ጥበብ መከሰቻዋ እልፍ ነው፤ መተላለፊያ መንገዷም እንዲሁ ብዙ ነው። የአገራችን የኪነ ጥበብ ጉዞ በሥነ ጽሁፍና በሙዚቃ ዘውጎች ዘለግ ያለ ዓመታትን ያሳላፈ ቢሆንም የእድሜውን ያህል እያደገና እየጎለመሰ የሚሄድ አይመስልም። ለዚህ ማሳያው ቀደም ባሉት ዘመናት የቀረቡትን የሙዚቃና የሥነጽሁፍ ሥራዎች ዘመን የማሽራቸው መሆናቸው ነው። አሁንም ድረስ ለአብነት የምንጠቅሳቸው ሥራዎች የሚያስረሱና የሚያስንቁ ፈጠራዎችን ለማየት እምብዛም አልታደልንም።
በተለይም ቀደም ባሉት ዘመናት በዓላት በመጡ ቁጥር በየቴአትር ቤቶቹ የሚደረጉት ዝግጅቶች ከፍተኛ የፉክክር መንፈስን የተላበሱ ነበሩ። ለጥበባዊ ፋይዳ ቅድሚያ የሰጡና ታዳሚዎቻቸውን የሚመጥኑና በእጅጉ ያከበሩም ነበሩ። ባሉት ከአንድ እጅ ጣት በማይበልጡት ቴአትር ቤቶች የሚቀርቡት የመዝናኛ ዝግጅቶች፤ በአንድ ለእናቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚቀርቡት የበዓል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ዘመን ተሻግረው ዛሬም ድረስ በአብነት የሚጠቀሱ እንደነበሩ ለመናገር ጥናት ማቅረብ አያስገድድም። ወደ ኋላ መለስ ብሎ የተሰሩትን ዘመን አይሽሬ የበዓል ሥራዎች ማስታወስ በቂ ነው።
የአገራችን የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል እንደወትሮው አልነበረም። ዓለማችን ብሎም ሀገራችንን በጭንቀት የወጠራት የኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስን ተከትሎ የሀዘን ጥላ ያጠላበት ነበር። ግብይቱም ሆነ ሥርዓተ ጸሎቱ እንዲሁም ባህላዊ ክዋኔው የተገደበ በመሆኑ ለምእመኑም ይሁን ለሁሉም ማህበረሰብ ብዙ የጎደሉ ነገሮች እንደነበሩበት ድባቡ በራሱ ያሳብቅ ነበር።
በዓልን በዓል ከሚያሰኙት በርካታ ጉዳዮች መካከል በየቴሌቪዥን መስኮቱ የሚቀርቡት የመዝናኛ ዝግጅቶች ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ይታመናል። ቀደም ባሉት ጥቂት መንግሥት ተኮር የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለበዓል የሚቀረቡ ሥራዎች ዘመን ተሻግረው ዛሬም ድረስ ለአብነት የሚጠቀሱት የመዝናኛ ዝግጅቶች እንዳሳዩን አንክድም።
አሁን የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በጣም በዝተዋል። ቴክኖሎጅውም እጅግ በጣም ተራቋል። በፍጥነት መረጃዎቹን ከሚያሰራጩት የማህበራዊ ሚዲያዎች ባለፈ በርካታ የግል የቴሌቪዥንና የራዲዮ ጣቢያዎች በዓልን ለማድመቅና መረጃዎችን በፍጥነት ለማቅረብ፤ አዝናኝና ቁምነገር አዘል ፕሮግራሞችን በርትተው በመሥራት ላይ መሆናቸው እሰየው የሚያሰኝ ነው። ይሁን እንጂ የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረውን መቀዛቀዝ ለመቀነስ በርካታ የቴሌቪዥኝ ጣቢያዎች ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የሚፈለገውን ያህል ተሳክቶላቸዋል ለማለት አያስደፍርም።
ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ዝግጅቶ ከማሳቅ ይልቅ የሚያሳቅቁ፤ ከማስተማር ይልቅ የሚያማርሩ፤ መሰለቸትን የሚያባብሱ፤ ረብ የለሽ በመሆናቸው ከአንዱ ጣቢያ ወደሌላው ቢቀያየርም ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ›› ሆነው አልፈዋል።
