የዘንድሮ ዐብይ ጾም የመጠናቀቂው ዕለት ላይ እንገኛለን። ብዙ ጊዜ ጋዜጠኞች እንደሚሉት የዘንድሮውን የትንሳዔ በዓል ለየት የሚያደርገው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለማችን ክፉኛ በተመታችበት፣ በሥጋት በተወጠረችበት ሰሞን የሚከበር መሆኑ ነው። ቀላል እና ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሕዝብን ባጠቃበት፤ በ100 ሺዎች ወደሞት በነዳበት በዚህ ክፉ ወቅት የሚከበር መሆኑ ነው። የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦች መሠረት መንግሥታት ዜጎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ፣ አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ… ባወጁበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ነው። በኢትዮጵያም በዓሉ የሚከበረው ኮሮና ባመጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስር ሆነን ነው። የእምነት ተቋማት ጭምር ለጥንቃቄ ሲባል ጸሎትና ስግደትን በቤት ውስጥ እንዲደረግ ወይንም በቤተእምነት መሰብሰብን በከለከሉበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል በዓሉ ሲከበር የተለመደው የእርድ ሥርዓት ምን ይሆናል፤ ይኖራል ወይንስ አይኖርም የሚለው ጥያቄ ግራና ቀኝ እያነጋገረ ነው። የጥሬ ሥጋ ነገርም እንዲሁ።
በአጠቃላይ ጾም ማለት ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢአት መከልከል፣ ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት፣ ውሀ ከመጠጣት መታቀብ ወይንም ለተወሰኑ ወራት ከሥጋ፣ ከቅቤ፣ ከእንቁላል በአጠቃላይ ከእንስሳት ውጤቶች መብል መራቅ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዋጅ ጾም ተብለው ከሚታወቁት አጽዋማት አንዱ አብይ ጾም ነው። አብይ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት መካከል በሚጾሙት ቀናት ብዛት ከሁሉም የሚበልጥ ነው።
የእንስሳት እርድን በተመለከተ፣
በነገው ዕለት ተከብሮ የሚውለው የትንሳኤ በዓል የእርድ በዓል ነው። ሰዎች እንደየአቅማቸው በግልና በጋራ በሬ፣ በግ፣ ዶሮ አርደው በዓሉን ከቤተሰብና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማክበር የተለመደ ነው። ዘንድሮ ግን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ይህን የቆየ ልማድ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ጥሎታል። ችግሩ ቫይረሱ የሚሰራጭባቸው መንገዶች ሙሉ በሙሉ ተጠንተው የሚታወቁ አለመሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት ሳይንቲስቶች የቫይረሱን ስርጭት ሁኔታ በማጥናት ብቻ የእንስሳት ተዋጽኦ (ጥሬ ሥጋን ጨምሮ) መመገብ በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን ሊጨምር እንደሚችል እየተናገሩ ነው።
የኢትዮጵያ የጤና እና የግብርና ሚኒስትር መ/ቤቶች እንደጥሬ ሥጋ ያሉ ምግቦችን መመገብ አይመክሩም። በተጨማሪም እንደ ጥሬ ሥጋ ያሉ ያልበሰሉ የእንስሳት ምርትና ተዋፅኦዎችን አለመመገብን ከጤና አንጻር የተሻለ ውሳኔ እንደሚሆን ተናግረዋል። ማንኛውም የእንስሳት ተዋፅኦ በአግባቡ መብሰል ይኖርበታል። የበሰሉና ያልበሰሉ የእንስሳት ውጤቶችን መቀላቀል አይመከርም ብለዋል።
የእርድ ሁኔታን በተመለከተ በጋራ የሚካሄድ እርድ (ቅርጫ) ለቫይረሱ የተጋላጭነትን ደረጃ ስለሚጨምር አይመከረም ካሉ በኋላ የእንስሳት እርድ በቄራዎች መደረግ አለበት።
ቄራ በሌለበት አካባቢ የሚደረግ የእንስሳት እርድ የአራጁም የእንስሳውም የአሳራጁም ወገን የበሽታ ተጋላጭነት በሚያስወግድ መንገድ መከናወን እንደሚኖርበት የግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል።
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ሰለሞን ክብረት ከጋዜጠኛ ተስፋዬ ወልደስላሴ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ እንዲህ ብለዋል።
የኮረና ቫይረስ መተላለፊያ መንገዱ በትንፋሽና በንክኪ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም ነው ንክኪ መቀነስ፤ እጅን በሳሙና መታጠብና ማህበራዊ ፈቀቅታ የሚመከረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚጠየቅ ጥያቄ ግን ምግብን በተመለከተ ሆኗል። “የኮረና ቫይረስ በምግብ ይተላለፋል ወይ?” ይህን ለመመለስ የተለያዩ ጥናቶችን ለመዳሰስ ሞክሪያለሁ።
የአሜሪካ የበሽታ መከላከል ማዕከል (CDC) ይህንን ጥያቄ በማስመልከት ማርች 17 በሰጠው መግለጫ; “There is no evidence that food has been associated with the transmission of the virus although more research is still required. Foodborne exposure to this virus is not known to be a route of transmission”
“እስካሁን ያለው መረጃ የሚያሳየው የኮረና ቫይረስ በምግብ ምክንያት እንደማይተላለፍ ነው። ቫይረሱ ከምግብ ጋር በመግባት የበሽታ መተላለፍ መንስኤ አይሆንም” በማለት መልስ ሰጥተዋል።
በቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ዊልያም ሻፍነር ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ “የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ነው እንጂ ሆድ ውስጥ ያሉ የምግብ መፍጫ አካላትን የሚያጠቃ አይደለም ስለሆነም በመተንፋሻ አካላት በኩል ዘልቆ ካልሆነ ከምግብ ጋር አብረን ስለተመገብነው በሽታው አይዘንም። ሆድ ውስጥ ቢገባ እንኳን የጨጓራ አሲድ ሲሳይ ይሆናል።” ይልቁንስ ይላሉ ፕሮፌሰር ዊልያም “ምግቡ ሲዘጋጅ ንክኪ ከተፈጠረ፤ ለምሳሌ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምግቡን ሲያዘጋጅ ቢያስነጥስበት ወይም እጁን ሳይታጠብ ካዘጋጀውና እኛም ምግቡን ወይም ምግቡ የታሸገበትን እቃ በእጃችን ነክተን ከዛም ከፊታችን ጋር ንክኪ ስናደርግ ቫይረሱን ቀጥታ ወደ መተንፈሻ አካላችን እንዲገባ እናመቻችለታለን። ይህ ንክኪ በተለይ በእጃችን በቀጥታ በመንካት የምንመገባቸው ምግቦችን (ምሳሌ፤ ፍራፍሬዎች፤ ሳንድዊች፤ ጥሬ ስጋ) ቫይረሱ ቀደም ሲል ምግቡን ከነካው ሰው ወደ እኛ እጅ በተወሰነ መልኩ (አነስተኛ እድል ቢኖረውም) የመተላለፍ እድሉን ሊፈጥር ይችል ይሆናል።”
ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን?
መዘንጋት የሌለብን ነገር ይህ ቫይረስ የሚተላለፈው በንክኪና በትንፋሽ መሆኑን ነው። ስለዚህ፤ ማንኛውም ምግብ የሚያዘጋጅ ሰው እጁን በሳሙና ታጥቦ [እና የፊት መሸፈኛ ማስክ አድርጎ] ምግብ ያዘጋጅ፤ አስታውሱ ምንጊዜም ምግብ ዝግጅት ከመጀመራችን በፊት እጃችንን በሳሙና በደንብ መታጠብ አለብን።
ከምግብ ተራ የገዛናቸውን ፍራፍሬዎችና አትክልት በተለያዩ ሰዎች ተነካክተው ስለሚሆን በሚፈስ ውሃ [running water] አጥበን እንጠቀም፤ [በሳሙና ወይም በኮምጣጤ ማጠብ አይገባም፤ ውሃ በቂ ነው](በእቃ ላይ የታቆረ ውሃን ሳያፈሱ ለብዙ ሰዓት ለማጠቢያነት መጠቀም ከማጠብ ተግባሩ ይልቅ ከአንዱ ወደ አንዱ የመበከል ሁኔታን ሊፈጥር ስለሚችል ምንጊዜም የሚወርድ ውሃን እንጠቀም].
ምግቡ የታሸገ ከሆነ የታሸገበትን ካርቶን/ወረቀት ካነሳን በኋላ በትክክል ማስወገድና ወዲያውኑ እጃችንን በሳሙና መታጠብ ይገባል [ለማስታወስ ያህል በቅርብ የተደረገ ጥናት ኮሮና ቫይረስ በካርቶን ላይ እስከ 24 ሰዓት መቆየት ይችላል] ተጨማሪም ምግብን አብስሎ መመገብ የተለያዩ በሽታ አምጭ ተህዋስያንን ስለሚገልልን ልናዘወትረው ይገባል።
የጥሬ ሥጋ ነገር
የተለያዩ ባለሙያዎች እየመከሩ ያሉት ምግብን አብስሎ መብላትን ነው። ጥሬ ሥጋ መመገብ ለኮሮና ቫይረስ የሚኖርን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ዶ/ር እንዳለማው አበራ ስለዚህ ጉዳይ የሠጡት አጭር ማብራሪያ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት እዚህ ላይ እጠቅሰዋለሁ። ከበዓሉ ጋር ተያይዞ “ኮሮና በጥሬ ሥጋ ይተላለፋል ወይ?” የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ለዚህ ጥያቄ ሳይንሳዊ መልስ እንስጥ ከተባለ ልናወሳስበው እንችላለን።
ለምሳሌ…. “ወዲያው የታረደ እንስሳ ሥጋ የሚበላ ከሆነ.. አራጁ ወይም ሥጋውን አዘጋጅቶ የሚያቀርብልን ሰው ኮቪድ 19 ካለበትና ሲስል ወይም ሲያስነጥስ ወይም ሲተነፍስ ቫይረሱ ሥጋው ላይ ካረፈ… ሊተላለፍ ይችላል። (በዚህ ላይ በየሉካንዳ ቤቶቻችን ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች የንጽህና አጠባበቅ ግንዛቤ የላላ መሆን ሊፈጥር የሚችለውን ችግርም ማሰብ ይገባል) ሥጋው በፍሪጅ ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት ወይም ቀናት የቆየ ከሆነ ደግሞ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ነው”… እያልን ምናባዊ ትረካ ማቅረብ እንችላለን።
ይህ ሁሉ ግን እርግጠኛ አይደለም። ስለዚህ ቫይረስ ያለን ዕውቀት ከቀን ወደ ቀን እየዳበረ በመሄድ ላይ ስለሆነ በአሁኑ ሰዓት ደረታችንን ነፍተን ጥሬ ሥጋ መብላት ኮሮናን ያስተላልፋል ወይም አያስተላልፍም ለማለት አንችልም።
በዚህ አይነት ወቅት ‘አያስተላልፍ ይሆናል’ ብሎ ከመዘናጋት ‘ሊያስተላልፍ ይችላል’ ብሎ መጠንቀቅ ይሻላል። ስለዚህ .. ጥሬ ሥጋ እንዳትበሉ እመክራለሁ።”(ቅንፍ የተጨመረ)
እንደመቋጫ
የኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) በ210 አገራትና ድንበሮች የሚገኙ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሰዎችን አሳድዶ ይዟል። ባለፉት ወራት 134 ሺ 685 ሰዎች በሞት የወሰደ ሲሆን 515 ሺ 475 ሰዎች አገግመዋል። በአገራት ደረጃ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በቫይረሱ ብዛት በመያዝም በሞት መጠንም የመጀመሪያውን ረድፍ ላይ ተቀምጣለች። እስካለፈው ሐሙስ ዕለት ጠዋት ብቻ 644 ሺ 348 ሰዎች ተይዘው 28 ሺ 554 ሰዎች ሞተዋል። ስፔን 180 ሺ659 ሰዎች ተይዘው 18 ሺ 812 ሰዎች ሞተዋል። በኢጣሊያ 165 ሺ155 በመያዝ 21 ሺ 645 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።(ወርልዶሜትር)
በኢትዮጵያም እስከአለፈው ረቡዕ ዕለት ድረስ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 85 የደረሰ ሲሆን የሶስት ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።
የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ጠቅሶ አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው በ52ቱ የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ መመዝገቡን ጠቁሞ አስካለፈው ረቡዕ እለት ድረስ ብቻ በጠቅላላው 16 ሺ 200 ታማሚዎች ሲገኙ 873 ሰዎች ሞተዋል። 3 ሺ 235 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። በሌሎች አገራት በቀን እየሞቱ ያሉ ሰዎች ቁጥር ጋር የአፍሪካው ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑ የፈጣሪን ረቂቅ ሥራ የሚሳይ ነው ባይ ነኝ። በቅርቡ አሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 2 ሺ 492 ሰዎች ሞት በማስመዝገብ ዓለምን ድንጋጤ ላይ ጥላለች። በተመሳሳይ ሁኔታ ፈረንሳይ በቀን 833፣ እንግሊዝ 854 ከፍተኛ በ24 ሰዓታት የሞት መጠን አስመዝግበዋል። ከእዚህ አንጻር ሲታይ አሁንም በአፍሪካ ባለፉት ሶስትና አራት ወራት በድምሩ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጎበዝ ይህ ቁጥር የሚነግረን ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን ስንል ከቫይረሱ ለመዳን የጥንቃቄ መንገዶችን ሁሉ እንድንፈጽም እንጂ እንድንዘናጋ አይደለም። ምንም እንኳን የጥሬ ሥጋ ፍቅራችን ከፍተኛ ቢሆንም ከፍላጎታችን በላይ የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ መስማት ጠቀሜታው የላቀ ይሆናል። በእርግጥ ከኮሮና በፊትም ቢሆን በጥሬ ሥጋ ከ150 በላይ በሽታዎች የሚተላለፉበት መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከእነዚህ በሽታዎች መካከል 11 ያህሉ ገዳዮች ናቸው። የኮሮና ሲጨመር ደግሞ ቁጥሩን ወደ 12 ከፍ ያደርገዋል። እናም ጥሬ ሥጋ የሌለበት፣ ጥንቃቄያችን ያየለበት በዓል ለማሳለፍ ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ።
በመጨረሻም የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ የምክር ብዛት ለጭንቀት እንዳይዳርገን ማስታወሻ ቢጤ ያስቀመጡት ወዳጄ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ጥቂት ሃሳብ በማጋራት ሐተታዬን እቋጫለሁኝ።
“ዛሬ በዓለማችን ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚረዱ ምክሮች ይጎርፋሉ። እኔን ያስጨነቀኝ ይህ ሁሉ ምክር አእምሮ ላይ የሚፈጥረው ጫና ነው።
ከበርካታ ምክሮች መሃል ጥቂቱን አበክረን ብንይዝ አእምሮአችን ሳይጨነቅ በመጠንቀቅ መከላከል የሚቻል ስለመሠለኝ እነዚህን ጠቃሚ ነጥቦች ማቅረብ ፈለግሁ።
- አእምሮአችንን የመረጃ ቋት አናድርገው!! አገኘን ብለን ከልዩ ልዩ ምንጭ በልዩ ልዩ መንገድ የምንሠበስበው መረጃ አእምሮአችንን ያስጨንቀዋል።እናም ተገቢ መረጃ ከተገቢ ምንጭ!!
- ፍርሃትን መለየት ስጋትና ጭንቀት የሚያበረታ ፍርሃት አይጠቅምም፤ ጥንቃቄን የሚያጎለብት ከሆነ ጥሩ ነው።
- ሌሎችን ማየት በተለይ ከኛ ባነሰ ደረጃ ያሉትን አስተውለን ባገዝን መጠን የመንፈስ ብርታት ይሠጠናል።
- ከሌሎች መማር ጭንቀትን ሳይሆን ብርታትን ከተጠቁ ሰምቶ መማር
- ሙዚቃ ይጠቅማል፤ መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ ለሰለስና ጣፈጥ ባለ ይዘቱ መንፈስ ይጠግናል፣
- አዝናኝ ጽሁፎችና ፊልሞች ይረዳሉ፣
- ቀላል አካላዊ እንቅስቃሴ አእምሮን የማስደሰት አቅም አለው።”
መልካም በዓል!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ፍሬው አበበ