
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የወጪ ንግድ ማሳለጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም የንግድ ሚዛንን ለመጠበቅ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ፣ ማዕድናትን እና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ ለገቢ ንግድ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በዚህም የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ከዚህ አንጻር ታቅዶ ተሰርቷል፡፡ይሁንና የወጪ ንግዱ እንደሚጠበቀው ሊሆን አልቻለም፡፡በወጪ ንግዱ የታቀደው ባለመሳካቱ የንግድ ሚዛኑ ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል፤በእዚህ የተነሳም ሀገሪቱ ለሚያስፈልጋት የገቢ ምርት ሌላ የውጭ ምንዛሪ ማማተር ውስጥ ገብታለች፡፡
ሀገሪቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመንም የወጪ ንግዱን የሚያሳድግ እቅድ አዘጋጅታ በመተግበር ላይ ናት፡፡በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ የወጪ ንግድ ገቢውን በየዓመቱ በአማካይ በ36 ነጥብ 3 በመቶ በማሳደግ ፣በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት ግብ አስቀምጣለች፡፡ ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ ከግብርና ምርቶች 7ነጥብ7 ቢሊዮን ዶላር ፣ከኢንዱስትሪ ምርቶች 4ነጥብ2 ቢሊዮን ዶላር እና ከማዕድን የ2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ በእቅድ ተይዟል፡፡
ይሁንና አሁንም ስለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደጠቆመው፤በ2009 በጀት ዓመት ወደ ውጭ አገር ከሚላኩ የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ምርቶች፣ከማዕድን ውጤቶች እና ሌሎች የወጪ ምርት ዓይነቶች ከ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ማግኘት የተቻለው 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላሩን ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይም በ2010 በጀት ዓመት ከነዚሁ ምርቶች ከ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገባት ቢታቀድም ማግኘት የተቻለው ግን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
የወጪ ንግዱ ቆፈን ውስጥ ስለመሆኑ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ ሁለት ዓመታት አፈጻጸም ሁነኛ ማሳያ ናቸው፡፡
ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ቀደም ሲል የግብርና ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ መውደቅ በዋና ምክንያትነት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መጥፋቱም ይጠቀሳል፡፡ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን የዘርፉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ይጠቁማሉ፡፡
በወጪ ንግድ ላይ መስራት የሀገር የህልውና ጉዳይ ነው፡፡የግብርና ምርትም ይሁን በቀጣይ ብዙ የሚጠበቅበት የኢንዱስትሪው ምርት የውጭ ገበያውን በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡ይህን ለማሳካት ደግሞ የዘርፉን እያንዳንዱን ችግር እየነቀሱ በማውጣት ለመፍታት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጻር መከናወን ያለባቸው በርካታ ተግባሮች እንዳሉ ይታመናል፡፡የወጪ ምርቶች የግብርና ብቻ አይደለም፡፡እንደ ወርቅ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ያሉትም ወደ ውጭ በስፋት ይላካሉ፡፡ይሁንና ከወጪ ንግዱ አንጻር ኢትዮጵያ በስፋት የምትልከው የግብርና ምርት እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ ይበልጥ አተኩራ ልትሰራ ይገባታል፡፡
ሀገራችን አሁንም የግብርና ምርቶችን እየላከች የምትገኘው እሴት ሳትጨምር ነው፡፡ በምርቶቹ ላይ ምንም ዓይነት እሴት ባልተጨመረበት ሁኔታ የምትልከው የግብርና ምርት እንደቀድሞው የሚፈለገውን ገቢ ሊያስገኝ እንደማይችል ተረድቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ይህም በቀጣይም በእሴት መጨመሩ እንዲሁም ያለቀለት ምርት መላክ ላይ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል፡፡ለእዚህ ደግም እስከ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ጨምሮ ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የምትገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለበት የግብርና ምርቶችን እንደወረደ ከመላክ እሴት ወደተጨመረባቸው መላክ የማሸጋገሩም ሥራ አዲስ ገበያ የመፈለግ ያህል ሊሆን ስለሚችል ሊተኮርበት ይገባል፡፡
የግብርና ምርቶች ጥራትም አሁንም እንዳነጋገረ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እስከ አሁን የተከናወነው ተግባር በቂ ስላለመሆኑ አፈጻጸሙ ያመለክታል፡፡ የምርት ጥራትን ማረጋገጥ አሁንም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡ምርጥ ዘር መጠቀም፣ በማከማቸትና በማጓጓዝ ሂደት ጥራት እንዲጓደል የሚያደርጉ አሰራሮችን ማስወገድ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡
የቁም እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ወደ ውጭ ለመላክ የጥራት ጉዳይ በእጅጉ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ለእንስሳት ጤና፣ እሴት ለመጨመር፣ለገበያ መዳረሻ ማስፋት በትኩረት መስራት ይገባል፡፡
የወጪ ንግዱ ሌላው አብይ ችግር የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፡፡የቁም እንስሳት ንግድን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶች የኮንትሮባንድ ንግድ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እንደሚታወቀው ቀላል የማይባል የሀገራችን የከብት ሀብት በኮንትሮባንድ ንግድ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ነው፡፡ የእንስሳት ሀብቱ ብቻ አይደለም የኮንትሮባንድ ንግድ ሰለባ የሆነው፡፡ እንደ ቡና፣ ወርቅ ፣ የመሳሰሉትም የሀገሪቱ ሀብቶች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡
የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ የቆየው የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከደፈረሰው ሰላም ጋር ተዳምሮ ይህን ሀብት እንዳይቀራመት የወጪ ንግዱንም ይበልጥ እንዳይጎዳ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የወጪ ንግዱ በተወሰኑ ግለሰቦች እጅ ውስጥ መገኘቱ፣ ላኪም ተቀባይም እንደ ድርጅት እየሆነ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም የንግድ ፈቃድ አሰጣጡም እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል፡፡የወጪ ንግዱን ደንቃራዎች መፍታት የሞት የሽረት ያህል ተደርጎ ሊወሰድና ሥራውም በየጊዜው ሊፈተሽ ይገባል፡፡ይህ ካልሆነ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ቀርቶ ማሰብም ይከብዳ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011