የዘንድሮ ፋሲካ እንደተለመደው አይነት የበዓል አከባበር አይከበርም። ዓለም አቀፍ ሥጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችንም ጭንቅ መሆን ከጀመረ እነሆ አንድ ወር አሳለፍን። የተያዙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው የሚያልፍም አንድ ሁለት እያልን መቁጠር ጀምረናል። በሚፈጠሩ ነገሮች ሳንደናገጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በተደጋገሚ እየነገሩን ነው። በባለሙያና በመንግስት የሚነገሩንን መልዕክቶች ተግባራዊ እናድርግ።
ነገ የትንሳኤ በዓል ነው። በሃይማኖታዊ አጠራር ትንሳኤ፣ በሃይማኖታዊና ባህላዊ አጠራሩ ደግሞ ፋሲካ ይባላል። በሌላ ወቅት እንኳን ሞቅ ያለ ዝግጅት ሲታይ ‹‹ፋሲክ ሆነ እኮ!›› ይባላል። ፌሽታነቱን ለመግለጽ ነው።
ፋሲካ በባህላዊም ሆነ በሃይማኖታዊ አከባበሩ ጎረቤት ተሰባስቦ የሚያከብረው ነው። ከሩቅ ያለ ዘመድ አዝማዳም ይጠራራል። ይሄ ባህላዊ መገለጫችን ቢሆንም ለዘንድሮው ግን የተከሰተው ነገር የሚፈቅድ አይደለም። የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ካላደረግን ይሄን የምንወደውን አብሮ መጫወት ያሳጣናል። ስለዚህ የዘንድሮን የፋሲካ በዓል የምናከብረው በሚነገሩ ጥንቃቄዎች መሰረት ነው። ለዚሁ እንዲያግዘን ደግሞ መንግስት ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በቴሌቭዥን እየተላለፈ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በየቤታችን ሆነን እንድንጸልይ ነው።
ባህላዊ ስነ ስርዓቱ ደግሞ በጋራ የሚደረግ ስለሆነ ለዘንድሮ በቤታችን ሆነን በመገናኛ ብዙኃን እንከታተል። ዛሬ ከተጠነቀቅን ነገ እንደርስበታለን። እኛም በጋዜጣችን ለፋሲካ በዓል የሚደረጉ ባህላዊ ክዋኔዎችን እናስነብባለን።
የተለያዩ የጨዋታ አይነቶች አሉ። እንደየአካባቢው ይለያያሉ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ያለ ጨዋታ እናስተዋውቃችኋለን። ፋሲካ የሚታወቀው በሰርግ ስለሆነ ጨዋታዎም ሰርግ ላይ ያተኩራል።
አጫዋች ማለት ቃሉ እንደሚያመለክተው አንድን ሰው ማጫወት ነው። ይህ የሚሆነው ታዲያ ለማግባት የተዘጋጀችን ኮረዳ ወይም ጎረምሳ ብቻ ነው። ምናልባት አንድ ወንድ ወይም ሴት ከትዳር አጋሩ ጋር ቢፋቱና እንደገና ሌላ ቢያገቡ አጫዋች ሊደረግ አይችልም። አጫዋች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገቡ የሚደረግ ነው፤ ይህም የልጃገረድና የጎረምሳ ብቻ ነው ማለት ነው።
ጎረምሳም ይሁን ልጃገረድ ሲያገቡ አጫዋች ቢደረግም በሴቷ ቤት ያለው ይደምቃልና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሴቷን ቤት አጫዋች እናያለን፤ ነገሩ እንዲህ ነው።
አንዲት ልጃገረድ የሰርጓ ቀን ሊደርስ አምስት ቀን አካባቢ ሲቀረው (ቀኑ ከአምስት ሊበልጥም ሊያንስም ይችላል) አጫዋች ያስፈልጋታል። እነዚህ እሷን ለማጫወት የሚመጡ ልጃገረዶች ባልንጀሮቿ ሲሆኑ ያላጋቡት ብቻ ናቸው የሚመጡት። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እነዚህን ልጆች ‹‹ቆንጆዎች›› እያልን እንጠራለን። በአካባቢው ባህል ቆንጆ ማለት የምታምር ወይም መልከኛ ማለት አይደለም። ቆንጆ ማለት ያላገባች ማለት ነው። ለመሆኑ ይህ ባህል የት ነው ያለው?
ከአዲስ አበባ 220 ኪሎ ሜትር ርቀን ለመሄድ በስተሰሜን አቅጣጫ እንወጣለን። የፍቼ ሰላሌን ሜዳ እንደጨረስን ወደጎጃም የሚወስደውን መስመር ለቀን ወደ ሰሜን አቅጣጫ እንታጠፋለን። ከዚህ በኋላ የምናገኘው የጠጠር መንገድ ነው። ትንሽ እንደተጓዝን ጀማ ወንዝ እንገባለን። ወንዙን ከተሻገርን አሁን ደራ ወረዳ ውስጥ ነን።
ወረዳው በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ በሰሜን ደቡብ ወሎ፣ በምስራቅ መርሐቤቴ፣ በምዕራብ ምስራቅ ጎጃም እና በደቡብ ኤጀሬ ያዋስኑታል። ወረዳው ውስጥ የአማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲሆኑ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች፤ ቆላማ አካባቢዎች ላይ አማርኛ ተናጋሪዎች ይበዛሉ። በወረዳው ውስጥ በተለይም ቱቲ የሚባለው አካባቢ በደቡብ ወሎና በምሥራቅ ጎጃም የሚዋሰን ስለሆነ ባህልና ቋንቋው(እስከ አነጋገር ዘዬው) ተመሳሳይነት አለው። ይህ ጽሑፍ የሚቃኘው በደራ ወረዳ እና በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ያሉትን ነው፤ ምክንያቱም ተመሳሳይነት አላቸው።
እንዳልኳችሁ አጫዋች የቆንጆዎች ጨዋታ ነው። አንዲት ቆንጆ ልታገባ የሰርጓ ቀን ሲደርስ በአካባቢ ያሉ ቆንጆዎች ተሰባስበው ያጫውቷታል። ቆንጆዎቹ ወደ ልጅቷ ቤት የሚሄዱት በጊዜ ነው፤ በግምት ከምሽቱ 1፡ 00 አካባቢ ማለፍ የለበትም። ወንዶቹ ግን የሚሄዱት አመሻሽተው ነው። ምናልባት ገና ጉርምስና ዕድሜ ላይ ያልደረሱት ወንዶች ልጆች በጊዜ ይሄዱ ይሆናል። ጎረምሶች አምሽተው የሚሄዱት አንዱ የመጎርመስ ምልክት ስለሆነ ነው። በጉርምስና ወቅት በምሽት መሄድ ያለመፍራት ምልክት ስለሆነ ማለት ነው።
አታሞ ይዘው በጊዜ የሄዱት ቆንጆዎች ዘፈን ይጀምራሉ። የአጫዋቹ የመጀመሪያ ቀን ባለአጫዋቿ ልጅ(የምታገባዋ ማለት ነው) ታለቅሳለች(ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ የተባለው ከዚህ ይሆን?) እሷን ዝም ካሰኙ በኋላ እንግዲህ ዘፈኑ ይቀጥላል። የአጫዋች ስነ ሥርዓቱ የመጀመሪያው ቀን፣ ቀጥሎ ያለው ቀንና የመጨረሻው ቀን ድምቀት የተለያየ ሊሆን ይችላል።
የአጫዋቹ የመጀመሪያ ቀን ብዙም አይደምቅም፤ ምክንያቱም መጀመሩ ስላማይታወቅ ብዙ ጎረምሳ አይመጣም፤ አጫዋችን የሚያደምቀው ደግሞ ጎረምሳ ነው። መጀመሩ ከታወቀ በኋላ ግን በነጋታውና ከዚያ በኋላ ግቢው በጎረምሳ ይሞላል። የመጀመሪያው ቀንም ቢሆን ቀላል ነው ማለት አይደለም። በተለያየ መንገድ ጎረምሶች ሊሰሙ ይችላሉ። የምታገባዋ ልጅ የሰርጓ ቀን ቀድሞ ስለሚታወቅ አጫዋቹ መቼ እንደሚጀመር ይጠያየቃሉ፤ ይህን ደግሞ ቆንጆዎች ይነግሯቸዋል። ሌላም መግባቢያ አላቸው። አታሞ የምትባለዋ የሙዚቃ መሳሪያ ድምጿ ከሩቅ ይሰማል። የአታሞ ድምጽ የሰማ ጎረምሳ ከየትም ሊመጣ ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጎረምሶች ማን እንደምታገባ ሳያውቁ ራሱ የአታሞ ድምጽ ወደሰሙበት ይሄዳሉ፤ ምክንያቱም በዚህ በፋሲካ ወቅት ሌሊት ላይ አታሞ የሚመታው ለአጫዋች ብቻ ነው።
በጊዜ የተሰባሰቡት ቆንጆዎች እየዘፈኑ የጎረምሶችን መምጣት በጉጉት ይጠብቃሉ። ጎረምሶችን የሚጠራው የአታሞው አመታት እንደሆነ ስለሚያውቁ እንዲህ እያሉም ይዘፍናሉ።
አታሞውን ምችው
አርጊው ደምቧ ደምቧ፤
እንደወለደች ላም
አታሰኚው እምቧ።
የአታሞውን አመታት ሰምቶ ቀልቡን የነሸጠው ጎረምሳ ከሩቅ ሆኖ ‹‹አይ ሆይ! የአንችው ነኝ፣ አለ በይ!›› እያለ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያሰማል። የዚህን ጊዜ ቆንጆዎች ይሰማሉ። ጎረምሶችንም በድምጽ ነው የሚለዩዋቸው፤ የየትኛው ሰፈር አካባቢ እንደሆኑም ያውቁታል። የጎረምሶችን መምጣት የሰሙት ቆንጆዎች የጎረምሶችን ሰፈር ስም በመጥራት ያወድሷቸዋል።
ሽቶ ሸተተኝ ሽቶ ሸተተኝ
እገልየ እገሌ መጣ መሰለኝ።
ይህን ስትለው የሰማ ጎረምሳ ዓለም ሁሉ በእሱ እጅ ያለች ይመስለዋል። ከሚመጡት ጎረምሶች ውስጥ የከንፈር ወዳጅ ያለውም የሌላውም ይኖራል። የከንፈር ወዳጅ ያለው ወዳጁ ታወድሰዋለች። ብዙ ጊዜ ለማወደስ ዕድል ያላት አቀንቃኟ ናት። በአካባቢው አጠራር አቀንቃኝ ማለት አውራጇ ናት። አቀንቃኝ የምትሆነው ግን አንድ ብቻ አይደለችም፤ በየተራ ሌሎችም ያቀነቅናሉ፤ ያም ሆኖ ግን ሁሉም ይችላሉ ማለት አይደለም።
ተራ ደርሷት የምታቀነቅነው ቆንጆ የከንፈር ወዳጇ ካልመጣ ስሙን ጠርታ ነው ብሶቷን የምትናገረው። እንዲያውም እሱ ካልመጣ ሌሎች ጎረምሶች ምንም አይደሉም ለእሷ። እንዲህም ትላለች።
የተሰበሰበው የአተር ገለባ ነው
እገልየ እገሌ አልመጣም ገና ነው
እሱማ ሲመጣ ለጋ ደመና ነው።
ሌላ ደግሞ እንዲህ ሊሆን ይችላል። ሁለቱ ቆንጆዎች የቅርብ ጓደኛሞች ናቸው፤ የከንፈር ወዳጆቻቸውም እንዲሁ ጓደኛሞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአጫዋቹ ላይ የአንደኛዋ የከንፈር ወዳጅ መጥቶ የአንደኛዋ ከቀረ እንዲህ ተብሎ ይዘፈናል።
አጣማጁን ሲያጣ እምቧ ይላል በሬ
እገልየ እገሌ ወደት ሄደ ዛሬ?
