መቼም ዘረኝነትን ከአፍሪካዊያን በላይ አውቀዋለሁ የሚል ቢኖር እንደሱ አይነት ውሸታም በአለም የለምና አትመኑት። በዘረኝነት ላይ ከረቀቀና ከተራቀቀ፣ ከተመራመረና ከተፈላሰፈው ሁሉ በላይ አፍሪካዊያን ሆነው አይተውታል፤ ኖረውት አውቀውታል።
በተለይ አፍሪካን የመቀራመት አጀንዳ እውን ከተደረገበት ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ዘረኝነት አፍሪካ ላይ ተሞላቋል፤ እስኪበቃው ነግሷል፤ ያሻውን ሆኖ የፈለገውን ሲያደርግ ኖሯል – እስከ ግብአተ መሬቱ ድረስ ቦጥቡጧታል። ዛሬም ድረስ አሻራው እያሰቃያቸው ያሉ በቅኝ የተገዙ የአፍሪካ አገራት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህን በዚሁ እንተወውና ወደ ሰሞንኛው ጉዳያችን እንለፍ።
በአገራችን “ያዳቆነ ሴጣን ሳያቀስ አይቀርም።” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አለ። ምንም ሊሸራረፍለት የማይችል የተዋጣላት አነጋገርና መዋቅራዊ ነው። አንድ ነገር አንዴ አይጀምር፤ አይጠናወት እንጂ መላቀቂያው የትየ ለሌ እንደሆነ ይታወቃል፤ ልክ እንደ ሱስ።
ሰሞኑን ኮቪድ-19 እያስከተለ ያለው ሁለንተናዊ ቀውስና እየቀጠፈ ያለው የሰው ልጅ ህይወት አንድ እራሱን የቻለ አስጨናቂና አሳዛኝ የዘመን ትራጀዲ ሆኖ ሳለ፤ ባንፃሩ ኮሮና በርካታ ጉዳዮች እያሳየን ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱና አውራው ደግሞ “ዘረኝነት” ነው።
በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ (COVID-19) ካመጣቸው፤ ኮሮና ወለድ ቀውሶች (Covid-19 crisis) ተብለው ከተለዩት መካከልና እሱን ተከትለው ከመጡት ውድቀቶች፣ ክስረቶችና ቀውሶች፣ እድሎች ወዘተ ተብለው ከተመዘገቡት አንዱ ይሄው “ዘረኝነት/racism” መሆኑ ታውቋል።
የአሁኑን የዘረኝነት ግጥምና ዜማ የማቀንቀኑ ጉዳይ የተጀመረው በአሜሪካና ቻይና መካከል ሲሆን እሱም የቫይረሱን የ”ባለቤት”ነት “መብት”ን በተመለከተ አሜሪካ ለቻይና መስጠቷን በመቃወም ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱን “የቻይና ቫይረስ/ Chinese virus” ነው በማለት ታርጋ ለጠፉ። ቻይና እንዴት ሆኖ አለች። በቃ በዚሁ ቀጠለ …
ትራምፕ “የቻይና ቫይረስ” ማለታቸውና በ”ዘረኛ/ racist”ነት መመደባቸው ሳያንስ ጭራሽ ጉዳዩን ወደ አለም ጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተር ወስደው ቅጥ እያሳጡትና እራሳቸውንና የሚመሩት አገራቸውን ለከፋ ትችት አጋለጡት።
ዋና ዳይሬክተሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖምን “ለቻይና በመወገን እውነቱ ላይ ለመድረስ የማይፈልግ” “የቻይና ወገን” “እውነቱን ለማወቅ የማይፈልግ” አድርገው “China centric”፣ “biased”፣ “been wrong about a lot of things” እና ሌላም ሌላም በማለት ዘልፈዋቸዋል።
አስቀድሞ ነገር “የኮሮና ቫይረስ ወደ ግዛቴ የገባው በአሜሪካ ወታደሮች አማካኝነት ነው እንጂ ከግዛቴ አልተነሳም” (the US military could have brought the novel coronavirus to China — and it did not originate in the Chinese city of Wuhan.)፤ የሴራ ፖለቲካ ተፈፅሞብኛል የምትለዋ ቻይና የትራምፕን ንግግር ከቧልት ለይታ አላየችውም።
የትራምፕ “China virus” እና “Chinese virus”ን እያቀያየሩ መጠቀማቸው አፍታም ሳይቆይ ከውስጥም ከውጭም ያስከተለባቸውን ጫና አስመልክተው ሊያስተባብሉ ቢሞክሩም አልሳካ ያላቸው ያለ ምክንያት አይደለም። ከምክንያቶቹ አንዱ የራሷ የቻይና በጉዳዩ ላይ ማምረሯና ከፍተኛ ድጋፍና የፖለቲካ የበላይነትን ማግኘቷ ነው።
የትራምፕ የቫይረሱ አፈራረጅ ያልተወደደላቸውን ያህል የቻይና ጉዳዩን መቃወምና አባባሉ ዘረኝነት የተጠናወተው መሆኑን በተደጋጋሚ ለአለም ማስረዳቷ የራሳቸው የሆነ ጫና ፈጥሯል። እራሳቸው፤ ምራቅ የዋጡት አሜሪካዊያንም ቢሆኑ የትራምፕን አገላለፅ ከዘር ጥላቻ (xenophobia) እና ሁለቱን አገራት ከማቀያየም ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳ እንደሌለው በተደጋጋሚ መግለፃቸው ነው። ከእነዚህም አንዷ የምክር ቤት አባሏ ናንሲ ፔሎሲ እየተጠቀሱ ነው።
ይህ የትራምፕ ዘረኛ ጋዜጣዊ መግለጫ በመጀመሪያ ደረጃ ካበሳጫቸው ተቋማት አንዱ (ከቻይና ቀጥሎ) የአለም ጤና ድርጅትና ባለሙያዎች ሲሆኑ ከትራምፕ ንግግር በመቀጠል ሲኤንኤን “እንዴት አያችሁት?” ሲል ለእነዚሁ ወገኖች ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ያገኘውን መልስ “ፍፁም ስህተትና አግላይ” (that name is both inaccurate and is considered stigmatizing.) መሆኑ ላይ በመድረሱ ይህንኑ ለህዝብ ይፋ አድርጓል። (ይህ ሁሉ እንግዲህ ዘረኝነት የወለደው ኮሮና ያሰማንና ያሳየን ሳይሆን ኮሮና ገላልጦና ከፋፍቶ ያሳየን የተፋፈነ ዘረኝነት መሆኑ ነው።)
ይህን የአሜሪካው ፕረዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን በተመለከተ ኢትዮጵያም በዶክተር አቢይ አማካኝነት ግልፅ አድርጋለች። የፕሬዚዳንቱ አፍ እላፊ እንደተሰማ በነጋታው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ “በሽታ [ኮሮና ማለታቸው ነው] ዘር የለውም” ያሉት የዚሁ ማረጋገጫ ነው።
እርግጥ ነው “ኖቭል” የተባለው (አሁን በ ተሰርዟል) ኮቪድ-19 በአሁኑ ሰአት የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል እያረገፈ ነው። የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ከሚረግፍባቸው አገራት መካከል ደግሞ ቀዳሚዋ አሜሪካ (1ኛ) ነች። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ከየትም ይነሳ ከየት በአሁኑ ሰአት አደጋ ሆኖ የተከሰተውና የሰውን ልጅ ህይወት እየቀጠፈ ያለው በአንድና ሁለት አገራት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ የአለም አገራት ነው። በመሆኑም የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ አለም በጋራ ቆሞ ይህንን በሰው ልጅ የመጣን መቅሰፍት አንድ ሆኖ በአንድነት ላይ መከላከል ነው። በቃ – እየታየ፤ እየተመከረና እየተዘከረ ያለው ምክር አንድ ሆኖ በአንድነት ቆሞ ይህንን ገዳይ ወረርሽኝ መቋቋም መቻል ነው እንጂ ጭራሽ ወዳልተፈለገ ፅንፍ (እጅግ ወደ ኋላ) የሚወስዱ ጉዳዮችን እያነሱ አለምን ማመስ አይደለም። በመሆኑም በሁሉም አይነት መስፈርት ፕሬዚዳንቱ ተሳስተዋልና ሊታረሙ ይገባል ባዮች እየበዙ ይገኛሉ። ቴዲ “እዛው ነኝ ለካ …” እንዳለው ሰውየው እዛው 18ኛው ላይ መሆናቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።
ትራምፕ ብቻ አይደሉም “እዛው ነኝ ለካ …” ሊሉ የሚገባቸው፤ “እድሜ” ለኮሮና ይሁንና ሌሎችም አሉ፤ ለዚያውም ሳይንቲስቶች።
የቫይረሱን መምጣት ተከትሎ ብዙዎች በተለያዩ ቫይረሱን የመከላከል፣ መቆጣጠርና ከተቻለም መፈወስ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከእነዚህም አንዱ ሁለት “ሳይንቲስቶች”ን ያቀፈው የመድሀኒት አጥኚ/አግኚ ቡድን ሲሆን፤ ቡድኑም አግኝቶ ባላገኘው መድሀኒት ምክንያት እራሱን ከሰውነት በታች አውርዶ እራሱን ለታሪክ ተጠያቂነት አሳልፎ ሰጠና አረፈው።
ይህ መዳኒቱን አገኘሁ ባይ ቡድን “አግኝተነዋል፤ በመሆኑም ስለፍቱንነቱ ለማረጋገጥ አፍሪካ ላይ ይሞከር” አለና አፍ አውጥቶ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ሳይንቲስቶቹ ለአለም አበሰሩ። ወደ ዝርዝሩ አልገባም። ሆኖም ግን ለዚህ ምላሽ የአለም ጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም “ይህ ፍፁም የሆነ የዘረኝነት አስተሳሰብ ነው። አፍሪካ መሞከሪያ አትሆንም፤ ተገኘ የተባለው መድሀኒትም አስፈላጊውን የምዘና ሂደት ካለፈ ሊሞከር የሚችለው እንደማንኛውም መድሀኒት መሞከር ባለበት ቦታና ጊዜ ነው።” በማለት የሰጡትን መልስ ጠቅሶ ማለፍ ግን ተገቢ ነውና አድርገነው እንለፍ።
ባጠቃላይ ኮሮና ድንገት መጥቶ የሰውን ልጅ ቢጨርስም፤ አሁንም ከባድ የሞት ጥላውን ከላያችን ባያነሳም፤ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ግን አሳይቶናል። አንዱም ይህ በጣም በጥቂቱ ያነሳነው ዘረኝነት ነው።
ለማንኛውም ግን ሁሉም ነገር ቀርቶብን ፈጣሪ ከገዳዩ ኮሮና ቫይረስ ይታደገን ዘንድ እንፀልያለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ግርማ መንግሥቴ
ኮሮና የገላለጠው ዘረኝነት