አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ አርብቶ አደሮች በዓል ከመጪው ጥር 11 እስከ ጥር 13 ቀን 2011ዓ.ም በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የክልሉ አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ሊበን አሬሮ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤በዓሉ የሚከበረው «የአርብቶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት ለአገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል ነው ፡፡
አርብቶ አደሩ በዓሉ የሚከበረው ለራሱ ጥቅም መሆኑን እንዲገነዘብ መደረጉን ጠቅሰው ፣በአሁኑ ወቅት በአካባቢ ሰላም መስፈኑን አስታውቀዋል፡፡ በዓሉን በተመለከተ ከአባ ገዳዎች ጋር ምክክር ተደርጎ በጋራ ለማክበር ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ በሰላም ዙሪያም በሰላም ሚኒስቴር በኩልም ጉባዔ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤በዓሉ በክልሉ በየሁለት ዓመት የሚከበር ሲሆን፣ አርብቶ አደሩ የሚገናኝበት መድረክ በመሆን እያገለገለም ይገኛል፡፡ውጤታማ አርብቶ አደሮች የሚሸለሙበት፣ ለአርብቶ አደሩ የሚሠሩ የተለያዩ አካላት ዕውቅና የሚያገኙበት፣ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው የአርብቶ አደሩን ችግር የሚያነሱበትና መፍትሔውን የሚጠቁሙበት፣ አርብቶአደሩ ምሁራኑና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሚወያዩበት ነው ።
በበዓሉ የተሞክሮ ልውውጥ እንደሚደረግ፣ ውጤታማ የአርብቶ አደር ሥራዎች በቦረና እንደሚጎበኙ ጠቅሰዋል፡፡ በበዓሉ ማጠናቀቂያ ሞዴል አርብቶ አደሮች ዞን ወረዳና ቀበሌዎች ለአርብቶ አደሩ ጥሩ የሠሩ አካላት ወጣትና ሴት ማኅበራት ዕውቅና እንደሚያገኙም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
በ ኃይለማርያም ወንድሙ