“ጊዜ ያለው ከጊዜ ይማር!”
“ትናንት” ከሃያ አራት ሰዓት በፊት የኖርንበት እለት ብቻ አይደለም። አምናም፣ ካቻምናም በትናንት ሊወከል ይችላል። ወደ ኋላ አፈግፍገን ዐሥር፣ ሃያ፣ ሃምሳ፣ መቶ ዓመታትንም ቢሆን ካለፈው ዘመን እየቆነጠርን “ትናንት” እያልን ልንግባባበት እንችላለን። “ትናንት” ብዙ ታሪኮች፣ ብዙ ትርክቶች፣ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶች፣ ብዙ ደስታና ሀዘኖች፣ ብዙ ብርታትና ሽንፈቶች የተከማቹበት የዓመታት ሽበት (ቢያሻም ሺህ ውበት በሉት) እና የኃላፊ ጊዜያት ካዝና ነው።
“ዛሬ” ትናንትን ተመርኩዞ የቆመ የነገ ምርኮኛ ነው። “ነገ” በምኞት የሚያማልል የዛሬ እቅድ ነው። ትናንት የታሪክና የትካዜ “ቅርስ” የመሆኑን ያህል “ዛሬ” ደግሞ ነገን ተስፋ አድርጎ ወደ ኋላ የሚሸሽ የጊዜ ጥላ ነው። “ነገ” የምኞት ዓለም፣ የተስፋ መዳረሻ “በቆይ ብቻ” ተስፋ የሚፎከርበት መጽናኛ ጭምር ነው። ቢሆንም ግን ከትናንት ይልቅ ዛሬ፣ ከዛሬም ይልቅ ነገ በእጅጉ ይናፈቃል። ትናንትን በትምህርትነቱ፣ ዛሬን ለመሻሻል፣ ነገን በተስፋ ካልኖርንበት ሕይወት መሪርና ኮምጣጣ ሆና ተጎመዝዛለች። ለመንደርደሪያነት የመረጥኩት ይህ ጊዜ ተኮር ፍልስፍና ብዙ ሃሳቦች እንደታጨቁበት ይገባኛል። ልቀጥል …
“ሀገር የደነገጠበት ትናንት”
የዛሬ ሦስት ዐሠርት ተኩል ዓመታት በፊት ነበር። 1978 መጨረሻ ግድም። እንደ ዛሬው ሀገርን በድንጋጤ የመታ አንድ አዲስ ክስተት ይፋ ተገልጦ የሕዝብ ሁሉ የጋራ መወያያ አጀንዳ ሆኖ ነበር። እንደ ዛሬው የሀገርን ጉልበትና አቅም በመፈታተን ብቻ ሳያበቃ “በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ በእርስ በእርስ ጦርነትና በርሃብ አሳር ስቅሏን እየተጋተች ለነበረችው ኢትዮጵያ ሌላ የራስ ምታት ሆኖባት ናላዋን አዞራት። ጉዳዩ የኤች.አይ. ቪ/ ኤድስን ወረርሽኝ የሚመለከት ነበር።
ለሀገራችን ብቻም ሳይሆን ለትልቋ ዓለማችን ጭምር እንደ ዛሬው ኮቬት-19 ወረርሽኝ አዲስ ክስተት የሆነው ይህ የቫይረስ ጥቃት ከዳር ዳር ማነጋገር ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም ሽብር ላይ ጥሎ እግዚኦ ያሰኘ ክፉ ዜና ነበር። በኢኮኖሚያቸው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የነበሩ ሀገራት የበሽታውን አጀማመር፣ ዓይነትና የመተላለፊያ መንገዶቹንም በአብዛኛው ለይተው ካወቁ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠሩ ቢሆንም ከሀገራችን ጆሮ የደረሰው ግን ዘግይቶ ነበር።
የበሽታው ጉዳቱ እንጂ ምንነቱና የትመጣነቱ ገና ፍንትው ብሎ በውል ያልለየለትን ይህንን አዲስ ክስተት ለመግታትና ሕዝቡን ከወረርሽኙ ለመታደግ መንግሥት አንድ ብሔራዊ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ነበር። ዋናው ተወርዋሪ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ይመራ የነበረው ጊዜው ረዘም ከማለቱ የተነሳ ካልተሳሳትኩ በስተቀር በወቅቱ የጤና ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር ሰብሳቢነት እንደነበር ትዝ ይለኛል። በዋናው ግብረ ኃይል ሥር የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቫይረሱን ጥቃት ለመከላከል የምክቶሽ ዘመቻው በፍጥነት እንዲጧጧፍ ርብርቡ ተጀመረ።
እንደማስታውሰው የሚዲያውን ኮሚቴ ይመሩ የነበሩት የያን ጊዜው የፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና ትንታግ ብዕረኛው አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ሲሆኑ ከኮሚቴው አባላት መካከል የቅስቀሳ ሥራውን የሚያስተባብረው ደግሞ ተወዳጁና የምናከብረው የፕሬስ ድርጅቱ ባልደረባና ደራሲው ብርሃኑ ዘሪሁን ነበር።
የደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን (በወቅቱ አብዛኞቻችን የምንጠራው ጋሽ ብርሃኑ እያልን ነበር) ዋነኛ ኃላፊነት በሚዲያ የሚተላለፉ የፀረ ኤች. አይ. ቪ/ኤድስ ጽሑፎችን ማዘጋጀትና ማስተባበር ነበር። የእርሱ ቢሮ ይገኝ የነበረው በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሰባተኛ ፎቅ ላይ ሲሆን የእኔ ቢሮ ይገኝ የነበረው ደግሞ በዚያው ሕንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነበር። እርሱ ባልደረባነቱ ለፕሬስ ድርጅት ሲሆን፣ እኔ ደግሞ የእለት እንጀራዬን የማገኘው ለማተሚያ ቤቱ ተቀጥሬ ቢሆንም ቅርርባችን ግን እንደ አንድ ተቋም የሥራ ባልደረቦች ነበር። ያቀራረበን ልክ እንደ ዛሬው በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣና በክፉ አመራሮች መክና በቀረችው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ከአንድ መደበኛ የተቋሙ ጋዜጠኛ ባልተናነሰ መልኩ “የበጎ ፈቃድ” አምደኛ ሆኜ አገለግል ስለነበር ነው።
ይሄው የኤች. አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳይ የሀገሪቱ ዋነኛ ትኩረት ሆኖ በገነነበት አንድ እለት ጋሽ ብርሃኑ ዘሪሁን ቢሮው አስጠርቶኝ “ብሔራዊ ዘመቻ” የታወጀበትን ያንን ሀገራዊ አጀንዳ ከግብ ለማድረስ እንዲያግዝ የጋዜጣና በመድረክ ላይ የሚቀርቡ ጽሑፎችን በማዘጋጀት እንድተባበር በአደራ የከበደ ጥያቄ አቀረበልኝ። መቼም የሙያችን አርዓያ ሰብ (Role Model) እና የዕድሜ አንጋፋችን የሆነን ጎምቱ ተምሳሌት ትዕዛዙን እምቢ ማለት ስለማይቻል ፈቃደኛነቴን ገልጬለት ከቢሮው ተሰናብቼ ወጣሁ።
ቃሌን በማክበርም ሳልውል ሳላድር “መልካም ቅንዓት በታከለበት ስሜት የወዛ” አንድ ጠብሰቅ ያለ የቅስቀሳ ጽሑፍ አዘጋጅቼ አቀረብኩለት። በጣም ደስ አለው። ዝምተኛ የሚባለው ጋሽ ብርሃኑ የዚያን እለት ፍልቅልቅ እያለና እየቀለደ ደስታውን የገለጸበት ሁኔታ ዛሬም ድረስ ከትዝታዬ አልደበዘዘም።
በማግስቱ እንደተለመደው ቢሮው ድረስ አስጠርቶኝ ጽሑፌን ከኮሚቴው ጋር በሚገባ ማንበባቸውን ከገለጸልኝ በኋላ ቅሬታ ባረበበት ገጽታ አስተያየቱን እንዲህ ሲል ሰጠኝ። “ጽሑፍህን ከኮሚቴው አባላት ጋር በሚገባ አንብበነዋል። ሥነ ጽሑፋዊ ውበቱ እንዳለ ሆኖ ለማስተላለፍ የፈለግኸውን መልእክት በተመለከተ ግን አቀራረብህ ከበሽታው ይልቅ የሚያስፈራና የሚያሸብር ነው። ስለዚህ ለታሰበው ዓላማ መዋል ስለማይችል እንዲመለስልህ ተወስኗል።”
“ከበሽታው ይልቅ የሚያሸብር” የሚለው አባባሉ በተመላሹ ጽሑፌ የመጀመሪያ ገጽ ላይ በአረንጓዴ ብዕር ሠፍሮ ነበር። ለጊዜው የወጣትነት ስሜቴ ቢነዋወጥም ቆም ብዬ ሳሰላስል ግን ታላቁ ጋዜጠኛና ደራሲ ጋሽ ብርሃኑ የሰጠኝ አስተያየት እውነትነት ነበረው። እርሱስ ምን ያድርግ የጽሑፌ መልእክት “በጎ ቅንዓት የወለደው የከፋ እውነት” ቢሆንበትም አይደል።
ዕድሜውን ያደለን የዚያ ዘመን ዜጎች እንደምናስታውሰው ልክ እንደኔ ጽሑፍ ሁሉ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን አስመልክቶ በሚዲያ ይቀርቡ የነበሩት የወቅቱ የቅስቀሳና የማስተማሪያ ጽሑፎች፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ምን ያህል ያስፈራሩና ያስደነብሩ እንደነበር እናስታውሳለን። በወቅቱ ከተሰሩት ሀገራዊ “ያለማወቅ ስህተቶች” መካከል አንዱ ቫይረሱ እንደ ማንኛውም በሽታ እንዲቆጠር ከማስተማር ይልቅ ልክ እንደ አንድ የፈጣሪ የኃጢያት ቅጣትና ቁጣ ተደርጎ ይገለጽ ስለነበር ብዙ የቫይረሱ ተጠቂዎች ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉና እንዲገፉ ምክንያት ሆኗል።
በዚሁ በተሳሳተ ቅስቀሳ በሽታውን አንዴ ከሲኦል፣ አንዴ ከገሃንም እሳት ጋር እየተነጻጸረ ይቀርብ ስለነበር ብዙዎቹ ህመምተኞች ባህሪይው በውል ያልለየለት የህመሙ ጉዳይ ሳያንሳቸው በሞራላቸው ላይ የደረሰው ስብራትና የስሜት ህመም ይህ ነው የሚባል አልነበረም። ከማሕበረሰቡ እንዲገለሉ፣ አንዲገፉና ባይተዋር እንዲሆኑ በተፈጠረባቸው ጫና ምክንያትም ብዙ ዜጎቻችን ድርብርብ ጉዳት እንዲያስተናግዱና ድብርት ውስጥ እንዲወድቁ ተፈርዶባቸው ነበር። “አንድ ክረምት የገደለውን ዘጠኝ ክረምት አያስነሳውም” እንዲሉ ከጅምሩ የተሳሳተውን ቅስቀሳ ሳይውል ሳያድር ለማረም ቢሞከርም ዘርፈ ብዙ የሆነ የገዘፈ ሀገራዊ ጠባሳ ትቶብን ሊያልፍ ግድ ሆኗል።
“ብልህ ከታሪክ ይማራል፤ የተኮነነ ደግሞ የታሪክን ስህተት ይደግማል”፤
ዛሬም የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የሚሠጡና በቀላሉ እየታዩ የሚደጋገሙ አሉታዊ ገለጻዎችና ቅስቀሳዎች ጉዳታቸው ሳይከፋ መታረም ያለባቸው ይምስለኛል። እርግጥ ነው ወረርሽኙ እንኳን ከድህነት ጋር ወላንሶ (ትግል) ለገጠምነው ለእኛ ቀርቶ ለባለጠጎች ሀገራትና ለጠበብቱ ሳይቀር ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ግራ እንዳጋባቸው ይታወቃል።
ቢሆንም ግን በሽታውን ከሞት ጋር ብቻ አቆራኝቶ መግለጽና ማስተማር ከትናንቱ በከፋ ደረጃ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ሊጤን ይገባል። በተለይም የሚዲያ ባለሙያዎችና የኪነ ጥበባት ተሰላፊዎች ይህንን ጉዳይ በሚገባ ቢያስቡበት ይበጃቸዋል፤ ይበጀናልም።
ሕዝቡ በተቻለ መጠን ራሱን በጥንቃቄ እንዲጠብቅ መምከርና ማስተማር ተገቢ ነው። ጉዳዩ በቅርበት የሚመለከታቸው ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች የሚሠጧቸውን ምክሮች መተግበርም ግዴታ ነው። ስናስነጥስ በክንዳችን አፍንጫችንን መሸፈን፣ አካባቢያችንንና የነካካናቸውን ቁሳቁሶች በቫይረሱ ማምከኛዎች ማጽዳት፣ እጅን በሳሙናና በውሃ ደጋግሞ መታጠብ፣ ማሕበራዊ ርቀትንና ትፍግፍግን በአዋቂ ሰው ሁለት እርምጃ መራቅ፣ ለቫይረሱ አጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ራስን ማራቅና የአፍና የአፍንጫ ጭምብል ማድረግ፣ ድንገት እንኳ ቫይረሱ የእኛን ጤንነት “ማንኳኳት” ከቻለም ራሳችንን ማግለልና ቤተሰቦቻችን እንዳይጠቁ ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ዋናው የውዴታ ግዴታችን ጭምር መሆኑን በሚገባ ማስገንዘብ ለኮሮና ቫይረስ ዋና የመከላከያ መፍትሔዎች ናቸው። እኒህን መሠረታዊ ዕውቀቶች ነው አጽንኦት ሰጥተን ልናስተምርና ለሕዝቡ ልናስገነዝብ የሚገባው። ደጋግሞ አንድን ጉዳይ ማስታወስ ሊያሰለች የሚችል ቢመስለንም መደጋገሙ ያነቃል እንጂ ጉዳይ አይኖረውም።
ከዚህ በተረፈ ግን ኮቬት-19 ቫይረስ ወደ ሞት የሚያደርስ መረማመጀ ጎዳና እንደሆነ ብቻ ደጋግሞ መስበክና ማስተማር ተስፋን መግደል ብቻ ሳይሆን የቫይረሱን ተጠቂዎች በማሸበር ሌላ አደጋ መፍጠር እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። በቫይረሱ የተጠቁትን ብቻም ሳይሆን ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ዜጎችም ሳይቀሩ ከሙያቸውና ከሥራ ጠባያቸው ጋር እያቆራኙ ማሕበራዊ መገለል እንዲደርስባቸው ማድረግ ነገ ተነግወዲያ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረጉ በእጅጉ ተገቢ ነው። በሌሎች ሥነ ልቦና ላይ አላስፈላጊ ጉዳት ማድረስ ጥፋት ብቻ ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም።
የምንሰማቸውና የምናስተውላቸው አንዳንድ ድርጊቶች ውሎ አድሮ አደጋ የሚፈጥሩ ስለመሆናቸው በሚገባ ሊታወቅ ይገባል። በተለይም በተወሰኑ የሥራ መስኮች ላይ በተሰማሩ ነጻ ዜጎቻችን ላይ የሚሠጡት ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶችና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በእንጭጩ ሊቀጩ ይገባል።
ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ቢታወቅም የሆቴል ቤት ባለሙያዎች፣ የበረራ ሠራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሥራቸው ከሕዝብ ጋር የሚያገናኛቸው ዜጎችና ከውጭ ሀገራት “ሀገሬና ሕዝቤ” ብለው በሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላይ መገለልና መገፋት እየደረሰባቸው እንደሆነ እያደመጥንም እያስተዋልንም ነው። ቤት አናከራይም፣ በጋራ ትራንስፖርት አንጠቀምም፣ ማዕድ አብረን አንቆርስም ከሚሉት መገለሎች አልፎ ተርፎ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንኳን እንዳይገናኙ ቀጥተኛና የእጅ አዙር ጫና እየተፈጠረ እንደሆነ በስፋት እየተወራ ነው።
በቫይረሱ ተይዘው ወደ መደበኛ ጤንነታቸው የተመለሱትንና የኳራንቲን ጊዜያቸውን ጨርሰው የሚወጡ ወገኖችን እንደ አስፈሪ ፍጡር ቆጥሮ መሸሽም በአለፍ አገደምም ቢሆን እያስተዋልን ነው። አንዳንድ እድሮችም ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ሽብር እያስፋፉ ስለመሆናቸው በማሕበረሰቡ ውስጥ በስፋት የሚናኝ ወሬ ሆኗል። የውጭ ዜጎችንማ ሁሉም የሚመለከታቸው በጎሪጥ ነው። ይህን መሰሉ አግላይነት “ያወቅን መስሎን” በካሁን ቀደሙ የኤች. አይ.ቪ/ኤድስ እንቅስቃሴ ላይ ተስተውሎ የምን ያህሉ ዜጎቻችን መንፈስና ቅስም እንደተሰበረና ለብዙ ችግር ሰበብ እንደነበር ለማስታወስ የሞከርኩትም ከቀዳሚ ስህተታችን ትምህርት ማግኘት ይቻል እንደሆን በማሰብ ነው።
እናስ ምን ይደረግ!?
የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰው ጥፋትና ጥቃት ዓለምን የማርበድበድ አቅም ቢኖረውም ከሰው ልጆች እውቀት በታች መሆኑን ማመን ግን ግድ ይሏል። ኃያልነቱ የሚመሰከርለትን ያህል በያንስ ቢያንስ በሳሙና አረፋ ሳይቀር እንደሚመክን ስንሰማ ደግሞ ቫይረሱ አቅሙ ምን ያህል ኢምንት እንደሆነና በቀላሉ ልንከላከለው እንደምንችል እንረዳለን። እርግጥ ነው ኮቬት-19 ቫይረስ ሳይርቅ በሩቁ ድል ሆኖ እንደ ተረት መወራቱ አይቀርም። ሕዝባችን የባለሙያዎችን ምክር ከሰማና ጥንቃቄውን የማያጓድል ከሆነ፣ የሃይማኖት ቤተሰቦችም የምህላ ማስፈጸም ድርሻቸውን በአግባቡ ከተወጡ ከቫይረሱ ጋር ወደሚደረገው የተፋፋመ ጦርነት ከመግባታችን በፊት ድሉ ቀድሞ እንደሚበሰር ትልቅ እምነት አለኝ። ቀዳሚው መፍትሔ ጥንቃቄ! ጥንቃቄ! ጥንቃቄ! ብቻ ነው።
በተለይ የሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች ቅስቀሳና የግንዛቤ ትምህርት ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የቋንቋ አጠቃቀማቸውን፣ አካላዊ እንቅስቃሴያቸውን፣ ነገሩን አድምቆ ለማቅረብ በማሰብ “ቅንነት በተሞላበት ሁኔታ” አግላይነትን እንዳይሰብኩ ጥንቃቄ ሊያደረጉ ይገባል። “የከፋ እውነት ከመልካም ቅንዓት ይፈጠራል” የሚለውን የጽሑፌን ርእስ የመረጥኩትና የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜ ያለውን ገጠመኜን ያጋራሁት ይህን መሰሉን የልቤን ሸክም ያስተላልፍ ይሆናል ብዬ በማመን ነው። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com