እያንዳንዱ ማህበረሰብ፣ ሕዝብ ያለመተቸት ፣ /ያለመሄስ/ ልዩ መብት /privilege/ የቸራቸው «መልአክ አከል» ዜጎች አሉት፡፡ አዎ! ዓለማችን በአንድ ድምፅ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ለኔልሰን ማንዴላ፣ ለማህተመ ጋንዲ፣ ለማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ወዘተ… ያለመተቸት፣ ያለመሄስ ልዩ መብት ለግሳቸዋለች፡፡
እኛም በተንሸዋረረው የማንነት ዓይናችን ስለምናስብና የዘርጣጭነት አባዜ ስለተጠናወተን ሆኖ እንጂ በሀገራችን በደርዘን የሚቆጠሩ ይሄ ልዩ መብት ያላቸው ዜጎች አሉን፡፡ እንደ ማህበረሰብ ይሄን ያለመተቸት ልዩ መብት ፈቅደን የሰጠናቸው ፖለቲከኞች ፣ ምሁራን፣ ልሂቃን፣ ታዋቂ ሰዎች አሉን፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ይሄን ልዩ መብት የሰጠናቸው ቸር፣ ለጋስ ስለሆን ሳይሆን ለሀገር፣ ለወገን ካበረከቱት አስተዋጽኦ ፤ ከከፈሉት መስዋዕትነት ተነስተን እውቅና የምንሰጥበት አንዱ መንገዳችን ስለሆነ ነው ፡፡
አለመታደል ሆኖ ሁላችንም የምንቀበለው፤ የምንስማማበት የጋራ፣ መሪ፣ ታሪክ፣ ጀግና እንደሌለን ሁሉ፤ ሁላችንም የምንግባባበት ያለመተቸት፣ ያለመነቀፍ ልዩ መብት የምንሰጠው ዜጋ አለ ለማለት ባንደፍርም በየግላችን ግን አሉን፡፡ ባደግሁበት ማህበረሰብ ይሄን መብት የሰጠነው፤ ጀግና፣ መሪ፣ ፖለቲከኛ፣ ልሂቅ፣ አክቲቪስት፣ ወዘተ… ሰው ይኖራል፡፡ በግሌ በሙያዬ ያለመነቀፍ ልዩ መብት የሰጠኋቸው ጋዜጠኞች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የሸገሯ መዓዚ፣ የጦቢያው ጋሼ ሙሉጌታ፣ እስክንድር፣ ተመስገን ፣ ወዘተ… ይገኙበታል ፡፡
ይሁንና ይሄ ያለመነቀፍ ልዩ መብት ሁልጊዜ ከለላ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም፡፡ ነገር ግን ጉድፍ ድክመት፣ ስህተት ከተገኘባቸው ጊዜ ሚዛናዊና ተጨባጭ በሆነ አግባብ በጨዋነት የሚተቹበት «ፍትሕ!» መፅሔቱን ትንታግ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ያለመተቸት ልዩ መብቱን፣ መድኑን ከይቅርታ ጋር ገፍፌ ልሄሰው ወደድሁ፤ ከዚያ በፊት ድፍረቱን፣ አርበኝነቱን፣ ፅናቱን ፣ ጀግንነቱን፤ ከእስክንድር ውጭ የሚስተካከለው፣ የሚወዳደረው ጋዜጠኛ እዚች ሀገር ላይ አልተፈጠረም ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ቀደም ባለው የጋዜጠኝነት ህይወቱ የመብት ተሟጋችነትን፣ ተቃዋሚነትንና ጋዜጠኝነትን እየቀላቀለ፣ መሳ ለመሳ ሊያስኬድ እየሞከረ እንደ ጋዜጠኛ ለመቀበል እቸገር ነበር ፡፡
አሁን ግን በሙያው በስሎ፣ በሚያነሳቸው ሀሳቦች ጎልብቶ፣ ጠልቆ ከመምጣቱ ባሻገር የመብት ተሟጋችነትን፣ ተቃዋሚነትን ከጋዜጠኝነት ጋር ማሳከርን ትቶ ገዝፎ ጋዜጠኛ እና ጋዜጠኛ ብቻ ሆኖ መምጣቱ ከጠበቁት በላይ እንደሆነብኝ አልሸሽግም፡፡” ‘ በዳግማዊ’ ፍትሕ ” አምስት ተከታታይ ህትመቶችም ይሄን ጥሬ ሀቅ ነው ማረጋገጥ የቻልኩት፡፡ ተሙ በዚሁ ከቀጠለ ፤ ገድሉ በዚች ሀገር መፃኢ የህትመት ጋዜጠኝነት ገፅ ከቀዳሚዎች ተርታ በወርቃማ ቀለም እንደሚከተብ አል ጠራጠ ርም፡፡ ” በፍትሕ ፣ 1ኛ ዓመት ፣ ቁጥር 05 ፣ ታህሳስ 2011 ዓ.ም ” እትም ፤ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በመፅሔቱ ሽፋን አስቀድሞ ፤ ” የዐብይ መንገድ ” በሚል ርዕስ ይዞት በወጣው የተሙ መጣጥፍ ላይ ያለኝን ልዩነት በቅንነት መግለፅ ወደድሁ፤ የዚህ መጣጥፍ አፅመ መልዕክት በአጭሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም ትናንት እንዳጋጠሙን ገዥዎች ነገ ወደ ፈላጭ ቆራጭነት፣ አምባገነንነት የማይቀየሩበት ምክንያት የለም የሚል በስጋት ላይ ያነጣጠረ ሥጋት ነው፡፡ በኢትዮጲስ፣ በሪፖርተርና በተለያዩ ድረ ገፆች የበቁ ምሁራን ይሄን ሀሳብ በተደጋጋሚ በተለያየ ርዕስ ግን በተመሳሳይ ጭብጥነት ሲያነሱት ሲጥሉት መመልከቴ ለመጣጥፌ አብይ መነሻ ነው ፡፡
ይሄ ገና በይሆናል፤ በስጋት ላይ የተመሰረተ የእነ ተሙ ስጋት ውሃ የማያነሳ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድፍረት በተለይ በመከላከያ፣ በደህንነት፣ በምርጫ ቦርድ፣ በዳኝነት አካሉ፣ ወዘተ… ላይ እየወሰዷቸው ያሉ ሀቀኛ ማሻሻያዎች እና ተክለ ሰብዕናቸው የተዋቀረበትን አውድ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ፤ ንፅፅሩም ዘመነ ጓዴነት /contemporary/ የሌለውና አግባብነት የጎደለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ መነፃፀር ካለባቸው ከራሳቸው ጋር ነው ፡፡ አዎ ! ወደስልጣን ሲመጡ ከገቡት ቃል አኳያ፤ ለፍትሐዊነት፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር እንደሚተጉ በፓርላማው የበዓለ ሲመት ንግግራቸው ካመላከቱን ፈለገ ካርታ አኳያ ነው ሊነፃፀሩ የሚገባቸው፡፡ በምንም መመዘኛ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አይደለም ከዓለማችን ሰው በላ አረመኔ፣ ደም ጠጭ፣ አውሬው ኢዲ አሚን ጋር ከዘመኑ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ነን ይሉ ከነበሩ መሪዎች ጋር አይነፃፀሩም፡፡
ተሙ በመቀጠል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመንግሥቱ ኃይለማርያምና ከመለስ ዜናዊ ጋር ሊያነፃፅር ከጅሏል፡፡ እነዚህ አምባገነኖች፣ ኢዲ አሚንን ጨምሮ ወደስልጣን በመጡ ሰሞን ሕዝባዊ ቅቡልነትን /legitimacy/ ለማግኘት አስመሳይ ማሻሻያዎችን /pseudo reforms/ አድርገዋል፡፡ ዛሬም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እያደረጉት ያለው ማሻሻያ ከዚህ የተለየ ላይሆን ይችላል ይለናል ፡፡ በነገራችን ላይ ስጋት በገደምዳሜ፣ በአገም ጠቀም ሌሎች ፀሐፍትም ይጋሩታል፡፡ ይሁን እንጅ በምንም የንፅፅር መንገድ አይደለም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ከመንግስቱና ከመለስ ጋር ፤ መንግሥቱን ከመለስ ጋር ማነፃፀር ተቀባይነት የለውም፡፡ መንግሥቱ በዘመኑ ከነበሩ አምባገነኖች፤ መለስን በተመሳሳይ ጊዜ ወደሥልጣን ከመጡና ከነበሩ ገዥዎች ጋር እንጂ ከቀደሙት መሪዎች ጋር ለማነፃፀር መሞከር የሚደረስበትን መደምደሚያ ተጠያቂያዊና አመክኖአዊ አያደርገውም ፡፡
መንግሥቱም ሆነ መለስ የወሰዷቸውን ማሻሻያዎች ማነፃፀር ቢያስፈልግ እንኳ መነፃፀር ያለባቸው በየዘመናቸው የነበሩ መሰል አገዛዞች ከወሰዷቸው ማሻሻያዎች ጋር እንጂ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አይደለም ፡፡
እነዚህ አገዛዞች ያመጧቸው ” ለውጦች ” ከቀደሟቸው አገዛዞች ማለትም ደርግ ከንጉሳዊ አገዛዙ፤ ኢህአዴግ ከደርግ አንፃር እንጅ በራሳቸው ስልጣን ባለው አገዛዝ ላይ የተወሰዱ ማሻሻያዎች አልነበሩም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የለውጥ ኃይሉ እየወሰዷቸው ያሉት ማሻሻያዎች ግን ራሳቸው በሚመሩት አገዛዝ ላይ መሆኑ ከቀደሙት አገዛዞች ” ማሻሻያዎች ” ፍፁም የተለየና የማይነፃፀር ያደርገዋል፡፡
የተሙ ሌላ ማነፃፀሪያ ኢህአዴግም፣ ደርግም ታዋቂ ሰዎችን ይሾሙ እንደነበረው ሁሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም ታዋቂ ሰዎችን ሾመዋል የሚለው ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይሄ ንፅፅርም ውሃ አያነሳም፡፡ ለምን ቢባል ክቡርነታቸው የሾሙት ድርጅታቸውን አምርረው ይቃወሙና ይተቹ እንዲሁም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ሞገስ ያላቸውን ሰዎች ነው፡፡ ለእዚህም ክብርት ብርቱካንን ፣ ወ/ሮ መዓዛንና አርቲስት ሰርፀን ያጤኗል ፡፡ በአንፃሩ ደርግም ሆነ ኢህአዴግ የሾሟቸው ታዋቂ ሰዎች ግን ደጋፊዎቻቸው እንጂ ተቃዋሚዎቻቸው አልነበረም ፡፡
መለስም ሆኑ መንግስቱ የወሰዷቸው ማሻሻያዎች ተሙ ” ማደንዘዣ !? ” ያላቸውን ለውጦች ያመጡት ዙፋናቸውን ለማደላደልና ሥልጣን ለመያዝ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም አስበው እንዳልነበር የመጨረሻ ውጤታቸው አረጋግጦልናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የወሰዷቸው ጅምር ማሻሻያዎችና ያመጧቸው ለውጦች ግን የኢህአዴግን ስልጣን እና አይዶሎጂ የሚያደላድሉ ሳይሆኑ፣ በተቃራኒው የሚገዳደሩና የሚነቀንቁ ከመሆናቸው ባሻገር ሀገርን፣ ሕዝብን ከሚያስቀድም ቅን ልብ የፈለቁ ናቸው ፡፡
አዳዲሶቹን የማንነትና የወሰን ጉዳዮች እንዲሁም የዕርቅ ኮሚሽን አዋጆችም ሆኑ፤ የዳኝነት ሥርዓቱ፣ ምርጫ ቦርድ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ደህንነቱ፣ ፖሊሱ፣ መከላከያው፣ ወዘተ… ነፃ ሆኖ ከተደራጀ፤ የፀረ ሽብር ሕጉ፣ የምርጫ ሕጉ፣ የፕሬስ አዋጁ፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ወዘተ… በአጠቃላይ አፋኝ ሕጎች ከተሻሻሉ ለውጦቹ ሀቀኛ በመሆን የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታውን ተቋማዊ ለማድረግ ያግዛሉ እንጂ ተሙም ሆነ ሌሎች እንደሚሉት በምንም መመዘኛ የኢህአዴግን ሥልጣን ዘመን አያራዝሙም፤ ሕዝብን የማዘናጊያ “ማደንዘዣ” የይስሙላ ማሻሻያዎችም አይደሉም ፡፡
ተሙ፦ ‘ ጠለፋው ‘ በሚል ርዕስ ያቀረበው ሀሳብ ግልፅነት የጎደለውና እርስ በእርሱ የሚጣረስ ቢሆንም ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳባቸውን የሚቃወሙ፤ ስልጣናቸውን የሚገዳደሩ ኃይሎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ የዚያን ጊዜ እንደአለፉት ገዥዎች አምባገነን ይሆናሉ፤ ለውጡንም ለግል ሥልጣናቸው ሊጠልፉት ይችላሉ የሚለውም የምንአልባት ስጋት ድምዳሜ ነው፡፡
ይህም ከአለፉት አገዛዞች ያዞረ ድምር /hangover/ ድባቴ ላለማገገማችን ማሳያ ነው፡፡ አሁንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን በእነ መለስ፣ በእነ መንግሥቱ ሽንቁር የማየት የተሳሳተ አባዜ አለቀቀንም ማለት ነው፡፡ እሳቸውን በራሳቸው ፖለቲካዊ ተክለ ሰብዕናና በገቡት ቃል መመዘን እየተቻለ፤ ያልተገባ ማነፃፀሪያ ፍለጋ ግራ ቀኝ መባዘን አስፈላጊም ምክንያታዊም አልነበረም ፡፡
ተሙ ፦ የ ” የዶ/ር አብይ መንገድ ” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ፤ ቃል በቃል ” የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አጀማመርም ከተጠቀሱት መሪዎች የተለየ አይደለም ፡፡ ” ይለናል ፡፡ በምንም መመዘኛ ፤ በቅርፅም በይዘትም ፤ በወጡበት አውድም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አጀማመር ከመንግስቱ፣ ከመለስ፣ ከኢድ አሚን ጋር ተመሳሳይ አይደለም ፡፡ ሊሆንም እንደማይችል ከላይ ለማሳየት የሞከርሁ ቢሆንም፤ ሌላ መለያቸውን ላንሳ ፡፡
ደረጃው ይለያይ እንጂ መለስም፣ መንግሥቱም ልበ ደንዳኖች፣ ሸረኞች፣ አረመኔዎች፣ በስልጣን ለመቆየት ምንም ከማድረግ የማይመለሱ ጨካኞችም ነበሩ፡፡ ለእነሱ ቃል ኪዳን፣ ጓደኝነት፣ ሞራ፣ ህሊና፣ ይሉኝታ፣ በአጠቃላይ ሰውነት ከግል ፍላጎታቸው፣ ከስልጣናቸው መረገጫ ሥር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሁለቱም ገዥዎች፣ ነጂዎች እንጂ መሪዎች /leaders/ አልነበሩም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ተፈጥሮአዊ መሪ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ አሳይተውናል ፡፡
ሌላው ተሙ ፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ፑቲን በስፖርት ቤት የተዋወቋቸውን ሰዎች ሹመዋል ቢልም እነማንን እንደሆነ ስላልገለፀ ከአሉባልታ ያላለፈ ቢሆንም፣ አቅምና ብቃት እስካለው ድረስ ችግሩ አልታየኝም፤ በየትኛውም ዓለም ያለ መሪ የሚያደርገው ነው፡፡ በአቅሙ፣ በብቃቱ የሚያውቀውን አልያም በቅርቡ ባሉ ባለሟሎቹ የተጠቆሙን /recommend/ ወደ ኃላፊነት ማምጣት የተለመደ አሰራር ነው ፡፡
ተሙ ፦ ራሱ ለመፅሔቱ ጋዜጠኞችን የቀጠረው በሆነ አጋጣሚ ያወቃቸውን እንጂ በክፍት የሥራ ቦታ በግልፅ አወዳድሮ አይደለም ፡፡ ይሁን እንጂ የብሔር ተዋፅኦን መሰረት ያደረገው የኢህአዴግ አሰራር ጠቅላይ ሚኒስትርን ብዙ የሚያወላዳ አይደለም፡፡
ሌላው ተሙ ” መርህ ይከበር ” በሚል ንዑስ ርዕስ የለገሀር መልሶ ማልማት ያለጨረታ ለ Eagle Hills መሰጠቱ መርህን የሚጥስ ነው ይለናል፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በየትኛውም ዓለም በአብዛኛው ማለት ይቻላል በድርድር፣ በሚፈጥረው የሥራ ዕድል፣ በሚያስተዋውቀው የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግር ፣ ይዞት በሚገባው ካፒታል፣ ወዘተ… ይመረጣል እንጂ የግድ በጨረታ ይሁን የሚል አሰራር የለም፡፡ መንደሩን እኮ መንግስት አይደለም የሚያስገነባው፤ ለምንድን ነው ጨረታ የሚያወጣው? ስለሆነም በዚህ ግዙፍ ኢንቨስትመንት የተጣሰም፣ የሚከበርም መርህ የለም ፡፡
የአሜሪካ ግዛቶች መሪዎችና የየከተሞች ከንቲባዎች አማዞን ዋና መሥሪያ ቤቱን በግዛታቸው፣ በከተማቸው እንዲገነባ ለማግባባት፣ ቀልቡን ለመሳብ የገቡበትን የእኔ እበልጣለሁ እኔ ውድድር፤ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የምትወጣ ከሆነ ባንኮችና ዓለማቀፍ ኩባንያዎች ገና ከለንደን ዋና መቀመጫቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ በሚል ፓሪስ እና በርሊን የገቡበትን ውድድር ላስተዋለ የተሙ መርህ ይከበር ውሃ አያነሳም ፡፡ በመዲናዋ መሪ ዕቅድ ለከተማዋ አረንጓዴ ስፍራ ለ/city park/ የተያዘ ቦታ ለመንደር ግንባታ መዋሉ አግባብ አይደለም ያለውም መንደሩ መናፈሻ ያካተተ እንደሚሆን ስለተገለፀ ብዙ የሚያሰጋ ሆኖ አላገኘሁትም ፡፡
ምኒልክንም ሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ስንገመግም ከኖሩበትና ካሉበት ዘመን አውድ አኳያ ካልሆነ ሒሱ፣ ትችቱ የተንሸዋረረ ከመሆኑ ባሻገር መሪዎችም ሆኑ ገዥዎች በታሪክ ተገቢውን ገፅ እንዲያገኙ ስለማያደርግ፤ ግምገማችንና ንፅፅራችን ሁል ጊዜ ዘመነ ጓዴነትን የተከተለ ሊሆን ይገባል ፡፡
እንደ ቶማስ ፣ ናቡከደነፆር ካላየሁ አላምንም ማለት የእነ ተሙ መብት እንደሆነው ሁሉ፤ ባለፉት ስምንት ወራት ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ ተስፋ ሰጭ ማሻሻያዎችን፣ ለውጦችን ሲመለከቱ ደግሞ እውቅና መስጠት፣ ማመን ያባት ነው፡፡ ገና ለገና ደርግ በአደራ የተሰጠውን አብዮት ቅርጥፍ አድርጎ በልቷልና ፤ ሕወሓት/ ኢህአዴግ በቃሉ አልተገኘምና ፤ ዛሬም የለውጥ ኃይሉን በዚህ የዞረ ድምር ስሌት ብቻ አይታመንም ብሎ አበክሮ መደምደም አመክኖአዊነት የጎደለው ከመሆኑ ባሻገር ውሃ የማያነሳ ተጠየቅ ነው ፡፡ በእርግጥ ተጠየቅ ሊባል ከተቻለ ፤
እምዬ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን !!!
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
በጋዜጠኛ ቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )