አሁን በዚህ ሰዓት በጭንቀት እንጉርጉሮ፣ በፍርሃት ኑሮ ተሸብበን ባለንበት ወቅት ሀገር ከስጋት አፋፍ ላይ ተንጠልጥላ ቆማ ስንመለክት ጴጥሮስ ያችን ስዓትን ማስታወስ ለምን እንዳቃተን ባይገባኝም፤
በዓለም ያስተጋባው ማስጠንቀቂያው ደውል፣
ነፍስ አድን ጥሪ ነው ፣ እናዳምጠው በውል፣
የዜማ ደራሲዎች በዜማቸው፤ ፀሐፍት በብዕራቸው እንዲህ ሲሉ ያልሰማን ሰዎች መቼ ልንሰማ ነው ብዬ እጠይቃለው። አብዛኞቻችን ስለኮሮና ሰምተናል፣ አውቀናል፤ ነገር ግን የጥንቃቄ መንገዶቹን በሚገባ እየተገበርናቸው አይደለም። የሚተላለፉ መመሪያዎችንም ቢሆን በደንብ ጠዋትና ማታ አድምጠናል። ከሰሞኑ በገበያ ቦታዎችና በአምልኮ ስፍራዎች የሚስተዋለውን መዘናጋትና ቸልተኝነትን ልብ ላለ ሰው ‹‹አረ ጎበዝ ልብ ግዛ›› እናስተውል ማለቱ አይቀርም።
ይህንን ጥሪ ደግሞ ደጋግሞ ያልሰማ ከእጅ ንኪኪ መራቅ፣ ማህበራዊ ፈቀቅታን ወይንም ጥግግትን ማስወገድ፣ ሳል ካላባቸው ሰዎች እራሳችን ማራቅ፣ እጃችንን በንፁህ ውኃና በሣሙና መጠበቂያ መሳሪያዎች ማፅዳት፣ በዋነኝነት ደግሞ ከቤት ባለመውጣት የሚሉት መልዕክቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ካጠላብን ጥላ ለመሸሽ፣ ለማምለጥ እንደ ጅረት ውኃ የምናመልጥበት አማራጭ መንገዳችን መሆኑን ተረድተን ዘወትር እንደ ፈረስ ቃጭል ከጆሮው ላይ ማሰር ያስፈልገዋል።
ዓለማችንን እየተፈታተነ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይና ሁዋን ግዛት ከወራት በፊት የተነሳው መላ ኤሽያን፣ አውሮፓን፣ ላቲን አሜሪካን፣ ሰሜን አሜሪካን፣ አውስትራሊያንና አፍሪካን በጥቂት ወራት አዳርሷል። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው እስከ አሁን ድረስ ባለው መረጃ መሰረት በ211 ሀገራት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል። የሰዎችን ህይወት በከፍተኛ ፍጥነት እየቀጠፈ ነው። በወረርሽኙ ምክንያት ከ125 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ከደካማ የጤና መሠረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪካ አህጉር በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚዛመትና የወረርሽኙ አስከፊ ውጤት በአህጉሩ ጠንከር እንደሚል የዘርፉ ባለሙያዎች ትንበያቸውን ሠንዝረዋል። ወደ ሀገራችንም ብቅ ካለም ሰነባብቷል። በዚህም በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል። ዓለማችን ወረርሽኙን ለመቋቋም አቅም እንዲሆናት የጥንቃቄ መልዕክቶቿን እንካችሁ ስትል ላለመስማትና ላላመተግበር የደደረ ጆሮ ስንት አለ።
መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ለመከላከል ህብረተሰቡ እራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ መመሪያ ከማስተላለፉ ባሻገር እጃችንን በውኃና በንፅህና መጠበቂያ ማፅዳት እንደለብን፣ ከእጅ ንክኪ መራቅ እንዳለብን ከመንገር ባለፈም ወረድ ብለው ሲታጠቡም አይተናል። እኛስ ምን እያደረግን ነው።
ከሜክሲኮ ወደ አራት ኪሎ በሸገር ትራንስፖርት ሲጓዝ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ እናት፤ ከጎኔ ካለው ወንበር ላይ አረፍ ብለው ራሳቸውን ካመቻቹ በኋላ እንደምን አደርክ ልጄ፣ እግዚአብሔር ይመስገን የኔ ምላሽ ነበር። ቀጠል አድርገው እኔ በፊትም ቢሆን የእግዜር ሰላምታ የምሰጠው እጅ በመንሳት ነው እንጂ እጄን ለሰላምታ ዘርግቼው አላውቅ። አሁን ደግሞ በየመንደሩ፣ በየሬድዮኑ አትጨባበጡ እየተባለ ይነገራል። ህረተሰቡ ግን ከመስማት ይልቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። አንተ ግን ራስህን ጠብቅ፣ በል ደህና ዋል።
ከእኚህ እናት ንግግር የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ያለውን መልካም እሴት ለመልካም ተግባር ማዋል ብልህነት መሆኑን ነው። የእጅ ሰላምታችን መተው ወይም ማቆም ከመልካም መስተጋብራችን አንዱ ነው። የእጅ ሰላምታችንን በመተው የምናተርፍበት ጊዜ አሁን በመሆኑ ሁላችንም ለዚህ ተግባር እንትጋ።
በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ አብሮነታችን፣ አንዳችን ለአንዳችን ድጋፍ መሆናችንን የምናሳይበት መልካም እሴቶች መካከል እንደምን አደርክ፣ እንደምን ዋልክ መባባላችን የነገ ተስፋን መስነቅ ነው። ዛሬ ላይ እጅ ለእጅ ባለመጨባበጣችንና የእጅ ንኪኪዎችን በመቀነሳችንን ለብዙዎች መዳን፣ ለብዙዎች ሕይወት መትረፍ ትልቅ ዋጋ አለው። እጃችንን መሰብሰብ ከህመም፣ ከሞት ከስጋት እንኳን አተረፈክ የምንልበት መተኪያ የሌለው በሕይወት የመኖር ፍቱን መድኃኒት ስለሆን ስንቶቻችን አውቀንንና ሰምተን እየተገበርነው እንዳልሆነ ከሰሞኑ ካየነው ቸልተኝነት መረዳት በቂ ነው።
እጅ ለእጅ መጨባበጥ የሚያጎልብን ነገር እንዳለ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ በጎ ፍሬ የምናፈራበት፤ ነገ ካጠገባችን የሚጎለውን ለማዳንና ለመጠበቅ የሚያገለግለን መድኃኒት መሆኑን ተረድተን ተግባራዊ እናድርገው። ያወቀ እጁን ሰበሰበ፤ ያላወቅ እጁን ለሞት ሰጠ እንደይሆንብን ነገሩ፣
ከገደል አፋፍ ላይ ነብሴ ተንጠልጥላ
እጅህን ስጥ አለኝ፣ ዘርጋው ለሰ ላምታ
እንዴት እጄን ልስጥ፣ ልዘርጋው ወደ አንተ
ዓለም ሲከለክል፣ ጆሮዬ እየሰማ
እጄን ላንተ አልሰጥም፣ ከቶ አላደርገው
እጄን በመሰብሰብ፣ እጅ ነሳህና ጤና ይስጥህ እላለው።
በሌላ በኩል በማህበራዊ መስተጋብራችን አብሮ መብላት፣ ሰብሰብ ብሎ ማውጋት፣ አብሮ መሄድም እንዲሁ የተለመደ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ አብሮ ሰብሰብ ብሎ መቀመጥ ሳይሆን የሚያዋጣን በተን በተን ብለን፣ ተራርቀን ስንቀመጥ የሕይወት ፈውስ ወይም የሕይወት መድኃኒት እንሆናለን፤ ለብዙዎች መዳንም እንዲሁ። ማህበራዊ እርቀታችንን መጠበቅ፣ ተራርቆ መሄድ አለምን ለስጋት ከዳረጋት የኮሮና ወረርሽኝ ማመምለጫ መንገድ ስለሆን መተግበር ከሚያስፈልጉን ጉዳዮች አንዱ ነው።
ተራርቆ መሄድ ተራርቆ መቆም በሃሳብ ብቻ አይደለም፣
ካካላዊ ንኪኪ ተራርቆ መሄድ፣ ተራርቆ መቆም
ዓለምን ላሰጋት፣ ነፍስን ላስጨነቃት
የቫይረስ ወረርሽኝ፣ ፍቱን መድኃኒት ነው፤
አብዝተን እንውሰድ፣ ተራርቀን እንሂድ
ጆሯችን ከፍተን፣ አይናችንን ገልጠን
ሕይወት ላልተሰጠው፣ ሕይወት እየሰጠን
ሞተን እንዳንቀር ነው፤ የኔም ያንተም ስጋት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ወንድማገኝ አሸብር