የሚገርመው ነገር አንድን ኮሜዲ በሦስት የተለያዩ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ለማየት የተገደድንበት ጊዜ ነበር። ካለኮሜዲያን ማዝናናትና ቁምነገር ማስተላለፍ አይቻልም የተባለ ይመስል በአንድ ቀን በሦስት ፕሮግራሞች ላይ የተከሰቱት ተመሳሳ ኮሜዲያን መመረጣቸው እንዴት? አሰኝቶናል።
ችግሩ ኮሜዲያኑ መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን የሚያቀርቡት የይዘት ተመሳስሎ ነገሩን የፈጠራ ንጥፈት የጎላበት በመሆኑ አሰልች አድርጎታል። የቀረቡት ዝግጅቶች የፈጠራ ንጥፈት የታባቸው መካሪና አማካሪ የሌላቸው፤ ሃላፊነት የማይሰማቸው፤ ባዶ ጩኸት የበዛባቸው ነበሩ ለማለት ያስደፍራል። ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ስፖንሰር የተደረጉት እንኳን በአሳፋሪ ሁኔታ ወርደው መታየታቸው ነው። ኮሜዲያኑ ‹‹የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ›› እንዲሉ ለህፃናት በሚያዝናኑበት እውቀታቸው አዋቂን ሊያዝናኑ ማሰባቸው በራሱ የእውቀታቸውን ልክ የሚያመላክት ነበር። ሌላው የሚያሳዝነው ጉዳይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለሚቀርቡት ፕሮግራሞች አለመጨነቃቸውም ጭምር ነው። አብዛኛዎቹ የበዓል ሥራዎች ተመልካችን ከመናቅ የመነጩ በመሆናቸው ብዙዎቻችንን አሳዝነውናል። ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ማለፉ ተገቢ አይደልምና ይብቃችሁ! ሊባሉ ይገባል። ለዚህም ነው ሳምንቱን ሙሉ የማህበራዊ ሚዲያ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆነው የሰነበቱት።
በፕሮግራም አዘጋጆቹ የሚቀርቡ ቃለመጠይቆችም የማስታወቂያ አዋጁን የጣሱ ወፍራም ማስታወቂያዎች ነበሩ። አንድ ስፖንሰር ያደረገን መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ እያንቆለጳጰሱ ስለድርጅቱ መልካም ገጽታ ሳይሆን ስለግለሰቡ ብቃት ቃለምልልስ መሥራት ለድርጅቱና ለማስታወቂያ ነጋሪው ካልሆነ በቀር ለተመልካች የሚኖረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ድርጅቱ በከፈለው ገንዘብ ግለሰብን ማስተዋወቅ ምን ያህል ሙያዊ ስነምግባርን የጣሰ መሆኑን ለመረዳት ብዙ ማንበብን ሚጠይቅ አልነበረም።
የሙያ ስነምግባርም ሆነ የማስታወቂያ አዋጁም አይደግፈውም። የግድ ቃለምልልሱ አስፈላጊ ነው ከተባለም አዝናኝ የሚባሉ የአጠያየቅ ስልቶችን በመከተል ስለግለሰቡ ሳይሆን ስለድርጅቱ እንዲወራ የሚደረግባቸው ቴክኒኮች ነበሩ። ምክንያቱን የበዓል እንግዳ ሳይሆን ስፖንሰር አድራጊ በመሆኑ። ለነገሩ በዘመናችን የቃለምልልስ ቴክኒኮችም ሆኑ የሙያ ስነምግባሮች ተጥሰው ማንም እድሉን ያገኘ ሁሉ እየተነሳ የሚከውነው በመሆኑ ስለጥራትና ብቃት ለማውራት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ። ይህን ክፍተት የሚፈጥሩት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት የሚዲያ ሃላፊዎችና አርታኢያን ትልቁን ተጠያቂነት ሊወስዱ እንደሚገባ አምናለሁ።
በአንፃሩም ደግሞ ጋዜጠኞች የተዋኒያን ቦታ ወስደው ተዋኝ የሆኑባቸው ስራዎችንም አስተውለናል። መተወናቸው ባልከፋ፤ ስለመተወናቸው እንጂ ስለብቃታቸው ያልተጨነቁ መሆናቸው ነው ክፋቱ፤ ሁለገብነትና ሁሉ ሙሉነት መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ተስጥኦ ወይም መክሊት የሚባል ነገር እንዳለ ማስታወስ ይገባል። ማይክ የጨበጠ ሁሉ ጋዜጠኛና ዘፋኝ ሊሆን እንደማይችለው ሁሉ ጋዜጠኞቹም መድረኩን ስላገኙ ብቻ ተዋናይ ሊሆኑ እንደማይችሉ ማወቅ ነበረባቸው። መተወን ከተፈለገም መሰልጠንና ብቃትን ማደበር ይገባል። አሁን አሁን የምናየው ግን ያልሆኑትን መሆንን ወይም ያለመክሊት መንገታገት ፋሽን የሆነ ይመስላል። በመሆኑም ነው ብዙዎች ካለመክሊታቸው ወይም ካለችሎታቸው ወይም መገኘት በማይገባቸው ቦታዎች በሚገኘታቸውና በአጉል ድፍረታቸውና በማን አለብኝነታቸው ነው ለትዝብት የተዳረጉት።
ብዙ የምናደንቃቸው ጋዜጠኞች ሙያቸውን አክብረውና ለሙያው ስነምግባር ተገዝተው በጋዜጠኝነታቸው ብቻ አንቱታን እንዳተረፉ ኖረዋል። በአንፃሩም በብቃታቸው የተመሰገኑ ተዋንያን የጋዜጠኝነት ማይክ ሳይጨብጡ በመድረክ ብቃታቸው ብቻ ተወደውና እንደተደነቁ ኖረዋል። አሁን ግን የምናየው ነገር በሁሉ ቦታ ያለብቃትና ያለችሎታ መገሰጥን ነው። በተለይም ጋዜጠኝነት ሙያ መሆኑ የቀረ እስኪመስል ደረስ ማይክ የጨበጠ ሁሉ ጋዜጠኛ ነኝ የሚልበትን ሆኗል። በተለይ በዓል በመጣ ቁጥር በሌላ ሙያ ያሉ ሁሉ ጋዜጠኛ ሆነው ማይክ የሚጨብጡበት አጋጣሚ የተለመደ ነው።
ወደ የዘመነ ኮሮናው የትንሣኤ በዓል የመዝናኛ ፕሮግራሞቹ እንመለስ። በዘንድሮው ፋሲካ አብዝተን ከታዘብናቸው ጉዳዮች የፈጠራ ንጥፈትን ነው። ብዙዎቹ ሥራዎች አዲስነት የሌላቸው፤ የምናውቃቸው ኮሜዲያን በድጋሜ የምናውቀውን ጉዳይ እንዲነግሩን በማድረጋቸው የፈጠራ ንጥፈትና የተመልካች ንቀት እንደተጠናወታቸው ያስተዋልንበት ነው።
በዘንድሮው ፋሲካ አዳዲስና በፈጠራ የታሹና የበለፀጉ ሥራዎችን ለማየት አልታደልንም። የቴሌቪዥን ባለቤቶች ወይም የሚዲያ ሃላፊዎች ብቃት ትዝብት ላይ የወደቀበት ነበር። ምክንያቱም የሚዲያ ሃላፊዎች ለሚቀርብላቸው ፕሮፖዛሎች እንደመስፈርት የሚያቀርቡት ‹‹እነማን ታዋቂ ሰዎች አሉበት›› እንጂ እነማን አዋቂ ሰዎች ይሳተፋሉ? የሚል አለመሆኑ አዝናኝና አስተማሪ ሥራዎችን እንዳናይ ያደረገን ይመስላል።
በእርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለው ለበዓል ቀርበው ካሳቀቁንና ካሳፈሩን ፕሮግራሞች የበለጠ ወይም የተሻለ ፕሮጀክት ሳይቀርብላቸው ቀርቶ እንዳልሆነ ይታሰባል። እስኪ እራሳቸውን ለመታዘብ ከፈለጉ የማርኬቲንግ ክፍሎች ሎከራቸውን ከፍተው ይፈትሹት። በእውቀት እና በሙያ ስነምግባር ላይ የተመሠረቱ ትላልቅ ሃሳብ ያላቸው ሥራዎችን አያጡም። ችግሩ ያለው አርታኢዎቹም ሆኑ ፕሮጀክቶችን የመፍቀድ ስልጣን ያላቸው የሥራ ሃላፊዎች በትውውቅና በጥቅም ትስስር የሚሰሩ መሆናቸው ነው።
በትውውቅ የሚሰሩ የበዓል ፕሮግራሞች ትልቁ ችግራቸው ታዋቂነትን እንጂ ለእውቀት ቦታ አለመስጠጣቸው ነው። ፕሮጀክት ገምጋሚ የሚባሉት ባለሙያዎችም በቴሌቪዥን ጣቢያቸው ላይ ስለሚፈጥረው ተቀባይነት ሳይሆን ተሞዳሙደው ስለሚቀበሉት ጉርሻ ማሰባቸው ነው።
አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ የሚቀርቡላቸውን ፕሮፖዛሎች በጥልቀት ሳያዩ በታተመበት ወረቀት ውበት አለፍ ሲልም በርዕሱ ወይም በእነማን እንደሚሰራ ካዩ በኋላ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ አድርገው ወደ ቅርጫታቸው ይወረውሩታል። ሳምንት ሳይሆነው የጣሉትን ሃሳብ እየቀነጫጨቡ የራሳቸው ሀሳብ እንደሆነ አድርገው ይሰሩታል። ለዚህም ነው አንድን ፕሮፖዛል ሙሉ በሙሉ በኮሚቴ ገምግመው ጥንካሬና ድክመቱን በግብረመልስ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑት።
ሌላው ለበዓል መዝናኛ ዝግጅቶች ለዛ ማጣት በምክንያትነት የሚጠቀሰው የስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ናቸው። በመሰረቱ ስፖንሰር ማድረግም ሆነ በትብብር ለመስራት የሚቅርቡላቸውን ፕሮፖዛሎች በሚገባ መገምገመና በግልጽ መስፈርት አወዳድረው መምራት ይገባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የግል ድርጅቶች በጥቂት ደላሎች የተያዙ በመሆናቸው የተለመዱና አዲስነት የሌላቸው መሆናቸው የማይቀር ሆኗል። የድርጅቶቹ የገበያ ልማት ሠራተኞችም በአዋጭነትና በመሰል ጉዳዮች መዝነው ሳይሆን በሃላፊዎችና በደላሎቹ በሚያቀርቡላቸው ጥቅማ ጥቅም ተጠምዝዘው የሚወሰኑ መሆናቸው ነው። ደላሎችም የሚያገኙትን ዳጎስ ያለ ገንዘብ እያሰቡ ከአዋቂዎቹ ይልቅ ወደ ጥቅም ተጋሪያቸው ታዋቂዎቹ ፊታቸውን ማዞራቸው የተለመደው አሰራራቸው ነው።
የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከፍተኛ የሚባል ማህበራዊ ሃላፊነት ሊሰማቸው እንደሚገባ ይታመናል። በተለይም በበዓል ወቅት የሚተላለፍ ከሆነ ከቤተሰብ በጋራ የሚታዩ በመሆናቸው ሁሉንም የሚያማክሉና ከማሳቅ ባለፈ ቁምነገር የሚያስተላልፉ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ከሌሎች ቻናሎች በልጦ ለመገኘትም የተሻለ ነገር ማቅረብና በይዘቶቻቸው ላይ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም በውስጥ አቅም ሊሰሩ የማይችሉ ፕሮግራሞች መመረጥ ያለባቸው ቢያንስ በውስጥ ጋዜጠኞች መሰራት የማይችሉና እነርሱ ከሚሰሩት በእጅጉ የተሻሉ መሆን ይኖርባቸዋል።
አንድን ታዋቂ ሰው ለአንድ ሰዓት አስቀምጦ ቃለምልልስ ለማድረግ ከሆነ የውስጥ አቅም በቂ መሆኑ አይካድም። ሙያዊ ድጋፍ የሌለው ከስነምግባር ያፈነገጡ፤ የማህበረሰቡን አስተሳሰብ የማይመጥኑ፤ ከዓመት በፊት የቀረፁትን ዘጋቢ ፊልም እድሉን ስላገኙት ብቻ እንዲጠቀሙ መፍቀድም ተመልካችን ከመናቅ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው አይችልም። በውጭ አቅም የሚሰሩት ጊዜ ወስደው ተጨንቀውና ተጠበው ብቃታቸውን በይዘት፣ በምስልና በድምጽ ጥራት እንዲሁም በኤዲቲንግ የተሻሉ ሆነው እንደሚቀርቡ ይታመናል። ይሁን እንጂ በዘመነ ኮሮናው የፋሲካ በዓል እጅግ በጣም የወረዱና የሚያሳፍሩ ሥራዎችን ለማየታቸው ዋናዎቹ ተጠያቂዎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሃላፊዎች መሆን ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ በዘንድሮው የኳራንቲን ፋሲካ በዓል ብዙ ታዝበናል። የቴሌቪዥን ቻናሎቻችን ሁሉ ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ›› ሆነው አሳቀውን አልፈዋል። ኮሮና ቫይረስን እንደመልካም አጋጣሚ የተጠቀሙበት አርቲስቶችም ብዙ ነበሩ። አርቲስት የሚለው ቅጽል መጠሪያ የሚሰጠው ለጥበበኛ የሚሰጥ እንደሆነ አይካድም። ጥበብ ደግሞ ባህሪዋ ፈጠራና አዲስነትን ትፈልጋለች። በአንድ ሙያተኛ የተገለፀውን ሀሳብ አርቲስት ወይም ጥበበኛ በተለየ መንገድ አስውቦና አዕምሮ ውስጥ እንዲቀመጥ አድርጎ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።
የኮሮና ቫይረስ የሚተላለፍባቸውን መንገዶች ሐኪሙ በገለፀው መንገድ የሚያስተላልፍ ከሆነ እርሱ በቀቀን እንጂ ጥበበኛ ሊባል አያስችልምና በጥበበኛ ስም የምትጠሩ ሁሉ እባካችሁ የጥብብን ክብር አታርክሱ ማለት መልካም ይሆናል። በጉዳዩ ላይ ያሉት ሀሳቦች ብዙ አነጋጋሪ ናቸው፤ ሀሳቡን ሳልቋጭ በእንጥልጥል ለሳምንት ላሻግረው ወደድኩ። የሳምንት ሰው ይበለን! መልካም ቅዳሜ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
ዳንኤል ወልደኪዳን