«ያደረኩት ስላለኝ ሳይሆን ስለተደረገልኝ ነውመስጠት መሰጠት ነው።» የሚል እምነት አላቸው። ስለዚህም ሁልጊዜ ለተቸገረ መድረስ እንዳለባቸው ራሳቸውን አሳምነዋልይሄ ደግሞ ውስጣዊ ደስታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ የሚደረገው ነገር ለአገርና ወገን ሲሆን ደግሞ የተለየ ስሜት እንዳለው ይናገራሉ።
ከቁስ በላይ ስብዕናን ያስቀድማሉ፡፡ በዚህም በቤት ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን ከልጆች እኩል ስፍራ ሰጥተው ይንከባከባሉ፡፡ ባለሀብትነት ለእርሳቸው ለተቸገሩ መድረሻ እንጂ ዝናን ማትረፊያ አይደለምና ሁሌም በጎ ተግባር ሲያደርጉ «ቀኝ ሲሰጥ ግራ አይመልከት» የሚለውን ሀሳብ መከተል ይሻሉለሌሎች ሲደርሱ እንዲነገርላቸው አይሹምዛሬ እንኳን ትንሽ አድርጎ ብዙ እንዲነገርለት በሚፈለገው ጊዜ እርሳቸው ስጦታዬን አምላክ ይይልኝ በማለት ነው ተሸሽገው ያሉት።
ከበጎነት ማትረፍ እንደሚቻል እርስ በርስ መማማር አለብን ከእርስዎም ሰዎች ብዙ ነገር ይማራሉ፡፡ እናም ለማስተማር ፈቃድዎ ከሆነ የህይወት ተመክሮዎትን ያጋሩን ባልናቸው መሰረት ነው ፈቃዳቸውን የሰጡንየዛሬው ‹‹የህይወት እንዲህ ናት›› አምድ እንግዳችን አቶ ዳኜ ዳባ።
ብቸኛው ልጅ
አባታቸውንም ሆነ እናታቸውን በእድሜ ከፍ እስኪሉ ድረስ አያውቋቸውምእድገታቸው በአያታቸው ቤት ነውበእርግጥ አባት ለቤተሰቡ ብቸኛ ናቸውስለዚህም አቶ ዳኜም ለዚያ ቤተሰብ ብቸኛ ሆነው አድገዋልሁሉ ነገር የእርሳቸው ነውወተቱን ትኩስ ምግቡን አባወራው ሳይቀምሰው ለእርሳቸው ይሰጣልግን ምን ያደርጋል በአዛውንቶች ቤት በመኖራቸው የሚፈልጉትን የማድረግ አቅሙ አልነበራቸውም፡፡ በአቅማቸው ምክንያት መሬቱ የሚታረሰው በመጋዞ በመሆኑ የሚደርሳቸው እህል ጥቂት ነውበዚህም ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ እንደነበር አይረሱትም፡፡ እንዳውም ከሰፈሩ ሁሉ ችግረኛ እኛ ብቻ ነበርን ይላሉይሁንና ቤተሰቡ ባለው ደስተኛ በመሆኑ የልጅ ልጃቸውም በመልካም ስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ አድርገዋል።
በምዕራብ ሸዋ ግንደበረት የተወለዱት እንግዳችን፤ አባታቸው በኢትዮ ሱማሌ ጦርነት እንደተለዩዋቸውና እናታቸው ብቸኛ ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸው ስለወሰዷቸው የአባታቸው ቤተሰቦች ብቸኛ የልጅ ልጃቸውን አያቶች ለማሳደግ ወስደዋል፡ እናትም ሆነ አባታቸው አያቶቻቸው ይመስሏቸው እንደነበር እና በአያት እጅ እያደጉ መሆናቸውን ከፍ ካሉ በኋላ እንዳወቁም አጫውተውናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ እናቶች በተለይ ልጆቻቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ያስረዳሉም ክንያቱም የእናት ፍቅርን ሳያዩ በማደጋቸው እናታቸውን እንደማንኛውም የቤተሰቡ አባል እንዲመለከቷቸው አድርጓል።
በአብዛኛው አርሶአደር ቤት እንደሚሆነው ሁሉ የክረምት ወቅት ጎተራ ይራቆታልበዚህም ጊዜ ርሀብ የጎበኛቸው ጊዜያት በርከት ይሉ እንደነበር ያስታውሳሉይህ ደግሞ ገና ባልጠነከረ ጉልበታቸው ሥራን እንዲለማመዱ እንዳደረጋቸውም አይረሱትምበተለይ ቤተሰቡ የሚኖርበት የግብርና ሥራ የእርሳቸው ኃላፊነት ሆኖ ነበር።
እረኝነቱ፤ ከዚያም አልፎ መላላክና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን በቻሉት መጠን መከወኑም ቤተሰቡን የሚያግዙበት ሌላው የሥራ ድርሻቸው ነበር፡፡
ጎረቤት አባትና ቤተሰብ በሆነበት አካባቢ በማደጋቸው ማንንም በስማቸው ጠርተው እንደማያውቁ የሚያወሱት አቶ ዳኜ፤ ብዙዎችን ባዳም ቢሆኑ አጎቴ ፤ ሴቶቹን ደግሞ አክስቴ እያሉ እንደሚጠሯቸው ያስታውሳሉ።
‹‹ችግር ብዙ ነገሮችን ያስተምራል›› የሚሉት እንግዳችን፤ ዛሬ ድረስ የእርሻ ሥራ ላይ ውጤታማ የሆኑት የዛን ጊዜ በነበራቸው ታታሪነት እና ስራ ወዳድነት እንደነበር ይገልጻሉልጅነታቸው ታዛዥና ቀና ሆነው እንዲያድጉ እንዳስተማራቸው ያወሳሉ ቀናነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ከእንስሳት ጭምር አይተዋልከብት በሚያግዱበት ጊዜ ከብቶቹን በስማቸው ሲጠሯቸው ይመለሱላቸዋል፡፡ከዚያም ባሻገር በሚገባ እንዲመገቡ ስለሚያደርጓቸው ላሞቹ ቤት ገብተው በቂ ወተት ይሰጣሉይህ ደግሞ ትንሹን ዳኜ ከማስመስገን አልፎ የአካባቢው እናቶች ወተት ይሰጧቸው እንደነበር አይረሱትም።
በቤተሰቡ ዘንድ የተለያየ ስም የተሰጣቸው አቶ ዳኜ፤ ሴት አያት ተስፋዬ ይሏቸዋል። ምክንያቱ አባታቸው ስለሞቱ ተስፋዬ አንተ ነህ ነውወንድ አያት ደግሞ ሺመልስ ይሏቸዋል፡፡ ብዙውን ነገር መክተው እንደሚመልሱ በመመኘት ነውአንዳንድ ዘመዶች ደግሞ ‹‹ቦሮ›› ወይም የነገ ሰው የሚልም ስም አውጥተውላቸዋል ይህ ደግሞ ቤተሰቡ አንዳንድ ልጅ ብቻ ያላቸው በመሆናቸው ነገን የሚያበዛ የሚለውን በማሰብ እንዳወጡላቸው ይናገራሉ።
ብዙ ጊዜያቸውን በጨዋታ የሚያሳልፉት ባለታሪኩ፤ ከጨዋታ ሁሉ እግር ኳስን አጥብቀው ይወዱ ነበርበዚህም በፍቅር ከጓደኞቻቸው ጋር ከመጫወት ውጪ አንድም ቀን ተጣልተው አያውቁም
‹‹ጨዋታ ዋጋ አይተመንለትም እናም ከልጅነቴ የምወደውና ዛሬ ድረስ ቢኖረኝ ብዬ የማስበው ከሰዎች ጋር በፍቅር መጫወትን ነውበኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከሁሉ ጋር አብሮ መብላትን በይበልጥ እደሰትበታለሁ›› የሚሉት አቶ ዳኜ፤ ከወራት ሁሉ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ያሉ ወራት ላይ ትዝታዎች አሏቸውበእሸት ወቅት ደግሞ ከጓደኞቻቸው ጋር አብረው እየተጫወቱ ሲመገቡ መዋልን መናፈቃቸው አንዱ ነው። የአካባቢው ሰው የሚሰባሰብበትና በፍቅር ጨዋታን የሚያከናውንበት ጊዜም በመሆኑ ሌላ ትዝታ ይጭርባቸዋል።
የልጅነት ህልማቸው ባለመኪና መሆን ነው፡፡ምክንያቱም በአደጉበት አካባቢ መኪና ማየት ብርቅ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ያዩትም በ14 ዓመታቸው ነበር ይህንን ጊዜ ደግሞ እንቅልፍ ሳይወስዳቸው መኪናውን ሲጠብቁ አድረዋል፡፡እናም በወቅቱ ለአንድ አጎታቸው ‹‹እኔ መኪና ገዝቼ እመጣለሁ ›› የሚለውን ሀሳብ ነግረውት ነበር፡፡
በወቅቱ ማህበረሰቡ ግለሰቦች መኪና ይገዛሉ የሚል እምነት አልነበራቸውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው መንግስት ብቻ ነውስለዚህም አቶ ዳኜ በተናገሩት ሀሳብ አጎታቸው እስኪበቃቸው ድረስ ሳቁለእግሩ ጫማ የሌለው ሰው ይህን ማሰቡም አስገርሟቸው እንደነበርና በየዋህነት እንደተናገሩት አምነው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም የዛን ጊዜው ታዳጊ የዛሬው ጎልማሳ አቶ ዳኜ፤ ከማክሰኞ ገበያ ሁሉ መግዛት እንደሚችሉ አስበው ነበርነገር ግን እንደማይቻል ሲረዱ ለጊዜው ሀሳቡን ትተው ተቀመጡግን ህልማቸው ነበርና በ10 ዓመት ውስጥ ተግባራዊ እንዳደረጉት ይናገራሉ።
ትምህርት
በየዕለቱ የአራት ሰዓት መንገድ በባዶ እግራቸው እየተጓዙ ተምረዋል፤ ለሁለት ዓመታትየመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ከቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጎሮ ጉርጦ በተሰኘ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረውበታልቀጣዩ ደግሞ አራት ሰዓት ሙሉ በባዶ እግራቸው እየተጓዙ የተማሩበት ‹‹ጊጥሬ›› የሚባል ትምህርት ቤት ነውሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ተከታትለውበታል።
በወቅቱ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 98 በመቶ ያመጡት እርሳቸው ብቻ ቢሆኑም በዚህ ውጤታቸው ግን ዘጠነኛ ክፍልን መቀጠል አልቻሉም፡፡በዋናነት ሁለት ችግሮች ገጥመዋቸዋልየ። መጀመሪያው ትምህርት ቤቱ ያለው አምቦ በመሆኑ እዚያው ቤት ተከራይቶ ምግብ እያዘጋጁ መቆየት ነበር ሆኖም ግን አቅም ለሌለው በፍጹም አይሞከርም።
ሁለተኛው ርቀቱ በአራትና አምስት ሰዓት ጉዞ የሚተመን አለመሆኑ ሲሆን፤ ይህም ባለመቻሉ ትምህርታቸው በስምንተኛ ክፍል ላይ እንዲያከትም አስገደዳቸው።
መማርና ለቤተሰብ መድረስ ህልማቸው የነበረው አቶ ዳኜ፤ የሚያስተምራቸውን ፍለጋ ጋምቤላ ድረስ ተጉዘዋልግን አጎታቸው የጥበቃ ሰራተኛ በመሆናቸው አይደለም እርሳቸውን ልጆቻቸውን እንኳን አብልተው ለማደር የማይችሉ ነበሩትምህርት የመማር ፍላጎት ቢኖራቸውም በእነዚህ ምክንያት ተስፋ ቆረጡ፡፡
በእርግጥ አጎታቸው እንዲማሩ ይፈልጋሉ፡፡ስለዚህም ያጠራቀሟትን ገንዘብ ከልጆቻቸው አፍ ነጥቀው ‹‹እኔ በቤቴ ሁሉን ነገር አሟልቼ ላስተምርህ አልችልምነገር ግን ይህቺን ገንዘብ ያዝና ቤተሰቦችህ ጋር ተመልሰህ እየሰራህ ተማር›› እንዳሏቸውም አይረሱትም፡፡እንግዳችን ግን ይህንን ማድረግ አቃታቸው፡፡ ከሌለው ሰው ላይ መቀበል ከባድ እዳ እንደሆነ ተሰማቸው መማር የሚለውን ሀሳብ አቆሙና በልምድ መስራት ወደሚችሉበት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፊታቸውን አዞሩ።
ጉልበት ሰራተኝነት
ሥራን ሀ ያሉት አጎታቸው ጋር ጋምቤላ በሄዱበት ወቅት ነበርየአጎታቸው አቅም ማጣት ከመማር ቢያግዳቸውም እንዲሰሩ ግን ድጋፍ ሆኗቸው ነበርያስተምረኛል ያግዘኛል የሚለውን ሀሳብ ትተው ሰርተው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች መድረስ እንዳለባቸውም ጉልበት ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህም ሰርተው ለመለወጥ «ሳትኮን» በተባለ የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጠሩበቀን ስምንት ብር እየተከፈላቸውም መስራታቸውን ቀጠሉገንዘቡን ሲያገኙ ደግሞ በአጎታቸው ቤት መቆየቱ ምቾት አልሰጣቸውም፡፡ በተጨማሪም ከሳትኮን ወጥተው በ10 ብር ደመወዝ የሚሰሩበት ቦታ ስላገኙ ጉዟቸውን ወደ«ሀበቦ እርሻ ምርምር» አደረጉ በዚህ ብር ለቀናት ያህል እንኳን አልሰሩበትም፡፡ እድላቸው ቀና ነበርና በቀጥታ መጻፍ የሚችል ሰው ተፈልጎ ስለነበር እርሳቸው በደህና ቀን በተማሩት ትምህርት የእርሻ ምርምሩ የሰዓት ተቆጣጣሪ በመሆን ደመወዛቸው ወደ 15 ብር ከፍ አለየእድል ሀሁ ማለት ይሄኔ ነው።
ሰዓት ተቆጣጣሪነታቸው ተጨማሪ የሥራ እድል ይዞላቸው እንደመጣ የሚናገሩት አቶ ዳኜ፤ አሰሪዎቻቸው ብቅ የሚሉት አስገዳጀ ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነበርና የክትትልና የቁጥጥር ስራው እርሳቸው ላይ ወደቀ የመስሪያ ቤቱም ኃላፊ እርሳቸው ሆኑ።በዚህም ከወራት በኋላ የእርሻ ምርምሩን ህንጻ ለመስራት ከተስማማው አንድ ኮንትራክተር ጋር ቅርበት ፈጠሩየኮንትራክተሩ ባለቤትም አመናቸውና ከእርሳቸው ጋር መስራት እንደሚፈልግ ገለጸላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩናም ሀሳቡን ተቀበሉት።
‹‹መጀመሪያ ሥራው ሲጀመር 10 ሺ ብር ነበር የሰጠኝ በዚህም ፈርቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህንን ያህል ገንዘብ አይቼም ሆነ ነክቼ አላውቅም፡፡ እናም ብቀማስ ነበር ያልኩትእርሱ ግን እንደማይሆን ያውቃልና ችግር የለውም አለኝ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ሌሎች የጉልበት ሰራተኞችን ቀጥረው ማሰራት የጀመሩት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ የጉልበት ሥራን በሚገባ ያውቁታልና እነርሱም ሆኑ ባለሀብቱ እንዳይጎዳ እያደረጉም ያሰሩ ጀመር፡፡
የታዘዙትን ሁሉ ሰርተው ገንዘቡ ግን እንደተረፈ ነበርዳግም የተላከላቸውን 10 ሺህ ብር ጨምሮ ብዙ ነገሮችን ሰርተው ሰውዬው ሥራዎቹን ለማየት ሲመጣ ዘጠኝ ሺህ 700 ብር ተርፏቸው ነበርበታማኝነትና በስራ ባህላቸው ምስጉን ሆነው አድገዋልናም የተረፈውን ለአሰሪያቸው ‹‹ይኸው ጌታዬ›› አሉእርሱ ግን በወቅቱ አላመነም ነበርምክንያቱም ሥራው በጥራትና በፍጥነት ነው የተጠናቀቀውበዚያ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ገንዘብ ተርፏል።
‹‹በል ይህ ገንዘብ የእኔ ሳይሆን የአንተ ነውከዚህ በኋላም ብዙ ሥራዎችን አብረን የምንሰራ ይሆናል›› ብሎ ብሩን ሰጣቸው በወቅቱ በጣም ተደሰቱ አላመኑምም ይሁንና አንድ ነገር ግን አይረሱምያ ጊዜ ብዙ ነገርን አስተምሯቸዋል፡፡ የሙያ ባለቤትና ገንዘብ የማያጥረው ሰውም አደረጋቸውበስፋት መስራት እንዲችሉ ሆኑ።
በታማኝነት ነገሮችን ማድረግ ባለው ላይ መጨመር ማለት መሆኑን ተረዱሀቀኛ፣ ታታሪና ቅን ሰራተኛ መሆናቸው ለቀጣዩ እድገታቸውም በር ከፋች ሆኖ ቀጠለ በቋሚነት የሚሰሩበት መስሪያ ቤት ደመወዛቸውን ከ15 ብር ወደ 30 ብር ከፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ከዛም የግምጃ ቤቱ ተቆጣጣሪ ሆነው በ60 ብር እንዲሰሩ ተደረገ።
ያመሰግኗቸዋል፡፡ ምክንያቱም በብዙ ነገር ደግፏቸዋል፡፡ ሙያውንም እንዲለምዱ ያደረጓቸው እርሳቸው ናቸውጥሩ ግንበኛ፣ አናጺና ዲዛይነር መሆን እንዲችሉም አግዘዋቸዋል፡፡ ከዚያም አልፈው ሥራ አልቆ እንኳን ከእርሳቸው እንዳይለዩ በመፈለጋቸው ሳይሰሩ ይከፍሏቸው ነበርእናም ዛሬ ድረስ ያመሰግኗቸዋል፡፡ የህይወቴ ቤዛ የእንጀራዬ አባት ናቸውም ይሏቸዋልግን በአካል አግኝተውት ስላላመሰገኗቸው ይቆጫሉ፡፡
ቀጣዩ የስራ ጉዟቸው የሚወስደን ሰቆጣ ላይ ሲሆን፤ ድርጅቱ የቀድሞ ቤታቸው ነው የሚለየው የሚከፍላቸው ደመወዝ ሲሆን፤ አራት ሺህ ብር ይከፍሏቸዋል። ጥራት ያለው ስራ ሰርተው በፍጥነት ስለሚያስረክቡ ፈላጊያቸው በመብዛቱ ሳትኮን የሚከፍላቸውን እጥፍ አድርጎ የበለጠ እንዲሰሩለት መክፈል ጀመረያም ሆኖ ተቀናቃኙ ብዙ ነበርና አማራጩ ተቀየረ፡፡
ስራን ለነገ የማይሉት እንግዳችን ሌት ተቀን መስራት ልምዳቸው በመሆኑ የበለጠ የሚሰሩበትን መንገድ በማየት ድርጅቱ ከሰባት ወር በኋላ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ላይ እንዲሰሩ በ13 ሺህ ብር ደመወዝ ወሰዳቸው ለሰባት ወር ከሰሩ በኋላ ግን በዚያ ድርጅት ውስጥ ታጥረው መቆየታቸውን አልፈለጉትም፡፡ ስለዚህም ጎን ለጎን ውጪ ላይ በግል የሚሰሩበት አጋጣሚ ነበርና ያንን አጠናክረው ለመስራት መልቀቂያ አስገቡ፡፡ በግላቸውም ኮንትራት እየወሰዱ መስራት ቀጠሉ
‹‹በጅቡቲ ውል የሚባል ነገር አይታወቅምቅዳሜ ቅዳሜ የደመወዝ ቀን በመሆኑም የተሰራውን ያህል ክፍያ ይሰጣልእኔ ደግሞ መጨረስ ያለብኝን በጊዜው ስለማጠናቅቅ ሁልጊዜ ሙሉ ክፍያዬን ነበር የምቀበለው›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ በጅቡቲ ያልሰሩት ሥራ አልነበረምበተለይ የግለሰብ ቤቶችና የውሃ ታንከሮችን የመስራት እድሉ ገጥሟቸዋል፡፡ እዚያም አራት ዓመታት ሲቆዩ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይዘው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አግዟቸዋል፡፡
‹‹መስራትና መብላት የሚያምረው በአገር ነውገንዘብ ሳገኝ ትዝ ያለኝ አገሬ ነው።›› ያሉን አቶ ዳኜ፤ በላባቸው ያፈሩትን ሀብት በመያዝ አያታቸውን ለማግኘት ቀን ሌሊት ተጉዘው አዲስ አበባ ገቡሆኖም አያታቸው በህይወት እንደሌሉ ሰሙተስፋም ቆረጡይሁንና ዘመድ መኖሩ አይቀርም በማለት ወደ ትውልድ ቀያቸው አመሩግን ብዙ ነገሮች እንደነበሩ አላገኙዋቸውምና ተመልሰው ቤት በመከራየት አዲስ አበባ ኑሯቸውን አደረጉ፡፡
የተለያዩ ሥራዎችንም በመስራት አገራቸው ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ጀመሩሚሊኒየም ላይ ደግሞ የትውልድ ቀያቸውን ለማገዝ በተደረገ ድጋፍ ላይ ተሳተፉ በዚያውም በኢንቨስትመንት ለማገዝም 500 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበው ለመስራት ቢታትሩም መንገድ ባለመኖሩ የተነሳ ብዙ ገንዘብ ከሰሩበዚህም ሌላ አካባቢውን የሚያግዙበት ስራ ላይ ተሰማሩ፡፡
ከመብራት ኃይል ጋር በመነጋገር ገጠሩ ላይ በግል ኮንትራት እየወሰዱ መስራታቸውን ቀጠሉሙሉ እቃ ተቋሙ ይችል ነበርና ጉልበት እያዋጡ ነበር ሲሰሩ የቆዩት ሆኖም ይህ አዋጭነቱ ብዙ አልነበረምና በራሳቸው ብዙ እቃዎችን በመግዛት ሙሉ ኮንትራቱን በመውሰድ መስራቱን አጧጧፉትውጤታማ ሥራዎችን በአፋጣኝ ማስረከባቸው ደግሞ መታመናቸውን ከፍ ስላደረገው ከሌሎች ይበልጥ ተመራጭ አደረጋቸው
በሚሰሩት ሥራ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈው ያጡትን ጨምሮ በርከት ያለ ገንዘብ ማግኘት የጀመሩት አቶ ዳኜ፤ በዓመት ከ20 በላይ ከተሞችን ከ15 በላይ ገጠሮችን በመብራት ተደራሽ እንዳደረጉ ይናገራሉየሥራ ቅየራውም ከዚህ በኋላ የመጣ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
ከ30 በላይ ደረቅ መኪኖች ባለቤት መሆናቸውን ያጫወቱን እንግዳችን፤ በእነዚህ መኪኖች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉከዚያ ባሻገር የአስመጪና ላኪ ሥራንም ይሰራሉበዚህም ዘንድሮ ብቻ ከ300 ሚሊዬን ዶላር በላይ መላካቸውን አውግተውናልሌላው ባለቤታቸው የተሰማሩበት የዳቦ ማምረቻ ነው፡፡
የአስመጪና ላኪ ሥራን ለመጀመር ብዙ ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ የሚሉት ባለታሪኩ፤ ዋስትናቸው በላባቸው ያካበቱት ንብረት መሆኑ ያስደስታቸዋልይህ ሁሉ የሆነው ግን በሀቅና በእምነት እንዲሁም የሚያውቁት ሥራ ላይ በመሰማራታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹ብዙ ሀብታሞች ከነበሩበት ዝቅ የሚሉት የማያውቁትን ስራ በመስራታቸው ነውበዚያ ላይ ታችኛው ክፍል ላይ ምን እየተሰራ እንደሆነ ማየትን አይፈልጉም፡፡ ስለዚህም ንብረታቸው ምን ላይ እንደፈሰሰ አይረዱምለሀብት እንጂ ለህዝብም የማሰብ መጠናቸው አናሳ ነውስለዚህም አወዳደቃቸው የከፋ ይሆናልእናም ሥራ ሲሰራ ይህንን ሁሉ ማረም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል›› ይላሉ፡፡
የአገር አበርክቶ
የበጎ አድራጎት ተግባራቸው ዛሬ የኮሮና ቫይረስ በሀገር ላይ በመከሰቱ ብቻ የመጣ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ ለብዙ ችግረኞች ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ በተለይም እርሳቸው ደጋፊ በማጣታቸው ትምህርታቸውን እንዳይማሩ የሆኑበት ጉዳይ ሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል፡፡ ለ500 ተማሪዎች በየዓመቱ የትምህርት ቁሳቁስ በመስጠት እስከ ትምህርት ክፍያ ድረስ ወጪያቸውን ይሸፍናሉ፡፡
በእምነት ቦታዎች ላይም በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋልበተለይም ቤተ እምነቶቹን በማደስ በኩል የማይተካ ሚና ነበራቸው፡፡ አቅመ ደካሞችንም በቻሉት መጠን ይደግፋሉዛሬ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ እጃቸውን ለወገኔ ብለዋል፡፡
‹‹ይህ ችግር በመንግስት እና በባለሀብቱ ድጎማ ብቻ የሚገፋና የሚፈታ አይደለም፡፡ መተጋገዝ ባህሉ የሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ካለው ላይ ለጎረቤቱ መስጠትን ይጠይቃል፡፡ አብሮ ክፉ ቀንን ማለፍ ያስደስታል፡፡ እናም እኔም ይህችን ያህል ያደረኩት ከዚህ የተነሳ ነው›› የሚሉት አቶ ዳኜ፤ ያደረጉት ነገር በቂ ነው ብለው እንደማያምኑና በቀጣይም ድጋፋቸው ባስፈለገበት ሁሉ እንደሚደርሱ ነግረውናል፡፡
ለኮሮና መከላከል ሀገር ላቀረበችው ጥሪም እርሳቸው ለኦሮሚያ ክልል አንድ ሚሊዬን ብርና ከ200 እስከ 400 ኩንታል የሚጭኑ ሦስት መኪኖችን አበርክተዋል «ዛሬ የሰጠነው ጥቂት ነውነገ ችግሩ ሲብስ ከዚህ በላይ ማድረግ ግዴታችን ነው» ይላሉ
‹‹ በሀገራችን ላይ ያፈራነው ሁሉ የራሷ የኢትዮጵያ ነውና ለእርሷ ከመስጠት ወደኋላ አልልም›› የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው፡፡
የሰው ልጅ ለመኖር መብላት አለበትመንግስት ደግሞ ብቻውን ይህንን ማድረግ ይከብደዋል፡፡ስለሆነም ወደፊት ሁኔታው እየከረረ ከመጣ ቢያንስ ዳቦ በልተው እፎይ ብለው በየቤቱ እንዲቀመጡ ለማድረግ በየቤቱ እየተዞረ የሚሰጥ ወይም ደግሞ መንግስት በፈለገው መንገድ የሚያከፋፍለው ዳቦ ፋብሪካችን እንዲያመርት ፈቅደናል ብለውናል።
ፋብሪካው በሰዓት እስከ 300 ሺህ ዳቦ የሚያመርት ሲሆን፤ መንግስት ዱቄቱን ብቻ በማቅረብ ሰራተኞችና ሌሎች ወጪዎችን እየቻልን እንዲጠቀምበት መፍቀዳቸውን አጫውተውናል፡፡ ችግር የሚታለፈው በክልል ታጥሮ ብቻ ሳይሆን በአንድነት ተባብሮ ነውና ለተቸገረው ሁሉ ዳቦው ቢደርስ እንደሚደሰቱ አውግተውናል፡፡
እርሳቸው በባዶ እግራቸው ብዙ ተጉዘው ዛሬ እንደደረሱ ሁሉ በችግር ውስጥ የሚማቅቁትን በዚያው እንዲቆዩ ማድረግን አይሹም፡፡ ስለዚህም ለእነዚያ ጫማ አጥልቀው የሚራመዱበትንና ለአገራቸው የሚቆሙበትን መንገድ ነው ማሳየት የሚፈልጉት በመሆኑም ‹‹ዛሬም ነገም በህይወት እስካለሁ ድረስ አገሬም ሆነ ህዝቤ ሲራብና ሲቸገር ማየትን አልሻም፡፡አሁን ትንሽ አድርጌያለሁ፡፡ በቀጣይ ደግሞ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግም እፈልጋለሁ›› ብለውናል፡፡
‹‹ለአገር የሚበረከት ነገር ክፍያው ህዝብ የሚሰጠው ምርቃት ነውበዚህም ሁልጊዜ ስሰራና ሳደርግ የምደሰተው ማህበረሰቡ በሚሰጠኝ ምርቃት ነው›› የሚሉት እንግዳችን፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ተሰማርተው እያሉ የሚጓተቱ ነገሮች ሲገጥሟቸው መንገድ ሳይቀር በራሳቸው ዶዘር አስጠርገው በነጻ የሚሰሩበት አጋጣሚ መኖሩን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ደስተኛ እንደሚሆኑ ይናገራሉ፡፡
ሌላው ለአገራቸው እያበረከቱ እንዳለ የሚያሳየው በፋብሪካው የሚመረተውን ዳቦ አትራፊም ባይሆኑ ህዝቡ እንዲጠቀም በማሰብ ኪሎውን ሳይቀንሱ በ2 ብር ዋጋ ማቅረባቸው ነውቢችሉ ብዙዎችን ቢደግፉ ያስደስታቸዋል፡፡ ሆኖም አይቻልምና በተንቀሳቀሱበት ሁሉ መኪና የሚጠብቅ ሰው ፈልገው በመያዝ ነው ጉዟቸውን የሚያደርጉት ብቻቸውን እንደማይሄዱም አጫውተውናል፡፡
ቤተሰብ
የዛሬዋን ባለቤታቸውንና የልጆቻቸውን እናት የተተዋወቋት ቤተሰቦቿ ቤት ተከራይተው በሚኖሩበት ጊዜ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ በጣም ደግ እርሷም መልካም ሴት በመሆኗ ልባቸው ተሸነፈላት በዚህም እየፈሩም ቢሆን ቤተሰብን ጠየቁእርሷንም አሳመኑውሃ አጣጭ እንድትሆንላቸው እድል አላቸውና ሁሉም በእሽታ ተጠናቀቀ፤ ጋብቻም ተፈጸመ፡፡
ቤተሰቡን ለማስደሰት በጊዜ እቤታቸው እንደሚገቡ ያጫወቱን አቶ ዳኜ፤ የሰዎችን መብት በምንም መልኩ መጋፋት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ፡፡ በዚህም ጥበቃቸው የሚፈልገውን ነገር ከልጃቸው እኩል እንዲያደርግ ይፈቅዱለታል፡፡ ጥበቃቸው የነበረው ሰው መጀመሪያ ሚስት እንደሚያገባ ሲናገር ሶስት ክፍል ቤት ሰጥተው ድረውታል፡፡ ከዚያም ወልዶ ከብዶ ሲኖር ቆየና ወደ ገጠር መሄድ እንደሚፈልግ ሲገልጽላቸው ደግሞ መቋቋሚያ እንዲሆነው መቶ ሺህ ብር ሰጥተው ሸኝተውታል፡፡
ማንኛውም ሰው በሚሰራው ስራ መከበር አለበትለስራውም ተገቢው ክፍያ ሊቸረው ይገባል ብለው የሚያምኑት እንግዳችን፤ ባለቤታቸውም የፈለገችውን እንድትሰራ መብት ይሰጣሉ፡፡ በዚህም ‹‹ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳል›› እንዲሉ ሁለቱም በጎ በማድረግ ያምናሉ ያደርጋሉም፡፡ ከዚያም አልፈው ልጆቻቸው ይህንን ለምደው እንዲያድጉ መስጠትን ያስተምራሉ፡፡
በቤት ውስጥ አንድ አይነት የበጎነት ሀሳብ መኖሩ ቤተሰቡ ደስተኛ እንዲሆን አድርጓልስለዚህም በጎነትን ምግባር ማድረግ ኑሮን ደስተኛ፤ መንገድን ቀና ያደርጋልና ብዙዎች ቢጠቀሙበት ነጋቸው ይስተካከላል ይላሉ፡፡
መልዕክት
ሰዎች ዝቅ ብለው መስራት እስከቻሉ ድረስ በአገሪቱ ስራ ሞልቷል ዝቅ ብሎ ከመስራት ከፍ ማለት ይቻላል፡፡ እናም ሥራ የለም ብሎ ውጪ ውጪ ከማየት መቆጠብ ይገባል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነውቤተሰብ በተለይም ሀብቱ ያለው ልጆቹን በስራ ማሳደግ አለበትመስራት እንዲችሉና የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ከልጅነታቸው ጀምረው እየነገሩ ማሳደግ ግዴታ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የሚያወርሱት ሀብት ነገን ላያሻግር ይችላል፡፡ አላቂም ነው፡፡ ስለዚህ ያንን እያሳሰቡ ማሳደግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
ሌላው መልዕክታቸው መልካም ማድረግ ልምድ ይሁን የሚለው ነውይህም ለራስ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በመስጠት ውስጥ ሌላ መሰጠት እንዳለ እያሰቡ ማድረግ ይገባልበሰው ሁሉ ማግኘት መደሰትም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ በረከቱ ሁልጊዜ መንገድን ቀና ያደርጋል፤ ከፍም ያደርጋል ይላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው