በአትሌቲክስ ስፖርት ትልቁ ውድድር ዓለም ሻምፒዮና፤ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ውጤት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ከሚቀመጡት አሥር ሀገራት መካከል ይገኛሉ። ይህም አህጉሪቷ በአትሌቲክስ ስፖርት የተሻለ እንቅስቃሴ አላት ለማለት ያስችላል። የኢትዮጵያ እና ኬንያ ደረጃ ደግሞ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ስላለው የስፖርቱ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ነው። በቀጠናው ስፖርቱን የሚመራው አካልም የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ካሉት ማህበራት ይመደባል።
የማህበሩ አባላት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ መገናኘታቸው ይታወሳል። በስብሰባው ላይም የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ርስቱ ይርዳው፣ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሃማድ ካልካባ ማልቡም፣ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /አይደብልኤፍ/ ተወካይ ጂ ኢስራም፣ የማህበሩ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጃክሰን ቱዋይ እንዲሁም የማህበሩ አባል ሃገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በዕለቱ ከተያዙት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላትን መምረጥ ነበር። በምርጫውም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆና በሙሉ ድምፅ ተመርጣለች። አትሌት ደራርቱ ከዚህ ባሻገርም በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ ማህበሩን በመወከል የቦርድ አባል ሆና ተመርጣለች።
ማህበሩ ከሁለት ዓመታት በፊት በቀድሞው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ ይመራ ነበር። እሳቸው ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚነት መነሳታቸውን ተከትሎም ማህበሩ፤ ጃክሰን ቱዋይ በተባሉት ኬንያዊ በጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሲመራ ቆይቷል።
በቅርቡም በኤርትራዋ አስመራ በተደረገው ጉባኤ ምርጫውን በኢትዮጵያ ለማድረግ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት ባሳለፍነው ቅዳሜ ተካሂዷል። በዚህም ጃክሰን ቱዋይ በፕሬዚዳንትነታቸው እንዲቀጥሉ እና ምክትላቸውም ሻለቃ አትሌት ደራርቱ እንድትሆን ተወስኗል።
በምርጫው የኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ መግባት ሃገሪቷ በዘርፉ ያላትን ተሰሚነት እንደሚጨምር ይጠበቃል። ሃገሪቷ በአህጉር እና በዓለም አቀፎቹ ማህበራት በአመራርነት ለሚኖራት ሚናም የተሻለ መንገድ ይከፍትላታል። ሌላው በአመራርነት የመገኘት ጥቅሙ ተናግሮ የማሳመን እድልን የሚያስገኝም ይሆናል።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር 215 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን፤ በአወቃቀሩ መሰረት አባል ሀገራቱ በስሩ ባሉት ስድስት ማህበራት ይመራሉ። ከማህበራቱ መካከል አንዱ የሆነው ደግሞ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ነው። መቀመጫውን በሴኔጋሏ ዳካር ያደረገውና በካሜሩናዊው ፕሬዚዳንት ሃማድ ካልካባ ማልቡም በሚመራው ኮንፌዴሬሽን ሥርም፤ በቀጠና የተከፋፈሉ አምስት ማህበራት ይገኛሉ።
የመጀመሪያው የሰሜን (ሳህራ) ቀጠና ሲሆን፤ አራት ሀገራትን በአባልነት ይይዛል። በኒጀር ወይም በምዕራቡ ቀጠና ደግሞ 16 ሀገራት ይገኛሉ። የምስራቅ (ናይል) ቀጠና 10 ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ቀጠና 10 እንዲሁም በደቡብ (ካልሃሪ) ቀጠና 14 ሀገራት በአባልነት ታቅፈው ይገኛሉ። ማህበራቱ በቦርድ የሚመሩ ሲሆን፤ የራሳቸው ኮሚቴ፣ ዓመታዊ ስብሰባ እንዲሁም የሚመሩበት መርሃ ግብርም አላቸው። ከዓለም አቀፉ ማህበር በሚመደብላቸው በጀትም ስልጠናዎችን እና ውድድሮችንም ያዘጋጃሉ። የምስራቅ አፍሪካው ማህበርም እነዚህን በመተግበር ከሌሎች የስፖርት ተቋማት አንጻር የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ነው። ኢትዮጵያም ማህበሩን በመምራት ረገድ የተሻለ ተሞክሮ ያላት ሲሆን፤ ወይዘሮ ብስራት ጠናጋሻው እና አቶ አለባቸው ንጉሴ ከዚህ ቀደም በፕሬዚዳንትነት ማህበሩን የመሩ ኢትዮጵያዊት ናቸው።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
ብርሃን ፈይሳ