የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ማመስ ቀጥሏል። ታላቋ ዩናይትድ ስቴትስ እስከትናንት ድረስ ከ42 ሺህ በላይ ዘጎችዋን አፈር አልብሳ ሐዘን ተቀምጣለች። ጣሊያን 24 ሺህ 114፣ ስፔን 20ሺህ 852፣ ፈረንሳይ 20 ሺህ 265 ዜጎቻቸውን ቀብረዋል። በኢትዮጵያም ምንም እንኳን የሟቾች ቁጥር ገና ሦስት ቢሆንም የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት… እያለ ዕድገቱን መቀጠሉ አስጊ ሆኗል።
ይኸን የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ወስኗል። በተለይ የግል ት/ቤቶች የወርሃዊ ክፍያ መቋረጥ ተከትሎ ለሕንፃ ኪራይ፣ ለመምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች ደመወዝና የመሳሰሉ ወጪዎች አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን በመመልከት የትምህርት ሚኒስቴር ሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን 2012 መመሪያ አውጥቷል። በተለይ በአዲስ አበባ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተጀምረው የነበሩ የምገባ ፕሮግራሞች መቋረጥ በርካታ ተማሪዎችና ወላጆችን እንዲሁም የተደራጁ ምግብ አቅራቢዎችን የጎዳ ቢሆንም የዛሬው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ባለመሆኑ ለጊዜው እንዘለዋለን።
ሚኒስቴሩ መመሪያውን ለማውጣት መነሻ የሆነው ትምህርት በተቋረጠባቸው ጊዜያት በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች ባለሀብቶች እና ወላጆች መካከል ወርሐዊ የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ ውዝግብ ወይንም አለመግባባት መነሳቱ ነው። ሚኒስቴሩ ከትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከወላጅ ተወካዮችና ከባለሀብቶች ጋር ከመከረ በኋላ ት/ቤቶች በቴክኖሎጂ ቤት የተቀመጡ ልጆችን እንዲደግፉ፣ ወላጆች የወርሐዊ ክፍያቸውን ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲከፍሉ የሚደነግግ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያው ከወጣ በኋላ በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች በድጋፍም ሆነ በተቃውሞም ፈጣን የሆነ የመወያያ አጀንዳን ፈጥሯል።
መመሪያው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነደፈውን ማዕድ ማጋራት መነሻ በማድረግ በመተጋገዝ መንፈስ ችግሩን መሻገር ይቻል ዘንድ ተማጽኖ ያዘለ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ወላጆች በኩልም ጉዳቱ የሁላችንም በመሆኑ ወላጆች በተለየ የመምህራንን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ወጪዎች የሚጋሩበት አቅም የላቸውም የሚል መከራከሪያ ይቀርባል።
የፕላን ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሕይወታቸው በመናጋት ላይ ያለ ወይንም ድጋፍ የሚፈልጉ 15 ሚሊየን ያህል ዜጎች አሉ ማለቱ የሚታወስ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያመጣሉ። የጭፈራ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት ….ሥራ መቀዛቀዝ በዚህ ዘርፍ በቀጥታ ተቀጥረው የሚሠሩ እንዲሁም በተለያየ መልክ ከዘርፉ ገቢ የሚያገኙ ወገኖችን እንደሚጎዳ፣ ባስ ሲልም ሥራ አልባ እንደሚያደርግ የሚታወቅ ነው።
ይኸም አጠቃላይ ሁኔታ ድህነትን ከማባባስ ባለፈ እንደዝርፊያ ያሉ ወንጀሎች እንዲስፋፉ በር ሊከፍት እንደሚችል የማህበራዊ ጥናት ባለሙያዎች ከወዲሁ ሥጋታቸውን እየገለፁ ይገኛል።
የሚኒስቴሩ መመሪያ ጭብጥ ሲዳሰስ
በትምህርት ሚኒስቴር የወጣውና ለሚመለከታቸው አካላት የተሰራጨው መመሪያ በዓለም ላይ ብሎም በሀገራችን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በመንግሥት በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ይጠቁምና ከእነዚህ እርምጃዎች አንዱ በመላው ሀገራችን የሚገኙ ት/ቤቶች ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዲዘጉ መወሰኑን ያስታውሳል። ይኸን እርምጃ ተከትሎ በአንዳንድ የግል ት/ቤቶች እና በተማሪ ወላጆች መካከል ከት/ቤት ክፍያ ጋር ተያይዞ ውዝግብ ተነስቷል። ይህንን ችግር ለመፍታት ትምህርት ሚኒስቴር ከክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከግል ት/ቤቶች ባለሀብቶች፣ ከግል ት/ቤት ማህበራት እና ከወላጅ ኮሚቴዎች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ የጋራ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በዚህ መሠረት በቀጣይ የቫይረሱ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር እስከሚውልበት ጊዜ ድረስ በሁሉም የግል ት/ቤቶች ላይ በየደረጃው ባሉ የሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ መሆን የሚገባቸው ዝርዝር ተግባራትን አውጥቷል።
የተማሪዎችን ጤንነት እና ትምህርት ተደራሽነት በተመለከተ
- ማንኛውም ት/ቤት ለተማሪዎቹ እና ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጤንነት ቅድሚያ መስጠት አለበት፣
- ሁሉም የግል ት/ቤቶች ከተማሪ ወላጆች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በማድረግ ለተማሪዎቻቸው እገዛ የሚያደርጉበት ዘዴን ማመቻቸት አለባቸው። ዘዴው ግን አካላዊ ግንኙነትን ማካተት የለበትም፣
- ትምህርት ቤቶች የቴሌግራም ቻናል በመክፈት ለተማሪዎቻቸው ኖቶችን በመጫን ተማሪዎች በደብተሮቻቸው እየገለበጡ እንዲቆዩና ሲመለሱ ገለፃ በማድረግ የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንደሚሠሩ፣ በተጨማሪም አሳይመንቶቻቸው በቻናሉ እየላኩ ተማሪዎች ሲሰሩ እንዲቆዩ ፕሮግራም በማውጣት ጭምር እንዲሰጧቸው ማድረግ፣ለተማሪዎቹ አስፈላጊ የሆኑ ወርክሽት፣ ኖት እንዲሁም ሌሎች ሰነዶች ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ አለባቸው።
- የትምህር ሚኒስቴርንና የክልሎችን ድረገጽ ለተማሪዎች በፈጠሩት የቴሌግራም ቻናል መሠረት በማሳወቅ የሚተላፈውን ትምህርት እንዲከታተሉ ማድረግ፣ የቴሌግራም ቻናል መክፈት ለማይችሉ ወላጆች ስልክ በመደውል መረጃዎችን የመስጠት ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ፣የራዲዮ ትምህርት ፕሮግራምን ለወላጆች በመላክ ተማሪዎች እንዲከታተሉ ማድረግ አለባቸው።
- በአጠቃላይ በዚህ ጊዜ የግል ት/ቤቶች ወቅታዊው ችግር ምክንያት በማድረግ ወላጅ ማስጨነቅ ሳይሆን ይህን ችግር በጋራ ተረዳድቶ ለማለፍ መክፈል ያለባቸውን ሁሉ መሰዋዕት መክፈል አለባቸው።
ክፍያን በተመለከተ፣
የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ክፍያን በተመለከተ ትምህርት ቤቶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ትርፍን ሳይሆን በሥራቸው ያሉ ሠራተኞች ህልውና ታሳቢ አድርገው መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው፣የወላጅ ኮምቴም ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ተደጋግፎ ማለፍ ላይ ያተኮረና የተማሪዎቻቸውን ጤንነት፣ የትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም የትምህርት ቤቶች መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ በማያናጋ መልኩ ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በመወያየት እና በመተማመን መሥራት እንዳለባቸው ያስቀምጣል።
የትምህርት ቤቶች ወላጅ ኮሚቴ እና የት/ቤቱ አመራር በጋራ በመሆን የወላጆችን የመክፈል አቅም በመፈተሽ አስፈላጊ ድጋፎችን ማድረግ አለባቸው ይላል። ይህንን ሲያብራራም በዚህ በሽታ ምክንያት ወርሐዊ ክፍያን በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ የተማሪ ወላጆች ክፍያውን ለረዥም ጊዜ እንዲከፍሉ ማድረግ አለባቸው። ወርሐዊ ክፍያ ከእነጭራሹ መክፈል ለማይችሉ ወላጆች ክፍያውን መሰረዝ እንዳለባቸው ይጠቅስና ት/ቤቶች ለሚያስተዳድሯቸው ሠራተኞች ደመወዝ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መክፈል አለባቸው በሚል ያስቀምጣል።
መምህራንና ሠራተኞችም ከዚህ ቀድም ያገኙ የነበረውን ሌሎች ክፍያዎች ማለትም የትራንስፖርት አበልና የመሳሰሉ እንዲተው ይጠይቃል።
የግል ት/ቤቶች እንደቴሌግራም ባሉ ቴክኖሎጂዎች ተማሪዎችን መደገፋቸው እንደግዴታ የሚያስቀምጠው የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ክፍያን በተመለከተ ወላጆች የወርሐዊ ክፍያቸውን ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲከፍሉ ያስቀምጣል። ይህም የሚወሰነው የትምህርት ቤቶች አስተዳደር የወርሐዊ ወጪው ዕቅድ በግልጽ ለወላጅ ኮሚቴ አቅርቦ በማጽደቅ የሚወሰን መሆን እንዳለበት ተቀምጧል።
መመሪያው በወላጆች ላይ ያሳደረው ስሜት፣
አንዳንድ ወላጆች ዘንድ የሚነሳው አስተያየት ከመነሻው ይህ የውል ሰጪ እና ተቀባይ ጉዳይ እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር ጉዳይ አለመሆኑን የሚሞግት ነው። እንደሚታወቀው የት/ቤቶች እና የወላጆች ግንኙነት ሁለቱ ወገኖች ካደረጉት ውል የሚመነጭ ነው። ት/ቤቶች አገልግሎት ይሰጣሉ፣ ወላጆች ደግሞ ለዚህ አገልግሎት ተመጣጣኝ ነው የተባለና የተስማሙበትን ወርሐዊ ክፍያ ይከፍላሉ። በተፈጥሮም ሆነ በሌሎች አደጋዎች ይህን ስምምነት መፈፀም ባይቻል ምን ይሆናል የሚለው ለመወሰን የሁለቱ ወገኖች ስምምነት መኖር ይሻል። በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ወላጆች ትምህርት ሚኒስቴር በክፍያ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የክፍያ ጣሪያ እስከመወሰን የሄደበትን አግባብ ትክክለኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ባለፉት ዓመታት የግል የትምህርት ተቋማት የወላጆችን አቅም ያላገናዘበ የክፍያ ጭማሪዎች ሲያደርጉ እና ወላጆችን ሲያስጨንቁ የት ነበሩ የሚሉ ወላጆች፤ ያኔ ላቀረብናቸው አቤቱታዎች “በዚህ ጉዳይ አያገባንም፣ ነፃ ገበያ ነው….” ሲሉ የነበሩ የትምህርት ቢሮ አመራሮች ዛሬ በእኛ የክፍያ ስምምነት ጉዳይ ወሳኝ ሆነው እንዴት ብቅ ሊሉ ቻሉ ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሌሎች ወገኖች ከሚኒስቴሩ የቀረበው ሐሳብ ከተፈጠረው አስጨናቂ ሁኔታ አንፃር በሚገባ የሚረዱት መሆኑን በማስቀመጥ ወላጅ ከ50 እስከ 75 በመቶ ይክፈል በሚል ጫናውን ወደወላጆች የሚገፋ መመሪያ እንዴት ሊያወጣ እንደቻለ ግን ግራ እንደተጋቡ ይገልፃሉ። ወላጅ ብቻውን ከግማሽ በላይ የት/ቤቶችን ወጪ የሚሸፍነው በምን ምክንያት ሲሉም ጠይቀዋል። ት/ቤቶች በአሁን ሰዓት እያስተማሩ ባለመሆኑ ተማሪዎች ካሉበት ጊዜያት ይልቅ አስተዳደራዊ ወጪዎች ሊቀንሱ እንደሚችሉ የሚታወቅ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪ ወላጆች እስከ 75 በመቶ ወጪ እንዲከፍሉ ከተገደዱ ት/ቤቶቹ ትርፋቸውን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ገቢ እንዲያገኙ የሚረዳ ነው በማለት የሚኒስቴሩን መመሪያ ተቃውመዋል።
ለዚህ ጉዳይ ሲባል ያነጋገርኳቸው ሌላ ወላጅ ሚኒስቴሩ የመጀመሪያና ትልቁ ችግሩ ከ50 እስከ 75 በመቶ ክፍያ ወላጆች ላይ መጫኑ ለሌላ ዙር ውዝግብ እና አለመግባባት ሊዳርግ የሚችል ነው፤ የሚል ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ት/ቤቶች ትልቁን ክፍያ ለማስወሰን፣ ወላጆች ደግሞ አነስተኛውን ክፍያ ለማስወሰን ትግል እንዲገጥሙ የሚያደርግ፣ ምናልባትም ላለመግባባት ሌላ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ተንብየዋል። ከዚህ ይልቅ ወላጆች እና ት/ቤቶች እኩል ችግሩን እንዲካፈሉ በማድረግ ወላጆች ከ50 በመቶ ያልበለጠ እንዲከፍሉ ማድረግ የተሻለ መፍትሔ ነበር ብለዋል።
እ.ኤ.አ በ2018/19 በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር 22 ሚሊየን ገደማ የደረሰ ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ ወጣት በሆነበት አገር ሽፋኑ ገና አነስተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል።ይህ ደካማ የኢንተርኔት ሽፋን ባለበት ወይንም አብዛኛው ሕዝብ ኢንተርኔት የሚባል ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በማያውቅበት ሁኔታ ትምህርትን በኢተርኔት ማሰራጨትን እንደትልቅ አማራጭ አድርጎ ሚኒስቴሩ የተቀበለበት አግባብ ትክክል አለመሆን ብቻ ሳይሆን ሚኒስቴሩ በዚህ ውሳኔው ለትምህርት ባለሀብቶች ያልተገባ ውግንና አሳይቷል በሚል ቅሬታቸውን የሚገልፁ ወላጆች ብዙ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በኢንተርኔት የሚላኩ ማቴሪያሎች ለማየት እና ፕሪንት አድርጎ ለልጆች ለመስጠት በወላጆች ላይ ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትል መሆኑም ሌላው በችግርነት የሚነሳ ነው።
ምን ይደረግ?
ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያውን ከማውጣቱ በፊት ከወላጅ ኮሚቴዎች ጋር ተወያይቻለሁ ብሏል። ሚኒስቴሩ ከእነማን ጋር ምን ተወያየ? ሰዎቹ እንዴት ተመረጡ ? በምን ተስማሙ ? በምን ሳይስማሙ ቀሩ ?… የሚለው ግልጽነት የሚጎድለው መሆኑን ለማየት ሚኒስቴሩ ተማሪዎች ቤታቸው በተቀመጡበት ሁኔታ እስከ 75 በመቶ ወርሐዊ ክፍያቸውን ይክፈሉ የሚል መመሪያ ያወጣበት አግባብ ብቻ ማየት ይበቃል።
የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ተረዳድተን ይህን የፈተና ጊዜ እንለፍ የሚለው ጥቅል ተማጽኖ ተገቢና ትክክለኛ ሆኖ ሳለ ልጆች ላልተማሩበት እጅግ የተጋነነ ክፍያ መጠየቅና ጫናውን ወደወላጆች ጠቅልሎ መውሰድ ለየቅል ናቸው። የኮሮና ቫይረስ ያመጣው ማህበራዊ ምስቅልቅል ያረፈው በት/ቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ከባድ ጠባሳን ያሳረፈ ነው። የእኔ ቁስል ከአንተ ይሻላል ዓይነት አካሄድ ለማንም የሚጠቅም ባለመሆኑ ሚኒስቴሩ መመሪያውን የወላጆችን ጥቅም አንፃራዊ በሆነ መልክ እንዲያስከብር እንደገና ሊፈትሸው ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከመመሪያው አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ችግሮችና አለመግባባቶች ሚኒስቴሩ ኃላፊነትም እንደሚወስድ ሊዘነጋ አይገባም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012 ፍሬው አበበ