ሰዎች የዕድሜና ፆታ ገደብ ሳይኖርባቸው ከሚያዘወትሩባቸው መድረኮች አንዱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የስፖርታዊ እንቅሰቃሴ የሚያደርጉትም ፋይዳውን በሚገባ ከመረዳት ይመነጫል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ሥልጣኔ እና ዘመናዊነት የሰው ልጅ አካሉን ተጠቅሞ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በእጅጉ አራርቀውታል። የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን ተከትሎም በቀላሉ መከላከል በሚችላቸው ነገር ግን ገዳይ ለሆኑ በሽታዎች እየተጋለጠ ይገኛል።
ጥናቶች አንድ ሰው በቀን ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት በእግሩ እንዲጓዝ ይመክራሉ። ከፍተኛ እንቅስቃሴ የማይጠይቀውንና በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ ጉዞን በእግር በመተካት ብቻም በርካታ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል። ዕርምጃ አንዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደመሆኑ ለአካልና ለአዕምሮ ጤና የሚሰጠው ጥቅም በርካታ ነው።
የአካል እንቅስቃሴ እንደ ድብርት፣ ጭንቀትና መደበት ያሉ ስሜቶችን ለማስወገድም ሁነኛ መፍትሔ ነው። ጡንቻንና አጥንትን ለማጠንከር፣ የምግብ መፈጨትን ለማፋጠን፣ የደም ዝውውርን ለማስተካከል እንዲሁም የልብ፣ የደም ብዛት፣ የካንሰር፣… ህመሞችን ለመዋጋትም በየዕለቱ ከ3 እስከ 5ሺ እርምጃዎችን ማዘውተር መልካም እንደሆነም ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። የማስታወስ አቅምን ለማዳበርና ለፈጠራ ሥራዎችም ዝግጁ ያደርጋል። አካባቢን ለመቃኘት እና አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት እንደሚረዳም ያክላሉ።
ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማድረግ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የተረዱ ሀገራትና በጤና ላይ የሚሠሩ ተቋማትም ይህንኑ ጥቅም በመረዳት ህዝቡ በእግር መራመድን እንዲያዘወትር ያደርጋሉ። ከተሽከርካሪ ነፃ የሆኑ ቀናትን በመመደብም ህዝቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ጤናውንም እንዲጠብቅ ያበረታታሉ። ዕድሉንም ይፈጥራሉ።
ይሄንኑ በመረዳት ከሶስት አስርት ዓመታት ወዲህ የእርምጃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቋሚነት እንዲከናወን ቀን ተቆርጦለት ዘንድሮ ለ27ኛ ጊዜ ባለፈው ጥቅምት ወር በተለያዩ አገሮች ተከናውኗል፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ ባሳለፍነው እሁድ ሁለተኛ ጊዜ በተመረጡ 13 ከተሞች በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል። አምስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የእግር ጉዞ በሚታሰበው የእርምጃ ቀን ከ85 ሺ በላይ ሰዎች ተሳታፊ በመሆን በኢትዮጵያ የእርምጃ ቀን ተከብሮ ውሏል።
እለቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት በመዲናችን አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ክለቡ መብራት ኃይል እሰከ ጀሞ ኪሩ ካፌ ከፍተኛ የከተማና የፌዴራል አመራሮች በተገኙበት ስፖርታዊ ትርኢት በመንገድ ላይ እየቀረበ የእግር ጉዞም ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በነፃ የስኳርና የደም ግፊት ምርመራ እንዲሁም የምክር አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ ከ35 ሺ በላይ የመዲናዋን ነዋሪዎች ተሳታፊ አድርጎ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው የእርምጃ ቀን በድሬዳዋም በተለየ ድባብ መከበሩን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በልዩ ሁኔታ እለቱ የተከበረ ሲሆን፣ እለቱን አስመልክቶ መነሻውና መድረሻውን ምድር ባቡር አደባባይ ያደረገ 5 ኪ.ሜ የሚሸፍን የእግር ጉዞ ተካሂዷል ።
በዚህ የእግር ጉዞ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የመከተልና ጤናማ ህይወት የመምራት ልምድ ማጎልበት ለጤና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተረድተን በአካላዊ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት እናድርግ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል:: ሀዋሳም የዚሁ እለት ልዩ ገጽታ እንደነበራት ለማወቅ ተችሏል።
በከተማዋ ከመኪና ፍሰት የፀዱ መንገዶች ቀንን ምክንያት በማድረግ “ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለጤናማ ሕይወት” በሚል መሪ ቃል ዕለቱ የታሰበ ሲሆን፤ በእግር ጉዞው የተለያዩ የመሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ በርካታ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በዕለቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ በተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ፕሮግራሙን በክልሉ ማርሽ ባንድ በማጀብና ሌሎች አዝናኝና አስተማሪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች በማድረግ መከበሩን ለማወቅ ተችሏል:: የተጠቀሱትን ከተሞች ጨምሮ በሌሎች በተመረጡ 13 ከተሞች በደመቀ ሁኔታ የተከበረው ቀኑ፣ የዘገየም ቢሆን፤ በኢትዮጵያ የእርምጃ ቀን ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠይቋል።
በተለያዩ ከተማዎች ባሳለፍነው እሁድ የተከበረው የእርምጃ ቀን ዘርፈ ብዙ ዓላማዎችን ያነገበ ነበር። ከዓላማዎች ውስጥ ጠንካራና ጤናማ አምራች ዜጋን ለማበራከት፣ ለሕክምና የሚወጡ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ኅብረተሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ባህሉ እንዲያደርግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘገየ ሁኔታ ቢጀመርም ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚጓዝ መሆኑ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከስምንት በላይ በሚሆኑ የማይተላለፉ በሽታዎች በየዓመቱ ለሞት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለሞት አደጋ ከሚጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከልም 51 በመቶ ያህሉ ከ40 ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ አምራች ዜጎች ናቸው። ኅብረተሰቡ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል የሚያስችል እንደመሆኑ የእግር ጉዞ እንቅስቃሴው ቀጣይነት ባለው መልኩ መካሄድ እንደሚገባው ይታመናል። ከዚህ በተጓዳኝ የእግር ጉዞው አምራች ዜጋ ለመፍጠር፣ የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚዳብርበት፣ ከዚያም ሲያልፍ ዜጎች ጤንነታቸውን ለመጠበቅና ለመዝናናት እንዲሁም አካልን ለማጎልበትና አዕምሮን ለማበልጸግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው እሙን ነው። ከዚህ በመነሳት በእርምጃ የሚደረገው ስፖርታዊ እንቅሰቃሴው ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ መሥራት አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የእርምጃ ቀን ቀጣይነት ባለው መልኩ መከናወን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
ዳንኤል ዘነበ