‹‹እገልየ እገሌ›› በሚለው ቦታ ላይ የሰፈር ወይም የሰው ስም ይገባበታል። ሲወዳደሱ የሰፈራቸውን ስም ወይም የጎረምሳውን ስም በመጥራት ነው። በዚህ አጋጣሚ መታወቅ ያለበት ነገር፤ የሚወዳደሱት በትክክለኛ ስማቸው አይደለም፤ ለውደሳ ተብሎ ቅጽል ስም ይወጣል። ለምሳሌ አበበ የሚባል ጎረምሳ ቢኖር አበበ ተብሎ አይወደስም። ሌላ ስም ይወጣለታል። ይሄ የሚወጣው ስም ለጎረምሶች ከሆነ ጀግንነትን የሚያመለክት ሲሆን ለቆንጆዎች ከሆነ ቁንጅናን(መልከኛነትን) የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ለወንዶች የሚወጣው ስም ደምመላሽ፣ አንበርብር፣ አሸብር፣ አሸንፍ፣… የሚሉ ናቸው። ይህ ሲሆን የአባቱ ስም ግን አይቀየርም። የተወዳሹን ጎረምሳ ቅጽል ስም ያላወቀ ሰው ቢኖር እንኳን ማን እንደሆነ የሚታወቀው በአባቱ ስም ነው(የአባት ሞክሼም ሊኖር ይችላል)።
የአጫዋች ስነ ሥርዓት ብዙ የሚብራራ ነገር ያለው ነው። በውስጡም በርካታ ክዋኔዎች አሉ። በመጀመሪያው ቀን፣ ቀጥሎ ባለው ቀንና በመጨረሻው ቀን የሚከወኑ ክዋኔዎች አሉ። በተለይም የመጨረሻው ቀን ‹‹ተያዥ›› ተብሎ ይጠራል። ‹‹ተያዥ›› ማለት ቃሉ እንደሚያመለክተው ልጅቷ የተያዘችበት ቀን እንደማለት ነው። ይህን ነገር ግልጽ ለማድረግ ከዘመናዊው የጋብቻ ስነ ስርዓት ጋር እናነጻጽረው። አንዲት ሴት ቀለበት ያሰረችበት ቀን ቃል የተገባቡበት ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ተይዛለች እንደማለት ነው፤ ቃልም ይገባባሉ።
የተያዥ ስነ ሥርዓት ልክ እንደዚህ ነው። የአጫዋቹ የመጨረሻ ቀን ወይም የሰርጉ ዋዜማ ሲሆን በዕለቱ አመሻሽ ላይ የባሏ ስም ተጠርቶ ‹‹ተያዥ ብሎሻል እገሌ›› በማለት ራሷ ላይ ሻሽ ይታሰራል። የተያዥ ስነ ሥርዓት ሰፊ ስለሆነ በሌላ ጽሑፍ እንመለስበታለን።
በደቡብ ወሎ ውስጥም ተቀራራቢ ሥርዓተ ክዋኔ አለ። ክዋኔው ከደራ ወረዳ ጋር ተቀራራቢ ነው፤ ነገር ግን የተለያየ ስያሜ ነው ያለው። ደቡብ ወሎ ውስጥ ‹‹ተበቺሳ›› ተብሎ ይታወቃል፤ ሌላም መጠሪያ አለው ‹‹ነፍጄሌ›› እየተባለም ይጠራል። ቃሉ ኦሮምኛ ነው። ‹‹ተበቺሳ›› የሚለውን ቃል ይዤ የኦሮምኛ ቋንቋ አዋቂዎችን አማከርኩ። እንደነገሩኝም በኦሮምኛ ‹‹ተጳ›› ማለት ጨዋታ ነው ‹‹ተበቺሳ›› ሲሆን አጫዋች ማለት ነው። ‹‹ነፍጄሌ›› ለሚለው ቃል ያገኘሁት ትርጉም ከአጫዋች ወይም ተበቺሳ ጋር በቀጥታ ባይመሳሰልም ለአንድ ነገር መዘጋጀት ማለት እንደሆነ ነግረውኛል።
ወደ ሥርዓተ ክዋኔው ስንመለስ ደራ ወረዳ ውስጥ ከሚከናወነው ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር እስከ 15 ቀን የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል። ደቡብ ወሎ ውስጥ ቢበዛ ከሰባት ቀን አያልፍም። ይህ ባህል ግን በሁለቱም አካባቢዎች አሁን ላይ እንደተጠበቀ ማግኘት አይቻልም፤ እየተመናመነ መጥቷል።
