ዓለምን እያሸበረ ያለው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ በይፋ ከተነገረበት ቀን ጀምሮ በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት ባለስልጣናት አስቸጋሪ ጉዳይ ካልገጠመ በቀር ህዝቡ እቤቱ እንዲቀመጥ ሲነገር ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ አንዳንድ የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞቻቸውን በተለይ ለጤና ችግር ይጋለጣሉ ብለው ያሰቧቸውን የዓመት ፈቃድ ሰጥተው እቤት እንዲውሉ አድርገዋል። የተለገሰው ምክር በተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም ዛሬም ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በዘወትር እንቅስቃሴው ተጠምዶ ይታያል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ምንም እንኳ ከቤት ለመውጣት በቂ ምክንያት ባይኖራቸውም እንኳን መጨረሻው ላልለየለት ጊዜ ይቅርና ለአንድ ቀንም እቤት መዋል ተራራ የመግፋት ያህል አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ለመሆኑ እንዲህ ሳናስበው እቤት ዋሉ መባላችንን እንዴት ልንቀበለው እንችላለን? እቤታችንስ ስንውል ከቤተሰባችን ጋር የሚኖረንን ግንኙነት እንዴት ማድረግ ይጠበቅብናል? ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት ቤት መምህር የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ትእግስት ውሂብን አነጋግረን ተከታዩን ምክረ ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ቤት ውስጥ መዋል ሲባል ለሁሉም ሰው አንድ አይነት ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ሰው የየራሱ ፍላጎት እንዳለው ሁሉ ለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውም የራሱ ምላሽ ይኖረዋል። ለምሳሌ በሀገራችን በገጠርም ሆነ በከተማ እንደ ባህል ሆኖ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ጊዜ እቤት ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ በቤት ወስጥ ያሉ ስራዎችንም ለመስራት ልጆችንም ለመንከባከብ ቀዳሚዎቹ ሃላፊዎች ሴቶች ናቸው። በዚህም የተነሳ ለአብዛኛዎቹ ቤት ሲውሉ ለነበሩ ሴቶች ክስተቱ አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ በአንጻሩ ሚስት ወይንም ባል አልያም ሌላ የቤተሰብ አባል ገቢ ማስገኘት ስላለባቸው ውጪ በተለያዩ የገቢ ስራ ማስገኛዎች ላይ ያሳልፏቸው የነበሩ ጊዜዎችን አቁመው እቤት ዋሉ ሲባሉ ግን በክፉም ሆነ በደግ የሚፈጠርባቸው አዲስ ስሜት ይኖራል። ይህንንም ተከትሎ ከሌላው የቤተሰብ አባል ጋር በእቤት የምናሳልፈውን ግዜ እንዴት ሊሆን ይገባል የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም።
በአንድ ወገን ቤተሰብ እቤት ወስጥ የሚያሳልፈው ጊዜ መጨመሩ እስካሁን በስራ ብዛት ጊዜ ሳይሰጣጡ የቆዩ ጥንዶች ከነበሩ ፍቅር እንዲሰጣጡ አንዱ አንዱን እንዲንከባከብ፤ ብሎም ስለትዳራቸው፣ ስለቤታቸው ጊዜ ሰጥተው ተነጋግረው የማያውቁ ከሆነ በእርጋታ እንዲወያዩ እድል ይሰጣል። ይህ ግን ለሁሉም ይሰራል ማለት አይደለም፡፡ በቤት መዋሉ በጎ ብቻ ሳይሆን ሌላ ያልታሰበ ነገርም ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ በገንዘብ አጠቃቀም በኩል በአንድ ወገን አባካኝነት ከነበረ ሌሎች የተደበቁ አመሎችም ከነበሩ ይፋ መውጣታቸውና ጭቅጭቅ መፍጠራቸው አይቀርም። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም አብረው ረዥም ጊዜ አሳልፈው ካልነበረ በባህሪ አለመረዳዳት የሚፈጠር ተጽእኖም ይኖራል። እንዲህ አይነት ችግር በቅርቡ ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የእስያ አገራት እቤት በመዋላቸው ፍቺ እየጨመረ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል። ጉዳዩም አሳሳቢ በመሆኑ የሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚኒስትሮች ደረጃ ጨምሮ ችግሩን ለመቅረፍ ሴቶች ዘነጥ እንዲሉ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስተያየት ሲሰጡ ሲመክሩም ነበር። በዛ ደረጃም ባይሆን በእኛም ሀገር ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶች ስለሚኖሩ ይህን ጊዜ እንዴት እናሳልፈው ምን እናድርግ ብሎ በግልጽ መነጋገር ከባለትዳሮች ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ምንም ስራ ሳይሰሩ እቤት ውስጥ የሚቀመጡም ከሆነ ጊዜውም አይገፋም፡፡ በተጨማሪም ለተለያዩ ድብርቶችም የሚጋለጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። አንዳንድ እንደ መጽሀፍ ማንበብና ፊልም የማየት ልምድ ቢኖራቸውም ለረጅም ጊዜ እነዚህን ማድረግ አሰልቺ መሆኑ አይቀርም። በመሆኑም በተለይ ወንዶች እቤት ሲውሉ ከዚህ ቀደም ሰርተዋቸው የማያውቁት፤ ነገር ግን ሊሰሯቸው የሚችሉ ምግብ ማብሰል ልብስ ማጠብና ቤት ማጽዳት የመሳሰሉ ስራዎች ላይ በድፍረት መሳተፍ መቻል አለባቸው። ይሄ በራሱ ለቀጣይ ህይወትም መተሳሰብን የሚያስተምር፤ ሴቶች የተሸከሙትን ሃላፊነት ለመረዳትም እድሉን የሚሰጥ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢሮ ለሚውሉ ሴቶችም በተመሳሳይ ስራ ቢሳተፉ የቤት ሰራተኞችን ድካማቸውን ችግርም ካለባቸው ችግሩን ለመረዳት፤ እንዲሁም ሞግዚቶችንም ከልጆች ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ምን ያህል አድካሚና አስልቺ መሆኑን ለመገንዘብ እድሉን ስለሚሰጣቸው እነዛን ሰዎችም እንዲረዱ፤ ቤታቸውም ያለበትን ሁኔታ እንዲገመግሙ በር ይከፍትላቸዋል። በልጆች በኩልም እስካሁን ባልና ሚስቶቹ ጊዜያቸውን በስራ የሚያሳልፉ ከሆነና ስራ ውለው ማታ ገበተው የሚተኙ ከነበሩ አሁን የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ልጆቻቸውን በቅርበት ለመከታተል የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው።
ከዚህ ባለፈም ወቅቱ የፈጠራቸውን ሁኔታዎች ተከትሎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ መታሰብ አለበት። ከነዚህም መካከል እንደ ፌስቡክና ትዊተር ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች አለያም መደበኛውን ሚዲያ ለረጅም ሰአት የሚከታተል የቤተሰብ አካል ካለ በአንድ ቤት ውስጥ ቢሰባሰብም በአካል አንድ ላይ ሆነው ልብ ለልብ ግን ሳይገናኙ የሚያሳልፉበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ይህም በሌላው ወገን የሚጠበቅ የመጫወት የመነጋገር ሃሳብ ከነበረ አለመግባበትን፤ ከቤት ለመውጣት መፈለግ፤ መሰለቻቸትን ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ከባልም ከሚስትም ስህተት ኖሮ ሳይሆን መግባባት ባለመቻላቸው ብቻ ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ወቅት ችግሩን አሳሳቢ የሚያደርገው እንደሌላው ጊዜ ለጓደኛ፤ ለቤተሰብ ለማማከር አልያም የእምነት ቦታ ሄዶ ጸሎት ለማድረግና የእምነት አባቶችን ለማማከርም እድሉ ጠባብ በመሆኑ ነው። በመሆኑም አለመቀራረቡ በፊትም የነበረ ይሁን አዲስ የመጣ በትእግስት አንዳቸው ለአንዳቸው ሃሳብ ቅድሚያ በመስጠትና እየተደማመጡ በመወያየት ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መፍታት እንኳን ባይቻል ለመቀነስ መሞከር አለባቸው። ይህም ካልተቻለ ሌላ ጭቅጭቅ ንዝንዝ እንዳይፈጠር ራሳቸውን በተለያዩ ስራዎች መጥመድም ያስፈልግ ይሆናል። የባሰ ነገር ከመጣና እቤት በመዋላቸው የተፈጠረ ችግርም ካለ በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሄ ባይሆንም ለጊዜው ዞር ብሎ ሌላ ዘመድ አዝማድ ጋር ማሳለፍንም እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ ይቻላል።
በቤተሰብ ውስጥ በዚህ ወቅት የልጆች ጉዳይ ግን የተለየ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ ልጆች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሙሉ ጊዜያቸውን እያሳለፉ ያሉት እቤት ውስጥ እየሆነ መጥቷል።
ከዚህ ቀደም በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበሩት በትምህርት ገበታ ላይ ሆነው በመሆኑ ቤተሰባቸውን ለማግኘት የሚችሉት በበአልና በእረፍት ጊዜያቸው ብቻ ነበር። እነዚያንም ወቅቶች በቤት ውስጥ እንደፈለጉ እየተንቀሳቀሱ ከቤታቸውም እንደልባቸው እየወጡና እየገቡ ጓደኞቻቸውንም በፈለጉ ጊዜ እያገኙ ነበር። አንዳንዶቹ የሚማሩት ቤተሰቦቻቸው ባሉበት ከተማም ቢሆን እቤት ውስጥ ለምግብና ለመኝታ በሚያሳልፉት ጊዜ ብቻ ነበር ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት እድሉ የሚኖራቸው። አሁን ግን ከቤት የመውጣቱም በቤት ውስጥም የፈለጉትን እየነካኩ የመንቀሳቀሱ ነገር ገደብ ያለበት ነው። በሌላ በኩል እነሱ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ማሳለፍ የሚፈልጉት ከእኩዮቻቸው ጋር ከቤት ውጪ የተለያዩ ደስታ የሚሰጧቸውን ነገሮች እያደረጉ ነው።
እነዚህ ወጣቶች በአካልም በስነልቦናም ራሳቸውን ሲያዘጋጁ የነበረው ኮሮና ለሚያስከትለው ማእቀብ ሳይሆን ለውጪው እንቅስቃሴ በመሆኑ እቤት መዋሉ ለመልመድ የሚያስቸግር አጋጣሚ መሆኑ አይቀርም። በዚህ የተነሳም ጊዜውን በማንበብና በማጥናት ከማሳለፍ ይልቅ በርካታ ጥያቄዎችን የማብሰልሰልና የመጨነቅ ነገር ሊገጥማቸው ይችላል። በመሆኑም ቤተሰብ በቅርብ በመከታተልና ስሜታቸውን በመረዳት መረበሽና ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ በመጠንቀቅ መንከባከብ ይጠበቅበታል። ይሄ በየትኛውም ደረጃ ላሉ ልጆች መደረግ ያለበት ጥንቃቄ ነው። ቢቻል ቤተሰብ የሚፈልገውን ሳይሆን የተቀመጠውን ቫይረሱን የመከላከል ገደብ ሳይጥሱ ከጥናቱ ባሻገር ልጆቹ የሚያስደስቷቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ መፍቀድ ያስፈልጋል። ከእነዚህም መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፤ ምግብ ማብሰል፤ የሚሞክሯቸው የእጅ ሙያዎች ካሉ ማሰራት፤ ጌሞችን ማዘጋጀት፤ ልጆቹ ህጻናት ከሆኑ ደግሞ በቁም ነገር ብቻ ከመጥመድ ይልቅ ተረት ማውራት የመሳሰሉ ነገሮችን እንዲያዘወትሩ በማድረግ የተረጋጋ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማስቻል መሞከር አለባቸው።
እንዳጠቃላይ ደግሞ ለሁሉም ቤተሰብ በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በመደበኛ ሚዲያዎች ስለኮረና የሚለቀቁት መረጃዎች ጭንቀት የሚፈጥሩና የሚረብሹ በመሆናቸው ሚዲያ መከታታል ዜና መስማት ቢያስፈልግ ምን ያህል መከታተል እንደሚገባ መወሰን ያስፈልጋል። እቤት ውስጥ ቁጭ ብለው ስለኮሮና በሚዲያ የሚተላለፉት አስፈሪ ወይንም ስጋት ጫሪ መረጃዎች የሚፈጥሩባቸው ተጽእኖ ይኖራል። እነዚህ ነገሮች ጠንከር ካሉ የስነ ልቦና ባለሙያ የማግኘቱም ነገር አስቸጋሪ ስለሚሆን ድጋፉም እንክብካቤውም የሚጠበቀውም መደረግም ያለበት በቤተሰብ በኩል እርስ በእርስ ነው። እንደ ቤተሰብ ሁሉም ሰው አንድ አይነት ምላሽ አይኖረውም፡፡ አንዳንዱ የመቆጣት፣ የመነጫነጭ ባህሪ ሊፈጠርበት ይችላል፤ አንዳንዱ ደግሞ ነገሮችን ቀለል አድርጎ በማየት የማለፍ ብቃትም ይኖራል። በመሆኑም የትኛው ልጅ ወይንም የቤተሰብ አባል ፍርሃት ጭንቀት ውስጥ እየገባ ያለው የሚለውን አርስ በእርስ በመከታተል ድጋፍ ማድረግ ወይም ማዝናናት ይቻላል፡፡ ልጆችም ደስታ መፍጠርና ማረጋጋትም እንደሚችሉ በመገንዘብ እድሉን መስጠት ማዳመጥ የሚጠበቅ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ጭንቀት ሊፈጥሩ የሚችሉ በቤት ወስጥ ያሉም ሆነ አካባቢያዊ ነገሮችን ከልጆች ብቻ ሳይሆን አጠቃለይ ከቤተሰቡ በተቻለ መጠን ማራቅና አሉታዊ ተጽአኖ ካላቸው ነገሮች ራስን መገደብ የሁሉም የቤተሰቡ ሃላፊነት መሆን አለበት።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ የሚያጠቃው በመሆኑ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ለመፈጸም እንጂ ከይሉኝታ በመራቅ ትክክለኛ መሆናቸውን ብቻ መገንዘብ ይጠበቃል። ብዙ ሰው እየኖረ ያለው የራሱን ፍላጎት አስቀድሞ ሳይሆን ለማህበረሰቡና ለጓደኛ ፍላጎትና እሴት ቅድሚያና ትልቅ ዋጋ በመስጠት አንድን ነገር ራሱን ሊጠቅመው እንደሚችል እያወቀ ሳያደርግ፤ ብሎም የማያስደስተውን ነገር ለሌሎች ሲል እያደረገ ነው። ከንግግርም ጀምሮ እኔ ሳይሆን እኛ ማለት ይቀናዋል። ይህን የፈጠረበት ደግሞ ባህሉ ነው፡፡ ባህሉ በአንድ ጀንበር ሊቀየር አይችልም፡፡ ቢሆንም አንደ ሰው የሚጎዳው ነገር ከሆነ የግድ ለራሱም የእኔ ለሚለውም ሲል መታገል አለበት። ይሉኝታው ለቤተሰብ ቅርርብ ብቻ ሳይሆን የበሽታውንም ስርጭት ለመከላከል እንደ እንቅፋት እየገጠመ በመሆኑ መቀረፍ ያለበት ትልቅ ችግር ነው። ይሄ ማለት ግን ለሌሎች ማሰብን አብሮ መኖርን እንሸርሽረው ማለት አይደለም። የኮሮና ቫይረስ ክስተት በራሱ ለሰው ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያደርግ በሽታ ነው። ሀብት ያላቸው ስልጣን ያላቸው አለማምለጣቸው የሰው ልጅ ብቻውን ለምንድነው የሚኖረው መኖርስ ይችላል ወይ የሚለውንም ጥያቄ አስነስቷል።
እንደ ግለሰብ ራሳችንን ለሌሎች አሳልፈን እንድንሰጥም ያደረገ ነው። እንደ ማህበረሰብም ብናየው በኢትዮጵያ ባህል የነበረውንና አሁን አሁን የተቀዛቀዘውን አብሮ መኖርንና ለሌሎች መኖርንም እንደ አዲስ ያመጣ ነው። የተለያዩ እምነት ተቋማት ተከታይ የሆኑ ሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር በአንድ ላይ አሰባስቦ ለአንድ ዓላማ እንዲቆሙም አድርጓል። በጥላቻ ከመተያየትም አንዱ አንዱን እንዲያስብ እንዲረዳ በቅድሚያ ሰው መሆንን እንዲያስብ ያደረገ ነው። ጽንፍ ይዘው የነበሩ ፖለቲከኞችንና ሚዲያዎችንም በአንድ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ እያደረገ ነው። ይሄ በይሉኝታ የሚሰራ ሳይሆን ሁኔታው በአስገዳጅነት የፈጠረው ሁሉንም የሚጠቅም እውነታ በመሆኑ እንደግለሰብም ሆነ እንደ ቤተሰብ ከአካባቢ ነዋሪ ጀምሮ ለሌሎች በመጨነቅ ስለሌሎችም ብሎ በመስራት ራስንም፣ አገርንም መታደግ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