ይህ ወቅት በአትሌቲክስ ስፖርት የአገር አቋራጭ ውድድሮች በብዛት የሚካሄዱበት ነው። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻም በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ የተሰጠው የቫሌንሺያ አገር አቋራጭ ውድድር ተካሂዷል። በውድድሩም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ክብረወሰን በመሰባበርም ጭምር አሸናፊ ሆነዋል።
በስፔን ዋና ከተማ በተካሄደው በዚህ ውድድር13ሺ ሯጮች ተሳትፈውበታል። 11ሺ የሚሆኑትም የ10ኪሎ ሜትሩን የመጨረሻ መስመር መርገጥ ችለዋል። እጅግ ብርዳማ በነበረው ጠዋት የተጀመረው የሴቶቹ ውድድር ሊሟሟቅ የቻለው በኢትዮጵያዊቷ እና ኬንያዊቷ አትሌት መካከል በነበረው ፉክክር ነው።
አትሌት ጸሐይ ገመቹ ከስምንተኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ኬንያዊቷን ግሎሪያ ኬትን ጥላት በመሮጥም 30ደቂቃ ከ15ሰከንድ በሆነ ሰዓት የመጨረሻዋን መስመር በመርገጥ አሸናፊነቷን ማረጋገጥ ችላለች። አትሌቷ በአስቸጋሪው የአየር ሁኔታ የገባችበት ሰዓትም የርቀቱን የኢትዮጵያ ክብረወሰን በ15ሰከንዶች ያሻሻለ ሆኗል። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ርቀቱን 30 ደቂቃ30 በመግባት ለዓመታት ክብረወሰኑን የግሏ አድርጋ ነበር የቆየችው።
ፈጣን በነበረው ውድድር እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች በሰከንዶች ብቻ በመበላለጥ ከ31ደቂቃ በታች ነበር የሮጡት። የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርቱ ተፎካካሪ የነበረችው ኬንያዊቷ ግሎሪያ ኬት በበኩሏ በሰከንዶች ዘግይታ 30:26 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ለማጠናቀቅ ችላለች። ኬንያውያኑ አትሌቶች ኢቫሊን ቺርቺር እና ሮስመሪ ዋንጂሩ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ሲይዙ፤ 30:43 እና30:50 ደግሞ የገቡበት ሰዓት ነው። በውድድሩ የተካፈለችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሁነኛው ይስማን ደግሞ ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች።
በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ጫላ ከተማ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻልም ጭምር ድርብ ክብር አግኝቷል። በአንድ ኪሎ ሜትር 2ደቂቃ ከ43 እና 2ደቂቃ ከ45 ሰከንድ በተሮጠው በዚህ ውድድር ላይ፤ የምስራቅ አፍሪካዎቹ አትሌቶች በመምራት ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። ጫላ ከተማ፣ አባይነህ ደጉ እና በተስፋ ጌታሁን ኢትዮጵያን ወክለው፣ በኬንያ በኩል ማቲው ኮፕኮሪር፣ ኤድዋርድ ኪበት፣ ቪዲች ቺሩዮች እንዲሁም በኡጋንዳ በኩል ስቴፈን ኪሳ ከፍተኛ የአሸናፊነት ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩ አትሌቶች ናቸው። የርቀቱ አጋማሽ 13ደቂቃ ከ43 ሰከንዶች በሆነ ሰዓት የተሸፈነ ሲሆን፤ ይህም የቦታው የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት ነው።
ርቀቱን ለማጠቃለል 200ሜትሮች ሲቀሩትም ኢትዮጵያዊው አትሌት ጫላ ከተማ አፈትልኮ በመውጣት27ደቂቃ ከ23ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመጨረስ የቦታውን ክብረወሰን ጨብጧል። የከዚህ ቀደሙ ክብረወሰን የተያዘው በዓለም ሻምፒዮኑ ማርቲን ፊዝ በገባበት31:36 በሆነ ሰዓትም ነበር። ኡጋንዳዊው ስቴፈን ኪሳ በበኩሉ በአንድ ሰከንድ ልዩነት 27:24 ከመጨረሻው ሊደርስ ችሏል። ኬንያዊው ቪዲች ቺሩዮች 27:26 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኝ፤ ኢትዮጵያዊው በተስፋ ጌታሁን ደግሞ 27:39 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆኗል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አባይነህ ደጉ ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
ብርሃን ፈይሳ