እምነት የሰው ልጅ እስካሁን በበቂ ሁኔታ ሊገልጸው ያልቻለው ረቂቅ ነገር ቢሆንም የተለያዩ የሃሳብ ሰዎች አለምን በሚመለከቱበት መነጽር ተጠቅመው ጥቂት ገለጻ ከማድረግ ግን አልቦዘኑም። ታላቁ የስነጽሁፍ ሰው ጆርጅ በርናንድ ሾው “ብቸኛውና እውነተኛው የአለማችን አንቀሳቃሽ ሀይል” ሲለው እንግሊዛዊቷ ማህበራዊ ሳይንቲስት ቢያትሪስ ፖተር ዌብ በበኩሏ “እምነት ፍቅር ነው፤ በምንም አይነት መንገድ አመክንዮ አይደለም” በማለት ስለ ሃይማኖት የደረሰችበትን አጋርታለች። ሃይማኖትን የልብ አቅጣጫ፣ የንግግር ሳይሆን የእርምጃ አቅጣጫ፣ ሰው ከአዕምሯዊ ችሎታው በላይ ይኖራል ብሎ ስለሚያምነው ነገር ያለው አስተሳሰብ እንዲሁም ብዙ ብዙ ተብሎለታል። እምነትን ማስረዳት ለተመራማሪዎችና ለተናጋሪዎች ከባድ ይሁን እንጂ ራሳቸው አማኞቹ በጥልቀት የሚረዱትና ጊዜ ሰጥተው የሚያሰላስሉት ነገር ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህን ለመግቢያ አልን እንጂ እምነት በልዕለ ተፈጥሯዊ አካል ላይ ያለ እምነት ነው በሚለው ቀላል ትርጓሜ ወደ ዓቢይ አጀንዳችን መዝለቅ እንችላለን።
እምነት የአማኙን ህይወት ጣዕም፣ አቅጣጫ፣ ውሳኔ እንዲሁም ከዕለት ዕለት እንቅስቃሴ እስከ አጥናፈ አለም አተያይ ድረስ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ሃይል ነው። እጅግ የሚበዛው የፕላኔታችን ህዝብ በአንድም ሆነ በሌላ አይነት ሃይማኖት ውስጥ ራሱን መድቦ ገሚሱ በግል እምነት ደረጃ ሌላው ደግሞ የመንግስት ይፋዊ አቋም በማድረግ እየተዳደረበት ይገኛል። መንፈሳዊ እምነቶች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እጅግ ሰፊና ባለብዙ መልክ ነው። በዚህ ጽሁፍ ግን ከሚናዎቹ ሁሉ ስለሚልቀው አንድ ሚና ነጥለን እናያለን። እምነት በፈተና፣ በጭንቅና በመከራ ወቅት ያለው ሚና ምንድነው? በዚህ ጽሁፍ ሶስት አበይት ጉዳዮችን እንመለከታለን፤ ተስፋ፣ ለጋስነትና ዕርቅ።
የመጀመሪያውና እምነት በፈተና ወቅት የሚጫወተው እጅግ በጣም ጠቃሚው ሚና የተስፋ ምንጭ ነው። ተስፋ ምግብ፣ ተስፋ መጠጥ፣ ተስፋ ገንዘብ፣ ተስፋ ሀብት፣ ተስፋ ጉልበት፣ ተስፋ ብርታት በቃ በአጭሩ ተስፋ ሁሉ ነገር ነው። ተስፋውን ለጣለ፣ ነገውን ለማይሻ፣ በፊቱ ብርሀን ለማይታየው ወርቅና አልማዝ የመኖርን አቅም አይሰጠውም። ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ከምስኪን ሀገራት ይልቅ በሀያላኑ ዘንድ መብዛቱ ለዚህ ግልጥ ያለ ማስረጃ ነው።
ተስፋ ይሄን ያህል ጥቅም ይኑረው እንጂ መንፈሳዊ ያልሆነው አለም ለብዙዎች የተስፋ ምንጭ አይደለም። በእርግጥ አሁን አሁን መንፈሳዊ ያልሆኑ ብዙ አነቃቂ መጽሀፍትንና ንግግሮችን ማግኘት የሚቻል ቢሆንም አለም የአድሎአዊነት፣ የሀብት ልዩነት እንዲሁም የድካምና ኪሳራ ማዕከል ናት ሚለውን ድምዳሜ መቀልበስ የተቻላቸው አይመስሉም። ወቅቱ አለማችን ኮቪድ 19 በተሰኘ ቫይረስ እየተፈተነች የምትገኝበት፤ ሀገራችንም በፈተናው ደጅ ላይ እንደመገኘቷ ብዙዎች ስለነገ ሰንቀው የነበረው መልካም ሃሳብ ስለመፈጸሙ መጠርጠራቸው አይቀሬ ነው። በተለይ ከኑሮ ጋር እየታገሉ ከዛሬ ነገ በማለት አንገታቸውን ደፍተው ለሚሰሩ ወገኖቻችን ቫይረሱ እምነትን የሚሸረሽርና በተስፋ መቁረጥ የሚሞላ በመሆኑ የተስፋን ቃል ለመናገር አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው።
ሁለተኛ በፈተና ወቅት የሃይማኖት ተቋማት ሚና አማኛች ለሌላው የሚያካፍሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ይህም የሚሆነው ሁሉም የእምነት አይነቶች በሚጋሩት የለጋስነት አስተምህሮ ነው። መንፈሳዊው አለም በስጋዊው አለም አለ ብሎ የሚያምነውን የራስ ወዳድነት ሃሳብ በአማኝ ልቡ ውስጥ ወደ መቆረስ እና መካፈል ሃሳብ በማሸጋገር የደስታ ምንጭ ይሆናል። እምነቶች በሰላሙ ጊዜ አምላካቸው መልካም መሆኑን በመስበክ የማያምኑትን ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ፤ የመከራ ጊዜ ደግሞ እንደሚያምኑት አምላክ መልካም በመሆን ራሳቸውን ይገልጣሉ። በመከራ ውስጥ ላሉ ሰዎች የአምላክን መልካምነት ከመስበክ ጥቂት መልካም ማድረግ ተፅዕኖው የጎላ ነው።
በሚያስደንቅ መልኩ በሁሉም እምነቶች ፈጣሪ ለተወሰኑ የህብረተሰብ አካላት እጅግ ሲሳሳ እናያለን። እነዚህም የህብረተሰብ አካላት ምስኪኖች፣ ወላጅ አልባ ህጻናት፣ ጧሪ አልባ ወላጆች እና ያዘኑ ናቸው። በእንዲህ ያሉ የማህበረሰብ አካላት ተከቦ እጁን ሳይዘረጋ ቤተ ክርስቲያኑን፣ መስጂዱን፣ መቅደሱን እንዲሁም የአምልኮ ስፋራውን በመገንባትና በማስዋብ የተጠመደ ቤተ እምነት በፈጣሪው ዘንድ ቅቡልነቱ አጠራጣረ በህብረተሰቡ ውስጥም ተገቢውን ሚና ለመጫወት የሚያስችለውን ቁመና ያልተላበሰ ነው። በተለይ አሁን ያለንበት አስከፊ ጊዜ ቤተእምነቶች ለፈጣሪ ያላቸው መገዛት ለብርቱ ፈተና የተሰናዳበት፣ ለወደፊት የእምነት ተቋማት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን ምስል የሚገነባበት ወይም የሚፈርስበት ጊዜ ነው። በደጉ ሰዓት ፈጣሪ ደግ፣ ለጋስ፣ የምስኪኖችና የድኆች ወዳጅ ነው በማለት ሲያስተምሩ የነበሩ እምነቶች አሁን በአስከፊ ወቅት ከሁሉም በፊት ተሰልፈው የፈጣሪያቸው ምሳሌ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመጨረሻው፣ ነገር ግን ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስገኘው የእምነት የፈተና ጊዜ ሚና አማኞችን ወደ እውነተኛ ዕርቅና ንስሀ መምራት ነው። አንድ ሀገር በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮአዊ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ በምትገባት ወቅት ዜጎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ የመረጋጋት፣ ነገሮችን የማሰላሰልና በዕርጋታ የመመልከት አዝማሚያ ያሳያሉ። ታዲያ ለንስሀና ለዕርቅ ከእንዲህ አይነት ወቅት የተሻለ ጊዜ የለም። ስለዚህ በሀገራችንም አሁን ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለንስሀና ዕርቅ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በሀገራችን ያሉ ቤተ እምነቶች ሊያስቡበት ይገባል። በእርግጥ በህዝባችን ዘንድ በስፋት ወደ ንስሀ የመግባት ፍላጎት የተስተዋለ ቢሆንም በተደራጀና ግልጽ አላማ ባለው መልኩ እስካሁን የተደረገ እንቅስቃሴ የለም።
