
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው በኔቶ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) አጋርነት በኩል ለዩክሬን “ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን” እንደምትልክ ሲያሳውቁ፤ ሩሲያ ጦርነቱን በ50 ቀናት ለመቋጨት ስምምነት ላይ ካልደረሰች ታሪፍ እጥላለሁ ሲሉ ዛቱ። “ዩክሬን የምትፈልገውን እንድታደርግ እናመቻቻለን” ሲሉ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አዛዥ ማርክ ሩቴ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ገልጸዋል።
ሩቴ አሜሪካ ዩክሬን የሚያስፈልጋትን መሣሪያ በኔቶ በኩል በስፋት ለማስታጠቅ መወሰኗን አረጋግጠው አውሮፓ ሒሳቡን ይሸፍናል ብለዋል። የአውሮፓ ሀገራት ዩክሬን ከሩሲያ ጨራሽ የአየር ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል የምትተማመንበትን ‘ፓትሪዮት’ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት እንደሚልኩ እና መቀየሪያዎቹ ደግሞ በአሜሪካ እንደሚሰጡ ትራምፕ አሳውቀዋል።
ትራምፕም ሆኑ ሩቴ ለኪዬቭ እንልከዋለን ስላሉት የመሣሪያ አይነት ባያብራሩም፤ ሩቴ ስምምነቱ “ሚሳዔሎችን እና ጥይቶችን” እንደሚያካትት ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያወጡ “ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች” ዩክሬንን ለመደገፍ “በአፋጣኝ ወደ ጦር ግንባሮች ይከፋፈላል” ብለዋል።
“ዛሬ ቭላድሚር ፑቲንን ብሆን ከዩክሬን ጋር የሚኖረኝን ንግግር ጠበቅ አድርጌ ለመያዝ አጤናለሁ” ሲሉ ሩቴ፤ ትራምፕ ደግሞ መስማማታቸውን ግንባራቸውን በመነቅነቅ ገልፀዋል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በኤክስ ገፃቸው ከትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመው፤ “ዩክሬንን ለመደገፍ ላሳዩት ፍላጎት እና ግድያን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በጋራ መሥራት በመቀጠላቸው” አመስግነዋል።
“ሕዝቡን ከሩሲያ ጥቃቶች በተሻለ ለመጠበቅ አስፈላጊ መንገዶች እና መፍትሔዎች ላይ እና አቋሞቻችንን ለማጠናከር ከፕሬዚዳንቱ ጋር መክረናል። ሰላምን ለማስፈን በተቻለ መጠን ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ነን” ብለዋል። በታሪፍ በኩል ትራምፕ ሩሲያ በ50 ቀናት ውስጥ ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በቀሪ የንግድ አጋሮቿ ላይ የ100 በመቶ የሁለተኛ ወገን ታሪፍ እንደሚጥሉ ተናግረዋል። ይህም ከሩሲያ ጋር የሚነግዱ ሀገራት ወደ አሜሪካ የሚልኳቸው ምርቶች ላይ ታክስ ይጣልባቸዋል ማለት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ለአብነት ያህል ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቷን ከቀጠለች፤ ከሕንድ ምርት የሚሸምቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች እቃዎቹ የአሜሪካን ምድር ሲረግጡ 100 በመቶ የአስመጪ ታክስ ወይም ታሪፍ ይከፍላሉ። ይህም የምርቶቹን ዋጋ ውድ ስለሚያደርግ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ምርቶቹን ከሌላ ሀገራት በርካሽ እንዲገዙ ይገፋፋል፤ ይህም ሕንድ ገቢ እንድታጣ ያደርጋል።
የታሪፍ ሀሳቡ በሩሲያ ምጣኔ-ሀብት ላይ እክል እንደሚጥል ይታመናል። በሀሳብ ደረጃ ሞስኮ ነዳጇን ለሌሎች ሀገራት ሸጣ ገንዘብ ካላገኘች በዩክሬን ለጀመረችው ጦርነት ገንዘብ ያጥራታል። ነዳጅ እና ጋዝ ለሞስኮ ሦስተኛ ከፍተኛ ገቢ ማግኛ ምርቶች እና ከ60 በመቶ በላይ የወጪ ንግድ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ የ100 በመቶ ታሪፍ ለሀገሪቱ ፋይናንስ ቅርቃር ይከታል ተብሎ ይጠበቃል።
የታሪፉም ሆነ የኔቶ የመሣሪያ ስምምነት ዝርዝር ውስን ቢሆንም፤ ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዩክሬን መሣሪያ ለመላክ ቃል ገብተዋል። የሰኞው መግለጫ ትራምፕ ከቀን ወደ ቀን ቭላድሚር ፑቲን ላይ የሚያሰሙት ንግግር እየተካረረ መሆኑንም ያሳየ ነው። ከዚህ ቀደም ትራምፕ ሞስኮ በዩክሬን ላይ እ.አ.አ የካቲት 2022 ለከፈተችው ሙሉ ወረራ ኪዬቭ የተወሰነ ኃላፊነት እንደምትወስድ አመልክተው እንደነበር ይታወሳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ጦርነቱን ለማስቆም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ባለመታየቱ ብስጭታቸውን እየገለፁ ነው።
በሌላ በኩል የሰሜን ኮርያ ለሩሲያ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ዳግም ያረጋገጠችው ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ የመሣሪያ አቅርቦት ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም በጀመሩበት ወቅት ነው።ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ ለኤንቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት አሜሪካ ለዩክሬን የአየር መቃወሚያ ለመላክ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን መናገራቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም