እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
አሁን ባለንበት ወቅት መቼስ ከኮሮና ውጭ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የለንም።መሼም ጠባም ወሬያችንም ጭንቀታችንም እሱው ሆኗል።ለራስና ለወገን ሕይወት ዋጋ በመስጠት ብርቱ ጥንቃቄ እስካደረግን ድረስ ደግሞ ይህንን አስጨናቂ ጊዜ እንደምንሻገረው ግልጽ ነው፡፡
ያም ሆኖ እስከዛው ድረስ በአገር ኢኮኖሚና በሕዝቡም ኑሮ ላይ ሥጋት የደቀኑ ሁኔታዎች መፈጠራቸው አልቀረም።የኑሮው ውድነት በሁሉም ሕዝብ ላይ ሸክም ሆኗል።በተለይም ወጥቶ ወርዶ የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ ከማሟላት በዘለለ የተሻለ ሕይወትን በማይኖረው የማህበረሰቡ ክፍል ላይ ያንዣበበው ሥጋት ቀላል አይደለም።
እኛም ታዲያ በዚህ ጽሁፍ ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ በሸማቹ ላይ የተደቀኑትን ፈተናዎችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሊወሰዷቸው ስለሚገቡ ሕጋዊ ርምጃዎች እንዳስሳለን።
የሸማቹ ትከሻ ጎብጧል!
የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች በስጨት ብለው ተሳፋሪዎች ላይ ከሚወረውሯቸው ንግግሮች ውስጥ “ሰው መብቱ ትዝ የሚለው ታክሲ ውስጥ ብቻ ነው” የሚለውን ተደጋግሞ እናደምጠዋለን።
አብዛኛው ተሳፋሪ ታክሲ ውስጥ ሾፌርና ረዳት ላይ የሚጮኸው ግን ያለምክንያት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።ይልቁንም ታክሲዎች አቆራርጠው ስለሚጭኑ፤ ትርፍ ስለሚያበዙ፤ ከታሪፍ በላይ ስለሚጠይቁ አልያም ረዳቶች መልሷን ስለሚያረሳሱ ነው።በውሃ ቀጠነ ታክሲዋን ሶርያ ለማድረግ ምላሳቸውን የሚመዙ ተሳፋሪዎች እንዳሉም ሳንዘነጋ ማለት ነው።
ሾፌርና ረዳቶቹ ይህንን የብስጭት ንግግር ሲናገሩ ተሳፋሪው መብት እንዳለው አምነው ነገር ግን መብቱን ለማስከበር ሽንጡን የሚገትረው ወይም ጉልበት የሚያገኘው ታክሲ ላይ ብቻ መሆኑን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም።
በእነርሱ አረዳድ በሌሎች የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ግብይት ስፍራዎች ሕብረተሰቡ የቱንም ያክል መብቱ ቢገፈፍበት ቀና ብሎ ሳይተነፍስ ሸምቶ እንደሚሄድ ነው።
ሾፌርና ረዳቶቹ እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ሸማቾች ስለሆኑ በሁሉም የሸመታ ስፍራዎች በዋጋ፣ በጥራትም ሆነ በአቅርቦት እጥረት ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸው ጠንቅቀው ያውቁታል።የእነርሱ ዋና ትኩረት ግና ሕዝቡ በሌላው ሥፍራ ሸክሙን ተቋቁሞ ገዛዝቶ እየተመለሰ ታክሲ ውስጥ ለምን ብሶቱን ይወጣል፤ እዛም ዝም ካለ ታክሲም ውስጥ የተጠየቀውን መክፈል፤ የተባለበት ቦታ መውረድ አለበት የሚል ነው።
የሆነው ሆኖ አብዛኛው ሰው በየትኛውም የሸመታ ስፍራ ያልተገባ ነገር ሲያጋጥመው እሮሮውን ያሰማል፤ ይበሳጫልም።አብዛኛውም ተናግሮ ሲሰለቸውና ገበያው መሻሻል ሳይሆን “ዕብድ” እየሆነ ሲሄድ ያስተውልና በኪሱ ብር ሞልቶ ይዞ ገበያ ገብቶ በፌስታል ዕቃ ሸምቶ ቤቱ ይገባል።
የአገራችን ገበያ በኢኮኖሚ መርሆዎች በተለይም ዋጋን በሚወስኑት በፍላጎትና በአቅርቦት ላይ የሚመራ አይደለም።ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የምርትና የአገልግሎቶች ዋጋ ለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሰበብ እየተፈለገ ብቻ በየጊዜው እንዲንሩ ተደርገዋል።
“የመንግሥት ሠራተኛ ደሞዝ ተጨመረ፣ ነዳጅ አሻቀበ፣ መንገድ ተዘጋ፣ ወዘተ “ እየተባለ ለጊዜው በተፈበረከ ሰበብ ምርት ከገበያ እንዲጠፋና ዋጋም እንዲንር ይደረጋል።ያ ዋጋ ታዲያ በቀጣይ ሌላ ምክንያት ተፈልጎ ዋጋ እስከሚጨመር ድረስ በዛው በናረበት መጠን እንደተለመደ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ዋጋ ሆኖ ይቀጥላል።በቀጣይም እንዲሁ ሰበብ ይፈለግና በሸማቹ ትከሻ ላይ ሸክሙ እንዲበረታ ይደረጋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ነገሮች ወደአስከፊ ሁኔታ እያመሩ ይመስላሉ።መንግሥት በተደጋጋሚ ጠንከር ያሉ ርምጃዎችን ሲወስድ ቢታይም ገበያው ግን ይባስ ብሎ ጨርቁን ጥሎ አብዷል።በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚገቡ እስከሚመስል ድረስ በአገር ቤት ተመርተው በተገቢ ዋጋ መሸጥ የነበረባቸው ምርቶች ዋጋቸው ከቀን ቀን እየናረ ይገኛል።
ዛሬ ላይ መቼስ ስለ ሥጋ ዋጋ መነጋገር ጉንጭ ማልፋት ነው።አንዳንዱ ሥጋ ሲያምረው በልኳንዳ ቤት በር እያለፈ ሥጋውን አየት አድርጎ እጅ ነስቶ ያልፋል እየተባለ የሚቀለደው ያለምክንያት አይደለም።
አሁን ደግሞ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ኮሮናን ሰበብ በማድረግ የእህል ዋጋ ንሯል።በተለይም የጤፍ ዋጋ አሳሳቢ ሆኗል።ጋጋሪዎች የሚያቀርቡት እንጀራ ከመሳሳቱ የተነሳ እፍ ቢሉት ነፋስ የሚወስደው ይመስላል።“እንዴት ከምጣዱ ወጣላቸው!?” ያሰኛል።
ዘይት፣ ስኳርና ሌሎችም የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋቸው ያለአግባብ እየጨመረ ነው።የሸማች ማህበራት በአብዛኛው የተሻለ ሥራ እየሰሩ ቢሆንም ምርቶችን ያለአግባብ በማከማቸትና ለነጋዴዎች አሳልፈው በመስጠት ብልሹ ተግባር የሚፈጽሙት ግን ጥቂቶች አይደሉም።ይህ ደግሞ ሸማቹን በደንደሱ እንደማረድ የሚቆጠር መጥፎ ተግባር ነው።
በጣም አሳፋሪውም አስጊውም ደግሞ የንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ የአልኮልና የሳኒታይዘር ጉዳይ ነው።ፈቃድ ሳይኖራቸው እነዚህን ምርቶች የሚያመርቱት በጣም ተበራክተዋል።ሌላ ምርት ለማምረት በወሰዱት ፈቃድ የሚያመርቱም እንዲሁ።በዚህ ምክንያት በርካታ ምርቶች የጥራት ደረጃቸው የወረደና ይባስ ብሎም ለጤና ጠንቅ መሆናቸው ይነገራል።
እርግጥ ነው በቅርቡ መንግሥት በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚመረቱት ምርቶች እንዳይሸጡ ማገዱን አስታውቋል።ይሁንና በገበያው ውስጥ ከፍተኛ የአልኮልና የሳኒታይዘር እጥረት ከመኖሩም በላይ ለጤናም አስጊ የሆኑ ምርቶች አሁንም በስፋት ይቸበቸባሉ፤ ያውም በከፍተኛ ዋጋ።
እናም መንግሥት ምርቶቹን ማገድ ብቻ ሳይሆን ማምረቻዎቹን ወርሶ ለኮሮና ሕሙማን ማገገሚያና ለሌሎች ተያያዥ አገልግሎት መስጫ እንዲውሉ የሚያደርግ ሕግ እስከማውጣት የሚደርስ ርምጃ መውሰድ ይገባዋል።
ከንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎችም ጋር ሆነ ከሌሎች ምርቶች ጋር በተያያዘ እንዲህ አሳሳቢ የዕቃዎች እጥረት እንዲፈጠርና ዋጋ እንዲንር የሚያደረጉት በየስፍራው ያሉ በጣም ብዙ ነጋዴዎች ስለመሆናቸው አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል።ለዚህ ችግር ተጠያቂነት የተለመደውና “አንዳንድ ስግብግብና ሥነ-ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎች” የሚለው ለስላሳ አገላለጽ አያስማማም።
ማስተዋል የጎደላቸው ስግብግብ እና ቤታቸውን በጤፍ፣ በፓስታና በማካሮኒ ለመሙላት ሲያግበሰብሱ የሚውሉት ሸማቾችም ሳይቀሩ ለዚህ ችግር ጣት ሊቀሰርባቸው ይገባል።
ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለልማት ድርጅቶች የሚገዙ የአልኮልና የሳኒታይዘር ምርቶች የጥራት ደረጃም በጣም አጠያያቂ በመሆኑ የየተቋማቱ የግዥ ክፍሎች ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል።
“የሸማቾች መብት ጥበቃ መሥሪያ ቤት ሆይ ወዴት አለህ?!”
