ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ስሟ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡ በተለይም ማራቶንን ጨምሮ በረጃጅም ርቀት የአትሌቲክስ ዘርፎች የስፖርቱ ቁንጮ ሆና ቆይታለች፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ይህንኑ ክብሯን አስጥብቃለች፡፡ ሆኖም ዛሬ የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ክብሯ በጎረቤት ሀገር ኬንያ ከተነጠቀ ቆየትየት ብሏል፡፡
ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረገፅ ከሰሞኑ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ከአትሌቲክስ ውድድሮች ሁሉ ቁንጮ የሆነው የማራቶን ሩጫ ከከተማ ጎዳናዎች ውጪ እንደዚህም ይካሄዳል ይላል፡፡
ኦይማያኮን የተሰኘችው በሩሲያ የምትገኝ መንደር አማካይ የሙቀት መጠኗ ከዜሮ በታች ከ50 ዲግሪ ሴሊሺየስ ፈቀቅ የማይልና እጅግ ቀዝቃዛ ከሆኑ የዓለማችን ቦታዎች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ በዚህ የተነሳም ሰዎች ለፊታቸው መከላከያ ሳያደርጉ ቢንቀሳቀሱ በሰከንዶች ውስጥ ፊታቸው በቅዝቃዜው ምክንያት ይሰነጣጠቃል፤ በቴርሞ ሜትር ውስጥ የሚገኘው ሜርኩሪ ሳይቀር ይቀዘቅዛል፡፡
መንደሯ ለኑሮ ምቹ ናት ተብሎ ቢታሰብም ቀዝቃዛ የአየር ጠባይዋ ግን ስፖርታዊ ወድድርን ለማካሄድ አደገኛ እንደሆነ ይነገርላታል፡፡ ሆኖም በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ቅዝቃዜዋን ለመጋፈጥ በቆረጡ 16 አትሌቶች አማካኝነት በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቀዝቃዛ ማራቶን ውድድር አካሂዳለች፡፡
ጥር 5 በተካሄደው በዚሁ ውድድር ዕድሜያቸው ከ21 እስከ 71 ዓመት ውስጥ የሚገኙና በደንብ የሰለጠኑ ደፋር ሯጮች ቅልጥም በሚሰብረው የ42 ኪሎሜትር የማራቶን ሩጫ ውድድር ለ 5፣10፣20፣30 እና 42 ኪሎ ሜትር ተፎካክረዋል፡፡
ውድድሩ ሲጀመር የቦታው የሙቀት መጠን ከዜሮ በታች 52 ዲግሪ ሴሊሺየስ በመሆኑ ለሯጮቹ እጅግ ፈታኝ የነበረ ሲሆን የመጨረሻው ተወዳዳሪ 39 ኪሎሜትር ላይ ሲደርስ የሙቀት መጠኑ 4 ዲግሪ ሴሊሺየስ ብቻ ነበር የቀነሰው፡፡
‹‹ቀዝቃዛውን የማራቶን ወድድር ለመታደም ከአውስትራሊያ፣ ታይዋን ፣ጃፓንና ህንድ የመጡ ቱሪስቶች በውድድሩ እጅግ ተደንቀዋል›› ሲል ሳርጂላን ኒዮስትሮይቫ የተሰኘው የውድድሩ ተሳታፊ ገልጿል፡፡
‹‹እጅግ ቀዝቃዛ የማራቶን ወድድር ስናዘጋጅ ይህ የመጀመሪያችን ነው፤ በቀጣዩ ዓመት ሌላ ውድድር በዚሁ ቦታ እናዘጋጃለን፡፡ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ አትሌቶችንም እንቀበላቸዋለን›› ሲልም ተደምጧል፡፡
የማራቶን ውድድሩን ከዜሮ በታች 45 ዲግሪ ሴልሺየስ በሆነ የሙቀት መጠን በማካሄድ ውድድሩ ተቀባይነት እንዲኖረውና አትሌቶች በቅዝቃዜ መሮጥ እንዲለምዱ ማድረግ እንፈልጋለን›› ሲልም ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ ይጎር ብራሞቭ ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
በዚህ ቀዝቃዛ የማራቶን ሩጫ ረጅሙ ኪሎሜትር የተሸፈነው ኢሊያን ፔስቴሬቭ በተሰኘው የኢሚሳ መንድር ኃላፊ ሲሆን፣ እሱም 39 ኪሎሜትር ሮጧል፡፡ የውድድሩ ወጣት ተሳታፊ ደግሞ የሃያ አንድ ዓመቱ ኢኖኬነቲ ኦሌሶቭ ሲሆን 10 ኪሎ ሜትሩን በ 1 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ሲያጠናቅቅ በዕድሜ ትልቁ የውድድሩ ተሳታፊ የ71 ዓመቱ ይጎር ፔርማያኮቭ 15 ኪሎሜትሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ተኩል እንደፈጀበት ዘገባው ገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
አስናቀ ፀጋዬ