
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ነው። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከሚገኙ ምግብ ቤቶችና የሻይ ቡና በረንዳዎች በአንዱ ቁጭ ብለናል። ከእጅ መታጠቢያው አጠገብ ሁለት ወንዶች ተጣሉ፤ የተጣሉበትን ምክንያት አላወቅንም። ብቻ ግን ፀቡ ጠንከር ብሎ ነው መሰለኝ አንደኛው ለመደባደብ እየተጋበዘ ነው።
በወቅቱ ፈገግ ያሰኘን ነገር የተፈጠረው እዚህ ላይ ነበር። ካልተደባደብኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ሰው ቀጫጫ ሲሆን ካልደበደብኩት ብሎ የሚጋበዝበት ሰው ደግሞ ሰውነቱ በስፖርት የዳበረ ፈርጣማ ሰው ነው። በስፖርት የዳበረው ፈርጣማው ሰው በጨዋነት ከመናገር በስተቀር ብዙም ስድብ ነክ ቃላት አይናገርም፤ ካልተደባደብኩ ብሎም ያዙኝ ለቀቁኝ አላለም። ቀጫጫው ሰውዬ ግን የስድብ መዓት ያወርደዋል፤ ካልተደባደብኩ እያለም ያስቸግራል።
በዚህ ጊዜ የተቀመጥነው ሰዎች ውስጥ ሹክሹክታና ቀልድ ተጀመረ። ‹‹ይቺ ቀጫጫ ሰውዬ ይሄን የሚያክል ግድንግድ ሰውዬ ምን ልታደርገው ነው?›› እያሉ የተገረሙ ብዙዎች ነበሩ። ምክንያቱም የተለመደው ነገር ግድንግድ ሰው አስፈሪ፣ ቀጫጫ ሰው ደግሞ ሊፈራ እንደሚገባ ተደርጎ ነው።
ለማንኛውም እኔ በግሌ የታዘብኩት ነገር ስፖርታዊ ጨዋነትን ነው። ስፖርታዊ ጨዋነት ሲባል ብዙም ልብ ብዬ መርምሬው አላውቅም ነበር። ስፖርታዊ ጨዋነት ሲባል ይመስለኝ የነበረው፤ በስፖርት ሜዳ ላይ ከተጋጣሚ ጋር አለመጣላት፣ ተሸነፍኩ ብሎ ዳኛንም ሆነ ተጋጣሚውን አካል አለመሳደብ፣ በአጠቃላይ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ስፖርታዊ ጨዋነት ግን ይህ ብቻ አይደለም ማለት ነው፡፡
አንድ የምናውቀው ልማድ አለ። ሰውነታቸው በስፖርት የዳበረ ፈርጣማ ሰዎችን ተደባዳቢ አድርገን ስለናቸዋል። በየፊልሞችና ድራማዎች የተለመደውም ይሄው ነው። ሰውነቱ በስፖርት የዳበረ ክንደ ፈርጣማ ሰው የምሑር ወይም የትሑት ሰው ገጸ ባሕሪ ሲጫወት አይታይም። ሰውነቱ ፈርጣማ የሆነ ሰው የሚጫወተው ገጸ ባሕሪ ኃይለኛ፣ ተደባዳቢ፣ ሰዎችን የሚያስፈራራ፣ የሰው ሚስት የሚቀማ… ተደርጎ ነው።
ይህ ትርክት ከመለመዱ የተነሳ ሰውነታቸው በስፖርት የዳበረ ክንደ ፈርጣማ ሰዎችን ከእውቀት የራቁ አድርጎ የማሰብ የተሳሳተ ግምት አለ። ስፖርት አዕምሮ ላይ የሚሠራው ሥራ ብዙም አይነገርለትም። የስፖርት ሰዎች እንዲያውም ከሌላው ሰው በተሻለ ጨዋ እና ሥነ ምግባር ያላቸው፤ አንባቢዎች መሆናቸው ብዙም አይነገርም። የሰውነት መዳበር የግድ ለድብድብ ብቻ መዋል ያለበት አድርጎ የማሰብ ልማድ አለ። ይህ ልማድ ከመለመዱ የተነሳ ሥነ ምግባር ያለው ቢሆን እንኳን እንደ ፈሪ ይታያል ማለት ነው፡፡
እንዲያውም አንድ የማውቀው ልማድ አለ። ሰውነቱ ገዘፍ ያለ ሰው ተደባዳቢ ካልሆነ እንዲያውም ከሌላውም ሰው የተለየ ፈሪ ተደርጎ ይታሰባል። አንድ ቀጫጫ ሰው አንድን ፈርጣማ ሰው ሲሰድበው ወይም ሊደበድበው ሲጋበዝ ቢታይ በፈርጣማው ሰውዬ ይሳቅበታል። ‹‹ዋናው ልብ ነው እንጂ ሥጋ ቢሸከሙት ምን ያደርጋል!›› በሚል ቀጫጫውን የተሻለ እንደ ጀግና የማየት ልማድ አለ። ከዚህም አለፍ ሲል ወፍራም ሰዎችን እንደ ፈሪ፣ ቀጫጫና አጭር ሰዎችን ደግሞ እንደ ልበ ደፋር አድርጎ የማየት ልማድም አለ። ሁለቱም የተሳሳተ ግምት ነው፤ ደፋርነትም ሆነ ፈሪነት ከአዕምሮ ጋር እንጂ ከሰውነት ቀጫጫነትና ግዝፈት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።
