በግሌ አይደለም በማህበረሰብ፣ በሕዝብ እና በሀገር ስስ ብልት፣ ድክመት፣ ውድቀት፣ ቀውስ፣ ፈተና፣ ክፉ ቀን ፣ አሳር ይቅርና በግለሰብ ችግር፣ ፈተና ፣ መከራ፣ ውድቀት፣ ድክመት ወዘተ ግዳይ ለመጣል፣ ለመጠቀም፣ ለማትረፍ ፣ ነጥብ ለማስቆጠር ፣ ጥሎ ለማለፍ ፣ የግል ጥቅምንና ፍላጎት ለማሳካት የሚደረግን ሰይጣናዊ ስሌት አምርሬ እጠላለሁ ። እቃወማለሁ። አወግዛለሁ። ይህ አደገኛ አባዜ በቀዳማዊ ትህነግ/ኢህአዴግም ሆነ በአንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዝቤያለሁ። ሀገርና ሕዝብ በወረርሽኙ እየተጨነቁና እየተጠበቡ ባሉበት ፤ የዜጎችን ሕይወት ለማትረፍ ሀገርን ከለየለት ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመታደግ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ላይ በተጠመዱበት፤ የአቋራጭ፣ የቆረጣ ፖለቲካ ካርድን መሳብ ከማስተዛዘብ አልፎ በሀፍረት አንገት ያስደፋል።
ራሱን «አብሮነት» ብሎ የሚጠራ ነገር ግን «አብሮነት» ባለፈበት መንገድ ዝር ያላለ በተቃራኒው አብሮነትን ከከፋፋዮችና የደባ ፖለቲካ ጠማቂዎች ጋር ብቅል በመፍጨት ፣ በማበር ፣ በማሴር፣ አብሮነትን በመሸርሸር በመናድ በሚታማ ግለሰብ የሚመራ ስብስብ ስለ አብሮነት አይደለም የመታገል የማውራት የቅስም /ሞራል / ልዕልና እንዴት ሊኖረው ይችላል !? ይህ አልበቃ ብሎት የፌዴራል ሥርዓቱን ለመታደግ የተቀባሁ፣ የተመረጥሁት ፣ ኦርጅናሌው እኔ ብቻ ነኝ በማለት ሊያጃጅለን ይከጅላል ።
በዚያ ሰሞን ፣«የምርጫውን መራዘም እደግፋለሁ» በሚል ሽፋንና ጭምብል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ በስንት ጸሎት ፣ ምልጃ ፣ ሱባኤ ፣ ምህላ ፣ ዋቄ ፈና ፣ ዱዋ ፤ መጀመሪያ በግብፅ ፣ በኮቪድ – 19 ተመስሎ ከ30 ዓመታት የግዞትና የስደት መባዘንና መባተል በኋላ የተገኘን አንድነት «የሽግግር መንግሥት ! ? » በተሰኘ ሽብልቅ ልዩነትን መከፋፈልን ለመጎንቆል፣ ለማስፋት ያልተሳካና የከሸፈ ጥረት አድርጓል ማለት ይቻላል። «የምርጫውን መራዘም እደግፋለሁ ። » በሚል የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ከአንጀት ሳይሆን ካንገት ከመሆኑ ባሻገር አጋጣሚውን ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር ተጠቅሞበታል። እውነት አላማው የምርጫውን መራዘም መደገፍ ቢሆን ኑሮ ስለሽግግር መንግሥትና ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ስለማካሄድ ከመዘባረቅ ይልቅ ወረርሽኙን ስለ መከላከል ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ በነገረን። «አብሮነት » የሚለው ዓይነትን አገር አቀፍ ምክክር ሳይሆን ብሔራዊ የእርቅና እውነት የማፈላለግ ሂደትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምደግፍ መግለፅ እወዳለሁ ።«አብሮነት» የምርጫውን መራዘም «የደገፈው » እንዲህ ባለ ዘወርዋራ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መረዳት ያሻል። «ወረርሽኙን በብቃት መከላከላችንን እርግጠኞች ከሆንን በኋላ ግን በፍጥነት ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሒደት መጀመርና አገራችንን ወደፊት ሊገጥማት ከሚችል ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ መታደግ የምንችልበት ሁኔታ ይመቻች፤ ›› የሚል ሃሳብ በመግለጫው ተንጸባርቋል።
