ዓለማችን እና ከድህነት የመውጣት ሰናይ ዕቅዷ
ዋነኛው የሰው ልጆች ጠላት ድህነት መሆኑ የገባት ዓለማችን በተናጠል ስታደርግ የነበረውን ጥረት ወደ ጋራ ትግል ቀይራ በድህነት ላይ ይፋዊ ዘመቻ ከጀመረች ሁለት ድፍን አስርታትን ጨርሳ ወደ ሦስተኛው አስር ከገባች ሦስት ወራትና አስራ አምስት ቀናትን አስቆጥራለች።በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2000 መሪዎቿን ሰብስባ ድህነትን ለመቀነስና ብሎም ለማጥፋት ያስችላል ያለችውን “የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች” በሚል በሰየመችው የአስራ አምስት ዓመት የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የዓለማችን ሰዎች ከድህነት አረንቋ ማውጣት ችላለች።ይህንንም የዓለም ባንክ “ከአንድ ትውልድ ዕድሜ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ህዝብ ከድህነት ማውጣት መቻሉ ለዓለማችን መልካም ዜና ነው” በማለት ዓለማችን በድህነት ቅነሳ ላይ የሰራችውን ሥራ አሞካሽቶላታል፡፡
በዓለም ባንክ ትርጓሜ መሰረት በቀን ከ1.90 ዶላር በታች ማግኘት ዓለም አቀፍ የድህነት መስመር ይባላል።እንግዲህ 1990 ላይ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሰዎች ይህችን ቀጭን መስመር ማለፍ ተስኗቸው በቀን 1 ነጥብ 90 ዶላር እንኳን ማግኘት የማይችሉ ወገኖቻችን ነበሩ ማለት ነው።በእርግጥም እስከ 2015 ድረስ አስከፊው የድህነት ሁኔታ በግማሽ ቀንሶ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ወገኖቻችን ከአስከፊው የድህነት ማቅ ውስጥ መውጣት መቻላቸው በድህነት ለተጎሳቆለችው ዓለማችን ትልቅ እርምጃ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ይሁን እንጂ የድሆችን ቁጥር በመቀነስ ረገድ ዓለም አቀፋዊ የድህነት ትግሉ አበረታች ውጤት ያስመዘገበ ቢሆንም የተገኘው ድል ጣፋጭ እንዳይሆን ያደረጉ መሰረታዊ ችግሮች ያጋጠሙት መሆኑንም በ2015 የመንግስታቱ ድርጅት የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት መግለጹ የሚታወስ ነው።ይህም በድህነት ቅነሳ ትግሉ የተገኘው ስኬት በከፍተኛ ደረጃ አለመመጣጠን የሚታይበትና ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑ ነው።ይኸውም እስከ 2015 በዓለማችን ላይ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በአምስት ድሃ አገሮች ብቻ መሆኑ ነው።በምግብ ዕጥረት ምክንያት የቀነጨሩ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የዓለማችን ህጻናት መካከል አብዛኞቹ በእስያና በአፍሪካ ድሃ አገራት የሚኖሩ መሆናቸውም በድህነት ላይ የተመዘገበው ስኬት ሚዛናዊነት የጎደለው ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ይሆናል።እናም የዓለም ሃገራት በ2015 የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች አፈጻጸም ቁጭ ብለው ከገመገሙ በኋላ “ዘላቂ የልማት ግቦች” በሚል እስከ 2030 ድረስ ለቀጣይ 15ዓመታት የሚቆይ ሌላ የድህነት መዋጊያ ስትራተጂ አስቀምጠው ለሁለተኛው ዙር ፍልሚያ ወደ ሥራ ገቡ።
በዚህኛው ስትራቴጂ ቀዳሚ ግብ ሆኖ የተቀመጠውና ሁሉም የዓለም ሃገራት የተስማሙበት የመጀመሪያው ግብ “በ2030 አስከፊ ድህነትን ከሁሉም ዓለማችን አካባቢዎች ማስወገድ” የሚል ነበር።በስትራተጂው የመጀመሪያ አምስት ዓመታት በ2020 ደግሞ የአስከፊ ድህነት መጠንን ዘጠኝ በመቶ ለማድረስ ግብ ተጥሎ ነበር።እነሆ 2020 ከገባ ሦስት ወራትንና 15 ቀናትን አስቆጥሯል።እናስ እንደታሰበው ድህነት በዚህ ደረጃ ቀንሶ ይሆን?
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ በሕንድ እና ቻይና ያሉ ድሆች ቁጥር ከአንድ ቢሊዮን በታች መውረድ የቻለ ሲሆን ከሰሃራ በረሃ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ግን በተቃራኒው ድህነት እየጨመረ መጥቷል።ለ2030 የተቀመጠው ትንበያም ከዓለም አቀፍ የድህነት መስመር በታች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ይጨምር ይሆናል እንጂ አይቀንስም። የዓለም ባንክን ጨምሮ ሌሎችም ታዋቂ የትንበያ ድርጅቶች እንደሚሉት የ2030 የድህነት ቅነሳ ትንበያው ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት መልካም ዜናን ያየዘ አይደለም። እኤአ በ2015 ከዓለማችን ድሆች ግማሾቹ የሚኖሩት በአምስት የዓለማችን ሃገራት ነበር። እነዚህም የእኛዋን ኢትዮጵያ ጨምሮ ሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎና ባንግላዴሽ ናቸው።ትንበያዎቹ አንድ ሚሊዮን ገደማ ድህነት ሰቅዞ የያዛቸው ሰዎች ሃገር በመሆን አፍሪካዊቷ ሃገር ናይጄሪያ ሕንድን በመተካት ከፍተኛ ድህነት ያለባት ሃገር ትሆናለች ብለዋል።
እንደ ዓለም ባንክ ባለሙያዎች ገለጻ የችግሩ ዋነኛው መንስኤ የበርካታ ሃገራት ዕድገት የተመጣጠነና አካታች አለመሆኑ ነው። በተለይም በታችኛው የሰሃራ በረሃ ባሉ ሃገራት ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት እንኳን ቢኖር ዕድገቱ ሥራ እየፈጠረ አለመሆኑ ኢፍትሃዊነቱን እያባባሰው ይገኛል።ምክንያቱም የሰው ሃብት ለድሃ ሃገራት የገቢ ምንጭ እየሆነላቸው ቢሆንም ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቱ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ባለመሆኑ ድህነትን መቀነስ ስለማይቻል ነው፡፡
የኢትዮጵያችን ዋና ችግር ሆኖ የቀጠለው ድህነት
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም ድህነትን በመቀነስ ረገድ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን የመንግስት ብቻ ሳይሆን ተዓማኒነት ባላቸው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋማት የተሰሩ መረጃዎችም ያመለክታሉ።በዚህም በሃገሪቱ ያለው አጠቃላይ የድህነት መጠን እ.ኤ.አ በ2000 ከነበረበት የ45 ነጥብ 5 በመቶ በ93፣ በ2016 ደግሞ 23 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ጥናት ያመለክታል።ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከ22 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ ይገኛል።የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ባወጣው አዲስ መረጃ መሰረት ደግሞ ከዚህ ቀደም ከተቀመጡ ትንበያዎች አኳያ በአንዳንድ ዓለማችን አካባቢዎች በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮችና በአንዳንድ የእስያ ሃገራት የድህነት መጠኑ በተለይም ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሰዎች ቁጥር በመቀነስ ፋንታ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል።
ለዚህም በማሳያነት የቀረቡት ኢትዮጵያና ባንግላዴሽ ናቸው።በኢትዮጵያና በባንግላዴሽ ቀደም ሲል በተደረጉ ቅድመ ትንበያዎች መሰረት ይሆናል ተብሎ ከተገመተው መጠን በላይ በእያንዳንዳቸው ተጨማሪ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ወደ አስከፊ ድህነት ውስጥ መግባታቸውን የሚያዝያ 2018ቱ የዓለም ባንክ መረጃ ይፋ አድርጓል።በዚህ ረገድ አሁንም ድረስ የሃገራችን ዋነኛ ጠላት ሆነው ከቀጠሉ ችግሮቻችን መካከል ድህነት ግንባር ቀደሙን ቦታ ይዞ እየተዋጋን መሆኑን አመላካች ነው።ይህም “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በተለይም ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየጊዜው እየተበባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ህዝቡን በዓለም አቀፉ መመዘኛ መሰረት ከ1 ነጥብ 25 ዶላር በታች በሆነ የቀን ገቢ የሚተዳደረውንና ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን ድሃ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገባና የሰቀቀን ኑሮ እንዲመራ አስገድዶታል።
ኑሮን ፈተና ያደረገው የኑሮ ውድነት
በሃገሪቱ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች በተለይም በዋና በከተሞች አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ መጥቷል።አሁን ላይ ያልጨመረ ነገር የለም፣ ሁሉም ከምግብ እስከ መድሃኒት፣ ከትንሽዋ መርፌ እስከ ትልልቅ ማሽነሪዎች ያልጨመረ ነገር የለም።ክብሪት እንኳን በአቅሟ አንድ ብር ከሃምሳ ገብታለች።150 ግራም የማይሞላ ዳቦ ሦስት ብር ይከፈላል።በተዓምር ካልሆነ በስተቀር ከምጣዱ ላይ እንዴት እንደተላቀቀ ለማወቅ የሚያዳግት፣ እፍ ቢሉት አርባ ክንድ የሚበር፣ ህጻን ልጅ የማያጠግብ አንድ እንጀራ ሰባት ብር ከገባ ሰነባብቷል።እርሱም ጀሶ ወይም ሰጋቱራ ያልተቀላቀለበት ከሆነ ነው።ሥጋማ ዋጋው የማይቀመስ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን የቅንጦት ምግብ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ።
ካደጉ አይቀር እንደ እኛ ነው እንጅ ዕድገት፤ “ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” ተብሎ የተቀለደበት፤ ለማጣፈጫ ካልሆነ በስተቀር ከብቶች እንጂ ሰዎች በብዛት የማንጠቀምበት ጨውስ የቅንጦት ዕቃ ሆኖልን የለ¡።እና ህዝቡ የኑሮ ውድነቱ ከአቅሙ በላይ እየሆነበት መምጣቱን ህዝቡ በተለያየ ጊዜያት ምሬቱን እየገለጸ ይገኛል።በተለይም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከወራት በፊት ለኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች “ፍጹም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ከአቅማችን በላይ ሆኗል” ሲሉ ተደምጠዋል።ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው “መብላት እንኳን የማንችልበት ደረጃ እየደረስን ነው፤ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።ከእነዚህ መካከል አቶ ጋሹ መርከቡ የተባሉ አዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ፤ “ለበርካታ ዓመታት በሚኒባስ ታክሲ ሾፌርነት ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ኖረዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የኑሮ መወደድ ከአቅሜ በላይ ሆኖ እያንገዳደገደኝ ነው” ይላሉ።
“በዋጋ ላይ ያለውን ለውጥ ከቀን ወደ ቀን እያየሁት የመጣሁት ጉዳይ ነው፤ በእኔ ህይወት እንኳን ታክሲ ሠርቼ ብሩን ይዤ ብገባም ምንም የሚገዛው ነገር የለም” ይላሉ አቶ ጋሹ።“የልጆች ትምህርት ቤት፣ የእህሉ ውድነት፣ እንዲያውም ተስፋ ወደማስቆረጥ ደረጃ እየደረሰ ያለ ይመስለኛል”።ይህም የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ የምግብ ወጪዎች ሲደመሩበት “ናላን የሚያዞር” ሆኗል። በዚህ ላይ የቤት ኪራይ ወጪ ይታከልበታል። “ህይወታችንን ለማቆየት እየሰራን ነው እንጂ እየኖርን ነው ብዬ አላወራውም”።ይህ እንግዲህ የአቶ ጋሹ ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑን አዲስ አበቤ ብሎም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያለበትን የኑሮ ሁኔታ የሚያመላክት ነው።እናም በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ኑሮን ፈታኝ አድርጎታል፡፡
መሰረታዊ መንስኤዎችና የመፍትሔ እርምጃዎች
ይህን ለመሰለው የሸቀጦች መረን የለቀቀ የዋጋ ንረትና በህብረተሰቡ ላይ ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን መሆኑን መንግስት ይገልጻል።ከዚህ በተጨማሪ በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ በርካታ ህገ ወጥ ደላሎች መኖራቸውና ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሬ የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች መበራከታቸውም የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።በህብረተሰቡ ውስጥ “መንግስት በህገ ወጦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ አይደለም” የሚል ከፍተኛ ቅሬታና ወቀሳ ቢኖርም መንግስት በበኩሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የእርምት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ ይሰማል።ለአብነትም ከሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የባሰ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ በመጣበት በአዲስ አበባ ከተማ በግንቦት 2011 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ችግሩን አባብሰዋል ያላቸውን ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት፣ ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይ ደግሞ ይህንን የሚከታተል ግብረ ኃይል በማቋቋም እርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ነው።ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአቅርቦት ሥርዓቱን ማስተካከል የከተማዋ አስተዳደር የሚያከናውናቸው ተግባራት መሆናቸውንም ቢሮው ገልጾ ነበር። እንደዚሁ በሃገር ደረጃ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትም መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን እንደሚያስገባና ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ በመከተል ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።ሆኖም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።ለምን? በየጊዜው እየተባባሰ ከመጣው ከዚህ ሁሉ የኑሮ ውድነት ጀርባ በሸመታ ባህላችን ውስጥ አድፍጦ ተቀምጦ ከትውልድ ወደትውልድ እየተሸጋገረ ለዘመናት በችግር ሲያስጠቃን የኖረ ሥር የሰደደ ምክንያት አለ።
ለባርነት የተመቸው የአድርባይነት ባህላችን
ኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ እንዳለ ሆኖ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ አንድ ያልተነቃበት መንስኤ አለ።እንደሚታወቀው በምጣኔ ሃብት ሳይንሱ በመሰረታዊነት የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በህብረተሰቡ የፍጆታ ፍላጎትና በአምራቹ የምርት አቅርቦት መካከል አለመመጣጠን ሲኖር ነው።አሁን ላይ በእኛ ሃገር እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረትና ይህንን ተከትሎ የተፈጠረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ግን ከዚህም ያለፈ ነው።ምክንያቱም አቅርቦት ቢኖርም ባይኖርም ምርትና አገልግሎቶች የሚሸጡት በውድ ዋጋ ነው።አቅርቦቱ ሙሉ በሆነበት ወቅትም የዋጋ ንረት አለ፤ ሁሌም የኑሮ ውድነት አለ።በሃገሪቱ ውስጥ አምራች፣ ነጋዴ ወይም ሻጭ ሁል ጊዜ ተጠቃሚ፤ ሸማችና ገዥ ደግሞ ሁልጊዜ ተጎጂ ለመሆን የተስማሙበት ያልተጻፈ ህግ መኖሩን መታዘብ ይቻላል።ለዘመናት በህዝቡ ልቦና ውስጥ ሰርጾ የኖረ እምቢ ማለትን የማያውቅ፣ ጭቆናን የተላመደ፣ ተገዥነትን የሚያወድስ መጥፎ ባህል!
ሻጩ ወይም ነጋዴው እንደፈለገ ዋጋ መጨመር ይችላል።ምክንያቱም የፈለገውን ቢያደርግ “እምቢ” የሚለው ገዥ የለማ! ይህ ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ ከመጣው ከአሳሳቢው የኑሮ ውድነት ጀርባ ያለው ያልተነቃበት መንስኤ።ኢትዮጵያውያን ካሉብን መጥፎ ልማዶችና እና ተሃድሶ ከሚያስፈልጋቸው አስቀያሚ ባህሎቻችን ውስጥም አንዱና ዋነኛው ይኸው ይመስለኛል።ሰዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑብን የመፍቀድና ራሳችንን ለጭቆና የማመቻቸት መጥፎ ባህላችን ከፖለቲካው አልፎ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ኑሯችንም ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።የገንዘብ እንጂ የወገን ፍቅር የሌላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች እነርሱ እንደፈለጉት በየቀኑ ዋጋ ሲጨምሩብን አሜን ብለን የጠየቁንን እንከፍላለን።ትናንትና ሃምሳ ብር የገዛነውን ዕቃ ዛሬ መቶ ብር ሲሸጡልን ዝም እንላለን፣ ሣምንት ቆይተው መቶ ሃምሳ ብር ሲያደርጉትም ዝም ብለን እንገዛቸዋለን።ለምን ብሎ መጠየቅ የለም፣ ትንሽ ካጉተመተሙ በኋላ የተጠየቁትን አስረክቦ መሄድ ነው።በዚህም በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ያህል ዋጋ ቢጨምሩ “እምቢ” የሚላቸው ሸማች እንደሌለ ያረጋገጡት በህብረተሰቡ የ“ሁሉን እሽ” ባህል የልብ ልብ የተሰማቸው ሻጮቻችንም ከቀናት ልዩነት በኋላ “ሁለት መቶ ብር ገብቷል” ይሉሃል።በዚህ ጊዜ ከረፈደ በኋላ ሲመርህ “ኧረ ምነው እንዲህ ተወደደ፣ የዛሬ ሳምንት…የዛሬ ወር እኮ ሃምሳ ብር ነበር፣ መቶ ብር ነበር..” ብትል በየቀኑ ዋጋ እየጨመረ እንደፈለገ እንዲበዘብዝህ መብትህን አሳልፈህ ሰጥተህ አንባገነኑ ሻጭ “ጨምሯል ካልኩህ ጨምሯል ነው፣ ከገዛህ ግዛ ካልፈለክ ተወው” ማለት ይጀምራል።አንተ ብትተወው በጎን ሌላው መጥቶ እንደሚገዛው ሻጩ እርግጠኛ ነው።ለምን ብትል አንደኛው ላይ በደል ሲደርስ ሁሉም ከተበደለው ወገን ጋር ተባብሮ ፍትህን እንደማያስከብር፣ ቤቱ ድረስ አንኳኩቶ ገብቶ ካላየውና በራሱ ላይ ካልደረሰበት በቀር ለሰው ብሎ ሐበሻ ሙግት ውስጥ እንደማይገባ ጠንቅቆ ያውቀዋልና! ዝም ብሎ የሚገዛ(ላ)ቸው ሲያገኙ እንዴት ፈላጭ ቆራጭ “ሻጭ” አይሆኑ?
የሚያሳዝነው ነገር ዛሬም ዓለም በአስጨናቂ ወረርሽኝ ክፉኛ እየተሰቃየች ባለችበት በዘመነ ኮሮናም ስግብግቦች ለሚሉት ሁሉ አቤት ወዴት ብሎ በገዛ ፈቃድ ራስን ለጭቆና የማመቻቸቱ ይህ ክፉ የአድርባይነት ባህል በመቀነስ ፋንታ ጨምሮ መታየቱ ነው።በዚህም የሰማንያ ብርን ሽንኩርት ሁለት መቶ ሃምሳ ብር እስከ መግዛት የደረሰ ፍጹም ለስግብግቦች ያደረ አሳፋሪ ባህሪይ ተመልክተናል።ስለሆነም ከቆዩት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችና ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ እየፈጠረ ከሚገኘው የንግድና ኢኮኖሚ የማዳከም ጫና ጋር ተዳምሮ ከዚህም በባሰ የኑሮ ውድነት እንዳይቀጣ ህብረተሰቡ ራሱን የመፍትሔው አካል ማድረግ አለበት እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
ይበል ካሳ