ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች የምታገኘው ገቢ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ያለፉት ሁለት ዓመታት የወጪ ምርት እቅድ እና ገቢ ከፍተኛ ልዩነትም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
በ2009 በጀት ዓመት ወደ ውጭ አገር ከሚላኩ የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ምርቶች፣ከመዓድን ውጤቶች እና ሌሎች የወጪ ምርት ዓይነቶች ከ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ማግኘት የተቻለው 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላሩን ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይም በ2010 በጀት ዓመት ከነዚሁ ምርቶች ከ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገባት ቢታቀድም ማግኘት የተቻለው ግን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ በየጊዜው የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ይህን ችግር ለመፍታት አቅጣጫዎች ቢቀመጡም ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ገቢው ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት መጥቷል፡፡ ለምን ይሆን ?
የወጪ ንግዱ ገቢ ችግር እንዲፈታ ዘለቄታዊ መፍትሄ የማይበጅለት ከሆነ የአገሪቷ ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንዲሚችልም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ያሳስባሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ ስለ ወጪ ንግድ ሲታሰብ የምርት አቅርቦትና ፍላጎት ጉዳይ አብሮ መታየት አለበት ይላሉ፡፡ አገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው የምርት ዓይነቶችና ምርቶቹን የመግዛት ፍላጎት ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው፣የምርቱ ፍላጎት እያደገ ሊሄድ የሚችል ስለመሆኑ መገንዘብ እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ሀገሪቷ ለዓለም ገበያ በአብዛኛው የምታቀርባቸው የግብርናና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ያለቀላቸው ናቸው፡፡ይህ ብቻም አይደለም ምርቶቹ የሚፈለጉባቸውን የገበያ መዳረሻ ቦታዎችን ያለመለየት ችግርም ይስተዋላል፡፡እነዚህ ተግዳሮቶች ለወጪ ንግዱ መዳከም እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡
ምርቶቹ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚኖራቸው ቦታ ውስንነት ያለውና ዘላቂነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ይህም የወጪ ንግዱን እንደፈተነው ያብራራሉ፡፡ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች አነስተኛ የገበያ ልውውጥ ያላቸውና አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ መሆናቸውም ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ይጠቁማሉ፡፡
ዋጋ ሊያስጨምር የሚችል ፍላጎት ወይም የመግዛት ፍላጎት በዓለም ገበያ እንዲኖር የሚያስችል ምርትን ለመጨመር የሚጠቅም የኢኮኖሚ መዋቅር አለመኖርም የአገሪቱን የወጪ ንግድ እንደጎዳው ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስገነዝባሉ፡፡ በዚህ የተነሳም ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች የሚፈለገውን ገቢ ማግኘት እንዳልተቻለም ያመለክታሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ፤እስካሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ የወጪ ንግድ በአብዛኛው በጥቂት ግለሰቦች እጅ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ግለሰቦቹ ችግር ሲያጋጥማቸው የወጪ ንግዱም በተፅዕኖ ውስጥ ይወድቃል ይላሉ፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ እየተባባሰ መምጣትም ለወጪ ንግዱ መዳከም የራሱን ሚና መጫወቱን ይጠቁማሉ፡፡
ሀገሪቱ ያልተጠቀመችባቸው አንፃራዊ ጥቅሞችም ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡በተለይም ሀገሪቷ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በበለጠ የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም ይህን ሃብቷን ግን በሚገባ ልትጠቀምበት አልቻለችም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው አብዛኛዎቹ የግብርናና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነታቸውና የገበያ ተደራሽነታቸው ውስን መሆኑን የሚገልፁት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ምርቶቹ ተፈላጊነት እንዲኖራቸውና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኙ በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመርና በተለያየ መልክ በማምረት ለገበያ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ መፍትሄ ያሉትንም ያመለክታሉ፡፡ የዘርፉ ችግር ምርትን ለመጨመርና ለማሻሻል የሚያስችል የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባትና የፖሊሲ ለውጥ ማድረግም ይጠይቃል ይላሉ፡፡
አዳዲስ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሰድ ሌሎች አገራት ምርቶቹን ሊገዙ በሚችሉበት ሁኔታ የኢኮኖሚ መስተጋብርን ከአገራቱ ጋር በሚመጥን ሁኔታ ማዋቀር እንደሚገባም ረዳት ፕሮፌሰሩ ያመለክታሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚናገሩት፤ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የአገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ምርቶቹን ከውጭ ማምጣት ቢያስፈልግም በተመሳሳይ ወደ ውጭ አገራትም የአገር ውስጥ ምርቶችን መላክ የሚቻልበትን ድርድርና የገበያ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡
ሀገሪቱ የእንስሳት ሃብቷን በሚገባ በመጠቀም ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንድትችል ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የእንስሳት ተዋፅኦዎችን በማምረትና በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ያለቀላቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ይኖርባታል፡፡
የወጪ ንግዱ ፍትሃዊና በውድድር የተሞላ እንዲሆን ለማድረግ በወጪ ንግዱ የሚሳተፉ ተዋንያንን ማብዛት ያስፈልጋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ የወጪ ንግድ ፍቃድ አሰጣጥም ቢሆን ህጋዊና በርካታ ዜጎችን ሊያሳትፍ የሚችል መሆን ይኖርበታል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂ ተኮር እቃዎችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን በከፍተኛ ደረጃ በመጋበዝና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከውጭ የሚገቡት እቃዎች በንግድ ሚዛን ላይ ኪሳራ እንዳያስከትሉ መከላከል እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤እየተባባሰ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቀነስ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ጠንካራና ስልጡን የፋይናንስ ፖሊስ መደራጀት ይኖርበታል፡፡ ከሌሎች ወሰንተኛ ሀገሮች ጋርም የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት በማድረግ መተግበር ይገባል፡፡
ህግን ተላለፍው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን ህብረተሰቡ እንዳይገዛ የተለያዩ የቁጥጥር ዘዴዎችን መፍጠር፤ህብረተሰቡንም ማንቃትና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ባጠቃላይም ጠበቅ ያለ ህጋዊ የቁጥጥር ማዕቀፍ መዘርጋት ይገባል፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንደሚሉት፤ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ የሚጠቀሱ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ ዋነኛዎቹ ግን ችግሮች በአግባቡና በሚፈለገው ደረጃ እየተፈቱ አለመሆናቸው ነው፡፡
የወጪ ንግዱ እንዳይሳለጥ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ምርቶችን በሚፈለገው መጠንና ዋጋ ለውጭ ገበያ ያለማቅረብ ሲሆን፣ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የተካሄዱ የዘር ማባዛትና የምርምር ሥራዎች በሚፈለገው ልክ ውጤት ባለማምጣታቸው ችግሩን ከፍ አድርጎታል፡፡
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርናና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች በጥራት ረገድ ችግር እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ አሰፋ፣ይህም ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል ይላሉ፡፡
በጥራት ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነም አመልክተው፣ ከሎጀስቲክና የግብይት ስርዓት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ችግሮች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡እነዚህ ችግሮች አሁንም በሚፈለገው ደረጃ እየተፈቱ ባለመሆኑ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ የማድረጉ ጥረትም በቂ አይደለም፡፡ ይህም ችግር በተደጋጋሚ የሚነሳና ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስም ነው፡፡
ለወጪ ንግዱ መዳከም ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት የግብርና ምርቶች ዋጋ በየጊዜው መዋዠቅና በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ መንጠልጠል ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ ላይ እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ሥራዎቹ አሁንም በቂ አይደሉም ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እየተባባሰ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድም የወጪ ንግዱ አንዱ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ይጠቅሳሉ፡፡ ምርትን በአገር ውስጥ ከሚገዛበት ዋጋ በታች በማድረግ ለውጭ ገበያ ማቅረብን የመሳሰሉ ችግሮች ከወጪ ንግዱ የሚገኘውን ገቢ አሳንሰውታል በማለት ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ አባባል ፤በወጪ ንግድ የሚታዩ ችግሮችን በሚፈለገው ደረጃ መፍታት ያልተቻለው የወጪ ንግዱን የሚደግፉ አካላት በተበታተነ ሁኔታ መስራትና ደካማ ቅንጅታዊ አሰራር በመኖሩ ነው፡፡ችግሮቹን በዘለቄታው ለመፍታት በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ምርቶች ለማሳለጥ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
በተለይም የግብርና ምርቶች ተመርተው ወደ ገበያ እስከሚደርሱ ድረስ ያሉትን ተዋንያንና ባለድርሻ አካላት በተሻለ ቅንጅት በመምራት ብክነትን እንዲቀንሱ በማድረግ የተሻሉ ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ የምርት ጥራትን የሚጎዱ አሰራሮችን በቅንጅት በመከላከል ምርቶቹ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡የጉዳዩ ባለድርሻ አካላትን ለውጤት የሚያነሳሱና ወደ መፍትሄ የሚመሩ ትላልቅ የንቅናቄ መድረኮችንም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
እየባሰ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድን የመከላከል ሥራም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን እንደሚጠይቅ በመጠቆም የረዳት ፕሮፌሰሩን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የገቢዎች ሚኒስቴር የቁጥጥር ሥራውን ሊያግዙ ከሚችሉ አካላት ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ፣ከፌዴራልና የክልል ፖሊሶች ጋር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል ይላሉ፡፡
የወጪ ምርትን በአገር ውስጥ ከሚገዛበት ዋጋ በታች በማድረግ ለውጭ አገራት የመሸጥ ሁኔታ እንደሚታይም የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ይህ በምን ምክንያት ሊፈጠር እንደቻለ በጥናት ሊመለስ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ሻጭም ገዢም በመሆን ግብይት የመፈፀም ሁኔታዎችም እየታዩ ናቸው የሚሉት አቶ አሰፋ፣ የምርቶች የሀገር ውስጥና ከአገር ውጪ ዋጋ የተለያየ ሆኗል፡፡ ይህም ሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ አሳጥቷል፡ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በአንዳንድ ምርቶች ላይ በግልፅ እየታየ በመሆኑ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ውይይት እያደረገበት ይገኛል ይላሉ፡፡
ሰሊጥ በአገር ውስጥ የምርት ገበያ ሲገዛ የነበረበት ዋጋ በአማካይ በቶን 2 ሺ የአሜሪካ ዶላር ቢሆንም፣ ለውጭ ገበያ በቶን ከ1ሺ 700 እና 800 ዶላር ባልበለጠ ዋጋ እንደሚቀርብም በአብነት በመጥቀስ ጉዳዩ መፍትሄ እንደሚፈልግ ያመለክታሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት በጥናትና በመረጃ ተደግፎ የሚመለስ መሆኑን በመጥቀስም፣ መረጃውን መሰረት በማድረግ ተቋሙ እርምጃ እንደሚወስድም ያስገነዝባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011አ
አስናቀ ፀጋዬ