የሰው ልጅ ሁሉ ንጹህ ሆኖ ነው የተፈጠረው። በልቡ ክፋትና ጥመትን የሚማረው በምድር ላይ መኖር ሲጀምር ነው። ሌቦችንና ዘራፊዎችን ሲያይ መስረቅን፤ አፈ ጮሌዎችን ሲመለከት የምላስ አክሮባት ይማራል። ከአይን አውጣዎች ጋር ሲቀራረብ ክብርና ጨዋነት በአፍጢማቸው ይደፋቸዋል። በዚህ መሀል ግን የበጎነት ማሳያ የሚሆኑም እንደማይጠፉ መዘንጋት የለበትም። ደግነትን የሚሰብኩ፣ ሰላምን የሚቀድሱ፣ ምቀኝነትን የሚያወግዙ ፋና ወጊዎች በሽበሽ ናቸው። ታዲያ ወደ እነዚህ ንጹሃን የቀረበ ሰው ርሕራሔን፣ ትሁትነትን፣ ቅንነትንና አደራ ጠባቂነትን መማሩ የማይቀር ነው። እንዲህ ያሉ ወገኖች በሰው ልጅ ልቦና ውስጥ የጥፋት እሳት እንዳይቀጣጠል ስሜቱን በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ደንቦች ያለዝቡታል።
የሰው ልጆችን ማህበራዊ ህይወት በማሳካት ረገድ “ሞራል” ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ለዚህ ነው የዓለም ህዝቦች ሁሉ ባለፉባቸው ረጅም የታሪክ ጎዳናዎች የሞራል ደንቦች እያዳበሩ አሁን ላይ የደረሱት። የሞራል ደንቦች የሚያዙትን ‹‹አድርግ አታድርግ›› የሚሉ ህግጋቶችን የሰው ልጆች በትክክል ቢያደምጡና ቢተገብሩ ማህበረሰቡን እያሸበሩና እየጨረሱ ካሉ ጦርነቶች፣ ስደቶች፣ እንዲሁ እንደ ኮሮና ካሉ ወረርሽኞች ማምለጥ ይቻል ነበር የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሙሉ ለሙሉ ይሆናል ባይባል እንኳን የጉዳቱን መጠን መቀነስ ይቻላል ። ≪ለሁሉ ጊዜ አለው≫ እንዲል መጽሐፉ ሁሉም ሰው ጊዜው የሚጠይቀውን ሰው በመሆን ራስን በማስገዛት ጊዜ ካመጣብን ቁጣ ማምለጥ ይቻላል። ይህን ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝ አንድ ታሪክ ሊዮ ቶልስቶይ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል አጋርቶን ነበር። ለንባብ በሚመች መልኩ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርብላችኋለሁ።
ከብዙ ዘመናት በፊት የአንዲት አገር መሪ ንጉስ ነበር። ይህ ንጉስ ነገሮች የሚጀምሩበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ፤ ሊያዳምጣቸው የሚፈልጋቸውን መለየት፣ ጆሮ ሊሰጣቸው የማይገቡትን መለየት መቻል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ማድረግ ያለበት እጅግ ጠቃሚ የሆነውን ነገሮች ሁሌም ቀድሞ ቢያውቅ ይመኝ ነበር። ይህን ፍላጎቱን የሚያሟላለትና እውቀቱን የሚያስተምረውን ሰው መፈለግ ጀመረ። በግዛቱም አዋጅ አስነገረ። ይህን ለሚያደርግ ሽልማት እንደሚሰጥም አሳወቀ።
በጊዜው የነበሩ ጠቢባን ‹‹እንዲህ ብታደርግ፤ እንዲያ ቢሆን ›› እያሉ ከንባብም ከህይወታቸውም የተማሩትን ለንጉሱ አሳወቁ። ንጉሱ ግን የአንዳቸውም ምክር ልቡን ሊገዛው ጆሮውን ሊሞላው አልቻለም። በድንገት ግን ከዚህ ቀደም ሲል የህይወቱን እንቆቅልሽ የፈታለት በከተማ ዳር የሚኖር አንድ መናኝ እንደነበር አስታወሰ። ባለሟሎችን ሳያስከትልም በፍጥነት ወደዚህ ጠቢብ ቤት አቀና። መናኙ ንጉሱ ፈልጎ ሲያገኘው መሬት እየቆፈረ ነበር። ንጉሱ ከርሱ ጋር በተገናኘ ቅፅበት ‹‹ሦስት ጥያቄዎችን እንድትመልስልኝ ነበር ወደ አንተ የመጣሁት›› ብሎ ጥያቄዎቹን ይነግረዋል። መናኙ ንጉሡን ያለውን አዳመጠ ግን መልስ አልሰጠውም።
እጁን በምራቁ አሸት አድርጎ ቁፋሮውን ቀጠለ። “ደክሞሃል” አለ ንጉሡ “አካፋውን ስጠኝና ትንሽ ልቆፍርልህ።” አለው መናኙም “አመሰግናለሁ!” ብሎ አካፋውን ሰጥቶት መሬት ላይ ተቀመጠ። ንጉሱ መናኙን እያገዘ ሳያውቀው አንድ ሰዓት አለፈ። ፀሐይ ከዛፎቹ ጀርባ መጥለቅ ስትጀምር፤ አካፋውን መሬት ላይ ተክሎ እንዲህ አለ፤ “ወደ አንተ የመጣሁት ለጥያቄዎቼ መልስ ፈልጌ ነበር። ምንም መልስ የማትሰጠኝ ከሆነ ንገረኝና ወደ ቤቴ ልመለስ።” በዚህ ቅጽበት አንድ ሰው ከጫካ ወደ ንጉሱ እየሮጠ ሲመጣ ተመለከተ። ሰውየው ሆዱን በእጆቹ ጫን አድርጎ ይዟል፤ ደሙ እየፈሰሰ ነበር። ንጉሡ ጋር ሲደርስ፣ እያቃሰተ፣ ራሱን ስቶ ወደቀ።
ንጉሡና መናኙ ልብሱን አወለቁለት። ሆዱ ላይ ትልቅ ቁስል ነበር። ንጉሡ በደምብ ካጠበው በኋላ በመሀረብና በመናኙ ፎጣ አሰረለት። በመጨረሻ ደሙ መፍሰስ ሲያቆም ሰውየው ሕይወት መዝራት ቻለ። የሚጠጣ ነገርም እንዲሰጡት ጠየቀ። ንጉሡ ንጹሕ ውሀ አምጥቶ ሰጠው። ፀሃይ በመጥለቋ አየሩ ቀዝቅዛ ነበር። ሁለቱም ቁስለኛውን ተሸክመው ወደ ጎጆዋ ካስገቡት በኋላ፣ እነርሱም ደክሟቸው ስለነበር ጥግ ላይ ተኙ። በነጋታው ማለዳ “ይቅር በለኝ!” አለ ጢማሙ ሰው በደከመ ድምጽ፤ ንጉሡ መንቃቱን እየተመለከተው እንደነበር አይቶ።
ንጉሱም “አላወቅኩህም፤ እናም ይቅር የሚያስብል ምንም ምክንያት የለም” አለ ንጉሡ። “አታውቀኝም፤ ነገር ግን እኔ አውቅሀለሁ። ወንድሙን በመግደልህና ንብረቱን በመውረስህ ምክንያት ሊበቀልህ ቃል የገባው ያ ጠላትህ እኔ ነኝ። መናኙን ለመጎብኘት ብቻህን እንደሄድክ አውቅ ስለነበር ስትመለስ ልገድልህ ቆርጬ ነበር። ነገር ግን ቀኑም መሸ፣ አንተም አልተመለስክም። ስለዚህ ካደፈጥኩበት ወጥቼ ስፈልግህ፣ ከጠባቂዎችህ ጋር ተገጣጠምንና አስታወሱኝ፤ ከዚያም አቆሰሉኝ። ከነሱ አመለጥኩ፤ ነገር ግን አንተ ቁስሌ ላይ ጨርቅ ባታስርልኝ ኖሮ ደሜ ፈስሶ እሞት ነበር። ልገድልህ እመኝ ነበር፤ አንተም ሕይወቴን አተረፍካት። አሁን መኖር ከቻልኩ፣ የአንተም ምኞት ከሆነ፣ ልክ እንደ ዋና ታማኝ ባሪያህ አገለግልሀለሁ። ልጆቼም ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ እጠይቃቸዋለሁ። ይቅር በለኝ!” ንጉሡ ከጠላቱ ጋር እንዲህ በቀላሉ ሰላም በመፍጠሩና ጓደኛም በማድረጉ እጅግ ደስ አለው። ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን የግል ሃኪምና አገልጋዮቹም እንዲንከባከቡት እንደሚያደርግ፣ ንብረቱንም እንደሚመልስለት ቃል ገባለት።
ንጉሡ ቁስለኛውን ትቶ ወደ ውጭ ወጣና መናኙን ይፈልግ ጀመር። ከመሄዱ በፊት ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለመን ተመኘ። መናኙ ውጭ ተንበርክኮ ከአንድ ቀን በፊት በተቆፈሩት መደቦች ላይ ዘሮች እየተከለ ነበር። ንጉሡ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለው።
“ብልሁ ሰው፤ ለመጨረሻ ጊዜ ጥያቄዎቼን እንድትመልስልኝ እፈልጋለው” ሲል መናኙም “አስቀድሞ ተመልሶልሀል!” አለው መናኙ – በቀጫጭን ቅልጥሞቹ ላይ ቁጢጥ እንዳለና ፊት ለፊቱ የቆመውን ንጉሥ ቀና ብሎ እያየ። “እንዴት ነው የተመለሰልኝ? ምን ማለትህ ነው?” ንጉሡ ጠየቀ። “አታይም እንዴ” መናኙ መለሰ፤ “ትናንት ደካማነቴ ባያሳዝንህና መደቦቹን ሳትቆፍርልኝ ተመልሰህ ቢሆን ኖሮ ያ ሰው ጥቃቱን ያደርስብህና ከኔ ጋር ባለመቆየትህ ትጸጸት ነበር። ስለዚህ መደቦቹን ስትቆፍር የነበርክበት ጊዜ እጅግ ከሁሉም የበለጠው ትክክለኛ ጊዜ ነበር፤ እኔ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ አስፈላጊው ሰው ነበርኩ፤ ለኔ ጥሩ ማድረግህ ደግሞ ከሁሉም የምታስቀድመው ነገር ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ያ ሰው ወደ እኛ ሮጦ ሲመጣ እንክብካቤ ያደረግክበት ጊዜ ከሁሉም የበለጠው ትክክለኛ ጊዜ ነበር፤ ምክንያቱም ቁስሉን ባታሽግለት ኖሮ ከአንተ ጋር ሰላም ሳይፈጥር ይሞት ነበር። ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው የመጣብንን ቁጣ በብዙ ማብራራት እና ዛቻ ማሸነፍ አንችልም፤ ይልቅ የምንባለውን በማድረግ ራስን በመግዛት አሁን ያለውን እና ከዚህም በኋላ በህይወታችን ሊከሰቱ ያሉትን ፈታኝ ጊዜያት ማለፍ እንችላል›› በማለት ለጥያቄው አጥጋቢ መልስ ሰጥቶ ወደ አሰናበተው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