ለአጫዋች ባህል እየተረሳ መምጣት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ላይ የሚሰጡ ትምህርቶች አንድ ምክንያት ናቸው። ባህሉን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጋር ቀላቅለው ነው ያስተማሯቸው። በተለይም በአባላዘር በሽታዎች ላይ በሚሰጡ ትምህርቶች በመሳሳም እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያሉ በሽታዎች ይተላለፋሉ እየተባለ ተነግሯል። ከዚህ በተጨማሪም ወሲባዊ ግንኙነት ይደረጋል በሚል ሥጋት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በአጫዋች ስነ ሥርዓት ውስጥ ወሲባዊ ግንኙት ፈጽሞ የማይደረግና የማይታሰብ ነው። እንኳን ወሲባዊ ግንኙነት መሳሳም እንኳን ከከንፈር ወዳጇ ውጭ ማንም ሊስማት አይችልም።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ደግሞ የአጫዋች መቅረት ልጆቹን ጨዋ አላደረገም፤ እንዲያውም ይሄ ዘመናዊ የሚባለው የባሰ ነው ልቅ ያደረጋቸው። ከጋብቻ በፊት ወሲብ የሚፈጸመው፣ በየመንገዱ በይፋ መሳሳም የመጣው አሁን እንጂ በአጫዋች ስነ ሥርዓት ውስጥ እንዲህ አይነት ልቅነት የለም፤ ወሲባዊ ግንኙነትም አይደረግም። በአጫዋች ባህል ውስጥ ከጋብቻ በፊት ምንም ነገር አይደረግም፤ ስታገባ እንኳን ድንግል ሆና መገኘት ክብር ነው። ስለዚህ አጫዋች ጎጂ ባህል አይደለም። በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ላይ የተሰጠው ትምህርት ሥርዓተ ክዋኔው እንዲቀር አደረገ እንጂ ልጆቹ ጨዋ እንዲሆኑ አላደረገም፤ እንዲያውም ወደባሰ ጸያፍ ድርጊት እንዲገቡ ነው ያደረገው፤ ከጋብቻ በፊት ወሲብ እየፈጸሙ ነው ያሉት።
ይህን ባህል ጠብቆ ለማቆየት የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጥናት እየሰራ፣ ሥርዓተ ክዋኔውን በመገናኛ ብዙኃን እንዲተላለፍ እያደረገ ነው፤ በሥርዓተ ክዋኔው ላይ የሚባሉ የቃል ግጥሞች ተሰንደው እንዲቀመጡ እየሰራ ነው፤ የተሰነዱም አሉ። የአጨዋች ባህል ሀብት ነው፣ ታሪክ ነው፣ ኪነ ጥበብ ነው። በሥርዓተ ክዋኔው ላይ ልጆቹ ይዘፍናሉ፣ ለመወዳደስ ግጥም ይገጥማሉ፤ ይሄ ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። የቃል ግጥሞቹ በተለያየ መንገድ የውስጥ ስሜትን የሚገልጹ ናቸው።
የአጫዋች ባህል ጭራሹንም ከመረሳቱ በፊት የየአካባቢው ኃላፊዎች ልብ ሊሉት ይገባል። ባህል የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫ ነው። ባህልን መጣል ማንነትን መጣል ነው።
መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ዋለልኝ አየለ