
ኢትዮጵያ በሌማቶች ልማቶች ልመና ታቆማለች:: ሀገሪቱን የድህነት ጎራ ውስጥ የከተታት ዜጋው በጋራ ድህነት ላይ ባለመዝመቱ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው:: ድህነትን ለማጥፋት ታጥቆ በጋራ ለመነሳት ብዙ ክፍተቶች ታይተዋል:: ወኔ ያጠረው ደካማ ሕዝብ ሆነ:: በዚህም ምክንያት የአፍሪካ የውሃ ማማ የሆነች ሀገር ውሃ ስትጠማ ከመስማት ባለፈ በውሃ ድርቅ ስትመታ የነበረች ሀገር ሆነችና አረፈችው:: ተረትና ምሳሌው ‹‹ነገር አለኝ ከማለት ሥራ አለኝ ማለት›› ቢለንም ቅሉ፤ ወገኔ ነገር የሚፈትል ጦር የሚሾትል ሆነብን:: ድህነት አልላቀቅ አለን:: አሁን ታሪክ ተቀየረና ታንኩም ባንኩም በድህነት ላይ እየዘመተ ኢትዮጵያ ልመና ታቆማለች የሚል የምሥራች ሰማን::
ወደ ርዕሳችን እንመለስና ስለ ሌማቶች ልማቶች እናንሳ፤ የደስታ ተክለ ወልድ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ልማት የሚለውን ቃል ሲፈታው ‹‹ልምላሜ፣ ብጀታ፣ ብዛት›› ይለዋል:: ሌማት የሚለውን ቃል ደግሞ ‹‹በዕብራይስጥ ሌሔማት ሲባል ኅብስቶች፣ እንጀሮች ማለት ነው:: በተመሳሳይ በአማርኛ ፍቺው የእንጀራ፣ የኅብስት ማስቀመጫ መሶብ፣ ሲከደን ግጥም የሚል ዝንብ ከልክል፣ ሌማት (ለም ማት)፣ መዓተ ለምለም፣ የእንጀራ ብዛት በሚል ያስቀምጠዋል:: በኦሮምኛም ሌማት በሚል ነው መሶብ የሚታወቀው:: እንጀራ ምግባችን ነው::
ከስያሜዎቹ ስንነሳ የደስታ ተክል ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ልማት በራሱ ነጠላ አለመሆኑን ያሳየናል:: አንድ ሰው በትንሽ ቦታ ሦስት አራት ፍራፍሬ አልያም ሥራሥር ቢተክል ተከለ ነው እንጂ አለማ ብለን ብንናገር ሰዎች ስለልማት የማያውቅ ዓላማ ቢስ በሚል ሊተቹን እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም:: ሌማትም የልማት ቤተሰብ ነው:: እንደመዝገበ ቃላቱ ብያኔ ሌማት የእንጀራ ማስቀመጫ መሶብ እንደመሆኑ በተጨማሪ ልማቶች ልምላሜዎች እንጀራዎች የሚል ስያሜ አለው:: በልማት እና በሌማት መካከል ያለው ልዩነት ሌማት፤ ልማቶችንም፣ እንጀራዎችንም፣ መሶቦችንም ጠቅልሎ የያዘ ቃል መሆኑ ነው::
እየናፈቀን ያለው የዓባይ ግድብ ምርቃት የሌማቶች ልማት፤ ልመናን ያስቆማል ብለን አፋችንን ሞልተን እንድንናገር የሚያስችለን ነው:: ኢትዮጵያ በአፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት የበለጠ እንዲጨምርላት ኃይልና ብርታት የሚሆናት ነው:: አፍሪካውያን ያለ ዓለም ባንክ እና ምዕራባውያን ብድር ራሳቸውን ማልማት እንደሚችሉ ተምሳሌት የምንሆንበት ዳግማዊ ልማታዊ ዓድዋ ልንለው እንችላለን::
መቼም ዓባይ ራሱ ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊያለማት አይችልም፤ የእኛም ስንፍና ታከለበትና ‹‹ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ዓይነት ብሂል በኑሯችን አየንበት:: ዓባይ ክረምት በመጣ ቁጥር የኢትዮጵያን ለም አፈሯን እየጠረገ ይዞብን ይሄዳል:: ግብፃውያን ደግሞ ኢትዮጵያ ከምትበላ እኛ እናባላት እያሉ የብሔር ነፃ አውጪ ግንባር እየታቀፉ እየፈለፈሉና እያስታጠቁ እርስ በርስ ያባሉናል:: ከልማት ያደናቅፉናል::
መቼም ዓባይ በቀደሙት ዘመናት ‹‹አፉ ከእኛ ልቡ ከእነኛ›› ነበረ ብለን ብንናገር የአደባባይ ምስጢር መሆኑ እሙን ነው:: በቀደሙት ዘመናት በድርቅ ምክንያት ሀገራችን ብዙ ዜጎቿን አጥታለች:: የድርቅ ተምሳሌትም አድርገው በመዝገበ ቃላቶቻቸው ጭምር ኢትዮጵያን ጠቅሰዋት ነበር:: ዜጋው በሙሉ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ዝናብ ጠባቂ እንጂ መስኖ አልሚ አልነበረም::
ደግነቱ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው የምንለው እውነት እየሆነልን ይመስላል:: በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህሕመድ (ዶ/ር) ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ኢትዮጵያ በእኛ ጊዜ ልመና ታቆማለች…›› ማለታቸው በልማት ወደፊት እንደምንገሰግስ እና የድህነት ቀንበርን እንደምንሰብር የሚጠቁም የምሥራች ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ‹‹በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዓመት ጅማሮ እንደሚሆን መግለፄ ይታወሳል:: ማንሰራራት ብለን ያነሳነው ሃሳብ ለውጥ መትከል ለውጥ ማፅናት የለውጥ መሠረት ማስያዙ ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ ዕድገት፤ የሪፎርሙን ውጤት ወደ ምንሰበስብበት ጊዜ መሸጋገራችንን ለመግለጽ ነበር:: ያንን ቋንቋ መጠቀም ያስፈለገው፣ ዘንድሮ እንደተባለውም ለኢትዮጵያ በእጅጉ የማንሰራራት ዘመን ነው:: ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት አመርቂ ውጤቶች የታዩበት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው ያልታወቁ ድሎችን የተጎናፀፍንበት ዘመን ነው›› ብለዋል::
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ በሆነው ግብርና ዘንድሮ 31 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል:: በእህል ምርት ከአምናው 24 ነጥብ 7 በመቶ ምርት ጭማሪ አለ:: ይህም የተገኘው በመስኖ ነው:: ለመስኖ የሚሆኑ በፌዴራል መንግሥት 20 ገደማ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው:: የመስኖ ግድቦቹ ሲጠናቀቁ ደግሞ ከ220 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እንዲያለሙ ያስችላሉ:: በዓመት ሁለት ጊዜ ብናመርትባቸው 440 ሺህ፣ ሦስት ጊዜ ብናመርትባቸው ደግሞ 660 ሺህ ገደማ ይሆናል ማለት ነው:: እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ያሉ 84 ሺህ ሄክታር ማልማት የሚችሉ ስድስት የተለያዩ የመስኖ ግድቦች ይመረቃሉ::
ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች በቀጥታ ከግብርናው ጋር የተሳሰሩ ናቸው:: እነኚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሯቸው ነገሮች አዲሱ ዓመት ድህነትን የምንዋጋበት ዘመን እንደሚሆኑን የሚያሳዩን ናቸው:: ላለፉት 14 ዓመታት ዜጋው ብሔራዊ ግዴታውን ለመወጣት ለዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ያበረከተው አስተዋፅዖም የሚጠናቀቅበትና የሚመረቅበት ወቅት ነው:: ዓባይን ብዙዎቹ ዜጎቻችን የሚያውቁት በዘፈን እና በተረት ነበረ:: አሁን ደግሞ ከዘፈንና ተረት አልፎ በልማት የምናውቀው እየሆነ ነው::
ዓባይ ዓባይ
ያገር አድባር
የሀገር ሲሳይ
በተግባር የሀገር አድባር፣ የሀገር ሲሳይ (ምግብ) ሲሆን የምናይበት፤ ከኢትዮጵያም አልፎ ጎረቤት ሀገሮች ኤሌክትሪክ መስመር ይዘርጋልን እያሉ ከወዲሁ ደጅ የሚጠኑበት መሆኑን ብንናገር ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ዓባይን እንገድባለን ስንል ያፌዙብን ከወዲሁ ዕዳ ከሜዳ ብለው በኅዘኔታ እያዩት ነው::
ግድቡ ለሀገሪቱ የብርሃን ጎርፍ እየሆነ ነው:: የብርሃን ጎርፉ ብዙ ፋብሪካዎችን ለመክፈት የምንነሳበት፣ ብዙ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ የምንሰበስብበት፣ ብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት፣ የውጭ ምንዛሪ የምናመጣበትም ነው:: ለዚህም ከወዲሁ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ ከተሰጠው ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጨማሪ ታንዛኒያ በኬንያ ግዛት አልፎ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እንዲዘረጋላት ያቀረበችው ጥያቄ፤ ኬንያም ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም እንዲጨመርላት መጠየቋ የኢኮኖሚ ዋንጫው ከግብርናው ወደ ኤሌክትሪኩ ሌሄድ እንደሚችልም ለመገመት ያስችለናል:: ቀስ በቀስ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር እየተንደረደርን እንደምንቀየስ ጥርጥር የለውም::
የዓባይ ግድብ የፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ የቱሪስት መስኅብና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እየሆነን ነው:: ከታላቁ ህዳሴ ግድብ መንጭቶ ለአጎራባች ሀገራት በመሸጥ ብቻ በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል:: ይህም የግድቡን ወጪ በጥቂት ዓመታት ለመተካት የሚያስችል ነው:: ከሰው ሠራሽ ሐይቁ 70 ያህል ደሴቶች የውኃ ላይ ትራንስፖርትና መዝናኛ ቦታዎች ከፍተኛ የቱሪስት መስኅብ የሚሆኑ ናቸው::
ከጣና ሐይቅ ሦስት እጥፍ ይሰፋል ከሚባለው ሰው ሠራሽ ሐይቁ ዓሣ በማልማት እና በመብላት የአፍሪካ ጭራ የነበረችው ኢትዮጵያ በዓመት ከ10ሺህ ቶን በላይ ዓሣ በማልማት የአፍሪካ አውራ የነበረችውን ግብፅን በዓሣ ልማት ታስከነዳታለች:: የዓሣ ሀብት ልማቱ ግድቡ ከሚያስገኛቸው ትሩፋቶች አንዱ ነው::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም