እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቤተኛችን ሆኗል። የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ እንዲሁም ሕዝባዊ ተቃውሞው በበረታበት የለውጡ ዋዜማ የታወጁት አዋጆች “ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ተፈጥሯል” የሚል ሽፋን የተሰጣቸው ነበሩ።
የአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታሪካችን እንግዳ ሳይሆን አልቀረም። የሕዝቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል አስከፊ በሽታ በመከሰቱ ነው ሕጉ የታወጀው። እስካሁን ባለን ልምምድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚለው ቃል ሲነሳ ፈጥኖ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የፖለቲካ ምክንያት ነው። የአሁኑን አዋጅ ስናስብ ግን ከዚህ የተለየ ስጋት ነው ፊታችን ላይ ድቅን የሚለው – ኮሮና።
የአዋጁም ሆነ የማስፈጸሚያ ደንቡ ዝርዝር ድንጋጌዎች ሰሞኑን በተለያየ መልኩ ተደራሽ ሆነዋል። ይሁንና የሕጉን መታወጅ ምክንያት በማድረግ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ንቃተ-ሕግን ለማዳበር የሚያግዙ ጉዳዮችን ማንሳት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ሰው ሕጉን በማክበር የተደቀነውን አደጋ በጋራ መመከት እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ምክረ-ሀሳብ ማቅረብም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ነው።
በመሰረቱ ሕግ የማውጣት ሥልጣን በተለይም ደግሞ አዋጅ የመደንገግ ኃላፊነት ለሕግ አውጭው አካል (ለፓርላማው) የተሰጠ ነው። ይሁንና በሕገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የመደንገግ ሥልጣን ለአስፈጻሚው (ለሚኒስትሮች ምክር ቤት) ተሰጥቶታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሥሙ እንደምንረዳው አስቸኳይ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የሚተገበር የአዘቦት ያልሆነ ልዩ ሕግ ነው። ሕጉ የሚታወጀውም አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ሁኔታ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት መቆጣጠርና መቋቋም ሳይቻል ሲቀር ነው።
በመሆኑም መንግስት የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር በአስቸኳይ ሕግ ማውጣት ባስፈለገው ጊዜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያውጃል። አዋጁንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የማጸደቅ ግዴታ አለበት፤ ፓርላማው ውድቅ ሊያደርገውም ይችላል።
በዚሁ መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፤ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት፤ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት በፌደራሉ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል።
ክልሎችም በሁለቱ ምክንያቶች ማለትም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት በክልላቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአስቸኳይ ችግር ማስተንፈሻ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን ሊቆይ የሚችለው ለስድስት ወራት መሆኑን ሕገ-መንግስቱ ይገልጻል። ይሁንና ፓርላማው አዋጁን በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ስለሚያደርገው እንደችግሩ ሁኔታ እየታየ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህርዩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚታወጁት አዋጆች ዝርዝር ጉዳዮችንና ድንጋጌዎችን እንዲይዝ አይጠበቅም። ይልቁንም ሕብረተሰቡና በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በመገንዘብ ከወትሮው በተለየ የባህርይ ለውጥ ለማምጣት እንዲዘጋጁ የሚያደርግ የማንቂያ ደወል ነው። ዝርዝር ክልከላዎችንና እገዳዎችን የሚያካትቱ ደንቦችም በየጊዜው የሚወጡለት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ለማስፈጸም የሚያወጣቸው ደንቦች አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘ ደረጃ ሁሉ በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እስከማገድ ድረስ የሚደርስ ክልከላ የማስቀመጥ ስልጣን አለው።
በዚሁ መሰረት በአዋጁም ሆነ በማስፈጸሚያ ደንቦቹ መንግስት መሰረታዊ የዜጎችን መብትና ነጻነቶችን ሊጥስ ይችላል። ዜጎች የመናገር ነጻነታቸው፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶቻቸው እንዲሁም የኃይማኖትና የእምነት ነጻነት፤ የባህል፣ የመምረጥና የመመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውም ሊታገዱና ሊገደቡ ይችላሉ።
በተለመደው የፍትህ አሰጣጥ ሂደትም ሆነ ሕግ በማስከበር ሥነ-ሥርዓት ውስጥ የተቀመጡት መብቶችም በአግባቡ ላይተገበሩ ይችላሉ። ሰዎች ሊታሰሩ፣ ምርመራ ሊደረግባቸው፣ ሊከሰሱና ለፍርድ ሊቀርቡ የሚችሉበት የሥነ-ሥርዓት መብትም በተለመደው ሕግ የማስከበር ሂደት እንደማይመራ ማወቅ ይገባል።
በአዋጁ የማይገደቡ መብቶች
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና በደንቦች የሚወጡት ክልከላዎችና የሚወሰዱት ርምጃዎች በማናቸውም መልኩ ሊጥሷቸው ወይም ሊገድቧቸው የማይገቡ ጥብቅ መብቶችን (Non-derogable Rights) ሕገ-መንግስቱ ዘርዝሯል። አንደኛ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚለው የመንግስት ስያሜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሊቀየር አይችልም።
ሁለተኛው የሰዎች የአካል ደህንነት መብት ጥብቅ መብት በመሆኑ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የተከለከለ ነው። ይኸውም ጭካኔ የተሞላበት ወይም ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት፤ ባርነት ወይም የግዴታ አገልጋይነት ወይም በሰው የመነገድ ተግባር ወይም በኃይል አስገድዶ ሥራን ማሰራት አይቻልም።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይገሰስ ሶስተኛው መብት የእኩልነት መብት ነው። ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል በመሆናቸው ከዚህ በተቃራኒው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በዘር፣ በሐይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ በማናቸውም መልኩ ልዩነት ሳይደረግ እኩል ጥበቃና የሕግ ዋስትና የማግኘት መብታቸው ሊጣስ አይቻልም።
አራተኛው የማይገሰስ መብት ተብሎ በሕገ-መንግስቱ የተገለጸው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እስከ መገንጠል ነው። በዚሁ መሰረት ይህ መብት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜም ቢሆን ሊከበር እንጂ ሊጣስ አይገባውም።
የሕገ-መንግስቱ ሕጸጾች
የእኛው ሕገ-መንግስት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ሳንካ ያለበት ሆኖ እናገኘዋለን። የመጀመሪያው የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠልን በአስቸኳይ ጊዜም ቢሆን የማይገሰስ መብት አድርጎ መደንገጉ ነው።
በመሰረቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው በአገሪቱ ውስጥ የተለየ እንግዳ ነገር ሲያጋጥም፤ ያ እንግዳ ክስተትም አገርንና ሕዝብን አደጋ ውስጥ ሲከት እንዲሁም ይህ አስጊ ሁኔታ በተለመደው ሕግ የማስከበር ሂደት ባለመገታቱ የተለየ ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው።
እናም አገር እንዲህ ባለ አስጨናቂና አስቸኳይ ልዩ መፍትሔ በሚሻ ጽኑ ሕመም ውስጥ ሆና ሳለች ብሔርና ብሔረሰቦቿ የመገንጠል ጥያቄ ቢያነሱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን ሊጣስ ወይም ሊከለከል የማይገባው መብት ስለሆነ መገንጠል እንዲችሉ ፈቃድ መስጠቱ የሚያስነቅፈው ነው።
ሁለተኛው ሕገ-መንግስቱ የሚተችበት ጉዳይ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌደራል መንግስቱም ሆነ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጁበት ሁኔታ ነው። የፌደራሉ መንግስት የሚያወጣው አዋጅ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚነት አለው፤ ክልሎች የሚያወጡት ደግሞ በክልላቸው ውስጥ ይተገበራል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ታዲያ የሁለቱ መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ቢጋጩ አልያም በአፈጻጸም ረገድ መደነቃቀፍ ቢፈጠር ሕገ-መንግስቱ መፍትሔ አላስቀመጠም። በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ጋር ተያይዞ አንዳንድ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። የፌደራል መንግስቱም የራሱን አውጇል። በቀጣይነት ታዲያ በሁለቱ መንግስታት አዋጆች በይዘትና በአፈጻጸም ሂደቶች ላይ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።
ስለዚህ ሕገ-መንግስታዊ መፍትሄ ባይኖርም ፌደራሊዝሙ በትብብር ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ሁለቱም መንግስታት በመመካከር አዋጆቹን መፈጸም ይኖርባቸዋል። በዚሁም ላይ የእኛ አገር ፌደራሊዝም አንዱ መገለጫ በተጨባጭ ሁኔታዎች ከክልሎች ይልቅ የማዕከላዊው መንግስት ጠንካራነትና ሕግን የማስከበር አቅም ጎልቶ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ቫይረሱ የአንድ ክልል ችግር ብቻ ሳይሆን አገር አቀፍ ስጋት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ መላው የአገሪቱን ሕዝቦች ያለልዩነት የሚያሳትፍ የሕግ አተገባበር ሥርዓት ሊዘረጋ የግድ ይላል።
ሕገ-መንግስቱ የሚነቀፍበት አራተኛው ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆን ሊገደቡ የማይገባ ጥብቅ መብቶችን ሲዘረዝር አገሪቱ ያጸደቀቻቸውን ዓለምአቀፍ ሥምምነቶች ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ ማስቀመጡ ነው።
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን በአንቀጽ 4 ሥር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይጣሱ መብቶችን ዘርዝሯል። ኢትዮጵያም ፈራሚ አገር እንደመሆኗ እነዚህን መብቶች በሕጓ ውስጥ ልታካትት ሲገባ በሙሉ ባለማካተቷ ትተቻለች።
በተለይም ሕገ-መንግስቱ የመብቶች ሁሉ እናት የሆነውን በሕይወት የመኖር መብትንና የወንጀል ሕግ ተመልሶ ወደኋላ የማይሰራ መሆኑን (አንድ ድርጊት በተፈጸመበት ወቅት በሕግ ወንጀል ተብሎ ካልተደነገገ የማያስቀጣ መሆኑን) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይጣሱ መብቶች ዝርዝር ውስጥ ባለማካተቱ በጽኑ ይተቻል።
በዚህ ምክንያትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እነዚህ መሰረታዊ መብቶች በሕግ አስከባሪ አካላት እንዲጣሱ በር መከፈቱ ግልጽ ነው። ከዚህም ሌላ በአንድ በኩል የአካል ደህንነት መብትን የማይገደብ መብት በማድረግ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝን ከልክሎ በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወት የመኖር መብት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚጣስ መብት ማድረጉ ብዙም ትርጉም የማይሰጥ ነው።
እርግጥ ነው በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 13 መሰረት የዜጎችን መብትና ነጻነቶችን የያዙ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለምአቀፍ ሥምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም ስላለባቸው በሕገ-መንግስቱ ባይዘረዘሩም እነዚህ መብቶችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሊደፈሩ አይገባም የሚል ሃሳብ የሚያራምዱ አሉ። ይሁንና ሕገ-መንግስቱ እነዚህንም መብቶች ከማይገሰሱ ጥብቅ መብቶች ዝርዝር ውስጥ በግልጽ ማካተት እንደነበረበት ሊሰመርበት ይገባል።
ለሕግ ተገዥነታችን የሚፈተንበት ትክክለኛ ወቅት
“ኢትዮጵያዊነት መልካምነት፣ ደግነት፣ መተሳሰሰብ ነው” ሲባል አዘውትረን እንሰማለን። እኛም ይህንን ስንናገረውና ስንሰማው የልብ ሙቀት ይሰማናል። በኢትዮጵያዊነታችንም እንኮራለን።
አሁን ያለንበት ወቅት በእርግጥም ኢትዮጵያዊነት የመተሳሰብ ተምሳሌት መሆኑ ከቃል በላይ በተግባር የሚፈተንበት ጊዜ ነው። ቀደምት እናት አባቶቻችን በየዘመናቸው ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ የየወቅቱን የአገርና የትውልድ ጠላቶቻቸውን በተባበረ ክንዳቸው አንበርክከዋል።
የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደቀደምቶቹ ሁሉ በአንድነትና በመተሳሰብ ልንዋጋው የሚገባ የጋራ ጠላት መጥቶብናል። እርግጥ ነው ይህ ጠላት በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የተደቀነብን ሳይሆን በሰው ዘር ላይ የጥፋት ጥላውን ያንዣበበ ብርቱ ጠላት ነው።
ይሁንና ይህንን ክፉ ጠላት የመከላከያው ዓይነተኛ ዘዴ እየተቀየሰና እየተተገበረም የሚገኘው እንደአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታና የመንግስታት ውሳኔ ነው። በኢትዮጵያም በየወቅቱ የተለያዩ የጥንቃቄ ርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። በተለይም በአገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከተገኙበት ጊዜ ጀምሮ በፌደራል መንግስቱና በክልሎች ቫይረሱን የመከላከል ርምጃዎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው።
ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በመበራከታቸውና ሞትም በመመዝገቡ መንግስት ሕዝቡን ለመታደግ ጠንካራ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥም ዋነኛው የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው።
የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕገ-መንግስቱ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል። አዋጁንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ በአብላጫ ድምጽ አስጸድቋል። አዋጁን መሰረት በማድረግም የተከለከሉ ተግባራትንና የታገዱ መብቶችን ዝርዝር የያዘ የማስፈጸሚያ ደንብ ይፋ አድርጓል።
አሁን መሰረታዊው ነገር ታዲያ አዋጁን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያዊነት የመተሳሰብ መገለጫ መሆኑ የሚረጋገጠው መንግስት ያወጣውን ሕግ በማክበርም ጭምር ነው።
የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በሽታውን መከላከል የሚቻለው በተናጠል ሳይሆን በጋራ ነው። ብቻችንን ተጠንቅቀን ሳይሆን፤ በጋራ ተከላክለን ነው ድል የምንነሳው። ስለዚህ መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ያግዛል በሚል የወሰደውን ርምጃ መተግበርና ያወጣውን ሕግም ማክበርና ማስከበር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ግዴታ ነው።
ሕግ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። እስከ አምስት ሺህ ዘመን የሚዘልቅ የአገርነት፣ የመንግስትና የሕግ ልምምድ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ኢትዮጵያውያን። የኢትዮጵያውያን የመንግስት ታሪክና የሕግ አክባሪነት እንዲሁም የጨዋነትና የግብረ ገብነት ተምሳሌትነት በጥንታውያኑ የግሪክ የታሪክ የቀለም ቀንዶች ሳይቀር የተመሰከረ ነው።
ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ “በሕግ አምላክ” የሚሉ ሕዝቦች ናቸው። መርከብ ገንብተው፣ ሳንቲም ቀርጸው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሲገበያዩ የነበሩ፤ ያኔ ተቆናጠው የነበረውን የስልጣኔ እርካብ ለትውልድ ቁጭትም ኩራትም እንዲሆን አሻራ ትተው ያለፉ ቀደምት ስልጡን ሕዝቦች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ዓለምን በብዙ መልኩ የቀረጹና በተለምዶ “ታላላቅ” የሚባሉትን እምነቶች ገና ከማለዳው ጀምሮ ተቀብለው የዘለቁ ጽኑ ሕዝቦች ናቸው። የሕግ ምንጭ ፈጣሪ ስለመሆኑ፤ ሕግ ሰርቶ ትዕዛዝ ጨምሮ ለሰው ልጆች ማስተላለፉን፤ የሰው ልጆችም ከፈጣሪ ቀጥሎ በላያቸው ላይ በሚሾሙት መሪያቸው በሚወጣላቸው ሕግ መመራት እንዳለባቸው፤ እናም ሕግና የሰው ልጅ ጥብቅ አብሮነት ያላቸው መሆኑን በጽኑ አስተምህሮ ያሰፈኑ ሕዝቦች ናቸው።
እንዲህ ያለ የሺህ ዘመናት ዕድሜ ያስቆጠረ የሕግና የመንግስት ታሪክ ያላት አገር ሕዝቦች ታዲያ ለሕግ አክባሪነት እንግዳ አይሆኑም። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ቆም ብሎ ሊያስተውል ይገባዋል። የቫይረሱ ዋነኛ መዛመቻ ያልተገባ መቀራረብና ንክኪ በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት ያለመውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአግባቡ ተገንዝበን ማክበር ይጠበቅብናል።
የበሽታው ቀዳሚ መከላከያ ቤት ውስጥ ተሰብስቦ መዋል ማደር ነው። ግን እኛ ካለን አቅም አንጻር ይህንን ማድረግ የማይታሰብ በመሆኑ ነው መንግስት ሕብረተሰቡ በሚያደርገው መስተጋብር ውስጥ ንክኪንና ማህበራዊ መቀራረብን እንዲያስወግድ የሚያስገድድ ሕግ ለማውጣት የተገደደው።
እናም እያንዳንዱ ዜጋ ለሚያደርገው ነገር ሁሉ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት። እሱ የሚወስደው የጥንቃቄ ርምጃ ለሌላውም መዳን ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ አለበት። አድርጉ የተባለውን በማድረግ፤ አታድርጉ የተባለውን ባለማድረግ አንድም ቫይረሱን መከላከል፤ ወዲህም ጨዋነትን ማስመስከር ይቻላል።
ሕግ አክባሪነት የስልጡንነት መለኪያ ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትን አንድ ብለን ቆጥረን ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በፓርላማው ብቻ ከ1ሺ 100 በላይ አዋጆች ወጥተዋል። በየክልል ሕግ አውጭ አካላት የወጡ አዋጆችን ክልሎች ይቁጠሯቸው። አዋጆቹን ለማስፈጸም የወጡት ደንብና መመሪያዎችማ ለቁጥር ያዳግታሉ። ያም ሆኖ እነዚህ ሁሉ ሕጎች እንደታሰቡት በልዩ ልዩ ጉዳዮች የህዝብን ባህርይ ቀርጸው ከሕግ አክባሪዎችና የሕግ የበላይነት ከነገሰባቸው ስልጡን ሕዝቦች ተርታ ሊያሰልፉን አቅም አላገኙም።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሰከን ብለን ካንዣበበብን ፈተና መሻገር አለብን። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሕግን ማክበር የመጀመሪያው ግዴታ ነው። በዚህም ወደ ሞራል ልዕልና መጓዝ ያስፈልጋል። የሕሊና ሰው መሆን የግድ ነው።
ከሕግ አስቀድሞ ለሕሊና መገዛት ያስፈልጋል። በሕሊና መገዛት ደግሞ ምክንያታዊ ያደርጋል። ሃሳብ አፍላቂዎች፣ ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ዜጎች በአጠቃላይ ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች የወጣውን ሕግ ማክበርና ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል። ስለሆነም ሁሉም ሰው በራሱ ላይ የራሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይጠበቅበታል።
በደህና እንሰንብት!
አበቃሁ! አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
በገብረክርስቶስ