‹‹ከኢትዮጵያዊነት በላይ ትልቅነት የለም›› ይላሉ በአገር ፍቅር ልባቸው የቀለጠ ማንነታቸውን የሚወዱ፤ ባህላቸውን የሚያከብሩ። ‹‹ትልቅ አገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ሩህሩህ ዜጋ፣ አስታራቂ፣ ይቅርባይና ይቅርታን ጠንቅቆ የሚያውቅ›› ይሉታል ኢትዮጵያዊና የዚህ ማንነት ባለቤት የሆነውን ማህበረሰብ ሲገልፁት። ለአገሩና ለክብሩ የሚሞት ማኅበረሰብ ያለበትና የሚኖርበት መሆኑንም በሙሉ ልብ የሚያውቁትም ሆነ አብረውት ባህሉን የተጋሩት ሁሉ ይመሰክሩለታል።
ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ ብዙ ነው። ለውጭው ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ እና ያለስስት ይሄን ውብ ማንነት ማጋራት ግን ገና የሚቀር የቤት ስራ ነው። ኢትዮጵያዊ ደስታውና ጭፈራው ብቻ ሳይሆን ሐዘኑ ለቅሶው ያምራል። አደጉ የተባሉ አገሮች እንደ ጃፓን፣ ቻይናና ሌሎችም ባህላቸውን ይዘው የአያቶቻቸውን ቤት አሰራርና አልባሳት ከሽፈው አድገዋል። እዚህ ይሄን የመሰለ ጥንካሬ ይጎላል። በኢትዮጵያ የአገራችንን ልብስ ማሳደግ እየቻልን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ ልብስ እናስገባለን።
የተለያዩ ባህሎቻችንና አውድዓመቶቻችንን ማስተዋወቅ ሲገባን እዚህ ላይ ግን ስንፍናው በግልፅ ይታይብናል። በባህላዊ ልብሶቻችን ከመኩራት ይልቅ ዘመናዊነቱ በልጦብን በባህር ማዶው ባህል እስከ አንገታችን ድረስ እየተዋጥን ነው። ይህም ሆኖ ግን አያት ቅድመ አያቶቻችን ያወረሱን ድንቅ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ታሪካዊ እሴቶቻችንን አሁንም ከኛ ጋር አሉ። ጭርሱኑ ሳይጠፉ ትውልዱን የሚያስመሰግን ሃላፊነት ተወጥቶ ያለውን መጠበቅ፣ ሳይበረዝ ማሳደግ እንዲሁም በዓለም መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ እንዲታይ የማስተዋወቅ ሃላፊነት መወጣት ይኖርብናል።
ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ ካሉ የሰው ልጆች ለየት የሚያደርጓቸው በርካታ እሴቶች አሏቸው። ከነዚህ መካከል ቀልብን በሚስብ ሁኔታ የሚከበሩት አውደ ዓመቶች እና የሃይማኖት ስነ ስርአቶች ይጠቀሳሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የሚያከብሯቸው በዓላት ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ገና፣ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ደብረ ታቦር እንዲሁም ሌሎች በዓላትን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። እነዚህ በዓላት ከሃይማኖታዊ ስርአት ባሻገር ባህላዊ ይዘታቸው እራሱ ማህበረሰቡንም ሆነ የሌሎች ክፍለ ዓለማት ዜጎችን ቀልብ የሚይዙ ተወዳጅ ስነስርአቶች ናቸው።
ትንሳኤ
ዛሬ ሚያዚያ 11 ነው። ይህ ቀን ከሁሉም ለየት የሚያደርገው ደግሞ አንድ ነገር አለ። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳኤ በዓል ነው። ላለፉት 55 ቀናት በፆም በፀሎት እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የተቀበለውን መከራ እንዲሁም ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን ትንሳኤ በልዩ ድምቀት የሚዘክሩበት ነው።
ባለፉት ዘመናት ይህ በዓል በተለይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ ደማቅ በሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነስርዓት እየተከበረ እዚህ ደርሷል። በተለይ ዓመት አልፎ ሚያዚያ ከተፍ ባለ ቁጥር የሃይማኖቱ ተከታዮች በኢትዮጵያዊ ባህል ስነስርአት ታጅበው ቀኑንና ወሩን ደማቅ ያደርጉታል። ዘመድ አዝማድ የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ይጠያየቃል። ህፃናት አዋቂዎች እንዲሁም እናቶች በባዕላት ልብስ ደምቀው ቀኑን በደስታና በጨዋታ ያሳልፉታል። ይህ ብቻ ሳይሆን በባህሉ መሰረት የተቸገሩን መጠየቅ መረዳዳትና ቤት ያፈራውን ከጎረቤት ጋር ተጠራርቶ መቃመስ የዚሁ ስነ ስርአት አካል ነው።
ለዛሬ በስፋት የትንሳኤ በዓልና ወቅታዊ ጉዳይን ለማንሳት ወደናል። ከዚያ በፊት ግን በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የትንሳኤ በዓልና ቅድመ ዝግጅቶቹ ምን እንደሚመስል ለመመልከት ፈቅደናል። ይህ ልዩ በዓል ይበልጥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአቱን ጠብቆ የሚከበረው በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ ልዩ ስነስርአቱን አጉልቶ ሊያሳይ የሚችል አንድ ስፍራ መርጠን ።
ትንሳኤና ተጉለት
በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ የሰሜን ሸዋ ዞን ስር በሚገኘው ተጉለት ለክብረ በዓላት ልዩ ክብርና ትኩረት የሚሰጥ ቢሆንም፣ ፋሲካ ግን የተለየ ነው። ፆሙ ሲገባ ጀምሮ የእምነቱ ተከታዮች ቀኖናውና ዶግማው የሚያዘውን ቢፈጽሙም፣ ከሁሉም በላይ ከልብ ተቀብሮ ከትውልድ ትውልድ እየተተገበረ፣ ለልጅ ልጅ እየተላለፈና እየተነገረ ትዝታን ቋጥሮ የሚቀረው ባህሉ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የፋሲካ አከባበር ልዩ ሥነ ሥርዓትም አለው።
የፋሲካ ፆም እንደገባ ልዩ ሙክት የበግ ወይም የፍየል ማዘጋጀት በዓሉን ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ነው። ሙክቱ ከሌሎች ከብቶች ተለይቶ ስንዴ እየበላ እንዲደልብ ይደረጋል። ሰው ሲወጣ ሲገባም ለብቻው ታስሮ የሚቀለበውን ሙክት እያየ የፋሲካን መምጣት በጉጉት ይጠብቃል።
በህማማት ህልበት የሚበላበትም ነው። ፀሎተ ሐሙስ ደግሞ ጉልባን። ከልምድ እንዳየውም በተወለደበት አካባቢ ሰሞነ ህማማትን ለየት የሚያደርገው ‹‹የይቅርታ ሳምንት›› መሆኑ ነው። የስግደት ቀንና ‹‹የቀዳም ሱር›› ቀን ያለው የዋዜማ ድባብ ደግሞ ልዩ ነው። እናቶች ለአከፋዮች ተልባ ወቅጠው የሚያዘጋጁበት፣ ልጆች፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ዶሮ እስኪጮህ የመፈሰኩን ዜና በጉጉት የሚጠብቁበት ነው።
ልጆች ቅዳሜ ለእሑድ ሌሊት ዶሮ እስኪጮህ ከእናታቸው ስር ስር እያሉ ያግዛሉ እንጂ በፍፁም አይተኙም። ለምለም ሳር ፍለጋ መሄዱ፣ እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀቱም የበዓሉ ሥራ ነው። በተለይ ለፋሲካ የሚዘጋጀው እንጨት የተለየ ነው። ጅረት ወርዶ ‹‹የርግጣ እንጨት›› ማለትም ጭስ የሌለውና አጥንት ቶሎ የሚያበስል እንጨት ይዘጋጃል።
ልጃገረዶች ቤት በአዛባ ለቅልቀውና በአፈር ቀለም ነቅሰው ቤት ያስጌጣሉ። በሰሞነ ህማማት ደግሞ ድባቡ የተለየ ነው። አንዳንድ አካባቢ ሴቶች ራሳቸውን በሻሽ አስረው እስከ በዓሉ አይፈቱም። በባዶ እግር የሚሄዱም አሉ። በተጉለት ይህ ባይኖርም፣ ሳምንቱ የይቅርታ ነው። በአካባቢው በተለይ የተጣሉና የተቀያየሙ የሚታረቁትና ይቅር የሚባባሉት በሰሞነ ሕማማትና በጳጉሜን ነው።
ከአክፍሎት በኋላ የሚከበረው ፋሲካ ዘመድ የሚሰበሰብበት ያለው ከሌለው የሚካፈልበት፣ ሙክት የሚታረድበት ነው። አርሶ አደሩ ሲሠራ ከርሞ እፎይ ብሎ ከቤተሰቡ ጋር እንኳን አደረሳችሁ የሚልበት፣ የደከመበትን አጣጥሞ የሚበላበትና የሚጠጣበት የሚናፈቅ በዓል ነው። ከፋሲካ እስከ ዳግማ ተንሳይ ያለው ሳምንት ዘመድ ከዘመድ የሚገባበዝበት፣ በየቤቱ ከብትና ሙክት የሚታረድበት ነው።
ትንሳኤና ሰሞነኛው ኮሮና
ወቅታዊ ጉዳያችን ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ነው። ቫይረሱ የሰው ዘርን በሙሉ እያስጨነቀ በሽምጥ ግልቢያው መላውን ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል። ነገ ምን እንደሚፈጠር ባናውቅም እስካሁን ባለው መረጃ ሊገታው የሚያስችል አንዳችም ፍቱን መድሃኒት አልተፈጠረለትም። ሆኖም ካለፈው የሰው ልጅ ልምድና ኑረት እንደምንረዳው ይህን ጊዜ በድል እንደሚያልፍ ነው። እስከዚያው ግን እንደ ማስታገሻ አንዳች ሌላ መፍትሄ የሚያሻ ይመስላል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ አይነት ዓለም አቀፍ ተዛማች በሽታዎች ቀጥታ ታማሚውን ከማጥቃትና ለሞት ከመዳረግ ባሻገር የሰው ልጅ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ያስከትላሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የተቀረው የሰው ልጅ ‹‹ነገ እኔስ ምን እሆናለው›› በሚል የፍራቻ ጢሻ ውስጥ ተደብቆ በጭንቀት፣ በድብርትና ውጥረት አረንቋ ውስጥ እንዲሸሸግ ማድረጋቸው ዋነኛው ነው። የተለመደውን የየእለት የኑሮ ኡደት በማዛባት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማዳከምና እንቅስቃሴን በመግታት ለስነ ልቦና ውጥረትና ቀውስ መዳረግ አንዱ ባህሪያቸው ነው። አሁን ላይ የምናስተውለው የኮሮና ቫይረስ ዳፋም የዚሁ ባህሪ መገለጫ ነው።
ይህ ተዛማች ቫይረስ የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ በዚህ ብቻ የሚገደብ አይደለም። በተለይ ማህበረሰቡ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ ስርዓት ላይ ጫና ያሳድራል። ያለፉትን ሳምንታት የታዘብነውም ይህንኑ ነው። ወቅቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የአብይ ፆም ላይ የነበሩ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እንዳይስሙና የተለያዩ ስርዓቶችን እንዳይፈፅሙ እንቅፋት ሆኖ ተመልክተናል። ይሄ በማህበረሰቡ ላይ ያሳደረው ጫናም በቀላል የሚተመን አይደለም። ቫይረሱ በቀላሉ መፍትሄ የሚገኝለት ካለመሆኑ የተነሳም ተፅዕኖው ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ነው። የሃይማኖት አባቶችም ሆነ ምእመኑ ወቅታዊውን ችግር ተገንዝበው ራሳቸውን ከማህበራዊ መቀራረብ እየገደቡ መሆኑ መልካም ነው። ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝለት በሰው ንክኪ የሚተላለፈውን ገዳይ ቫይረስ ባህሪውን ተረድቶ ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው።
ይህ ከሆነ ብቻ ነው ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን እንደለመዱት ውብ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአታቸውን መከወን የሚችሉት። ለጊዜውም ቢሆን ግን የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤን የሚፈትነውን የኮቪድ ቫይረስ ለመከላከል ከለመድነው መንገድ ወጣ ማለት አስፈላጊ ነው።
የሰውን ልጅ የስልጣኔና የዘመናዊነት ግስጋሴ በየጊዜው ለመገደብ የሚሞክሩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያቶች ይከሰታሉ። ከነዚህ መካከል የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ድርቅ፣ ጦርነትን ጨምሮ ሌሎችም በምሳሌነት ይነሳሉ። ከሁሉም በከፋ ሁኔታ ግን እንደ ተዛማች በሽታ የዚህን ሰብአዊ ፍጡር ህልውና የፈተነው የሚገኝ አይመስልም።
ጥንቃቄና አውደ ዓመት
‹‹ጥንቃቄ ይጠብቃል ማስተዋልም ይጋርዳል›› ይላል ታላቁ መፅሃፍ ቅዱስ። ከላይ በስፋት እንደዳሰስነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን ከዚህ ቀደም በደማቅ ሁኔታ ነው የሚያከብሩት። እለቱ ከመድረሱ በፊትም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የአምልኮ ስርአት ከመፈፀም አንስቶ ለበዓሉ ዝግጅት ወደ ገበያ ይወጣሉ።
በዋዜማው ዶሮ፣ በግ፣ ፍየል፣ በሬ ይገዛል። ለእለቱ የሚሆኑ የምግብና የበዓሉ ማድመቂያ ቁሳቁሶችም እንዲሁ። በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ይሄን ማድረግ ግን በእጅጉ ለአደጋ የሚያጋልጥ ሆኗል። ዋናው ምክንያት ደግሞ በንክኪ ምክንያት ከሰው ወደሰው የሚተላለፈው ቫይረስ ቀዳሚው የዓለማችን ስጋት በመሆኑ ነው።
ምንም እንኳን ወቅቱ የምንወደውንና እምነታችን እንድናደርግ የሚፈቅደውን ስርዓት እንዳናደርግ የሚከለክለን ቢሆንም ዛሬ ላይ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክር መቀበላችን እራሳችንንና ቤተሰባችንን የምንጠብቅበት ብቸኛው አማራጭ ነው። ከዚህ ድርጊት መታቀብ በቀጣዩ ጊዜ ተወዳጁን የሃማኖትና ባህላዊ ስርዓት እንድናከብር ያግዘናል። በዚህ ምክንያት ከቤታችን በተቻለን መጠን ሳንወጣ፣ ንክኪ ከሚበዛባቸው ስፍራዎች ርቀን ነገ በእጅጉ የሚጠቅመንን ጤናችንን መጠበቅ ይኖርብናል።
ትንሳኤን እንዴት እናክብር?
ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፤ ዘመናት ነጉደው በአዲስ ሲለወጡ፤ በተመሳሳይ የሰው ልጅ በየፈርጁ የኑሮ ዘይቤውን፣ አመለካከቱን እና የስልጣኔ ደረጃውን ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደመ እንደሚቀያየር ማመን ይኖርብናል። ይህ ብቻ አይደለም። በተፈጥሮ ኡደት የሚከሰቱ አስቸጋሪ ለውጦችን የሚቋቋምበት ብልሃትም እንደሚዘይድ ማወቅ ያስፈልገናል። ስሪቱም እራሱን ከሁኔታዎች ጋር አላምዶ እንዲኖር ይፈቅዳል። ይህ ስጦታው ደግሞ በርካታ ዘመናትን አሻግሮ አሁን ያለንበት አስደናቂ የኑሮ ደረጃ ላይ አድርሶታል። ዛሬም ይህንኑ ባህሪ መድገም ያስፈልጋል።
እለቱ ተወዳጁን በዓል የምናከብርበት መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን በደስታ ውስጥ ሆነን ነገን መካን ማድረግ አይኖርብንም። ለዚህ ነው የትንሳኤ በዓልን ስናከብር እነዚህን የጥንቃቄ መልዕክቶች ተቀብለን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል የሚል መልክት በመጨረሻ ላይ ለማስተላለፍ የምንወደው።
የመጀመሪያው ጉዳይ የኮቪድ 19 ተዛማጅ ቫይረስ በንክኪ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ከመሆኑ አንፃር እራሳችንን ከዚህ ተግባር መቆጠብ ይኖርብናል። በቀጣይ አላስፈላጊ የሆኑ ጉዞዎችን መሰረዝም ተገቢ ነው። እለቱ ከዚህ ቀደም እንደምናደርገው ዘመድ አዝማድ የምንጠይቅበት አውደ ዓመት ቢሆንም ለዛሬ ግን እግራችንን ሰብሰብ ልናደርግ ይገባል። ይህን ተግባር ለመፈፀም ሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል።
ሌላውና የመጨረሻው መልዕክት የሚሆነው መረዳዳትና መደጋገፍን በሚመለከት ነው። ወቅቱ ከምንም ጊዜ በተለየ በአገሪቷ ዜጎች ኢኮኖሚ ላይ ጫና ያሳደረበት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ከኛ ያነሰ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጎረቤቶቻችንንና የተቸገሩ ወገኖቻችንን መደገፍ ያስፈልጋል። በተለይ በየጎዳናው ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ጥንቃቄ በተሞላበት በዓሉን የሚያከብሩበት እንዲሆን ልናግዛቸው ይገባል እንላልን። መልካም የትንሳኤ በዓል።!
ዳግም ከበደ