መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ ሰሞነኛውን ስቅለትና ትንሳኤን ታሳቢ በማድረግ ” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። ” የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል። ጨለማ ፣ የምድር መናወጥ፣ ክረምት ፣ ሰደድ እሳት ፣ በረዶ ፣ ጎርፍ ፣ መገፋት ፣ መዋረድ ፣ መገረፍ ፣ መቸንከር ፣ መካድ ፣ መሸጥ ፣ መሰቀል ፣ ወዘተረፈ አርብ ቢሆንም ፤ መንጋቱ ፣ ብርሃን በጨለማ ላይ መንገሱ ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ ፣ መከበሩ ፣ መፈወሱ ፣ ትንሳኤ ፣ ቀን መውጣቱ ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ ፣ ወዘተረፈ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ከችግር ፣ ከድህነት ፣ ከተመፅዋችነት ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከፈተና ፣ ከወረርሽኝ ፣ ከጭቆና ፣ ከአፈና ፣ ከጥላቻ ፣ ወዘተረፈ ነጻ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት ፤ ትንሳኤያችንን ፣ ህዳሴያችንን የምናይበት ቀን ይመጣል። እሁድ ይመጣል። ” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል። ” እያልን በእምነት በተስፋ እንጠባበቃለን። ደግሞም ይሆናል።
ከአምስት ዓመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና እክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ ቤት ለመዋል ፣ ተሽከርካሪ ወንበር(ዊልቼር )፣ አጓጓዥ / ወከር /ና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር ። ለመልበስ ፣ ለማውለቅ ፣ ውሃ ለመጠጣት፣ ለመመገብ ፣ ለመታጠብ ፣ ለመተኛት ፣ ለመነሳት የሰው እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር ። ስልክ ለማነጋገር ፣ ቻናል ለመቀየር እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር ። ሁሉ ነገሬ በሰው እርዳታ ላይ የተመሰረተ ነበር ። መላ ህይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር ። ስራዬን አጣሁ ። በጋዜጠኝነትና ኮሙንኬሽን ከአአዩ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ። ህልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ ። በመጨረሻ ለጭንቀትና ለድባቴ ተዳርጌ ነበር ።
ዓርብ ነበርና !
እንዲህ አይነት ብዙ የሕማማት ” ዓርቦችን ” በህይወቴ እንዳሳለፍሁት ሁሉ እናንተም ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በህይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን ፣ ህማማትን፣ አርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም። በግል ህይወታችሁ፣ በትምህርታችሁ ፣ በፍቅራችሁ ፣ በትዳራችሁ ፣ በንግዳችሁ ፣ በሕልማችሁ ፣ በራእያችሁ፣ በድርጅታችሁ፣ በሃይማኖታችሁ ፣ በጤናችሁ ፣ በቤተሰባችሁ ፣ በማህበረሰባችሁ ፣ በሕዝባችሁ ፣ በሀገራችሁ ፣ ወዘተረፈ ላይ አርብ ሆኖባችሁ / ጨልሞባችሁ / እንደ እየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ ፣ ተገምድሎባችሁ ፣ ታስራችሁ ፣ ተገርፋችሁ ፣ ተሰቅላችሁ ፣ ተቸንክራችሁ፣ ተዋርዳችሁ ፣ ተፈትናችሁ ፣ ባመናችሁት ተክድታችሁ፣ በባልንጀራችሁ በ ’33’ ብር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ ፣ ቀን ጨልሞባችሁ ፣ ወዘተረፈ ይሆናል ። ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ይሆናል ።
ዓርብ ነውና !
ካለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳ ብንወስድ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ሺህ አርቦችን ፣ በድርቅ ፣ በርሃብ ፣ በቸነፈር ፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 67ቱ በርሃብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት ፣ እንደ …77 … 87 … ወዘተርፈ ያሉ ጠኔዎችን ፣ ችጋሮችን አሳልፈናል። ዛሬም ከዚህ አዙሪት ሰብረን መውጣት አልቻልንም። እንደ ህዳር በሽታ ፣ ፈንጣጣ ፣ ከ76 ወዲህ ደግሞ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ፣ ካለፉት 40 ቀናት ወዲህ ደግሞ ኮቪድ – 19 የእልቂት ጥላውን አጥልቶብናል ። በግብፅ ፣ በደርቡሽ ፣ በቱርክ ፣ በእንግሊዝ ፣ በጣሊያን ፣ በሶማሊያ ፣ በኤርትራ ተወረናል ። ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎሹምብን አልጠፉም ። በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች አልፈናል። ከዘመነ መሳፍንት እንኳ ብንጀምር በመሳፍንቱ ፣ በመኳንንቱ ፣ በነገስታቱ መካከል ለስልጣን፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የእርስ በእርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል ። አጼ ቴዎድሮስ ፣ አጼ ዩሐንስ ፣ አጼ ምኒልክ ፣ ልጅ እያሱ ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግስቱ ጉዳቱ፣ ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በእርስ በእርስ ግጭት ፣ ጦርነት ተፈትነዋል ።
የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !
ባለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በተቀነቀነ የማንነት ፖለቲካ የተነሳ በሀገራችን ጥላቻ ፣ ቂም ፣ በቀል ፣ ልዩነት ተጎንቁሏል። ጎሳን ፣ ሃይማኖትን ፣ አይዶሎጂን መሰረት አድርገን ተጋጭተናል። ተጋለናል ። አብያተ ክርስቲያናትን፣ መስጊዶችን አቃጥለናል ። ቀይ ፣ ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል ። እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን እሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ጠይቀናቸዋል። የዚችን ሀገር ታሪክ እስከወዳኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ ጨርሰናል። በርስ በርስ ጦርነት በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠር ዜጋ አጥተናል። የሀገር ሀብት ወድሟል። ሀገር አጥተናል። ዛሬ ድረስ ከዚህ ሀንጎቨር አልወጣንም ።
የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !
በተለይ በቀዳማዊ ትህነግ /ኢህአዴ 27 ዓመታት በፖለቲካ አመለካከታችን ፣ በጎሳችን በጅምላ ተገርፈናል። ተገልብጠናል። ተሰቃይተናል። ተግዘናል። ተሰደናል። ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ፣ የመናገር ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ ፣ የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል። በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል። በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል። ተረግጠናል። ተገፍተናል። ሀብታችንን ሀገራችን በቀን በአደባባይ ተዘርፈናል። ሀገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች። የድሀ ጉሮሮ ታንቆ ፣ በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ ፣ በቅንጦት ፣ በደስታ ፣ በፍሰሐ ተንደላቀዋል ።
አርብ ነበርና !
ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ዴሞክራሲን ነጻነትን መሸከም ተስኖን ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋትን እንደ እኩይ አጋጣሚ ተጠቅመን ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል ፣ ገለናል ፣ ከእነ ህይወታቸው በእሳት አቃጥለናል። ወደ ገደል ጥለናል። ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ህጻን ብላቴና ብልት ሰልበናል። እህቶቻችንን ደፍረናል። ዛሬ ድረስ አግተናል ። በሕዝብ ፣ በክልልና በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀሰቀስና ሀገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል። ለፍፈናል።
አርብ ነበርና!
ለእሁድ መዳረሻ ፣ ለትንሳኤ ፣ ለንስህ ፣ ለጥሞና፣ ለአንድነት ፣ ለፍቅር ፣ ለሰላም ለይቅርታና ለሕዳሴ መጀመሪያ በግብፅ አንድ አደረገን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም አስቻለን ። ካለፉት 40 ቀናት ወዲህ ደግሞ ወደ ሰውነታችን ፣ ወደ ቀደመው ማንነታችን እንድንሸበለል ያለ ልዩነት የሰው ልጅንና ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ ቫይረስ ሰደደብን። ኮሮናቫይረስን። ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን ምርጫ ተክትሎ አንዣቦ ከነበረ የስጋት ፣ የግጭት ፣ የብጥብጥ ፣ የቀውስና የደባ ዳመና በመለኮታዊ ኃይሉ ታደገን።
የእሁድ አጥቢያ ነውና !
ዛሬ በኮሮናቫይረስ የተነሳ የሰው ልጅና የዓለም ህልውና ላይ አደጋ ተደቅኗል። ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል። ተገለባብጧል። ፍርሀት ፣ ጭንቀት ፣ ሞት በሰማዩ ረቧል። ሞት እንደ ጥላችን ይከተለን ጀምሯል። ከምንወዳቸው ተለይተናል። በየቤታችን ከተናል። በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤያችን ተቀይሯል። ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ከመስጊድ ደጆች ተባረናል። ከስራ ታቅበናል። ተገድበናል ። የእለት ጉርሳቸውን በእየለቱ እየሰሩ የሚያገኙ ወገኖች ለችግር ተዳርገዋል። ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርሲቲዎች በወረርሽኙ የተነሳ በራቸውን በመዝጋታቸው ተማሪዎች ቤት ለመዋል ተገደዋል። የሀገርና የሕዝብ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተጎዳ ነው። ከሕዳር በሽታ ፣ ከኩፍኝና ከፈንጣጣ ፣ ከፖሊዎ፣ 1ኛውና 2ኛው የዓለም ጦርነቶች በአንድ ላይ ተደምረው፣ ከ9/11 የሽብር ጥቃት በላይ የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈትን ወረርሽኝ ዙሪያችንን ከቦናል። አስደንብሮናል።
ዓርብ ነውና !
“ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። ” እያልሁ እጽናና ተስፋ አደርግ ነበር ። ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን ፣ የማይነጋ ፣ ዙሪያው ገደል ፣ ተራራ ፣ ተስፋ ቢስ ቢመስልም ፤ ነገ ቀን ይወጣል ፣ ይነጋል ፣ ደልዳላ ይሆናል እሁድ ይመጣል እያልሁ እጽናና ነበር ። እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም ። ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ። በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ ። የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች እገዛና ማበረታት በነጻነት ጀምሬያለሁ ። ተስፋዬ ለምልሟል ። በዋሻው መውጫ ብርሃን እየታየኝ ነው። ያቋረጥሁትን ትምህርቴን አጠናቅቄ ሶስተኛ ዲግሪዬን እሰራለሁ። በዚች ሀገር የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬ ላይ እንዲህ ህልመኛ የሆንሁት አርብ አልፎ እሁድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው። ከስቅላቱ በኋላ ትንሳኤው እንደሚመጣ በማመኔ ነው ።
እሁድ ይመጣል !
እየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደባት ፣ ከተተፋባት ፣ ከተገረፈባት ፣ ከተቸነከረባት ፣ እንደ ወንበዴ ፣ ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍ ፣ ነቀፋ ሳይገኝበት ፣ ሞት የተፈረደበት፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለባት ፣ ጎኑ ከተወጋባት በኋላ” አርብ ” እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም ። የጨለማ ፣ የስቃይ ፣ የመከራ ፣ የፈተና፣ የውርደት ፣ የግፍ ፣ የበደል ፣ የመገፈፍ ፣ የራቁትነት የመሰቀል ወዘተርፈ ተምሳሌት ጭምር እንጂ ። ኤልደር ” ዛሬ አርብ ነው ” ያሉት ይሄን መሰሉን ቀን ፣ ዓመት ፣ ዘመን ነው ፡፡
ዛሬ አርብ ነውና ፤
ሆኖም መግነዙን ፈቶ ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ፣ ሞትን ድል አድርጎ ፣ በብኩርና በሶስተኛው ቀን በድል ተነስቷል። አርጓል። በደሙ ዘላለማዊ ድህነትን፣ በግርፋቱ ህያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል። ሀጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል። ከኦሪታዊ ሕግ ፣ ከባርነት ፣ ከሀጢያት ነጻ አውጥቶናል ።
እሁድ መጥቷልና !
ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ ፣ ሕዝብና ሀገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ ፣ ፈተና ፣ መከራ ፣ ቸነፈር ፣ ውርደት ፣ ግርፋት ፣ መቸንከር ፣ ደም መፍሰስ ፣ ስጋ መቆረስ ፣ ጀርባ መተልተል ፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት፣ ጎን መወጋት ፣ የሾህ አክሊል መድፋት ፣ ወዘተረፈ አልፈዋል ። እልፍ አእላፍ አርቦችን አሳልፈዋል። ዳሩ ግን የትንሳኤው እሁድ ይመጣል ።
እሁድ ይመጣልና !
ከእዚህ ክፉ ወረርሽኝ ፣ ከፖለቲካ ስብራት ፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነት ፣ ከደባ ፖለቲካ ፣ ከድህነት ፣ ከእርዛት፣ ከርሃብ ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከልዩነት ፣ ወዘተረፈ ወይም ከአርብ ወጥተን ፤ የሀኪሞችን ምክር ፣ የመንግስትን ማሳሰቢያ በመተግበር አርብን አልፈን እሁድን እናያለን። የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን አርብን አልፈን ለእሁድ እንበቃለን ። የብልፅግና ትልማችንን ለማሳካት ሌት ተቀን በመትጋት ፣ ሙስናን ፣ ብልሹ አሰራርን ፣ ስንፍናን ፣ ዳተኝነትነት በማስወገድ አርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን ። እሁድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። ልዩነትን ፣ ጥላቻን ፣ ጎሰኝነትን ፣ የታሪክ እስረኝነትን ፣ የሴራ ፖለቲካን ወይም ብዙ አርቦችን በጽናት በብርታት አልፈን ለትንሳኤና ለህዳሴ / ለእሁድ እንበቃለን። ደግሞም እናምናለን ይሆናል።
” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ! “
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com