አንድ ነገር ግን ምክንያት ሊሆን ይችላል። ቀጫጫ እና አጭር ሰዎች ከግዙፍ ሰው ጋር ቢጣሉ ምናልባት እልኸኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ንቆኝ ነው፣ ተደፋፍሮኝ ነው የሚል መጠራጠር ሊኖር ይችላል። በዚህም ምክንያት ፀብ አጫሪ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም። ፍርሃትም ሆነ ድፍረት በሃሳብ እንጂ በድብድብ አይደለም። መደባደብ የምንም መገለጫ ሳይሆን የኋላቀርነትና ያለመሠልጠን መገለጫ ነው።
የሰውነት ቅርጽን ከውበት እና ከጤና ይልቅ ከድብድብ አንፃር እንድናየው ያደረገንም ይህ ኋላቀር ልማዳችን ይመስለኛል። የስፖርት አሠልጣኞችም ሆኑ በየትኛውም ስፖርት ቤት ስፖርትን ለድብድብ ተጠቀሙት ብሎ የሚመክር የለም። ቦክስ እና ትግል እንኳን ሳይቀር የሚመከሩት ራስን ለመከላከል እንጂ ለድብድብ አይደለም። ከጨዋነታቸው ባሻገር ችግር ቢያጋጥም ከጥቃት ራስን ለመከላከል የሚሠለጠኑ የተለያዩ የስፖርት አይነቶች አሉ። ይህ የሚሆነው ግን በመጀመሪያ ጨዋነትን በማሳየት ነው። የስፖርት ጨዋነትና ሥነ ምግባርም ይሄው ነው።
ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? ሰውነታቸው በስፖርት የዳበረ ሰዎች በሥነ ምግባራቸውም የታነጹ ናቸው። የአትሌቶች እና የእግር ኳስ ተጫዋቾች ስብዕና በጨዋነት የሚታወቅ ነው። እርስ በርስ እና አንዳንድ ጊዜ ከቅርብ ሰው ጋር እንደ ሰው ሊኖራቸው የሚችል የባሕሪ ችግር ሊኖር ቢችልም ሀገር ያወቀው ጋጠወጥነት ግን አይኖራቸውም። ስም መጥቀስ ባያስፈልግም አንዳንድ ሙያዎች ግን ስድብ እና ጋጠወጥነት ከሥልጠናው ጋር የሚሰጣቸው የሚመስሉ አሉ። በአጋጣሚ የሆነ ቦታ ሲገኙ ‹‹ውይ! እንዲህ ናቸው እንዴ ለካ!›› የሚያሰኙ ታዋቂ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ሥነ ምግባርና ጨዋነት ከማንም በላይ እንዲያውም ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች ዘንድ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ነው።
ስፖርት አካላዊ ቅርጽ ላይ እንጂ አዕምሮ ላይ የሚሠራው ሥራ ብዙ ጊዜ አይነገርለትም። በእርግጥ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ፤ ዳሩ ግን እንደ ሕዝብ ደግሞ ትርክቱን የገነባንበት መንገድ የተሳሳተ ነው። ለምሳሌ፤ ቀደም ሲል እንዳልኩት በፊልሞችና ድራማዎች በስፖርት የዳበረ ሰውነት ያለው ሰው ለተደባዳቢነትና ሰው ለማስፈራራት ይውላል። ከዚህ ይልቅ ታጋሽ እና ጨዋ በመሆኑ ነገሮችን ንቆ ሲተው ማሳየት ይገባ ነበር። አካላዊ ግዝፈቱን ብቻ ሳይሆን አዕምሯዊ ብስለቱን ማሳየት ይገባ ነበር።
እዚህ ላይ ግን አንድ የማይካድ እውነታም አለ። ሰውነታቸው ፈርጣማ መሆኑን ተጠቅመው የዝርፊያ ወንጀል የሚሠሩበት ይኖራሉ። ምናልባትም አንዳንዶቹ ብረት የሚገፉት ለእንዲህ አይነት ዓላማ ሊሆን ይችላል። ማንም አይነካኝም ብለው ሊሆን ይችላል። ነገርየው ከአዕምሮ ይልቅ በድንጋይ እና በብረት ይታሰብ ከተባለ ግን ማንኛውም ደካማ የሚመስል ሰው ሁሉ ጥቃት ማድረስ ይችላል። ጥቃት የግድ በሰውነት ግዝፈት ብቻ አይደለም። ስለዚህ ለዝርፊያና ለወንጀል ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች የስፖርትን መሠረታዊ መርሕ ጥሰዋል ማለት ነው።
የስፖርት ልህቀትና ከፍታ መታየት ያለበት ጡንቻ ላይ ብቻ ሳይሆን አዕምሮ ላይ ጭምር ነው። ለዚህም ነው ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች ታጋሽ፣ ጨዋ እና ትሑት ናቸው። ስፖርት አካልን ብቻ ሳይሆን አዕምሮንም ያዳብራልና የአዕምሮ ስፖርትም ይነገርለት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም