የሀገር መሪዎችና ፖለቲከኞች በተለይ የምዕራባውያኑ አስተያየታቸውን፣ አቋማቸውን፣ ፖሊሲዎቻቸውንና የግል አመለካከታቸውን እንደ ማንኛውም ተራ ዜጋ እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዎል ስትሬት ጆርናል፣ ፋይናንሽያል ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ታይም፣ ዘ ኢኮኖሚስት፣ ወዘተረፈ ባሉ አለማቀፍ ጋዜጦችና መፅሔቶች በመጻፍ በ (Op – ed ) ይገልጻሉ። በሀገራችን መሪዎችና ፖለቲከኞች ይቅርና በልሒቃኖቻችን ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን በታዋቂው የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ መሰናዘሪያ በሆነው በ’ ብሉምበርግ ‘ የፖሊሲና የፖለቲካ አምድ ላይ በስማቸው፣ ” What African Economies Need to Survive the Coronavirus ? “/ ” የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም ምን ይፈልጋል ? ” / በሚል ርዕስ ለንባብ አብቀተዋል። ይህ ብዙ ያልተሄደበት የእሳቸው ፋና ወጊ መንገድ ይበል የሚያሰኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ወረርሽኙን ለመከላከል ከሀገራችን አልፎ አህጉራዊ ጥረቱን በማስተባበር በሌላ በኩል ያጋጠመውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማስወገድ እየሰጡት ያለውን የሰከነ አመራር በልኩ እውቅና መስጠት እፈልጋለሁ። ከመቀመጫዬ በመነሳትም ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌያለሁ። ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ አዋርሼ የመለስሁትን መጣጥፍ እንዲህ አቅርቤ፤ የጥሪያቸውን ምላሽና ሰሞነኛ የወረርሽኙን ኢኮኖሚያዊ ጣጣ ለጥቄ አነሳሳለሁ።
” የኖቨል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለምን ሲያካልል ባጅቶ በመጨረሻ ወደ አፍሪካ ጎራ ብሏል። ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ በሆኑ አፍሪካውያን ጤና፣ ህልውና እና ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጫና ከበድ ያለ ነው። ሆኖም ቫይረሱ የሚያደርሰው ጉዳት በአህጉሩ ብቻ የሚወሰን አይሆንም። ወደ አንድ መንደርነት በተለወጠችው ሉላዊ አለም አፍሪካ ውስጥ የሚከሰት ቀውስ ወደ ተቀረው አለም መጋባቱ፣ መዛመቱ አይቀርም። ስለሆነም በአህጉሩ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ዘርፈ ብዙ አደጋ ለመከላከል በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንቆም ይገባል። የአፍሪካን እዳ ነገ ዛሬ ሳይባል በማቃለል፣ ከመቀነስ ልንጀምር እንችላለን። አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም / አይ ኤም ኤፍ / ከቀውሱ ለማገገም ከመደበው 50 ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ አፍሪካ ለአስቸኳይ የበጀት ማነቃቂያ 100 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል። በአጭር ጊዜ ከቀውሱ በቀላሉ ማገገም ስለማይቻል ለሚቀጥሉት ሁለት ሶስት አመታት ድጋፍና እርዳታው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በ2020 እ ኤ አ አፍሪካ ለሁለትዮሽ አበዳሪዎች የምትከፍለው እዳ 14 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህን እዳ መክፈል ስለማትችል፤ ከአለም ባንክ፣ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋማት ሆኑ ከሌሎች የገንዘብ ተቋማት የእዳ ቅነሳ እፎይታ እና የክፍያ ጊዜ ማስተላለፍ እንዲደረግላት ትጠይቃለች።
ከአለማቀፉ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከሌሎች አበዳሪ ሀገራት እና ከፈረንሳይ ቡድን አባላት ጋር የብድር ቅነሳን፣ ስረዛንና የእዳ ክፍያ ማስተላለፍን አስመልክቶ ፈጣን ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። የፈረንሳይ አበዳሪዎች ቡድን በመቀናጀት እኤአ በ2004 በሱናሚ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው የኢሲያ ሀገራት ብድር የመክፈያ ጊዜን እንደገና እንዳራዘሙት ሁሉ ዛሬም ተመሳሳይና ተጨማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ይህን አስመልክቶ ላቀረቡት ጥሪ፤ አይ ኤም ኤፍ፣ የቡድን 20 ሀገራትና የአውሮፓ ሕብረት ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪካን የንግድ ዘርፍ ከውድቀት መታደግ የሚሊዮኖች የስራ ዋስትና ማረጋገጥ ስለሆነ ከቀውሱ ለማገገም የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት የድህነት መጠኑን በግማሽ በመቀነስ፤ ገቢን ለእጥፍ በሚጠጋ በማሳደግ፤ ሰላምንና መረጋጋት በማስፈን ረገድ አበረታች ውጤትን አስመዝግበናል። ሆኖም ይህ ቀውስ በከፍተኛ ጥረት የተመዘገቡትን እነኝህን ውጤቶች ሊያሳጣን ይችላል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያችንን ባለፈው አመት ጀምረናል። በዚህም በ10 በመቶ የውጭ ንግድን፣ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚገኘውን መደበኛ የሀዋላ ገቢ/ሬሚታንስ/ በ32 በመቶ፣ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያችንን 40 በመቶ ለማሳደግ፤ እኤአ በ2030 ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት አቅደን እየሰራን ቢሆንም ኮሮና ቫይረስ እንዳያስተጓጉለን እንሰጋለን። የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአቅሙ 10 በመቶ ብቻ እየሰራ ከዚህ ቀውስ ያመልጣል ተብሎ አይጠበቅም። ሌሎች 10 ታላላቅ አፍሪካዊ አየር መንገዶችም ተመሳሳይ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። በመሆኑም አለማቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ዋስትና ሰጭዎች የገበያ እዳ ውልን እንዲያድሱ ማግባባት ይጠበቅበታል። ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ቀጣይነትና ተለማጭነት አዲስ አተያይ ያስፈልጋል። ሆኖም ከሁሉም ነገር በላይ አፍሪካ የሚያስፈልጋት ፈጣን የእዳ ክፍያ ማስተላለፊያ ውሳኔ ነው። ”
እንግዲህ ከዚህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው፤ የአይ ኤም ኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊያና ጆርጌቫ ተቋሙ ለ19 የአፍሪካ ሀገራት ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚሆን የብድር መክፈያን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን ገልጸዋል። የተቋሙ የብድር እፎይታ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እንግሊዝና ጃፓን የ280 ሚሊዮን ዶላር ተመሳሳይ የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ የሰጡ ሲሆን ቻይናና ኔዘርላንድ እንዲሁ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል። ሆኖም የሀገራችንን ስም በዚህ ዝርዝር አለመመልከቴ ስጋት ላይ እንደጣለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። የቡድን 20 ሀገራትም ለ76 ድሀ ሀገራት የ20 ቢሊዮን ዶላር የብድር ክፍያ እፎይታ ማድረጉን ይፋ አድርጓል። በእውነቱ ይህ አርዓያነት ያለው ተግባር ለአህጉሩ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ሲሆን ለአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ምዕራባውያን ደግሞ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።
ይሁንና ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ከባድ ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ እንደማይፈታ መረጃዎች አበክረው እየወጡ ነው። አይ ኤም ኤፍ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት የአለም ኢኮኖሚ ከ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ፤ እንዲሁም እኤአ ከ2008 የኢኮኖሚ ቀውስ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 3 በመቶ ያሽቆለቁላል ሲል አሟርቷል። ከ6 በመቶ በላይ እድገት ይመዘገባል ተብሎ ተተንብዮ የነበረው ኢኮኖሚ ነው እንዲህ የተንኮታኮተው። ዱላው አፍሪካ ላይ በተለይ ሀገራችን ላይ የበረታ እንደሚሆን ለመገመት የግድ የአዳም ስሚዝ ደቀ መዝሙር መሆንን አይጠይቅም። የአለም ጥቅል ምርት/ ጂ ዲ ፒ / የጃፓንና የጀርመን ድምር ኢኮኖሚ የሚያህል ማለትም በ9 ትሪሊዮን ዶላር ይቀንሳል ተብሎ ተሰግቷል። የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚ ከ6 በመቶ በላይ፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ደግሞ ከ2 በመቶ በላይ ይቀንሳል ተብሎ ተተንብዯአል። አሜሪካንን ጨምሮ የ170 ሀገራት የነፍስ ወከፍ ገቢ ይቀንሳል። እንዲሁም የአውሮፓ 7 ነጥብ 5 በወረርሽኙ ክፉኛ የተመታችው ጣሊያን 9 ነጥበ 1 በመቶ ይቀንሳል። ሆኖም ወረርሽኙን ከፈረንጆች አዲስ አመት በፊት መቆጣጠርና ውጤታማ የሆነ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ ከተቻለ እኤአ በ2021 ኢኮኖሚው እስከ 6 በመቶ ሊያንሰራራ እንደሚችል የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት ተስፋ አሰንቋል። ይሁንና ድህረ ኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ መነቃቃቱ የተሳካ ቢሆን እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞ ወደነበረበት ቁመናው ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም።
የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ /ዩኒሴፍ/ ወረርሽኙን ተከትሎ በመጋቢት ማብቂያ ባወጣው ጥናት የኢኮኖሚው እድገት በ1 በመቶ ሲቀንስ ከ14 እስከ 22 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለከፋ ድህነት ይዳረጋሉ። በኮቪድ – 19 ሳቢያ በሚከሰት የኢኮኖሚ ቀውስ ከድህነት ወለል የሚላቀቁ ሰዎች ቁጥር በ48 ሚሊዮን ይቀንሳል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ኮሚሽን
/ዩኤንኢሲኤ/ ይፋ ባደረገው ሌላ መረጃ የአፍሪካ ጥቅል ምርት በ3 ነጥበ 9 በመቶ ወይም በ70 ቢሊዮን ዶላር ያሽቆለቁላል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በ2 ነጥብ 9 ዝቅ ይላል ተብሎ ይሰጋል። የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ መዋዠቅ፣ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ሲቀንስ ከግብር የሚገኝ ገቢም ያሽቆለቁላል። አበዳሪና ረጅ ሀገራትም የወረርሽኙ ሰለባ ስለሆኑ ሀገሪቱ የምታገኘው ብድርና እርዳታም ይቀንሳል። ይህን ተከትሎ የበጀት ቅነሳ ይመጣል። ለልማትም ሆነ ለመደበኛ ወጭ የሚመደብ ሀብት ይቀንሳል። የበረራና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው መዳከም፣ የኀዋላ ገቢው መቀዛቀዝ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያን በእጅጉ ስለሚጎዳው አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችንና ሸቀጦችን ማስገባትን አዳጋች ያደርገዋል። እዳ ከፈላው ስለሚቋረጥ የዕዳ ጫናው እየከበደ ይሄዳል። የስራ እድል ፈጠራውም ወረርሽኙን ተከትሎ በመጣው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተነሳ 48 በመቶ ያሽቆለቁላል ተብሎ ተፈርቷል።
ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደሞከርሁት ወረርሽኙ በአፍሪካ አንድ እግሩን አስገብቷል። የመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ ካልተጧጧፈ ሁለት እግሩን ወደ አህጉሩ ለማስገባት ጥቂት ቀናት ይበቁታል። የደለበ ኢኮኖሚና የደረጀ የጤና መሰረተ ልማት ባነበሩ ምዕራባውያን ይህን ያህል የከፋ ጉዳት ካደረሰ ገና በቅጡ ከመሬት ያልተነሳ ኢኮኖሚ እና ልፍስፍስ የጤና ተቋማት ባሉበት አፍሪካ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ይህን መጣጥፍ እያጠናቀርሁ እያለ፣ በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ 5ሺህ ሲጠጋ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 150 እየተቃረበ ነው። አፍሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተረባረ ባለበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እስከ ዛሬ ከታየው የከፋ መሆኑ እየተነገረ ነው። የአፍሪካ ሀገራት የጤና በጀታቸውን በማሳደግ ወረርሽኙን መቆጣጠር፤ የሸማቹን የመግዛት አቅም ማጎልበትና የባንኮችን የወለደ ምጣኔ መቀነስ፣ ለንግድ ድርጅቶችና ለቤተሰቦች የገንዘብ አቅርቦትን ማመቻቸት እንደሚጠበቅባቸው የአለም ባንክ ይመክራል። ከዚህ ጎን ለጎን አበዳሪ ሀገራትና የገንዘብ ተቋማት የእዳ ክፍያ እፎይታን ጨምሮ የበጀት ድጎማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እየተለፈፈ ቢሆን እድሜ ለቀኝ አክራሪው፣ ሕዝበኛውና ለሉላዊነት ጠሉ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ታሪካዊ አጋጣሚ ካቀዳጃት የመሪነት አክሊል ስለአፈገፈገች ወረርሽኙን ለመከላከልም ሆነ እሱን ተከትሎ የተከሰተውን አለማቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመመከት የሚያስችል አመራር እየተመለከትን አይደለም። ትራምፕ አይደለም አለምን አቀናጅተው ሊመሩ ይቅርና የኋይታወሱን ጸረ ኮሮና ቡድን በቅጡ እየመሩም እያደመጡም ባለመሆኑ አሜሪካ በወረርሽኙ የተጎዱ ሀገራትን በአንደኝነት እየመራች ነው። እንደልማዳቸው ለአመራር ድክመታቸው የአለም ጤና ድርጅትን መስዋዕት፣ ሀጢያት ተሸካሚ አድርገዋል። አሜሪካ ለድርጅቱ ታዋጣው የነበረውን ከ400 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ማቋረጧን አስታውቀዋል። የአለም የጤና ድርጅት ድክመት ቢኖርበት እንኳ መደገፍ በሚገባው በዚህ ፈታኝ ሰዓት እንዲህ አይነት ግብታዊና ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱ አስተዳደራቸውን ክፉኛ እያስወቀሰው ይገኛል። ከምንጊዜም በላይ አለም ወረርሽኙን ለመከላከልና ከገባበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም መሪ በሚሻበት ቀውጢ ሰዓት በዚያ ሰሞን በተካሄደው የቡድን ሰባት ሀገራት ውይይት ማብቂያ ላይ ትራምፕ ኮቪድ – 19 ሳይሆን ” የቻይና ቫይረስ ” ካልተባለ በጋራ የአቋም መግለጫው ላይ አልፈርምም በማለታቸው ስምምነት ላይ ሳይደረስ ስብሰባው ተቋጭቷል። ዛሬ አለማችን እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እየተቅበዘበዘች፤ የምትይዘው የምትጨብጠው እንዳጣች እየታዘብን በሌላ በኩል የሉላዊነት/ ግሎባላይዜሽን/ ጀምበር እያዘቀዘቀች መሆኑን እየተመለከትን ነው። እኤአ በ2008 ከተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አገግሞ በፍጥነት ለመውጣት ባራክ ኦባማ እና የእንግሊዝ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን የሰጡት አይነት አመራር ዛሬ እዳማረን ቀርቷል። ቻይናም ትራምፕ በፈጠሩት የአመራር ክፍተት የተነሳ የመሪነት መንበሩን ለመረከብ መልካም አጋጣሚ የተፈጠረላት ቢመስልም ከኮሮና ቫይረስ የዞረ ድምር/ሀንጎቨር/ ገና በቅጡ ስላላገገመችና የወረርሽኙን ሒሳብ እያወራረደች ስለሆነ ይለፈኝ ያለች ይመስላል። በድምሰሳው አለማችን እንዲህ መሪ አልባ ሆና አታውቅም።
እንደ መውጫ
በወረርሽኙ የተነሳ ሀገራችን ከአሁኑ ኢኮኖሚያዋ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው። የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያችንም ሆነ የብልፅግና ትልሟ ላይ ጥላውን አጥልቷል። የውጭ ንግዷ፣ የበረራ ኢንዱስትሪዋ፣ ቱሪዝም በአጠቃላይ የአገልግሎቱ ክፈለ ኢኮኖሚዋ ክፉኛ እየተመታ ነው። ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ያበረክተው የነበረው አስተዋጾም በእጅጉ እየተዳከመ ነው። በእነዚህና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ መግፍኤዎች የተነሳ መንግስት ይሰበስበው የነበር ገቢ ስለሚቀንስ የበጅት ጉድለት ስለሚገጥመው ሚዛኑን መጠበቅ ይቸገራል። ጉድለቱ ለመሙላት ይጠቀምበት የነበረውን እርዳታና ብድር ደግሞ በወረርሽኙ የተነሳ በቀላሉ ማግኘት ስለማይችል በጀቱን ለመቀነስ ይገደዳል። ደረጃው ይለያይ እንጂ ወረርሽኙ ሁሉንም ተጎጂ ስለአደረገው ብድሩንም እርዳታውን ማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል። ለዚህ ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለገንዘብ ተቋማቱ፣ ለለጋሽና አበዳሪ ሀገራት ያቀረቡት ጥሪ በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ምላሽ ሊያገኝ ያልቻለው። በእርግጥ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና ሊሆን ይችላል። ሆኖም በመጀመሪያ አይኤምኤፍ ሰሞኑን ደግሞ የቡድን 20 አባል ሀገራት በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ሰጥተዋል። ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ እንዲሉ ቢሆንም በቀጣይ ተጨማሪ እገዛዎችን ለማግኘት የአፍሪካ ሕብረትን ያሳተፈና የተቀናጀ ተቋማዊ ጥረት ይፈልጋል። የአህጉሩ ችግር ከዚህ በላይ የተቀናጀ የእዳ ስረዛ፣ ቅነሳ እንዲሁም አዲስ ብድርና እርዳታ ይፈልጋል። ተስፋው ሙሉ በሙሉ የተሟጠጥ ባይሆንም ሌሎች አማራጮችን ማማተር እና የአህጉሩን አቅም አቀናጅቶና አሟጦ የመጠቀም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን
ይጠብቅ ! አሜን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com