ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፤ ዘመናት ነጉደው በአዲስ ሲለወጡ፤ በተመሳሳይ የሰው ልጅ በየፈርጁ የኑሮ ዘይቤውን፣ አመለካከቱን እና የስልጣኔ ደረጃውን ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደመ ይቀያይራል። ይህ ብቻ አይደለም። በተፈጥሮ ኡደት የሚከሰቱ አስቸጋሪ ለውጦችን የሚቋቋምበት ብልሃትም ይዘይዳል። ሥሪቱም እራሱን ከሁኔታዎች ጋር አላምዶ እንዲኖር ይፈቅዳል። ይህ ስጦታው ደግሞ በርካታ ዘመናትን አሻግሮ አሁን ያለንበት አስደናቂ የኑሮ ደረጃ ላይ አድርሶታል። ለዛሬ በኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ ልናነሳው ለወደድነው ርዕሰ ጉዳይ የሚጠቅሙንን ማሳያዎች ከሥር እንደሚከተለው ለማንሳት እንሞክር።
የሰውን ልጅ የስልጣኔና የዘመናዊነት ግስጋሴ በየጊዜው ለመገደብ የሚሞክሩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያቶች ይከሰታሉ። ከነዚህ መካከል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ረሐብ፣ የተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ድርቅ)፣ ጦርነት ጨምሮ ሌሎችም በምሳሌነት ይነሳሉ።
ከሁሉም በከፋ ሁኔታ ግን እንደ ተዛማች በሽታ የዚህን ሰብአዊ ፍጡር ህልውና እየተፈታተነ የሚገኝ አይመስልም። ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ቫይረስ የመኖር ህልውናውን በተደጋጋሚ ፈትኖታል። ስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ)፣ ኤች አይቪ ኤድስን ጨምሮ ታላላቅ የሚባሉ በሽታዎች ጎብኝተውታል። የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ፣ ቁስሉ ቢሽርም ጠባሳው ሳይጠፋ ክፉውን ዘመን በድል ተሻግሮታል።
እነዚህ በሽታዎች በመቅሰፍታቸው ሃይል በጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈሩ ይሁን እንጂ በሌላ ጎን የሰውን ልጅ የመመራመር፣ የመፍጠርና የመከላከል አቅሙን ቀድሞ ከነበረው በተለየ መልኩ አሳድገውታል። ህልውናው ላይ ጥፋት የሚቃጡ ቫይረሶችን በተሰጠው ጥበብ ተመራምሮ መድሃኒት ከማግኘት ጀምሮ ክፉውን ዘመን አጎንብሶ ሥነ ልቦናውን አደድሮ የሚያልፍበት መላ ከመዘየድ ወደ ኋላ አላለም።
ይህ ጥረቱ እዚህ ቢያደርሰውም የተፈጥሮ ለውጥ ደግሞ ተመሳሳይ ፈተናዎችን ከማምጣት አትቦዝንም። ለዚህም ይመስላል አሁንም ዓለምን በአንድ ከረጢት ውስጥ ከትቶ ከወዲህ ወዲያ የሚያላጋ አዲስ ፈተና የገጠመን። ወቅታዊ ጉዳያችን ኮቪድ 19 (የኮሮና ቫይረስ) ነው። ቫይረሱ የሰው ዘርን በሙሉ እያስጨነቀ በሽምጥ ግልቢያው መላውን ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል።
ነገ ምን እንደሚፈጠር ባናውቅም እስካሁን ባለው መረጃ ሊገታው የሚያስችል አንዳችም ፍቱን መድሃኒት አልተፈጠረለትም። ሆኖም ካለፈው የሰው ልጅ ልምድና ኑረት እንደምንረዳው ይህን ጊዜ በድል እንደሚያልፍ ነው። እስከዚያው ግን እንደ ማስታገሻ አንዳች ሌላ መፍትሄ የሚያሻ ይመስላል፡፡
ጥበብን እንደ ማስታገሻ
የኮቪድ 19 ቫይረስ አይነት ዓለም አቀፍ ተዛማች በሽታዎች ቀጥታ ታማሚውን ከማጥቃትና ለሞት ከመዳረግ ባሻገር የሰው ልጅ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ያስከትላሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የተቀረው የሰው ልጅ ‹‹ነገ እኔስ ምን እሆናለሁ ›› በሚል የፍራቻ ጢሻ ውስጥ ተደብቆ በጭንቀት፣ በድብርትና ውጥረት አረንቋ ውስጥ እንዲሸሸግ ማድረጋቸው ዋነኛው ነው። የተለመደውን የየዕለት የኑሮ ኡደት በማዛባት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅምን በማዳከምና እንቅስቃሴን በመግታት ለሥነ ልቦና ውጥረትና ቀውስ መዳረግ አንዱ ባህሪያቸው ነው። አሁን ላይ የምናስተውለው የኮሮና ቫይረስ ዳፋም የዚሁ ባህሪ መገለጫ ነው። ሆኖም ካለፉት ክፉ ጊዜያቶች ትምህርት የወሰደው ሰብአዊው ፍጡር ይህን ለመሰለው ቀውስ መፍትሄ ካበጀ ዘመናትን አስቆጥሯል። ጥፋት አጥፍታ ስትቀጣ ‹‹ዱላው እስኪመጣ በክርን ያዝግሙብኝ›› እንዳለቸው ባልቴት ዓለም አቀፍ ተዛማች በሽታዎች በሰው ልጅ ላይ የሚፈጥሩትን የሥነ ልቦና ውጥረት፣ ጭንቀትና ድብርት ለማከም ጥበብ ወይም አርት ቴራፒ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ ዘመናትን ተሻግሯል።
ድብርትን በጥበብ ማስታገስ ?
በጥበብ ድብርትን፣ ውጥረትንና መሰል የሥነ ልቦና ችግር የሆኑትን ማከም ‹‹art therapy›› በዓለማችን ላይ ዘለግ ያሉ ዘመናትን ማስቆጠሩን የተለያዩ መረጃዎች እና በዘርፉ ላይ የሚገኙ ምሁራን ይጠቁማሉ። ይህን የህክምና ዘዴ ምንነት እና ትርጓሜ የብሪቲሽ የአዕምሮ ህሙማን የአርት ቴራፒስት ማህበር ‹‹ህሙማኑን የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን በዋናነት እና በቀዳሚነት በመጠቀም ለመፈወስ የሚሠራ ሙያ ነው›› በማለት ሲያስቀምጠው፤ በተመሳሳይ የአሜሪካ የአርት ቴራፒ ማህበር ‹‹ትኩረቱን በዋናነት የአዕምሮ ህሙማን ላይ በማድረግ ግለሰቦችን፣ ቤተሰብ እንዲሁም ማህበረሰብን በተቀናጀ ጥበባዊ የፈጠራ ክህሎት የሥነ ልቦናና ተያያዠ ችግሮችን ለመፍታት የሚሰራ ነው›› ይለዋል። እነዚህ ሁለት ታላላቅ ማህበራት በተለያየ ቋንቋ ነገር ግን በተመሳሳይ አላማ የሙያውን አስፈላጊነት አጉልተው በማሳየት የህክምና ዘርፍ ላይ ሙያው ጉልህ ድርሻ መጫወት የሚችል መሆኑን ያስገነዝባሉ።
በተለይ ጥበብ ከመዝናኛ እና ነብስያን ከማስፈንጠዣነቷ በዘለለ የፈውስ እንክብል መሆኗን ይመሰክራሉ። አርት ቴራፒ በሰለጠኑ እና ወደፊት ዘልገው በተራመዱት አገራት ውስጥ ትኩረት ይሰጠው እንጂ ተመሳሳይ የህክምና ትኩረት የሚሹ ዜጎች ባሉባት አህጉረ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል አሻራ የለውም። ሙከራ በሚባል ደረጃና በግለሰቦች ጥረት ጅምር እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ግን አልጠፉም።
ከላይ በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ይህን ቁልፍ ጥበባዊ የህክምና ዘርፍ በዛሬው የኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ በስፋት በማንሳት በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተገቢው ትኩረት አግኝቶ ተግባራዊ ቢደረግ የሥነ ልቦና ችግርንና መሰል ጋሬጣዎችን በእጅጉ ሊፈታ ይችላል። አርት ቴራፒ በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሥነ ልቦና ችግርን (እንደ ውጥረት፣ ድብርት የመሳሰሉትን) ማከም እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የትኛውንም የኪነ ጥበብ መንገድ ለዚህ መሰል አላማ መጠቀም ይቻላል። በተለይ ሙዚቃ፣ ድራማ እንዲሁም ስዕልን የመሳሰሉ የጥበብ ሥራዎች ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችንም ለመፈወስ ግብዓት ናቸው። በተለይ ታካሚዎች ስሜታቸውን በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ሲገልፁ አንዱ የመተንፈሻ መንገድ እንደሚሆናቸው ይናገራሉ። የጥበብ ክህሎት ተሰጦ ያላቸው ህሙማንም አሳታፊ ለማድረግ እና ወደ ቀድሞ የሥነ ልቦና ጥንካሬያቸው እንዲመለሱ ለማገዝ እንደሚረዳም ያስረዳሉ።
ነባራዊ ሁኔታ
‹‹በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሰለጠኑት የዓለማችን ክፍላተ አገራት የአርት ቴራፒ አጥጋቢ በሆነ መንገድ አልተስፋፋም። በስፋት መተግበር ቢችል ግን ውጤታማ እንደሚሆን በሳይንሱ የተረጋገጠ ነው›› የሚሉት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅር እንግዳችን የነበሩት በየካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ዳዊት አሰፋ ናቸው።
ይህን ለማሳካት የህክምናውን እና የጥበብ ተሰጦን ያማከለ አርት ቴራፒስት ባለሙያ አስፈላጊ መሆኑን አንስተውልን ነበር። ማንኛውም ሰው እራሱን በአርት ቴራፒ የማከምና፣ የማረጋጋት ክህሎት ማዳበር እንደሚችልም ገልፀውልን ነበር። ጥበባዊ ሥራዎች ለታማሚዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ማህበረሰብም ግዙፍ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ እንዳላቸው ነው በምክረ ሐሳባቸው ላይ ያጫወቱን። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ በፊት ባወጣው ዳሰሳዊ ጥናት እስከ 27 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል በየደረጃው የአዕምሮ ህመምና የሥነ ልቦና ችግር ተጠቂ ሊሆን እንደሚችል አስቀምጧል። የሥነ ልቦና ችግር የሚባለው እብደት ብቻ አይደለም። ከ360 በላይ የህመም አይነቶች መኖራቸውንም ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከነዚህ ውስጥ ውጥረት፣ ጥልቅ ድብርት እና ጭንቀት ይገኙበታል። በተለይ ለዛሬ በርዕሰ ጉዳያችን ላይ ባነሳነው የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ቫይረስ ምክንያት ጠንካራየሥነ ልቦና ደረጃ የነበራቸው ሁሉ የችግሩ ተጠቂ እየሆኑ መምጣታቸውን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።
ዓለም አቀፉን የጤና ድርጅት ጨምሮ በርከት ያሉ የጤና ተቋማት የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና ሊያረጋጉ የሚችሉ ምክረ ሐሳቦችን በተለያዩ አማራጮች ሲያሳውቁ መመልከት ችለናል። የሥነ ልቦና ችግር ያለባቸው ዜጎች በርካታ ቢሆኑም የተለያዩ ቴክኒኮችን ተጠቅመው እራሳቸውን ከችግሩ ለማላቀቅ የሚሞክሩት ጥቂቶች ናቸው። ሌሎች አማራጮችን የሚጠቀሙ ማለትም ወደ ህክምና ተቋማት የሚያመሩት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ የዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ተያያዥ ችግር ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ይህንመንገድ የሚከተሉት ከ10 በመቶ የሚበልጡት እንዳልሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተገቢው መንገድ ክትትል የሚያደርጉትም ከ2 በመቶ እንደማይዘሉ እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህ ምክንያት ነው አገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች ዋናውን የህክምና መንገድ በአግባቡ መድረስ ሳይቻል አርት ቴራፒው (በጥበብ ህክምና መፈወስ) ላይም በተገቢው መንገድ መሄድ አስቸጋሪ እንደሚሆን እንደምክንያት ይጠቅሳሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጅምሮች መኖራቸው ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች አልጠፉም። ይህ ታላቅ ጥበብ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ በርካታ ሥራዎች መሠራት አለበት።
በተለይ በአገራች የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና የሚጎዱ መሰል አስጨናቂ ጊዜያቶች ሲከሰቱ ዜጎች አርት ቴራፒንና ሌሎች ፈዋሽ መንገዶችን በመጠቀም አዕምሯዊ ጥንካሬያቸውን እንዴት አስጠብቀው መቆየት እንዳለባቸው ግንዛቤ ሊያገኙ ይገባል። የኪነ ጥበብና የጥበብ ተሰጦ ያላቸው ማናቸውም አካላት ጋር በመተባበር ሙያውን ለማሳደግ ፍላጎት ያላቸው አካላት መረጃን ለዜጎች የማድረስ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
በተለይ ሙያው መሠረት እንዲይዝ የጥበብ ቤተሰቡ በበጎ ፍቃድ ሊሠራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ማህበራዊ ድረ ገፆችንና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ ነው። በፊልሙና በሙዚቃው ዘርፍ አርቲስት ብርሃኔ ጌታቸው፤ በቲያትሩ ዘርፍ ደግሞ እንደነ አርቲስት ፋሲል ግርማ አይነት ተነሳሽነት ያላቸው ሰዎች ሊበዙ ይገባል። መንግሥት ጥበብ ከማዝናናት ያለፈ የፈውስ ምክንያት መሆኑኗ ተረድቶ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይ በዚህ ወቅት ከማንኛውም ጊዜ በተለየ ከዚህ ዘርፍ እገዛ የሚሽበት ነው።
አርት ቴራፒ በቤት ውስጥ
ወቅቱ ተዛማች በሽታውን ተከትሎ ከቤት የማንወጣበት ነው። እንቅስቃሴያችን በመገደቡ ምክንያት ለድብርት፣ ጭንቀትና ውጥረት ልንዳረግ እንችላለን። ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት ደግሞ ጥበብ አንዱ መንገድ እንደሆነ እስካሁን እያነሳን እዚህ ደርሰናል። አሁን ደግሞ ያለማንኛውም የህክምና ባለሙያ አርት ቴራፒን እንዴት በግላችን መተግበር እንችላለን የሚለውን እንመለከታለን። የአሜሪካው አርት ቴራፒ ማህበር እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2016 ባሳተመው ጽሁፍ Journal of the American Art Therapy Association›› የሚከተሉትን ራስን ከውጥረት፣ ድብርት የምናላቅቅበትን መንገድ ለማስቀመጥ ሞክሯል። እኛው የርዕሰ ጉዳያችን መቋጫ አድርገነዋል። እንደ ማህበሩ ሙያዊ ምክረ ሐሳብ በቤት ውስጥ የሚተገበር አርት ቴራፒ ከተጠመድንበት ውጥረትና ጭንቀት እንድንገላገል፣ የተረጋጋ መንፈስና ጥንካሬ እንዲኖረን እንዲሁም ራሳችንን ጤናማ ጊዜያቶችን እንድናሳልፍ ይረዳናል። በመሆኑም እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት የሚከተሉት ጥበባዊ ልምምዶች ሊኖሩን ይገባል።
የመጀመሪያው የስዕል ክህሎታችንን በማዳበር በቤት ውስጥ በተለያዩ ቁሳቁሶች ስሜቶቻችንን የሚገልፁ ምስሎችን ለመሥራት መሞከር ነው። ማለትም የሚያስጨንቁንን ጉዳዮች በወረቀታችን አሊያም ባዘጋጀነው ሸራ ላይ ለመግለፅ መሞከራችን በንግግር መግለፅ የማንችለውን ስሜት ለማውጣት ይረዳናል። በዚህ መንገድ ውስጣችን ያለውን ጭንቀት ወይም ውጥረት ይቃለላል።
ሌላኛው መንገድ በተመሳሳይ በስዕል የምንገለፀው ነው። ይህም ማለት በህይወታችን አሊያም በቀን ውሏችን ውስጥ ጥሩ ስሜት የሰጡንና የሚሰጡንን ጉዳዮች በጥራዝ ማስቀመጥ አሊያም መሳል ነው። በተመሳሳይ ቀለማትን በመጠቀም ውስጣዊ የደስታ ስሜት የሚፈጥሩና ውጥረትን የሚገቱ ጥበባዊ የስዕል ውጤቶችን መሥራት ይመከራል። ለስላሳ ሙዚቃን ማዳመጥ፣ የድምፅ ልምምድ ማድረግ የዚሁ የአርት ቴራፒው አካል ናቸው። እነዚህ የግል ልምምዶች አሁን ለገጠመን ዓለም አቀፍ ችግር መድሃኒቱ እስኪገኝ ከማስታገሻዎቹ መካከል ናቸው። ሰላም !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2012
ዳግም ከበደ