላ ሀገር በተሰራ አልባሳት ላይ በፍቅር እንወድቃለን።
ሀገር ማሳደጊያ ግብርና ታክስ በሀቅ መክፈል ሲጠበቅብን ገቢ እንሰውራለን። ታክስ እንደብቃለን፤ ሌላም ሌላም ግን ደግሞ ያደገች ሀገር እንድትኖረን እንጠብቃለን። መስራትና ማሰራት በሚጠበቅብን ልክ ኃላፊነታችንን ሳንወጣ ቁጭ ብለን ተስፋ መቁረጥ ላይ እንተክዛለን። ስንቱ አቅም ያለው ጉልበት ያለው በልኩ ቢሰራ እኮ ሀገርም ግለሰብም እንደሚለወጥ ግልጽ ነው። በሀገራችን ለተመረቱ ምርቶች ቅድሚያ ብንሰጥ ራሳችን ገዢ ለባሽ ብንሆን አምራቹም ሰፊውም ሻጩም ይሻሻላሉ። ስራ አጥነት ይቀንሳል። በዚህ መሃል ሀገር ታድጋለች።
በሀገራችን የተመረቱትን ብንጠቀም ከውጪ የሚገባ ምርት ይቀንሳል፤የምርቱም ተፈላጊነት እየጨመረ ጥራቱም እያደገ ሄዶ የኤክስፖርት ገበያውንም እስከመቆጣጠር ይደርሳል። እኛ መቅዳት የሚያስፈልገን አሁን ካለንበት በተሻለ ሊያሳድገን የሚችል ቴክኖሎጂ ብቻ ነው። አጠገባችን ያልደረሱትን ለእድገትና ልማታችን የሚያስፈልጉትን ብቻ ነው ማሰስ ያለብን፤ ጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት ተፈላጊነትን ለመጨመር፤ ከዚያ ባለፈ ግን ሁሌም ባህር ማዶ ናፋቂ ሆነን ነው የምንቀረው።
በየጊዜው ‹‹የሀገርዎን ምርት ይግዙ! በሀገሬ ምርት እኮራለሁ! የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚሉ መልዕክቶችና ቅስቀሳዎች ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት መስጠቱ ገና እንዳልገባን የሚጠቁሙ ናቸው። ያመረትናቸውን አልባሳት እየተጠቀምን አለመሆናችንን የሚያመለክቱ ናቸው። አምራቾቹ ገበያ እያጡ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ከሆነ ደግሞ አምራቹም በአቅሙ ልክ አያመርትም። ሠራተኞችን አይቀጥርም፤ ገቢውም በዚያው ልክ አነስተኛ ነው። አነስተኛ ገቢ አነስተኛ ግብር ከፋይ ነው። ይህ ሁሉንም በአንድ ላይ የሚያዳክም ይሆናል። መሆን ያለበት ግን እንደተረቱ ‹‹ያቀረቡትን ሲበሉለት፤ የወለዱትን ሲስሙለት›› ነው። የቀረበልንን የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም አለብን ራሳችን አርዓያ መሆን አለብን። በሀገር ምርት እንኩራ የሚለውም አምራቹም፣ ባለስልጣኑም፣ ነጋዴውም ሁሉም ለባሽና ሸማች መሆን አለበት። ያን ጊዜ ብዙ ተከታዮች ይፈጠራሉ። ከሀገሬ ምርት ውጪ የሚል ትውልድ ይፈጠራል።
ለሀገር ብልጽግና አንድ ወገን ወይም ከፊሉ አስቦ ሰርቶና አሰርቶ ብቻ የሚጠበቀውን ያክል ለውጥ አይመጣም። የወጪ ንግድ ምርቶችን ማስተዋወቅ የንግዱ ማኅበረሰብም በኃላፊነት በመሥራት ሀገራዊ ግዴታውን ለመወጣት ጥረት ያደርጋል። ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችንና ነጋዴዎችን ማበረታታት ይቀጥላል።
ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት በመግዛትና በመጠቀም ለነገዋ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመት መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥትም በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተጨማሪ የንግድ ዕድሎችን የማመቻቸት፣ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚረዱ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያዎችን የማድረግ እና የንግዱን ዘርፍ ተዋንያኖች አቅም የማሳደግ ሥራ በመስራት ዘርፉን ማጠንከር እንዳለበት ይታመናል። ይህ ሲሆን ዕቅዱ ያሳካል፤ ፍላጎት ይሞላል። ወደ ውጪ ማማተር ቀርቶ በሀገር ውስጥ መስራት፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም፣ የስራ ዕድል መስፋፋት ይጠናከራል።
ሁሉም ለሀገሩ ስለሀገሩ ያስባል። በአየር ንብረት ሳይፈተኑ ሰርተው ሀገራቸውን የቀየሩ የበለጸጉ ሀገራትን ከመመኘት ወጥቶ ተፈጥሮ ፀጋውን በሰጣት ሀገር መለወጥ ይጠነክራል። ከዚያም አለፍ ብሎ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረጉ እያደገ ይሄዳል። ለዚህም ሁሉም አምባሳደር ሆኖ ምርቶችን ያስተዋውቃል። ገበያ ያፈላልጋል። ያኔ በታሰበው ልክ እድገቱም ልማቱም ይመጣል።
ከመንግሥት የሚጠበቀው የአሠራር ማነቆ የሆኑ የፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፎችን በጥናት በመለየት ማሻሻያ በማድረግ ለንግዱ ዘርፍ መዘመንና መጠናከር መስራት ነው፡፡ ቢሮክራሲውን መቀነስ፣ ሙሰኝነትን መዋጋት፣ የገበያ ማዕከላትን አደረጃጀትና ግብይትን ማስፋፋትና ማዘመን፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራችና ሸማቹን ማገናኘት በዘርፉ ለተሰማሩ ሁሉ ከተንዛዛ አሰራር ወጥቶ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው።
የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦችን ስርጭትና ግብይት ሥርዓትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማድረግ፣ ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር እስካሁን ያሉት ጅምር ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ዛሬም ህብረተሰቡን (ሸማቹን) አርክተዋል ማለት ግን አይደለም። በመሆኑም የግብይት ስርዓቱን ማዘመን ያስፈልጋል። በመንግሥትና በግሉ ሴክተር ተሳትፎ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው የውጪ ምርቶች ማሳያ ቋሚ የኢግዚቢሽን ማዕከል እና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።
ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ሥርዓት ተወዳዳሪ ለማድረግ እና የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋፋት መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራም አሳውቋል። የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል። የንግዱ ማኅበረሰብም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሀገርንና ራሳቸውን በመለወጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት አለባቸው። ከንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቀው ራሱን ለዘርፉ ታማኝና ብቁ አድርጎ መገኘት፣ ህጋዊ መንገዶችን መከተል ብቻ ነው። በሀገሩ ምርት የሚኮራ የሀገሩን ምርት የሚፈልገና የሚጠቀም ትውልድ የሚፈጠረውና አሁን ያለው ዜጋ ቅኝቱን ወደ ሀገር ውስጥ ምርቶች የሚያዞረው ሸፍጥ ያልተሞላበት ማራኪና ጥራት ያለው ምርቶችን ስናቀርብ ነው። እዚህ ላይ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም