ዓለማችን ከኖቭል ኮሮና ቫይረስ ጋር ከተዋወቀች ጊዜ አንስቶ ላለፉት አራት ወራት ወረርሽኙን በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ ይህ ነው የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ ቀናትና ሳምንታት ብሎም ወራት መፈራረቃቸውን ቀጥለዋል። ቫይረሱም በእያንዳንዱ ቀን በሺ የሚቆጠሩ በዓለማችን ህዝቦች እያጠቃና ወግ ስርዓቱን ባልጠበቀና በሚያሳዝን መልኩ ግብአተ መሬታቸው እንዲፈፅም ማድረጉን አላቋረጠም።
በቴክኖሎጂ የመጠቁ፣በኢኮኖሚ የበለፀጉና በህክምና አገልግሎት አቅርቦትም ሆነ ጥራት ከፊተኞቹ ተርታ ስማቸው የሚጠራላቸው ጣልያን፣ፈረንሳይ እንግሊዝ፣ስፔንና አሜሪካ በሟች ቁጥር የፊተኛው ረድፍ ላይ ናቸው። በስልጣኔ ከፍታ ቀድማ የምትጠቀሰው ባለጠጋዋ አሜሪካ በሽታውን መቋቋም የሚያስችል አቅም አጥሯት በተጠቂዎችም ሆነ በማቾች ቁጥር ዓለምን ትመራለች።
ወረርሽኙ የበረታባቸው እነዚህን ጨምሮ ሌሎች አገራትም የተቃጣባቸውን የቫይረስ ወረራ ጉዳቱን ለመቀነስ ከሆነላቸውም ድል ለማድረግ መፍትሔ ይሆናል የሚሉትን በተቻላቸው አቅም በመሞከር ተጠምደዋል። ይሕ የቁጥጥር ጥረትም የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ከመከላከልና ከመቀነስ ትሩፋቱ ባሻገር በርካታ ማሀበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ኪሳራን መፍጠሩም አልቀረም።
በተለይ ደሃ አገራት ያላቸውን ጥቂት ሀብት ተጠቅመው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የደረሰባቸው ኪሳራ ከሁሉ ከፍቶ ታይታል። ይሕ ጉዳት ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የሚቀጥል መሆኑ ደግሞ የቁስሉን ስቃይ እጥፍ ማድረጉ አይቀሬ ነው።
‹‹ከወረርሽኙ ሁለንተናዊ ቀውስ ለማገገም ዓመታት ይወስድባታል›› የተባለችውና ከድህነት ጋር ስሟ የሚነሳው አህጉራችን አፍሪካም፣ቫይረሱም ሆነ ቫይረሱን ለመከላከል በምትተገብራቸው ውሳኔዎች ክፉኛ መቁሰሏ እርግጥ ነው። በአህጉሪቱ የሚከሰተው ማናቸውም ቀውስም ተወደደም ተጠላ በድፍን ዓለም ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር መሆኑን ደግሞ በርካቶች ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ‹‹የወቅቱ አብይ አጀንዳ ነው›› እንዲሉ ምክንያት ሆኗቸዋል።
‹‹ሁሉም አገራት ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው እስካልተረጋገጠ፣አንድ አገር ሙሉ በሙሉ ነፃ ነኝ ማለት አይቻለውም›› የሚል እሳቤን ዋቢ የሚያደርጉና በዚህ ረገድ ሰፊ ትንታኔን በማቅረብ ላይ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንና ልሂቃንም፣ ‹‹አፍሪካ የኮቪድን ሁለንተናዊ ቀውስ በራሷ አቅም ብቻ ልትፋለመው አይቻላትም፣ ሁሉም የቀውሱ ገፈት ቀማሽ እስከሆነ ድረስ መፍትሔው ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ፣ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ትብብር መሆን እንዳለበት አፅእኖት ሰጥተውታል።
የአፍሪካ አገራት መሪዎችና የፋይናንስ ሚኒስትሮችም ኮቪድ 19ን ለመፋለም የጋራ ክንድን መሰብስብ ወሳኝ መሆኑን ከማስረገጥ በላይ ወረርሽኙ በአህጉሪቱ ከፈጠረውና ወደፊትም ከሚፈጥረው ቀውስ ለማገገም በገንዘብ ድጋፍ ረገድ ለ54 አገራት ቢያንስ አንድ መቶ ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህ የአፍሪካውያን መሪዎችና ባለሙያዎች ጥያቄ ግን ወረርሽኙ እያደር ካስመልከተው የጭካኔና የበለፀጉት አገራት በወረርሽኙ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከመደቡት የገንዘብ መጠን አንፃር ተመጣጣኝ ሆኖ አልተስተዋለም። ለዚህ ዋቢነትም የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ኮንግረስ የሁለት ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት ውሳኔ ማፅደቁን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማሰብ በቂ ይሆናል።
የበለፀጉት አገራት መሰል መጠን ያለው ድጎማ በማፅደቅ ኢኮኖሚያቸውን ለመታደግ ሲውተረተሩ በማደግ ላይ የሚገኙና በተለይ ደሃ አገራት በአንፃሩ፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የፋይናንስ አቅማቸውን ከወቅቱ ችግር አኳያ በይበልጥ በጤናው ዘርፍ ላይ ለማዋል ዓለምአቀፍ የዕርዳታና የብድር ጥሪን አቅርበዋል።
ከቫይረሱ መከሰት አንስቶ እስከ አሁን ባለው ሒደት ከዘጠና በላይ አገራት ከወረርሽኙ ጠባሳ ለማገገም አፋጣኝ የፋይናንስ ድጋፍን የጠየቁ ሲሆን፣ ይህና ያስተዋሉት አይ ኤም ኤፍም በታሪክ በዚህን ያሕል ቁጥር የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ ቀርቦለት እንዳማያውቅ አሳውቋል።
አንዳንድ የፋይናንስ ሊህቃንም፣ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር አገራትም ሆነ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት በተለይ ወረርሽኙ ለሚከፋባቸው ለደሃና የአፍሪካ አገራት ብድር ስረዛ ካልሆነም የብድር እፎይታ መስጠት ችግሩን ለመቋቋም የሚያግዝ ሁነኛ መፍትሔ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተውታል።
በእርግጥ እንደ አፍሪካ መሪዎች ብድር የሚደፍር የለም። አገራትም ከአጠቃላይ የመንግሥት በጀታቸው በየዓመቱ ለብድር ክፍያ የሚመድቡትና የሚያወጡት የገንዘብ ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። አገራቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ በሚል ደጅ ጠንተው ለመበደር የሚደፍሩትና የሚፈጥኑትን ያሕል ግን እዳ ለመክፈል እጅግ ቀርፋፋ ናቸው።
ውሸት ስለሚቀላቀልበት መጠኑ በትክክል አይታወቅም እንጂ ከአገራቱ መካከል አብዛኞቹ የውጭ ብድር እዳቸው እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ልሒቃን አበዳሪ አገራት እንዲሆን ዓለም ባንክም ሆነ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአንዳንድ አገራት የብድር ጫና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ሲገልጹና ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
በዚህ ረገድ ስመጥሩ የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ቹኩዋካ ኦንኩዌና አፍሪካ ፖርታል ላይ ባሰፈረው ሰፊ ሀተታ፣ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የእዳ ጫና እጅጉን መጨመሩንና በተለይ፣ ኬፐቨርዲ፣ ሞዛምቢክና አንጎላ ላይ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ አመላክቷል።
አፍሪካውያኑ በየዓመት ለብድር ክፍያ የሚመድቡትና የሚያወጡት ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያመላከተው ፀሐፊው፣ እኤአ በ2020 ናይጄሪያ ከመደበችው ዓመታዊ በጀት ሁለት ነጥብ አራት ሦስት /2.43/ ትሪሊየን የሚሆነው የእዳ ክፍያ 464 ቢሊዮን ደግሞ ለጤና ዘርፍ የተመደበ መሆኑን በዋቢነት አቅርቧል።
ይህ እንደመሆኑም በተለይ ብድር ወስደው ለመመለስ ያቃታቸውና የኮቪድ ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊትም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁ አገራትን መታደግ የአፍሪካን የመከላከል አቅም የሚያጎለብት ወሳኝና ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሔ ስለመሆኑም አስምረውበታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና መሰረተ ልማት የመጨረሻ ደካማ ተብለው ከሚጠቀሱ 50 አገራት መካከል አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፤ ከነሱም ውስጥ 34 የሚሆኑት ከሰሃራ በታች የሚገኙ ናቸው፤ይህ እውነታ በራሱ አህጉሪቱ የተለየ ድጋፍ እንዲሰጣት በቂ ምክንያት ስለመሆኑም አስረድተዋል።
‹በተለይ ኮሮናን የመሳሰሉ አስከፊ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ስለሚጠይቅ አገራት ቀውሱን ለመፋለም ብሎም ለማሸነፍ የሚሆን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም የላቸውምና የብድር እፎይታ ቢሰጣቸው የፋይናንስ አቅሞቻቸውን ከወቅቱ ችግር አኳያ ይበልጥ በጤናው ዘርፍ ላይ እንዲመድቡ ያግዛቸዋል›› ብለዋል።
ፀሐፊው ከዚህ ባሻገር በተለይ በፋርማሲቲካል ዘርፍ ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ተሳታፎ መሰል ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት በርካታ አገራት የህክምና ግብአቶችን፣ መሳሪያዎችን ለህዝባቸው የማቅረብ አቅም እንደሌላቸውና የኮቪድ ቫይረስ ህክምና የሚውል የትንፋሽ ማስተካከያ እንኳን ብንመለከት አለ ከሚባል የለም ለመባል የፈጠነ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለአብነት 195 ሚሊየን ሕዝብ እንዳላት በሚገመተው ናይጄሪያ የኮቪድ ቫይረስ ህክምና የሚውል የትንፋሽ ማስተካከያ ከ500 እንደማይበልጥና ይህ አሃዝ በሌሎቹ አገራት ደግሞ ከዚህም እንደሚከፋ የጠቆሙት ዶክተር ቹኩዋካ ኦንኩዌና፣ የወቅቱ ወረርሽኝ የዜጎችን ብሎም የጤና ባለሙያዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያግዙ የህክምና ግብአቶችን ግድ የሚልና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ለአፍሪካውያን የሚደረግ ማናቸውም የፋይናንስ ድጋፍም ሆነ ማሻሻያ ፋይዳው የላቀ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተውታል።
ይህን እሳቤ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ይጋራዋል። ኮሚሽኙ ከአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጋር ባካሄደው በቪዲዮ ኮንፍረንስ፣ የብድር እፎይታው ለሁሉም አገራት መሆን እንዳለበት ከማስረገጥ ባሻገር ትግበራውም ከሌላ ይልቅ የጋራ ትብብር ብሎም አጋራነትን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አፅእኖት ሰጥቶታል። የልማት አጋሮችም ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ከብድር እፎይታ ባሻገር ከሁለትን እስከ ሦስት ዓመታት የወለድ ክፍያን ስለመቀነስ ታሳቢ ማድረግ ይገባቸዋል›› ብላል።
ከቀናት በፊትም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤም ኤፍ) ለ19 የአፍሪካ አገራት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ የብድር እፎይታ ፈቅዳል። ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ሞዛምቢክ ቤኒን፣ ኮሞሮስ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሳኦቶሚና ፕሪንሲፔ፣ ሴራሊዮንና ቶጎ ከብድር እፎይታው ተጠቃሚ የሆኑ አገራት መሆናቸው ታውቋል።
ይህን የተቋሙን ውሳኔ ያስተዋሉ በርካታ ሊህቃንና የመገናኛ ብዙሃንም በአፍሪካ ምድር የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ፍልሚያ የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አህጉሪቱ ላለባት እዳ የእፎይታ ጊዜን መስጠት እጅግ ከፍተኛ እርዳታ ከመስጠት እንደማይተናነስ አመላክተዋል።
‹‹በተለይ አብዛኞቹ አፍሪካውያን አገራት ኢኮኖሚያቸው የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት ባልቻለበትና እጥረት ገጥሞት ባለበት በዚህ ወሳኝ ሰዓት መጠኑ ምንም ይሁን ማንኛውም የብድር ማስተካከያ ዕርምጃ በጣም ትልቅ ፋታ የሚሰጥ ነው››ብለውታል።
አንዳንዶች በአንፃሩ፣ የብድር እፎይታው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም የተቋሙ ውሳኔና የጊዜ ገደብ ነባራዊ ሁንታዎችን ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ደቡብ አፍሪካው ስመጥር የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ኢራጅ አብዲየን የተቋሙ የዕፎይታ ውሳኔ ከትሩፋቱ ይልቅ ተምሳሌትነቱ ጎልቶ የሚታይ፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገራትን ያገለለ›› ነው ብለውታል።
የተቋሙን እርምጃ ያደነቁት በበኩላቸው፣ የዓለማችን ሀብታም አገራት በተለይ ለአፍሪካ ከዚህ የበለጠ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ውሳኔው በተለይ ለመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ ለቻድ፣ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ለላይቤሪያና፣ ማላዊ ፣ ማሊ፣ ኒጀርና ሩዋንዳ ለመሳሰሉ አገራት አስደሳችና ትልቅ እፎይታ የሚለግስ መሆኑን ለቪኦኤ የተናገሩት ኢኮኖሚስቱ ኤሪክ ሊኮምቴ፣ ‹‹የበለፀጉት አገራት ከሁሉ በላይ 25 በመቶ የአፍሪካ አገራት ብድር የምትቆጣጠረው ቻይና፣ አህጉሪቱ የኮረናን ቀውስ እንድትሻገር የሚያግዝ ውሳኔን ማሳለፍ አለባት›› ብለዋል።
በእርግጥም የአፍሪካ ዋነኛ አበዳሪ ቻይና ናት። የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ጥናትም፣ የቻይና መንግሥት፣ ባንኮች እንዲሁም ካምፓኒዎች እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለሆኑ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ለአፍሪካውያን 143 ቢሊየን ዶላር ብድር ስለ መስጠታቸው አመልክቷል።
በአሁን ወቅት ቻይና አፍሪካን ለሁለት አስርት ዓመታት በማበደር የዋናውን አሽከርካሪ መቀመጫ መንበር እንደመቆጣጠሯ፣ ‹‹ተበዳሪዎቿ መሰል አስቸጋሪ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ሲዘፈቁ ምን እርምጃዎች ትወስዳለች›› የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ሂደት ግን ቢጂንግ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዘግይታለች።
አንዳንድ ባለሙያዎችም፣ ‹‹ቻይና ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከምታደርገው ጥረት ባሻገር እራሷም ቢሆን በኮሮና ወረርሽኙ ጥቁር ጠባሳ ክፉኛ በመጎዳቷ ለአፍሪካውያን እዳ ክፍያ የእፎይታ ጊዜን ስለመስጠት የምታስብ አይመስለንም›› ብለዋል።
በርካቶቹ በአንፃሩ፣ የአፍሪካ በኮረና ወረርሽኝ እንከን ቢበረታባትም እንኳ ቻይና ለዘላቂ ጥቅሟ ስትል አህጉሪቱን ገሸሽ ልታደርጋት አትችልም፣ የሚጠቅሟትን አገሮች የበለጠ ለመርዳት ትፈልጋለች›› የሚል ሙግት አቅርበዋል።
ኢንዲፔንደንት በአንፃሩ፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹የአፍሪካ እዳ እጅግ ውስብስብ ነው፣ የአገራት የእዳ መዝገብም የሚያስመለክተው ቁጥርም የተለያየ ነው፣ ይህም ሆኖ ቤጂንግ ለአፍሪካ የእዳ እፎይታ ለመስጠት ፍላጎት አላት፣ ለዚህም ከዓለም አቀፉ ተቋማት ጋር የጋራ ጥናት ታደርጋለች›› ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል›› ሲል አስነብባል።
ይህን የቻይና ውሳኔ በርካቶች አድናቆት ቢቸሩትም፣ አንዳንድ ምሁራንና ጸሐፍቶች በአንፃሩ አፍሪካ ከዚህ ቀውስ በመማር በቀጣይ ለታከናውናቸው ስለሚገቡ አበይት ተግባራትን አትተዋል። ከፀሐፍቶቹ አንዱ የሆነው Ngozi Okonjo-Iweala ብሩኪንግስ ላይ ባሰፈረው ሰፊ ምክረ ሃሳብ ፣ የአፍሪካ መንግሥታት፣ ለወረርሽኞች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ ማህበራዊ ደህንነትን የሚያስጠብቁ፣ በኢኮኖሚውም የግል በተለይ የመካከለኛና አነስተኛ አንቀሳቃሽ ዘርፎችን የሚደግፉ ተግባራትን መከወን እንዳለባቸው ያስገንዝባል።
ከአፋጣኝ ትግበራዎቹ ባሻገር በተለይ በረጅም ጊዜ እቅድ ትግበራ ከሁሉ ቀድሞ የጤና ስርዓትና መሰረተ ልማታቸውን ማጎልበት ግድ እንደሚላቸውና ይህን ማድረግም ለአህጉሪቱ ብቻም ሳይሆን ትሩፋቱ ለዓለም ስለመሆኑም አፅንኦት ሰጥተውታል።
የአፍሪካ መንግሥታት የምዕራባውያንን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ ወቅታዊና መፍትሔ ሰጪ ፖሊሲዎችን መተግበር ይጠበቅባቸዋል፤ለአብነትም ጊዜያዊ የግብር እፎይታ መስጠት፣ ዋነኛ የገቢ አማራጮቻቸውን ብሎም ከመንግሥት ወጪዎች መካከልም ቅድሚያ የሚሰወጣቸውን መለየት እንዳለባቸው ተጠቁማል።
ከገንዘብ ድጋፍ ጋር በተዛመደም በተለይ ከድጎማ ለመፋታት ‹‹መንግሥታት ከቀደመው የምዝበራ ታሪክ በመማር የውጭ እርዳታና ድጎማ አመዳደብና ስርጭት በግልጽነት ተጠያቂነት እንዲመራ ማድረግ ፤ሙስናና የሀብት ሽሽትን በመፋለም ጥንቃቄ ቁጥብነት የተሞላበት የፋይናንስ አጠቃቀምን መተግበር፤ጠንካራና ነፃና ብሄራዊ ተቆጣጣሪ ተቋማት መፍጠር ይኖርባቸዋል›› ተብሏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2012
ታምራት ተስፋ