ለመሆኑ ከሁለት ዓመታት በፊትም ሆነ ዛሬ የሀገራችን ፖለቲካዊ ምህዳር፣ ተቋማትና ሀገራዊ አውድ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም አስቻይ ሁኔታዎች አሉ? ጥያቄውስ ተጨባጭ /ፕራግማቲክ/ ነው። ሀገሪቱስ ሽግግር ላይ አይደለችም ? እውቅና ለመንሳት ወይም እኛ ከሌለንበት ሽግግር አይደለም ለማለት ነው ? «አብሮነት» የሽግግር መንግሥትን የፈለገው በቅንነት ነው? ወይስ በአቋራጭ በቆረጣ ሥልጣን ለመያዝ ? በተለይ ይህን ጥያቄ ከአመራሩ የኋላ የተበላሸ ታሪክ ጋር ማንሰላሰል መመርመር እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል።
ካለፈው ሁለት ዓመት በፊት ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች፣’ ተሟጋቾች ‘ ፣ ልሒቃንና ጋዜጠኞች ዋሻ ጮኽ ብለው ከሚሰሙ እና መልሰው መላልሰው ከሚያስተጋቡ ድምጾች እዝነ ህሊናን እረፍት የነሳው፣ አየሩን የተቆጣጠረው «የሽግግር መንግሥት ይቋቋም !» የሚለው ወለፈንዲ ጥያቄ ነበር። እንደ አሁን አብሮነት ለብቻው ሙጭጭ ብሎ ሳይቀርበት ። በእርግጥ ላይ ላዩን ሲመለከቱት ጥያቄው ተገቢ ይመስልና ከሸግግር መንግሥት ዓይነትና ባህሪያት አንጻር በጥሞና ሲመረምሩት ግን የለውጥ ኃይሉ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ባስገባ አግባብ አበክሮ እየመለሰው ሳለ የተነሳ የአርፋጆች ጥያቄ ነው ማለት ይቻላል።
ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የ ‘ቀዳማይ ‘ ኢህአዴግም ሆነ በእሱ ይመራ የነበረው አፋኝ አገዛዝ ትክሻም ሆነ ጀርባ ለማሻገር ዝግጁ አልነበረም ። ይሁንና በእግሩ የተተካውን ‘ ዳግማዊ ‘ ኢህአዴግንም ሆነ የመንግሥቱን አሠራርና አደረጃጀት ለሽግግር ማዘጋጀት ቀዳሚ ተግባር ነበር ። ከሞላ ጎደል ይህ ሥራ በሚፈለገው ፍጥነትና በተገቢው ልክ ባይሆንም እየተከናወነ ይገኛል። በእርገጥ ከሁለት ዓመት በፊት ተፎካካሪዎች፣ አቀንቃኞች እና ልሒቃን የሚጠይቁትን ዓይነት የሽግግር መንግሥት በሀገሪቱ ለመመስረት ተጨባጭ እና አስቻይ ሁኔታዎች አልነበሩም ። በዚህ ላይ ደርዝ ይዞ ለመሟገት ዝግጁ ነኝ።
በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ሽግግር ሲኖር አልያም የቀደመው መንግሥት በርስ በርስ ጦርነት፣ በሕዝባዊ አመፅ፣ በውጭ ወራሪ ኃይል ወይም በመፈንቅለ መንግሥት አልያም በፓርላማ የትምምን ድምፅ motion of no confidence ሲነፈግ ወይም ጥምር መንግሥቱ ሲፈርስ፣ ሲወድቅ አዲስ መንግሥት በምርጫ እስኪቋቋም ጊዜአዊ ፣ የሽግግር መንግሥት ይመሰረታል። ከዚህ አንጻር ከለውጡ በፊት የነበረውን የ ‘ቀዳማይ’ ኢህአዴግ መር መንግሥት በተመለከተ የሚከተሉትን ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። በሕዝባዊ አመፅ ፣ በእርስ በእርስ ግጭት ፣ በውጭ ኃይል ወረራ አልያም በመፈንቅለ መንግሥት ተገልብጦ ወይም ወድቆ ነበር ! ? መልሱ ግልፅ ነው። አልወደቀም ። አልተገለበጠም ። ሆኖም ከለውጡ ቀደም ብለው በነበሩ ተከታታይ ዓመታት በተካሄዱ ሕዝባዊ አመጾችና ይህን ተከትሎ በውስጠ ድርጅት በተፈጠረ ትግል እና ሕዝባዊ ወገንተኝነት በመዳከም ላይ እንደነበር አይካድም ። ስለዚህ ለውጡን ያመጣው የሕዝባዊ አመጹና የውስጠ ድርጅት መተጋገሉ ተመሳሳይ አቋም ላይ መገናኘት convergence መሆኑን ያጤኗል። በእነዚህ ኃይሎች መካከል ያለው ያልተጻፈ ቃል ኪዳን ደግሞ አንዱ ሌላውን አሸንፎ የመውጣት ትግል ሳይሆን በህቡዕም ሆነ በአደባባይ በአምባገነንነት የለዩትን ቡድን በአንድነት በመግፋት ከመንበሩ ገሸሽ ማድረግ ነበር ። ይሄ ታክቲካዊ አጋርነት ከተሳካ በኋላ ቀጣዩ ሂደት ጊዜአዊ፣ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነበር። ሆኖም የደህንነት፣ የፀጥታ ፣ የአስተዳደር፣ ወዘተ . መዋቅሩ ተሸናፊውን ቡድን በታማኝነት እንዲያገለግል ሆኖ ከጅምሩ የተዋቀረ ስለነበር ለአደራ፣ ለሽግግር መንግሥት ምስረታ ዕምነት የሚጣልበትና የሚበቃ አልነበረም። የሽግግር መንግሥት ለማቋቋምም አስቻይና ተጨባጭ ሁኔታዎች አልነበረም። ይሄ ኃይል ከመንግሥት መዋቅር ተገፍቶ እንኳ ምን ያህል እጀ ረጅም እንደሆነ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እስከ እዚች ሰዓት እየታዘብን ነው።
ስለሆነም ተፎካካሪዎችም ሆኑ ሌሎች የሚጠይቁትን የሽግግር መንግሥት ከመመስረት ይልቅ መቅደም የነበረበት በአንጻራዊነት ገለልተኛ የደህንነት ፣ የጸጥታ፣ የመከላከያ ፣ የዳኝነት ፣ የምርጫ ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የሚዲያ ወዘተ. ተቋማትን መመስረት እና ለውጡን ከእነ ወለምታው በሸንበቆ አጅሎ በሁለት እግሩ ማቆም ነበር። ባለፉት ሁለትና ከዚያ በላይ ዓመት የሆነውም ይኸው ነው። ጭፍን ተቃውሞና ጥላቻ እይታችንን ካልጋረደው በስተቀር ይህ ውሳኔ በፍፁም አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የተከወነ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በምንመኘው ፍጥነት፣ ጥራትና ጥልቀት ባይሆንም ማሻሻያውን ተቋማዊ ለማድረግ ፈታኙ ጉዞ ከተጀመረ ውሎ አድሯል። ሽግግሩን ተቋማዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተስፋ ሰጭ ጅምር ሥራዎችም ይበል የሚያስብሉ ናቸው።
አሁን ያለው የሽግግር መንግሥት እና ተፎካካሪዎች« አብሮነት!?» እና ጭፍራቸው የሚጠይቁት የሽግግር መንግሥት የትኛው ላይ እንደሚወድቁ ለመመልከት የሽግግር መንግሥት ዓይነቶችን በስሱ እንመልከት። እንደ የቴላቪቭ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ዮሲ ሼን እና የየል ዩኒቨርሲቲው የስነ ኅብረተሰብና የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር ዋን ጆዜ ሊንዝ አተያይ አራት ዓይነት የሽግግር መንግሥታት አሉ።
1ኛ. ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሽግግር መንግሥቱን ተግባርና ኃላፊነት ተክቶ ሲወስድ ሥልጣን ላይ ያለ የሽግግር መንግሥት ይባላል። አሁን በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የሽግግር ሂደት የዚህ ዓይነት ነው ማለት ይቻላል። ብልፅግና መር የሆነው መንግሥት አሁንም ሥልጣን ላይ ነው። የደህንነት ፣ የፀጥታና ሌላው መንግሥታዊ መዋቅሩ እንዳለ ነው። ሆኖም ይህን መዋቅር ከሞላ ጎደል ገለልተኛ ለማድረግ የሚያግዙ ማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል ። እየተወሰዱም ነው ። የዳኝነት አካሉን ፣ ምርጫ ቦርድን ፣ ሚዲያውንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግም በአሠራርና በአደረጃጀት የታገዙ ለውጦች እየተተገበሩ ይገኛሉ። ከለውጡ በፊት የነበረው አገዛዝ ለጭቆና ለአፈና ይጠቀምባቸው የነበሩ አዋጆች ተሻሽለዋል። በመሻሻል ላይም ናቸው። ተጨማሪ አዳዲስ አዋጆችና ሕጎችም ለመውጣት በሒደት ላይ ይገኛሉ። የሽግግር ሂደቱን የሚያግዙ በርካታ አዋጆችና ውሳኔዎች ፀድቀው ሥራ ላይ ውለዋል።
2ኛ . ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በሕዝባዊ አመፅ ከተወገደ በኋላ ሥልጣን በአስወጋጁ ኃይል ቁጥጥር ስር ሲውል አብዮታዊ የሽግግር መንግሥት በመባል ይታወቃል። ይሄን ዓይነት የሽግግር መንግሥት ሀገራችንን ጨምሮ በአፍሪካ ፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ በብዛት ተቋቁሟል። የጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ )ን እዚህ ላይ ያስታውሷል ።
3ኛ . የሽግግር መንግሥቱ በነባሩ መንግሥትና በለውጥ ፈላጊው ኃይል ጥምረት የሚመሰረት ሲሆን ስሙም የጋራ የሽግግር መንግሥት በመባል ይታወቃል። እዚህ ላይ የጎረቤታችንን የሱዳን የሽግግር መንግሥት በአብነት ማንሳት ይቻላል።
4ኛ . የሽግግር መንግሥቱን ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሲረከብ ዓለምአቀፍ የሽግግር መንግሥት ይሰኛል። ይሄ የሽግግር ዓይነት ፍትሕን ለማስፈንና በቀጣይ የሽግግር መንግሥቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ኃይሎችን ለመለየት የሚያግዝ የሽግግር መንግሥት ነው። ለዚህኛው ዓይነት የሽግግር መንግሥት ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አሜሪካን መራሹ ኃይል የሳዳም ሁሴንን አገዛዝ ከሥልጣን በኃይል ካስወገደ በኋላ በኢራቅ አቋቁሞት የነበረው የሽግግር መንግሥት ነው ።
በጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር ( ደርግ ) የሽግግር መንግሥትም ሆነ ባለፈው የተመሰረተው የሱዳን የሽግግር መንግሥት መካከል ዘመነ ጓዴነቱ / ኮንቴምፓራሪ /እና አውዱ የተለያየ ቢሆንም ሁለቱም የሽግግር መንግሥት ለመመስረት የቻሉት በብሔር ወይም በሌላ ማንነት የተከፋፈለ የደህንነትና የፀጥታ ተቋም ሳይሆነ በአንድነት የሚያምን ኢትዮጵያዊ አልያም ሱዳናዊ ተቋም ያላቸው በመሆኑ ነው። ከለውጡ በፊት የነበረው የሀገራችን የደህንነትም ሆነ የፀጥታ ተቋም ግን በብሔርና በማንነት ከመከፋፈሉ ባሻገር አንድን ቡድን እንዲያገለግል በ1 ለ5 የተጠረነፈ ስለነበር እንኳን ለሽግግር ለአባልና አጋር ድርጅቶች እንኳ የሚታመን አልነበረም ። «አብሮነት » ነጋ ጠባ የሚለፍፈውን የሽግግር ዓይነት በግልፅ ተንትኖ ስላላስቀመጠ ሙግቱን እዚህ ላይ መግታት ግድ ይላል።
እንደ መውጫ
ሀገር ችግር ፈተና ላይ ስትሆን ጠብቆ አድብቶ እንደ ውጪ ጠላት መሣሪያ ደግኖ አግቶ ፖለቲካዊ ሆነ ሌላ ዓላማን ለማሳካት እንደሚደረግ አሳፋሪ ክህደት የለም ። ግብፅ የውስጣዊ አንድነታችን መዳከም ጠብቃ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማስተጓጎል አባይ ወንዝ ላይ ያላትን ብቸኛ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል የሄደችበትን ርቀት ያጤኗል። ይህን መሰል ደባዊ እገታ በራስ ዜጋ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲቃጣና ሲሞከር ማየትም እንደማንኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ ያበግናል። ያማል። ስለሆነሞ ቀደም ብሎ ኦነግና ኦፌኮ ፤ በማስከተል «አብሮነት» የሞከሩት የቆረጣ ፖለቲካ ለእነሱም ከመተዛዘብና ነውራቸውን ገልቦ ከማሳየት ያለፈ ለማንም ስለማይበጅ ሊደገም አይገባም።
በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ እውን ከሆነበት ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን የያዙትም ሆነ በተቃዋሚነት የተጓዙት፤ የምስረታ ሂደትን ፣ የአይዲኦሎጂ ትንተናን ፣ የመንግሥት ሥልጠናንን ፣ ወዘተ በአቋራጭ ፣ በቆረጣ ፣ በኩረጃ ፣ በግብታዊነት ፣ በእብሪት ፣ በማንአህሎኝነት መከወንን የመረጡ ናቸው ። ለዚህ ነው ለሀገርና ለሕዝብ ባበረከቱትም ሆነ በፈጸሙት ጥፋት ላይ መግባባት ያልቻልነው። እነሱም ሞትንልህ፣ ቆምንልህ ባሉት ሕዝብ የተተፉት ። በመጨረሻም እንደ ባቢሎን የተንኮታኮቱት። ለዚህ ነው የቆረጣ ፖለቲካ ለማን በጄና ነው ! ? እርማችንን ማውጣት የተሳነን የምለው፤ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ አደገኛ ወረርሽኝ ይጠብቅ! አሜን ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com