በቡራዩ ልዩ ስሙ ከታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢንተማ ትሬዲንግ ንብረት በሆነ የሻማ ፋብሪካ ላይ በደረሰ ቃጠሎ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የተገመተ ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ ድንገተኛና እሳት አደጋዎች መከላከይ ባለስልጣን ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።
ትላንት ሌሊት በግምት ስምንት ሰዓት አካባቢ በተነሳው ቃጠሎ ፋብሪካውና ሁለት የንግድ ሱቆች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ አንድ መኖሪያ ቤት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አቶ ንጋቱ ገልጸው በህይዎት ላይ ምንም አደጋ ያልደረሰ ቢሆንም አንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ላይ ግን ቀላል ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
የእሳቱ መነሻ እስካሁን እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው ለአደጋው መባባስ ምክንያት የሆኑት ለሻማ መስሪያ የሚያገለግለው ንጥረ ነገር ተቀጣጣይ መሆንና ፋብሪካው መኖሪያ ቤት አካባቢ የተገነባ መሆኑ ነው ብለዋል።
የአይን እማኞች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት ለሻማ መስሪያ የሚያገለግለው ንጥረ ነገር እየቀለጠ በአካባቢው በመፍሰሱ አደጋውን እንዳባባሰው ገልጸው የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች በፍጥነት መድረስ ባይችሉ ኖሮ ጉዳቱ ከዚህ የከፋ ይሆን እንደነበር ተናግረዋል።
አደጋውን ለመቆጣጠር ከ217 ሺህ ሊትር በላይ ውሃና ከ 5ሺህ 900 ሊትር በላይ ኬሚካል ፎም መረጨቱን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል።
በተሾመ ተፈራ