አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሲቢኢ ብር አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ አገልግሎቱ ደንበኞች ከውጭ ሀገር የተላከላቸውን ብር በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት እጅግ ባጠረና በቀለጠፈ መንገድ የሚያገኙበት አዲስ አሰራር መሆኑን አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ ትናንት በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የክፍያ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ቸርነት እንደገለጹት፣ አዲሱ አሰራር በዓለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት የዳበረ ተሞክሮ ካለው ወርልድሬሚት ጋር በመተባበር በሲቢኢ ብር አማካኝነት ከውጭ ሀገር የሚላክ ገንዘብ በተንቀሳቃሽ ስልክ መቀበል የሚያስችል ነው፡፡ አገልግሎቱ ከቅርንጫፍ ባንኮች ርቀው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጭምር ገንዘብ ለማስተላለፍ፣ ክፍያ ለመፈጸምና ሌሎች የወኪል የባንክ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡
የወርልድሬሚት የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ክልል ኃላፊ ሻሮን ኪንያንጁዊ እንደገለጹት፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፍ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት መጀመሩ የአገልግሎት አድማሱንና የገንዘብ መቀበያ መዳረሻዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማስፋት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በ50 አገሮች የሚኖሩ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻቸው አማካይነት የሲቢኢ ብር ደንበኞች ሲሆኑ፤ ከዚህም በላይ ማንኛውም የኢትዮ ቴሌኮም ስልክ ተጠቃሚ ለሆኑ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ካሉበት ሆነው ገንዘብ ማስተላለፍ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ገንዘብ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲላክ ሰዎች የሚስጢር ቁጥራቸውን እየያዙ በቅርንጫፎች በኩል ገንዘባቸውን እንደሚቀበሉ ያስታወሱት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል መኒ ሥራ አስኪጅ አቶ ታፈሰ ወርቅ ንጉሴ በበኩላቸው ይፋ የተደረገው አገልግሎት ስልክ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ከውጭ ሀገር ገንዘብ በሚላክላቸው ጊዜ መረጃው በቀጥታ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንዲደርሳቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ይህ የሲቢኢ ብር አገልግሎት ከሌሎች መደበኛ አገልግሎቶች ለየት የሚያደርገው በዋናነት የክፍያ ስርዓቱ ዲጅታል በሚሆንበት ጊዜ በላኪው በኩል ያለውን ተጨማሪ ወጪ እስከ50 በመቶ ድረስ ይቀንሳል፤ የሥራ ሂደቱንም ያሳጥራል፤ ከውጭ የተላከው ገንዘብ በቀላሉ ወደ አካውንት ይገባል፤ ገንዘብ የተላከለትም ሰው የሚስጢር ቁጥር ማስታወስ አይጠበቅበትም፤ በተጨማሪም የባንኮችንና የወኪሎችን አፈጻጸም የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ እንደመሆናቸው ባንኩ ይህን ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊያግዝ የሚችልበት አንዱ መንገድ ነው፤ ያሉት ሥራአስኪያጁ፤ ሰዎች ከትንንሽ ገንዘብ ማለትም ከ10 እና ከ20 ዶላር ጀምረው በሲቢኢ ብር አማካይነት ከውጭ ሀገራት በቀላሉ መላክ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ አንደኛው የሀብት ማሰባሰቢያ መንገድ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪን በከፍተኛ መጠን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚን ያግዛልም ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
ፍሬህይወት አወቀ