
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት የአዲስ አበባ ወንዞች ተፋሰስ መነሻ በሆነው በጉለሌ እንጦጦ አካባቢ ችግኝ በመትከል የዚህን ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል። በአረንጓዴ አሻራ ሁሉም እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም ባሕል ይሆን ዘንድ በበጋ ወቅት አሳይተዋል።
ለመሆኑ የተተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ባሕላችን ምን ይመስላል?
‹‹ዘቅዝቃችሁ ትከሉት በሪፖርት ይፀድቃል›› ይባል የነበረው ነገር እንደዋዛ መጥፎ ልማድ እንዳይሆን! መልዕክቱ፤ ክረምት በመጣ ቁጥር የችግኝ ተከላ ዘመቻ ቢደረግም የሚተከለው ችግኝ እንክብካቤ አይደረግለትም ለማለት ነው፤ የተተከሉት ችግኞች የሚጸድቁት በውሸት ሪፖርት ነው። ስለዚህ አሠራሩ የግብር ይውጣው ስለነበር ተዘቅዝቆ ቢተከልም በውሸት ሪፖርት እንደ ጸደቀ ተደርጎ ይነገራል ለማለት ነው። እንዲህ ይባል የነበረው ከ2011 ዓ.ም በፊት በነበረው ዓውድ ነው።
ከሰኔ 2011 ዓ.ም ወዲህ ግን ችግኝ ተከላ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው። ችግኝ ተከላው ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ክረምት በመጣ ቁጥር በልዩ ትኩረት እየተሠራበት ነው፤ በዚሁ ዘመቻ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝታበታለች፤ ለአየር ንብረት አያያዝ ምሳሌ ትደረጋለች።
ይህን የዓለም ምሳሌነት ለማስቀጠል ግን አሁንም ያልቀረፍናቸው ችግሮች አሉ።
ዛፍ እየጠፋ በረሃማነት የተስፋፋው መሬቱ ዛፍ አላበቅል ብሎ ነው? ወይስ የዛፍ ዝርያ ከምድረ ገጽ ጠፍቶ ነው? ይሄ ሁሉ የሆነው በግዴለሽነቶቻችን ነው።
የመንግሥትም ይሁን የግል መሥሪያ ቤት መጸዳጃ ውስጥ ግቡ፤ አሳፋሪ ነገር ነው የሚታየው። ውሃውን እንዴት እንደሚደፉት አላውቅም! መጸዳጃ ቤቱ ባሕር ይሆናል። ይሄ አላዋቂነት በብዙ ነገሮች ነው። ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ ሀገር ይለውጣል በሚባለው የተማረው ማኅበረሰብ ዘንድ መሆኑ ነው።
ይህ አላዋቂነታችን፣ አርቆ ማስተዋል አለመቻላችን ለም መሬቶቻችን እንዲራቆቱ አድርጓል። ብዙ አካባቢዎች በጎርፍ እንዲጠቁ አድርጓል።
የክረምቱን መግባት ተከትሎ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ የተለመደ ቢሆንም ከ2011 ዓ.ም ወዲህ ያለው ግን የተለየ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው ያስጀመሩት። እርሳቸው በተከሉት ችግኝ ብቻ ሀገሪቱ አረንጓዴ በአረንጓዴ ትሆናለች ተብሎ አይደለም፤ መሪ ናቸውና አርዓያ ለመሆን ነው። ሕዝብ መሪውን ተከትሎ እንዲህ አይነት በጎ ነገሮችን ያደርጋል። መሪ ማለት እንግዲህ የሚመራ፣ የሚያሳይ ማለት ነው።
ተቃዋሚ ነን በሚሉት በኩል ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳየውን ፎቶ ለምስጋና ሳይሆን ለወቀሳ ተጠቅመውታል (ለችግኝ ተከላ) ተቃዋሚ የሚል ቃል መጠቀም በራሱ አግባብ አልነበረም)። ‹‹ ሀገሪቱ ስንት ችግር እያለባት እሱ ችግኝ ይተክላል›› የሚሉ ወገኖች አሉ። የሀገሪቱ ምድረበዳ መሆን ችግር አይደለም ማለት ነው? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ መትከል በምን መመዘኛ ሊያስወቅስ እንደሚችል ግልጽ አይደለም! በዚህ ችግኝ ተከላ ውስጥ ምን አይነት ማጭበርበርና ሕዝብን ማታለል ይኖረዋል ተብሎ ነው? ችግኝ መትከል ምን አይነት ስውር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይኖረዋል? ስለተውነው ተዓምር ሆነብን እንጂ ችግኝ መትከል የዕለት ከዕለት ተግባር ነው። ይሄ የሚያሳየው እነዚህ ወገኖች ከመቃወም ውጭ ምክንያታዊ ሀሳብ እንደሌላቸው ነው፤ ችግኝ መትከል በራሱ የተቀደሰ ሀሳብ ነው።
ከዚህ ይልቅ መቃወም የነበረብን ቆሻሻ የሚጥሉትን እና ችግኝ የሚያበላሹትን ነበር።
‹‹ቆዳ ፋቂ ሲደክመው ውሻ ያባርራል›› እንደሚባለው ነው። በፖሊሲና ስትራቴጂ መሞገት ነው መቃወም ማለት!
በደጋፊዎቻቸው በኩል ያለውንም እንታዘብ፤ ይሄ እንግዲህ በብዛት የሚታየው በመንግሥት ተቋማት ላይ ነው። እነዚህኞቹ ወገኖች ላይ ተቃዋሚዎች ‹‹ማሽቃበጥ›› የሚሉትን ቃል እጋራዋለሁ። አንዳንዶቹ ነገሩ ገብቷቸውና አምነውበት አይደለም የሚያደርጉት፤ ሲደረግ ስላዩ ብቻ ወይም አድርጉ ስለተባሉ ብቻ ነው።
በዚያው ዓመት (2011 ዓ.ም) በአንድ የመንግሥት ተቋም አማካኝነት ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ ነበር። የወጣንበት ሥራ ሌላ ቢሆንም ችግኝ ተከላ እንደ አንድ ፕሮግራም ተይዟል። ነገሩን ላሳጥረውና ችግኙ የሚተከልበት ቦታ ስንደርስ እየታዘብንም እየሳቅንም ነበር። ለችግኝ ተከላ በተዘጋጁ ጉድጓዶች ዙሪያ፤ የጠወለጉ፣ ጭራሹንም የደረቁ፣ የተገነጣጠሉ… የዕፅዋት አይነቶች አሉ። እነዚህ ዕፅዋት የደረቁትና የተገነጣጠሉት በእርግማን አይደለም፤ እንክብካቤ አጥተው ነው። እንኳን እንክብካቤ ማድረግ እንዲያውም በተቃራኒው የደረሰባቸው ጥፋት ነው፤ ለዚያውም የእንስሳት ሳይሆን የሰው ጥፋት! ከእነዚህ ዕፅዋት ጋ ነው ችግኝ የሚተከለው! በወቅቱ ‹‹አሁን የሚተከሉ ችግኞችም ነገ ይደርቃሉ›› እያልን ነበር።
አንዳንድ ሰዎች የመንግሥት ተቋማት ይህን የሚያደርጉት በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታዝዘው ይመስላቸው ይሆናል፤ ግን አይሆንም። የራሳቸው አስመሳይነት ነው። ማስመሰል የምንልበት ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የጠቀስኩት አይነት አተካከል ነው። ለምን እንደሚተከል፣ የት እንደሚተከል፣ እንዴት እንደሚተከል ካልታወቀበት ማስመሰል ነው።
አልኩ ለማለት ብቻ የሚደረግ ማለት ነው፤ ለሪፖርት ብቻ ነው።
የሚተከልበት ቦታ እና ሁኔታ ካልተጠና ችግኝ መትከል ግዴታ አይደለም አይደል? አልኩ ለማለት ብቻ ለምን ወጪ ይወጣል? ችግኙ የሚተከለው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኝ ነው። አውቀን እና አምነንበት ከሆነ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ነው ማስመስከር! አለበለዚያ አስመሳይነት ነው።
ላለፉት ስድስት ዓመታት ትኩረት በተሰጠው የችግኝ ተከላ ላይ በወቅቱ ከተሞች ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም የሚል ትዝብት ነበረኝ። ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ግን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መሄድ ችሏል። አሁን ችግር የሆነው ገጠራማ አካባቢዎች በቂ ግንዛቤ የመስጠት ጉዳይ ነው። አሁንም በከተሞች ብቻ ሳይሆን ትኩረቱ በገጠራማና ተራራማ አካባቢዎች መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆቱት እነዚያ አካባቢዎች ስለሆኑ። የመንግሥት አካላት በገጠራማ አካባቢዎች ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።
ዋናው ትዝብታችን ግን ገጠርም ሆነ ከተማ የሚተከሉ ችግኞች ክብካቤ አይዘንጋ የሚለው ነው። ችግኝ ለመትከል የሚደረገውን ዘመቻ ያህል የመንከባከቡ ዘመቻም ይታሰብበት። ለመትከል የሚደረገውን ዘመቻ ያህል ለመንከባከብ ሲደረግ አይታይም። ብዙዎች መንከባከብ ሲባል ውሃ ማጠጣት ብቻ ይመስላቸዋል። በዚህም ምክንያት ‹‹ደግሞ በክረምት ዝናብ አለ ምን መንከባከብ ያስፈልጋል?›› ሊባል ይችላል። መንከባከብ ማለት ግን ውሃ ማጠጣት ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ሆነ ሰዎች በችግኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ ነው። በበጋ ውሃ ማጠጣት፣ በክረምት ደግሞ ሰዎችና እንስሳት እንዳያበላሹት መጠበቅ ያስፈልጋል።
መትከል እና መንከባከብ አረንጓዴ ባሕላችን ይሁን !
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም