መቋጫ ያልተገኘለት የኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ውጥረትን እንዳባባሰው ቀጥሏል። በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በሰዎች ይህወትና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው። የአለምን ሕዝብም በነፍስ ወከፍ በተወሰኑ ወራት ሊያዳርስ ይችላል።
በዓለም ላይ የወረርሽኙ ተጠቂዎች ቁጥር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን 064 ሺህ ተሻግሯል። 516 ሺህ 930 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል። አሜሪካ ከ523 ሺ365 በላይ ዜጎቿ የተጠቁባት ቀዳሚ አገር ሆናለች። ስፔን ከ1982 ሺ በላይ፣ ጣሊያን 165 ሺ 155፤ ፈረንሳይ 147ሺህ 863 የሚጠጋ፣ ጀርመን ከ134ሺ 753 በላይ፤ ዩናይትድ ኪግደም ከ98ሺህ 476 በላይ ዜጎቻቸውን ወረርሽኙ ያጠቃባቸው ሲሆን እንደአቀማመጣቸው ይመራሉ። ቫይረሱ የጀመረባት ቻይና ደግሞ ከ82 ሺ በላይ ታማሚዎች ያሉባት ሰባተኛ አገር ነች።
በዓለም ላይ ከ 135 ሺ 670 በላይ ዜጎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። አሜሪካ ከ28 ሺ በላይ ዜጎቿን በወረርሽኙ ያጣች ቀዳሚ አገር ናት። ጣሊያን 21ሺህ 645 ዜጎቿን በሞት ስትነጠቅ ስፔን ከ19 ሺ 130 በላይ ዜጎቿ ለሕልፈት ተዳርገዋል። ፈረንሳይ 17 ሺ167 ሰዎች በወረርሽኙ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በአፍሪካ በወረርሽኙ የታመሙት ዜጎች ከ17 ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን 913 ሰዎች ሞተዋል። ከሶስት ሺ 556 በላይ ዜጎች ማገገም ችለዋል። ደቡብ አፍሪካ ሁለት ሺ 506 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ቀዳሚ የአፍሪካ አገር ናት። ግብጽ ሁለት ሺህ 505 ዜጎቿ የቫይረሱ ተጠቂ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። አልጀሪያ ከሁለት ሺ 170 በላይ ዜጎች በወረርሽኙ የተያዙባት በአፍሪካ ሶስተኛዋ አገር ስትሆን ሞሮኮ ሁለት ሺህ 024 ሰዎች በመያዛቸው አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በኢትዮጵያም ወረርሽኙ ከገባ ጀምሮ እስከ ትናንት ዕለት ድረስ አምስት ሺ 389 ሰዎች ምርመራ የተከናወነ ሲሆን በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች 92 ደርሰዋል። የሶስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። 15 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።
በዓለም ደረጃ የመን አንድ ሰው ብቻ በቫይረሱ የተጠቃባት አገር ናት። በአፍሪካ ሌሴቶና ኮሞሮስ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው የሌለባቸው አገራት ናቸው። የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዓለም እየጨነቀች ነው። እስካሁን ድረስም ከሙከራ ባለፈ የሚከላከል ክትባትም ሆነ ፈዋሽ መድሀኒት አልተገኘም። ብዙ አገራትም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል። እየወሰዱም ይገኛሉ። ህዝቡ ቤት እንዲቀመጥ ያደረጉ አሉ። የመንግስትን ውሳኔዎችና የጤና ባለሙያዎችን ምክር አጣጥመው ተግባራዊ ያደረጉም አልጠፉም። በተለይ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ጀርመን እየወሰዱት ያሉ የመከላከል እርምጃ ውጤታማ መሆኑን በአብነት የሚጠቅሱ ብዙ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012