ታላቁ ቤተመንግሥት ሰሞኑን በውቧ ፒኮክ ግርማ ደምቋል፡፡ “ፒኮክ” ተብላ የምትታወቀው የአዕዋፍ ዝርያ መስለ ቅርጽ ታትሞላት በታላቁ ቤተመንግሥት (የጠ/ ሚኒስትር ቢሮ) ደጃፍ ላይ ገዝፋ ተሰይማለች፡፡ ይኸ ምስለ ቅርጽ ለአደባባይ እይታ ከበቃ በኋላ በድጋፍም በነቀፌታም መልክ የሕዝብ መነጋገሪያ አጀንዳ ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ የጠ/ሚኒስትር ቢሮ ፒኮክ ተመርጣ በቤተመንግሥቱ ደጃፍ ምስለ ቅርጽዋ ሊቀመጥ እንደቻለ በዝርዝር የሰጠው መግለጫ በግሌ ባለማግኘቴ ምንም ማለት አልቻልኩም፡፡ ዞሮ ዞሮ በቂ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል መገመት ግን ይቻላል፡፡
ፒኮክ በኢትዮጵያ ክብር ስትቀዳጅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ በስሟ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ፓርክ ተሰይሞላታል፡፡ ቦሌ መስመር ከቦሌ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት በስተግራ ከዋናው መንገድ አንድ ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የተመሠረተው ቅጥር ግቢ ፒኮክ ፓርክ ይባላል፡፡ በውስጡ የሚገኙት የባህር ዛፍ፣ የጽድ ግራቪሊያ፣ ኦሜድላና ኒም ዕፅዋት ዝርያዎችና ከግርጌው የሚፈሰው የቀበና ወንዝ ጥሩ የዓይን ማረፊያዎች ሆነው ኖረዋል፡፡ በአሁን ሰዓት ታድሶ ተጨማሪ ግርማ ሞገስን ለብሷል፡፡
አንዳንዶች ከጥንት ጀምሮ እንደታላቅነት እና የጥንካሬ መገለጫ የሆነው አንበሳ ወደጎን ያሸሸ ውሳኔ ነው በማለት ከወዲሁ የትችት መዓት እያወረዱ ነው፡፡ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ በሚል የንጉሥ ኃይለሥላሴ ዓርማ የቤተመንግሥቱ መለያ ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል:: ሐውልቱም በአዲስ አበባ ለገሐር እና ብሔራዊ ቲያትር አጠገብ ተቀመጦለታል፡፡
የፒኮክ ሐውልት በአሁኑ ወቅት ቤተ መንግሥት ደጃፍ መቀመጥ የአንበሳን መታሰቢያ የማግለል ወይንም ታሪክን የመጠየፍ የሚያደርጉ ይኑሩ እንጂ በተቃራኒው የፒኮክን ታላቅነት በመመስከር በድጋፍ መልክ ሐሳባቸውን የሚሰጡ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡
ከቤተመንግሥቱ ጋር ተያይዞ ታድሶ ለሕዝብ እይታ ክፍት ከተደረገው የአንድነት ፓርክ የመካነ እንስሳት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ይህ የአንድነት መካነ-እንስሳት በውስጡ 37 አጥቢ እንስሳት እና የአዕዋፍት ዝርያዎችን ለመሰብሰብ ታቅዶ የተዘጋጀ መሆኑ መገለፁ የሚታወስ ነው።
መካነ እንስሳቱ ከወራት በፊት ሥራ ሲጀምር ቀጭኔዎች፣ ነጭ አናብስት፣ ተኩላዎች፣ ሰጎኖች፣ ማርካት፣ ሳላዎች፣ የሜዳ አህያዎች፣ የቆላ አጋዘን፣ ውድንቢ፣ የቶራ ፈረሶች እና ሌሎች እንስሳት ወደ መካነ እንስሳቱ ገብተው ለጎብኚዎች ክፍት ሆነዋል፡፡
አቦሸማኔዎች፣ ነጭ አውራሪስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ሌሎች አጥቢ እንስሳት፣ የጦጣ ዝርያዎች እና አእዋፋት ወደ መካነ እንስሳቱ በቀጣይ የሚገቡ መሆኑ መገለፁም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ምናልባት የፒኮክ አእዋፍ ምስለ ቅርጽዋ በቤተመንግሥቱ ደጃፍ ላይ መቀመጡ ካልሆነ በስተቀር እንደሱ ያለ የመካነ እንስሳት ማደሪያ በቤተመንግሥቱ አስቀድሞ የተገነባ መሆኑ ሲታሰብ የፒኮክ መኖርን በተለየ እንድናየው የሚያደርግ አይሆንም፡፡
ለመሆኑ ፒኮክ ማን ናት? ምንድናት?
ባለረጅም ላባው ወፍ በመባል ይታወቃል፡፡ በባህር ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ በርካታ አስገራሚ ፍጥረታት አሉ:: ከነዚህም መካከል አያሌ ዝርያ ያላቸው አዕዋፍ ይጠቀሳሉ::
አንዳንዶቹ አዕዋፍ የተለየ ውበትና ባህሪ ያላቸው ናቸው:: በዛሬው ጽሁፍ ፒኮክ ተብሎ ስለሚጠራው ወፍ መረጃ እንሠጣችኋለን፤ ተከታተሉን:: በተለምዶ ፒኮክ ብለን የምንጠራው ወፍ ቃሉ ወደ አማረኛ ሲመለስ “ጣኦስ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት እናገኘዋለን:: እኔም በዚህ ጽሁፍ ፒኮክ የሚለውን መጠሪያ መርጬ ተጠቅሜያለሁ::
ፒኮክ በዓለማችን በይፋ ከሚታወቁት ወፎች የሚያምርና የሚማርክ ቀለም ያለው ሲሆን መገኛውም በዋናነት በእስያ አህጉር ነው:: ዓይንን በሚስብና እይታን በሚማርክ የተለያዩ ቀለማት ያጌጠው ፒኮክ ፒፎውል / peafowl/ በሚል የጋራ ስያሜ በአብዛኛው የዓለም አካባቢ ይታወቃል:: ደማቅ ላባዎቹን ለማስዋቢያነት በብዛት ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ታሪክ ያስረዳል::
በዓለማችን ሦስት ዓይነት የፒኮክ ዝርያዎች አሉ:: እነርሱም የህንድ፣ የአፍሪካ እና አረንጓዴው ፒኮክ በመባል ይታወቃሉ:: እነዚህ ሦስት ዓይነት ዝርያ ያላቸው የፒኮክ ወፎች በዋናነት በእስያ የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪም በአፍሪካና በአውስትራሊያም ይኖራሉ::
ፒኮክ አብዛኛው በእርሻ ማሳ ውስጥ፣ በጫካዎችና በሞቃታማ ስፍራዎች ውስጥ የሚኖር ሲሆን የተለያዩ እፅዋቶችን እና አጫጭር ቁጥቋጦዎችን ስለሚመገብ በዝናባማ /Rainforest/ አካባቢም አይጠፋም:: ይህ ረጅም እና በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ ላባዎች ባለቤት የሆነው ፒኮክ በዋናነት በህንድ፣በስሪላንካ እና በበርማ በብዛት የሚገኝ ሲሆን በሰዎች መኖሪያ እና በፓርክ ውስጥ በመራባት ጥበቃ ይደረግለታል:: ከዚህም በቀር በእንግሊዝና በጃፓን በጥቂቱ ይገኛል::
ፒኮክ በአመጋገቡ ሁሉን ከሚበሉት /omnivours/ ይመደባል:: ሥጋም ሆነ እፅዋትን እንዳገኘ ግጥም አድርጐ ይበላል:: ጥራጥሬ፣ መካከለኛ መጠን ያላቸውን እባቦች፣ ጉንዳኖች፣ አንበጣዎችና ሌሎች ትናንሽ ነፍሳቶች የፒኮክ ምግቦች ቢሆኑም ጥራጥሬ ግን ተመራጭ ምግቡ ነው::
በአጠቃላይ ፒኮክ የሥጋም ሆነ የእፅዋት ዝርያዎችን አይቶ ማለፍ አያውቅም:: ፒፎውል /peafowl/ የሚለው የፒኮክ መጠሪያ ስም ሁለቱንም ጾታ የሚገልፅ ሲሆን በአብዛኛው ፒኮክ የሚለው መጠሪያ ለወንዱ ብቻ የተሰጠ ነው:: ሴቷ ፒሔን /peahen/ የሚል መጠሪያ እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ::
ቀልብ ሳቢ ተፈጥሮ ካላቸው ወፎች መካከል አንዱ የሆነው ፒኮክ ወንዱ ከአራት እስከ ስድስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን ሴቷ ደግሞ ከሁለት ነጥብ ሰባት እስከ አራት ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት አላት::
የወንዱ ቁመት ከስድስት እስከ ሰባት ጫማ የሚደርስ ሲሆን የሴቷ ደግሞ ከሦስት ነጥብ አምስት ጫማ አይበልጥም:: ጭንቅላቱ፣ አንገቱና ደረቱ አካባቢ የሚያብረቀርቅ ሰማያዊ ዓይነት ቀለም ያለው ፒኮክ የአፉ መንቆር ከአንድ ኢንች አይበልጥም:: በሰማያዊ እና በአረንጓዴ ያሸበረቁ ላባዎች የተመለከታቸውን ዓይኖች ሁሉ መማረክና ማማለል የሚችሉ ናቸው::
የተመልካችን ቀልብ በሚገዙ ህብረ ቀለማት የተዋቀረው ረጅሙ ላባው የጠቅላላ ሰውነቱን 60 በመቶ የሚሸፍን ነው:: የወንዱ ፒኮክ ላባ ከሴቷ የተለየ ረጅምና ውበቱም የተለየ ነው:: የላባዎቹ ቀለሞች እንደ ወፎቹ የተለያዩ ቢሆኑም በአብዛኛው ግን በቀይ፣ በወርቃማና በአረንጓዴ ቀለሞች የተዥጎረጎረ ነው:: የኋላው ረጅሙ ላባ ከ2ዐዐ ያላነሱ ላባዎች ሲኖሩት በየክረምቱ ይገፋቸዋል::
በአጠቃላይ ፒኮክ ቡናማ ቀለም እንዳለው መናገር ቢቻልም በላባዎች ላይ ባሉት አንፀባራቂ ብርሃን ምክንያት ቀለሙን ለይቶ ይሄ ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም::
ፒኮክ በተፈጥሮው ክንፍ ያለውና የሚበር ወፍ ቢሆንም መብረር የሚችለው ግን ለጥቂት ርቀት ብቻ ነው:: ብዙ ርቀት መብረር ባለመቻሉም አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው በመሬት ላይ ነው:: የሚበረውም አድነው ከሚበሉት እንደ ውሻ እና ነብር ያሉ እንስሳትን ለማምለጥ እና በምሽት ወደ ማደሪያው ለመሄድ ሲፈልግ ብቻ ነው:: ከዚህ ውጭ ፒኮክ ከስምንት እስከ አስር ሆነው በጋራ የመሄድ ልምድ አላቸው:: ጐጇቸውን የሚሰሩት በራሳቸው ላባ አማካኝነት ነው::ፒኮክ ለማዳና ማህበራዊ ወፍ ነው ሲሉ አንዳንዶች ይገልፁታል::
ከሰዎች ጋር አይጋጭም:: እሱን ለመጐብኘት ለሚሄዱት ላባውን እና ክንፉን በመዘርጋት አስደሳች ትርዒት ለማሳየት ይሞክራል:: በክልሉ ሌሎች ፒኮኮች ሲመጡ አይወድም፤ አይፈቅድምም በቶሎ የመቆጣት ባህሪ አለው:: ፒኮክ በተፈጥሮው አስራ አንድ የተለያዩ ድምጾችን ማውጣት ይችላል:: አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በማለዳ የመዝሙር ዓይነት ድምፅ ያወጣል:: ረፋድ ላይ የሚያምር ድምፅ ደጋግሞ እያሰማ እንስቷ ፒኮክ እንድትመጣ ይጋብዛታል::
የሚያማምሩ ላባዎቹንም እንስቷን ለማባበልና ለማማለል ይጠቀምበታል:: እየተሸከረከረም ዳንስ ቢጤ በማሳየት ይማርካታል:: በዙሪያዋም እየዘለለ ልቧን ያቀልጠዋል:: አንዴ ከተቀራረቡ በኋላ እንስቷ የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን ላባዎች በመሰብሰብ ጐጆዋን ትሰራለች:: ከሦስት እስከ ስድስት እንቁላሎችን ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ወራቶች ትጥላለች:: እንቁላሎቿንም ታቅፋ በ28 ቀናት ውስጥ በመፈልፈል ለጫጩቶቿ ምግብ በማቅረብ ታሳድጋቸዋለች:: በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዲያ ወንዱ ፒኮክ እሷን ጥሎ ወደ ሌላ እንስት ይሄዳል::
አዲስ የሚፈለፈሉት ፒኮኮች እንደ ወላጆቻቸው መሬት ላይ ብዙ ጊዜ አይታዩም:: በሰዓት እስከ 16 ኪሎ ሜትር መብረርና መሮጥ የሚችሉ ፈጣኖች ናቸው::
የፒኮክ ዕድሜ ጣሪያ በጫካ ውስጥ ከ15 እስከ 2ዐ ዓመት ሲሆን በሰዎች ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት በፓርክ ውስጥ ካደገ እስከ 4ዐ ዓመት መኖር ይችላል::
(በኩር የካቲት 11 ቀን 2011)
ፒኮክ ምንን ሊወክል ይችላል?
ቀደም ሲል በመነሻዬ ላይ እንደጠቀስኩት ፒኮክን ያስቀመጠው አካል ቅርፁ ስለሚወክለው ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር ስለመኖሩ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መረጃ የለውም፡፡ ይኸም ሆኖ ለምን ምስለ ቅርፁ ተመርጦ ተቀመጠ ለሚለው አንዳንድ መላምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አንዱ ጉዳይ ፒኮክ መልከመልካም መሆናቸው፣ ግዙፍነታቸው (እስከ 225 ሴንቲ ሜትር) መድረሳቸው፣ ለሰዎች ያላቸው ቅርበት እና ፍቅር ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ፒኮክ በቡድን የሚኖርና አንድነትን ጋሻ ያደረገ የአእዋፍ ዝርያ መሆኑ ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
እነዚህ ምልክቶች ብቻውን ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስተዋወቁትን የመደመር ፍልስፍና አብነት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ መደመር አንድነት፣ አብሮነትን፣ ትልቅነትን የሚሰብክ ፍልስፍና መሆኑ ፒኮክ በጥሩ ሁኔታ ሊገልፀው የሚችልበት ዕድል ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡
በተቃራኒው አንበሳው በፒኮክ ለምን ተተካ ለሚሉ ወገኖች ተገቢው ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ነገሩን ለጠጥ አድርገውት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ25 በላይ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋት መካከል ፒኮክ አለመኖሩን በማንሳት ጭምር የውጭ አዕዋፍ አገርን በሚወክል ቤተ መንግሥት ደጃፍ ላይ የተቀመጠበት ምክንያት ምንድነው ሲሉም ደጋግመው እየጠየቁ ነው፡፡ የሚመለከታቸው ወገኖች ይህን በቅርቡ ግልጽ ያደርጉታል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012
ፍሬው አበበ