በአሁኑ ወቅት በሸማቹ ላይ የኑሮው ሸክም እየበረታበት ነው።እርግጥ ነው ሁሉም ሰው ሸማች ነው።ነጋዴውም ቢሆን ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን ዕቃና አገልግሎት ስለሚገዛ እሱም ጭምር ሸማች ነው።አርሶና አርብቶ አደሩም ቢሆን ሸማች ነው።
ስለዚህ የዋጋዎች መናርና የምርቶች እጥረት በመላው ሕዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።ይሁንና በደመዎዝ የሚተዳደረውና በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው።
በአዘቦቱም ወቅት ሆነ የሰዎችን ችግር እየጠበቁ ዋጋ በመቆለል የሕዝቡን ሸክም የሚያከብዱ ስግብግቦች በሚበራከቱበት እንዲህ ባለው ወቅት ታዲያ ከሁሉም ቀድሞ ሸማቹን “አለሁልህ” እንዲል ታስቦ የተቋቋመው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነው።
እርግጥ ነው ይህ ተቋም ከኮሮና ጋር በተያያዘ የንግድ ውድድሩን የሚያቀጭጩና በሸማቹ ላይ የኑሮ ንዝህላል የሚያሸክሙ ነጋዴዎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ከሚወሰዱ ርምጃዎች ጋር በተያያዘ የራሱን ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ መናገር ይቻላል።
ይሁንና የከተሞች የከንቲባና የንግድ ጽህፈት ቤቶች እየወሰዷቸው ካሉ ርምጃዎችም በላይ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣኑ ግንባር ቀደምና ጉልህ ሚናውን የሚወጣበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ይገኛል።
እንዲያውም ሸማቹ “ጤፍ ይህንን ያክል ሆነ፤ ዘይት ጣሪያ ነካ፤ ይሄ ይሄ ጭራሽ ከገበያው ጠፋ…” የሚል ሮሮ በማሰማት የድረሱልን ጩኸቱን እያስተጋባ ባለበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሁሉም ተቋማት ቀድሞ እንደስሙ “የሸማቾች ጠባቂ” ሆኖ ዕለት በዕለት ከሸማቹ ጎን ሊቆም ይገባዋል።በግብረ-ኃይልም ሆነ በተቋማት በጋራ በሚወሰዱ ርምጃዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት እንዲንቀሳቀስ ይጠበቃል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በመመስረቻ አዋጁ በተጣለበት ኃላፊነት መሠረት በመንግሥት ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉ የንግድ ዕቃዎችን እየተከታተለ ለፍጆታና ለሽያጭ እንዳይውሉ በየጊዜው ለሸማቹ ማሳወቅ አለበት።
በአሁኑ ወቅት ይህ ርምጃ በራሱ ለሕብረተሰቡ ዓይነተኛ ትርጉም ያለው ነው።በሚመለከተው አካል ክልከላ የተጣለባቸውን የንጽህና ዕቃዎች እየተከታተለ በሕትመትና በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችና በሌሎችም መንገዶች ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል።የጤና ደህንነት መስፈርትን ያላሟሉ ምርቶንም በራሱ እያገደ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አለበት፡፡
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት አደረጃጀቱንና አሰራሩን በማስፋት እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ነጋዴዎች በሸማቾች ላይ አግባብነት የጎደለው ተግባር እንዳይፈጽሙ ማድረግ አለበት።
በዚሁ መሰረት በተለይም ፀረ-ውድድር የሆኑ የንግድ አሠራሮችን የመከላከል ሥራውን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።በተለይም አንዳንድ ነጋዴዎችና አምራቾች በተለያየ ምክንያት በበላይነት የያዙትን ገበያ ያለአግባብ በስፋት እየተጠቀሙ ያሉበት ውቅት ላይ እንገኛለን።
ይህ ደግሞ ተገቢ የንግድ ውድድርን ከመጉዳቱም በላይ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሸማቹን ጓዳ የሚጎዳ ተግባር ነው።መኖሪያቸውንና ሕንፃቸውን ሳይቀር ለተፈጠረው ችግር አገልግሎት እንዲውል የሚሰጡ፤ ገንዘብ የሚለግሱ፤ የቤት ኪራይ የማያስከፍሉና የሚቀንሱ፤ ለሠራተኞቻቸው የተለያየ ድጋፍ የሚያደርጉና መሰል የበጎ ሰው ተግባራትን የሚፈጽሙ በርካታ የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያውያን የመኖራቸውን ያክል በዚያው ልክ ምርትን የሚገድቡ አምራቾች፤ ዕቃ የሚያከማቹ እንዲሁም ዕቃዎች በመደበኛው የንግድ መስመር በግልጽ ገበያ እንዳይሸጡ የሚደብቁና ይዘው የሚያቆዩ ስግብግቦችም ተበራክተዋል።
ከዚህም ሌላ በአንድ በኩል ተቀናቃኞቻቸውንና ከሥር ተተኪ የሆኑ ነጋዴዎችን ለማፈንና ለማንበርከክ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሸማቹን አማራጭ ለማሳጣት “ሲቸግረው ይገዛል” በሚል ዕቡይ ሐሳብ ፀረ-ውድድር የሆነ ስምምነት የሚያደርጉና በሕብረት አቋም የሚይዙ ነጋዴዎችና አምራቾችም በዚህ ሰዓት መኖራቸው አይቀርም።እነዚህንም በጥናትና በክትትል በመለየት ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ የግድ ነው።
በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ውስጥ የሸማቾችን ጥበቃ በተመለከተ በተለይም ሸማቹ ሊከበሩለት የሚገቡትን መብቶች ዘርዝረው የያዙ በርካታ ድንጋጌዎች ተካተዋል።ሸማቹ እንደ ቀላል የሚታዩትን አማርጦ መግዛትን፣ የዋጋ ድርድር ማድረግን፣ በትህትናና በአክብሮት መስተናገድን፤ የዕቃዎችን ዝርዝር መግለጫና ዋጋን ተለጥፎለት ማየትን፤ ለዕቃው ዋስትና ማግኘትን ጨምሮ ሌሎችም መብቶቹ እንዲጠበቁለት ሕጉ ሰፊና ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካቷል።
እነዚህን የሸማቹን መብቶች ያላከበረ ነጋዴ የሚደርስበትን የፍትሐብሔርና የወንጀል ተጠያቂነትም ሕጉ አስቀምጧል።የንግድ ውድድርን የሚፃረሩና የሸማቹን መብት የሚጋፉ ድርጊቶችንም ለመቅጣት ባለሥልጣኑ የራሱን አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት አደራጅቷል።
ይሁንና በሕጉ ውስጥ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶች ሲከበሩ አይታይም፤ ወይም ተሸራርፈው ነው የሚከበሩት።ለዚህም የተለያየ ምክንያት ቢጠቀስም ቅሉ፤ የሕግ አስከባሪዎች ልልነትና ሸማቹ መብቱን ለማስከበር የሚያሳየው ዳተኝነት በግንባር ቀደምትነት ተደጋግመው ሲጠቀሱ ይደመጣል።
ያም ሆነ ይህ አሁን ያለንበት ወቅት ሸማቹም ሆነ በሕግ አግባብ ንግዱን የሚያከናውነው ነጋዴ ለጉዳት የተጋለጡበት ወቅት በመሆኑ ባለሥልጣኑ ሕጉን ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ የሚያውልበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮለታል።የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ርምጃ የመውሰድ አቅሙን ለማጎልበት ወቅቱ ምቹ ሆኖለታል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስም በተመሳሳይ የሕጉን የወንጀል ድንጋጌዎች በአግባቡ ለመተግበር እንዲቻል ወቅቱን ከግምት ውስጥ ያስገባ የተለየ የምርመራና የክስ አካሄድ አደረጃጀቶችን በመቅረጽ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል።
ከዚህም ሌላ ነጋዴዎች ለዕቃዎች ከገበያ መጥፋትና ለዋጋ ውድነት “በመላ አገሪቱ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመገደቡ ነው” የሚል ምክንያት ሲሰጡ ይደመጣል።እርግጥ ነው ተገድቦ የነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ በቅርቡ ከመለቀቁ ውጭ በበሽታው ምክንያት የሰዎችም ሆነ የምርት ዝውውር በቂ አልነበረም።
በመሆኑም በተለይም የምርት ዝውውሩ ሸማቹን የሚጎዳ ውጤት እንዳይኖረውና ለስግብግብ ነጋዴዎች ሰበብና ያላግባብ የመበልፀጊያ መንገድ እንዳይሆን በየደረጃው ያሉ የንግድ ቢሮዎችና ሕግ አስከባሪ አካላት ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል።አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና በማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያዎች መሠረት ተገቢ ርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ የለባቸውም።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
በገብረክርስቶስ