ንስሀና እርቅ በለቅሶና በዋይታ ብዛት ፈጣሪን ለማባባት የሚደረግ የከላይ ከላይ ጨዋታ አይደለም። ንስሀ እውነተኛ መጸጸትና መመለስ ነው። ሀገራችን በዘመናት ታሪኳ በርካታ በደሎችን አስተናግዳለች። ንስሀ የሚያስፈልጋቸው ኃጢያቶቻችን ደግሞ ፈጣሪ ላይ ብቻ የሰራናቸው አይደሉም፤ አንዳችን በአንዳችን ላይም የፈጸምናቸው እንጂ። የሀገራችን በደልና ጥፋት ደግሞ የእገሌና የእገሊት የማይባል፣ በሙሉ ልብ እኔ ነጻ ነኝ ለማለት የሚደፍር የሌለበት የሁሉም የጋራ ኃጢያት ነው። መንግስት በድሏል፣ ግለሰቦች በድለዋል፣ ቡድኖች በድለዋል፣ ወላጆች በድለዋል፣ ወጣቶች በድለዋል፤ ፣ የሃይማኖት መሪዎች በድለዋል፤ ሁሉም ግፍን የፈጸመ ነው። በሀገራችን የንጹሀን ደም ፈሷል፣ ሀብትና ንብረት ጠፍቷል፣ ሙስና፣ ማጭበርበር፣ መናናቅ፣ የእርስ በእርስ ጥርጣሬ፣ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ውሸት፣ አለመታዘዝ እንዲሁም ዘርዝረን የማንዘልቃቸው ጥፋቶች በኋላ ታሪካችንም ሆነ በእኛም ዘመን ልንክደው በማንችለው መልኩ አግጥጠው አሉ። እነዚህ ደግሞ በእውነተኛ ንስሀና እርቅ ዘግተን እንጂ አብረውን አዲስ ወደምንለው ምዕራፍ ልንገባ አንችልም።
መንግስት ይሄንን በመረዳት የእርቅና የሰላም ኮሚሽን አቋቋሞ እየሰራ ያለ ቢሆንም የእምነት ተቋማት ይህንን አጋጣሚ ከፈጣሪ እንደተቸረ ዕድል በመቁጠር ወደ ሰላም የሚወሰድውን መንገድ መጥረግ አለባቸው። ሁሉም በዳይ በደልኩ የሚለውን ኃጢያት በማስታወስ ቅድሚያ ከበደለው አካል ቀጥሎም ከፈጣሪው ምህረትን መለመን ይኖርበታል። ወንድም እህት አዝነው፣ እናት አባት አዝነው፣ ህጻናት ወጣቶች አዝነው፣ ግለሰቦች ቡድኖች አዝነው እንዲሁም የመንግስት መሪዎች አዝነው ወደ ፈጣሪ መሮጡ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ነው። የተቋቋመው ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ወደስራው እስኪገባ ድረስ የእምነት መሪዎች ራሳቸው ለበደሉት ኃጢያት ህዝባቸውን ይቅርታ በመጠየቅ መጀመርና ምዕመናንም ወደ ዕርቅና ሰላም እንዲገቡ ማበረታታት አለባቸው። እውነት ይህንን በሀገራችን አድርገነው ብናልፍ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ጉዳት በብዙ እጅ የላቀ ተዓምራት እናተርፍበታለን።
በመጨረሻም ውድ አንባቢዎች በመንግስትና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን መተግበር አንርሳ። እጅ ቶሎ ቶሎ እንታጠብ፣ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ። ተስፋ አንቁርጥ፤ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል። ያለንን ደግሞ እናካፍል፤ በጋራ ካልዳንን በጋራ እንጠፋለንና። የበደልናቸውን ሁሉ በስልክ፣ በኢሜል፣ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያየ መንገድ ተጠቅመን ይቅርታ እንጠይቅ እላለሁ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2012
በመጋቢ ዘሪሁን ደጉ