ጋዜጠኝነት ማብቂያ፣ ማቆሚያ የሌለው የህይወት ዘመን ልምምድ፣ ትምህርት ነው። በዕየለቱ መጽሐፍ፣ ማንበብ፣ ማድመጥ፣ ማንሰላሰልና ከባልንጀራ ጋር በቡድን መሥራት ይጠይቃል። በዚህ ልምምድ ያለፉ ጉምቱ ጋዜጠኞችን ሥራ ማንበብ፤ ማገላበጥ ይፈልጋል።
የሙያው ዋርካ የነበረውንና ልቅም ጥንቅቅ ያለውን የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን ሥራዎች፤ እንደ እናት ጡት የማይጠገቡትን የሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ወጎችን መሰለቅ ይጠይቃል። የፋናውን ዳዊት መስፍን ዜና፣ የሸገሩን እሸቴ አሰፋ መቆያ፣ የመዓዚን ሸገር ካፌን፣ የፊት ገፅ ዜናው ከርዕሰ አንቀፅ፣ ርዕሰ አንቀፁ ከካርቶኑ ያንሰላሰለውን ሪፖርተርን፣ የፍ-ት-ሕን ብርሃኑ ደቦጭ ጥልቅና የሰሉ የመጽሐፍ ግምገማዎችን ፣ የኃይለጊወርጊስ ማሞን፣ የበድሉ ዋቅጅራን እና እንደ እማ አሟምታ ሲያሻቸው ጎሜ ሌላ ጊዜ አሽሙር፣ ምፀትና ተረብ እያዛነቁ የሚመጡትን የዋጋዬ ለገሰ መጣጥፎችን ማንበብ ግድ ይላል፡፡
ከውጭ በአሜሪካ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ጉልህ አሻራውን እያኖረ ያለውን የሐርቫርድና የየል ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅና በትውልድ ሕንዳዊ የሆነው የዋሽንግተን ፖስት ቋሚ አምደኛና የCNN GPS አዘጋጅ ፋሪድ ዘካርያን አቋም ማንበብ፤ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን መከታተል፤ ከዚሁ CNN ላይ እሁድ እሁድ የሳምንቱ የሚዲያ ሥራና አዘጋገብ የሚተችበትን በብራያን ስቴልተር የሚዘጋጀውን ” Reliablel Source ” መመልከት፤ ከዚሁ ከCNN ሳንወጣ የክርስቲያን አማንፓርን ተወዳጅ ቃለ መጠይቆች፤ የBBCን HARDtalk በተለይ የስቴቨን ሳካርንና የቲም ሰባስትያንን፤ የኒክ ጎይንግንና የዘይነብ በዳዊን Intelligence Square እና World Debate በትኩረት መከታተል፤ እነ ታይምን፣ ዋሽንግተን ፖስትን፣ ዘ ኢኮኖሚስትን፣ ወዘተ . ማንበብ የምር ጋዜጠኛ ለመሆን ያግዛል።
የጋዜጠኞች ድምፅ የሆነውን CJR (Columbia Journalism Review )
የሚዲያና የጋዜጠኝነት ነቀሳዎችን፤ እንደ ፑሊትዘር ያሉ የጋዜጠኝነት ሽልማቶችን ያሸነፉ የምርመራ ዘገባዎችን፣ መጣጥፎችን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያና ሌሎች ሥራዎችን ጉግሎ ማንበብ፣ መመልከት ወደ ጋዜጠኝነት ድርበብ ያስጠጋል። በጋዜጠኝነት ሙሉኡነት ስለማይታሰብ።ጋዜጠኝነት” እንጀራዬ ነው ! ” ከማለት በላይ ነው። ጋዜጠኝነት እንደተለፈለፈ የአጋንት ጭፍራ ምሱ ብዙ ነው።
ላይ ላዩን ሳይሆን ከሚታየው ሥር፣ ከሚነገረው ባሻገር ያለውን ገልቦ፣ አገላብጦ መመልከት፣ ማዳመጥ ይፈልጋል። በቅቻለሁ፣ ነቅቻለሁ ብሎ መታበይ ለጋዜጠኝነት ሐጢያትም፣ ነውርም፣ ግብዝነትም ነው ፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሠርቻለሁ። ግን ዛሬም ተማሪ ነኝ። ዛሬም ጽሑፎቼ እንደ ሽንፍላ በአንድ ጊዜ አይጠሩም። ከእጄ እስኪወጡ ደግሜ ደጋግሜ አርሜአቸው ከቆይታ በኋላ ተመልሼ ሳያቸው የሆነ ግድፈት አላጣባቸውም። በዚህ ልምምዴ ጽሑፉ የማይሞት፣ ጊዜ የማያልፍበት ከሆነ በችኮላ ለህትመት ወይም ለስርጭት ማብቃት አልፈልግም። ከታተመ፣ አየር ላይ ከዋለ በኋላ እንኳ አንዳች እንከን አላጣበትም።ይህን የማደርገው ደደብ ስለሆንሁ አይደለም። ዛሬ የምጽፈው ዜና ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ ፕሮፌሰር ቶምስኪን ጠቅሶ በአንድ መጣጥፉ እንዳስነበበን ” ጋዜጠኝነት ራሱ በሰፊው የምናስበው የታሪክ ረቂቅ የሚቀርብበት ነው። ( Journalism is the first draft of history ) “ስለሆነ ጭምር እንጂ፡፡ ጋዜጠኝነት እራሱ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው የተለያዩ የታሪክ ምዕራፎችንና ጫናዎችን አልፎ ነው። ጋዜጠኝነት በዛሬው ቅርፅና ይዘት ባይሆንም ከሰው ልጅ ጋር አብሮ አደግ ነው ማለት ይቻላል። በ1440 እ.ኤ.አ ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ የፈለሰፈው ዘመናዊ ፊደል የሚቀርጽ ማተሚያ መሣሪያ ለህትመት ጋዜጠኝነት መጎልበት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
ሆኖም መጀመሪያ የሬዲዮ በማስከተል ቴሌቪዥን መፈጠር በህትመት ጋዜጠኝነት ህልውና ላይ አደጋ የደቀነ ቢሆንም የኢንተርኔት በመቀጠል የማህበራዊ ሚዲያ መምጣት ደግሞ ጫናው ቢለያይም በአጠቃላይ በመደበኛ ሚዲያው ቀጣይ ህልውና ላይ ከየአቅጣጫው ናዳ እየወረደበት ነው።በሌላ በኩል ጋዜጠኝነት የስፓኒሽ ፍሉን፣ የ1ኛው የዓለም ጦርነትን፣ ታላቁን የኢኮኖሚ ቀውስን፣ 2ኛው የዓለም ጦርነትን፣ ቀዝቃዛውን ጦርነት፣ ወዘተ አልፎ ዛሬ ላይ ቢደርስም የኖቨል ኮሮናቫይረስ ( ኮቪድ 19 ) ያህል ፈተና ገጥሞት እንደማያውቅ፤ ወረርሽኙ ከአለፈ በኋላም ጋዜጠኝነት እንደ በፊቱ እንደማይቀጥል፤ አሠራሩ፣ አደረጃጀቱ እንደሚቀየር የዘርፉ ልሂቃን እያሟረቱ ነው። ብዙ ሳይቆይ ሟርቱ ወደ ተጨባጭ ሥጋት በመቀየር ላይ መሆኑን እየታዘብን ነው። ጋዜጠኞች በወረርሽኙ ከመሞታቸው ባሻገር የሥራ ዋስትናቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል ።
መሪ ዜና አቅራቢዎች ( ኒውስ አንከርስ ) እና የፕሮግራም መሪዎች፣ ከተንቆጠቆጡ እስቱዲዮአቸው ሳይሆን ከመኖሪያ ቤታቸው በሲስኮ ዌቤክስ ቪዲዮ ማስተላለፍ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።የሚዲያዎች ገቢም እያሽቆለቆለ ነው። ወደ ሀገራችን ስንመጣ ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። በኢትዮጵያ የፕሬስ ድርጅት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ከተማ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋዜጠኞች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው መዘገብ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩ ባሻገር የመረጃ ምንጭ እጥረት እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ።
አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች ለገፅ ለገፅ ቃለ – መጠየቅ ፈቃደኛ አለመሆን ጀምረዋል። የጋዜጦች ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ሲሆን በተለይ አዲስ ዘመንና ሔራልድ ላይ ተጽዕኖው የከፋ መሆኑን አቶ ፈቃዱ ገለፀው የአዲስ ዘመን ስርጭት ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ቅጂ መቀነሱን ተናግረዋል። የማስታወቂያ ገቢም በእጅጉ እያሽቆለቆለ ነው ።
ይህን ክፉ ቀን ለማለፍ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቀውስ አመራር ኮሚቴ አዋቅሮ ዕቅዶቹን የመከለስ፣ አሠራርና አደረጃጀቱን ተለማጭ ( ፍሌክሲብል) ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።የማስታወቂያ ገቢያቸው መቀዛቀዝ፣ ቢሮ ተገኝተው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ቁጥር በግማሽ እስከ መቀነስ መድረሱንና የጋዜጣው ገፅ ብዛት በግማሽ ያህል መውረዱን ያረዱኝ ደግሞ የሪፓርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ መላኩ ደምሴ ናቸው።
በወረርሽኙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ቢገደብና ማተሚያ ቤት ቢዘጋ ወደ ኦን ላይንና ቪዲዮ (ዩቲውብ ) ሽግግር ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከልም ከተለመደው አይነት ጋዜጠኝነት መውጣት አስፈልጓል።ስለ ኮቪድ 19 የሚጠናቀሩ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ከተለመደው አሠራር ወጥተው የማብራራት ጋዜጠኝነት መርህን Explanatory Journalism እንዲከተሉ ጉምቱ ጋዜጠኞች እየወተወቱ ነው።
የCNN ” Reliablel Source ” አዘጋጅ ብራያን ስቴልተር በዚያ ሰሞን ብዙኃን መገናኛዎች በተለይ ዋና ዋናዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ቴሌቪዥኖች፣ጋዜጦችና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እንዴት እንደዘገቡት እና መዘገብ እንዳለባቸው ከሙያው ጉምቱዎች ዳን ራዘርንና ካርል በርኒስቲን ከአንጋፋዎቹ የአሶሴትድ ፕሬሷ ( ኤ ፒ ) ሳሊ ቡዝቤንን፣ የዎል ስትሬት ጆርናሉን ማት መሪ ጋር መክሮ ነበር። በውይይታቸው ከፍ ብየ እንደገለፅኩት ወረርሽኙ የጋዜጠኝነትን አሠራር እንዴት ከመሰረቱ አናዳናጋውና እንደቀየረው አውስተዋል። በተለይ አንጋፋዋ የአሶሴትድ ፕሬሷ ( ኤ ፒ ) ጋዜጠኛ ሳሊ ቡዝቤን ” ወረርሽኝ ፦ የማብራራት ጋዜጠኝነት ጎልቶና ገዝፎ የሚወጣበት ትልቅ ሁነት ነው።( Pandemic is ” The Olympic Of Explanatory Journalism ) ” ብላለች ። ኦሎምፒክ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ፣ ከ200 አገራት የተወከሉ እስከ 20 ሺህዎች የሚጠጉ አትሌቶች የሚሳተፉበት፣ ለአሸናፊ አትሌቶች ከፍ ያለ እውቅና ከማስገኘቱ ባሻገር ለቀጣይ ስኬት መስፈንጠሪያ ስለሆነ፤ ለዝግጅቱ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚወጣበት፣ ከዓለም ዋንጫ ባልተናነሰ የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ ቁንጮ ስለሆነ ነው እንግዲህ የማብራራት ጋዜጠኝነት አልፎ አልፎ ለሚከሰት ወረርሽኝ፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ዘገባ ፍቱን መድሃኒቱ ነው ያለችው። ለመሆኑ የማብራራት ጋዜጠኝነት ምንድን ነው፡፡
ለአንባቢው በሚገባ ቀላልና ግልፅ አረፍተ ነገር፣ እንግዳ የሆኑ ሐሳቦችን እና ውስብስብ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች የሚዘገቡበት የጋዜጠኝነት አይነት ነው። የብሩኪንግስ የኮሙኒኬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ፋዋል፣ ” explanatory journalism cure the internet? ” በሚል ባስነበበን መጣጥፍ፣ የማብራራት ጋዜጠኝነት አንድን ጉዳይ ግልፅ፣ ቀጥተኛና ተደራሽ በሆነ አግባብ መዘገብ ነው።
የእዝራ ክሌንስን ቮክስ፣ የኒው ዮርክ ታይምስ ” ዘ አፕሾት ” ፣ ቡዝፊድ እና የብሉምበርጉ ኩይክቴክን በአብነት ይጠቅሳል። የማብራራት ጋዜጠኝነት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምክንያታዊ ዘገባ ለአንባቢው ለማድረስ ከማገዙ ባሻገር እግረ መንገድ የህትመት ጋዜጠኝነትን መሠረታዊ ኃላፊነት ለመወጣት እገዛ እንደሚያደርግ ያስረዳል። ሌላው የዚሁ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ቶማስ ኢ ማን፣ ዛሬ ላይ እንደ አዲስ የማብራራት ጋዜጠኝነት እየተቀነቀነ ቢሆንም እ.ኤ.አ ከ1985 ጀምሮ ፑሊትዘርን ያሸለመ የጋዜጠኝነት ዘርፍ መሆኑን ያስታውሳል።
መረጃ ማዛባት በገነገነበት በዚህ የኢንተርኔት ዘመን እንደ ፈጣን መፍትሔም እየተወሰደ ይገኛል ይለናል፡፡ ቮክስ ከ5 ዓመታት በፊት በዲዝኒላንድ ፓርክ የኩፍኝ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ሁሉ በማሟላትና ግልፅ በሆነ ቋንቋ ፣ ሙያዊ አገላለፆች ( ጃርገንስ ) ቀላል በሆነ ገለፃ በመተካት እና መረጃ ሳያዛባ ያጠናቀረውን ዘገባ ፋዋል በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡
በዘገባው ኩፍኝ አደገኛ ተላላፊ በሽታ እና በክትባት ላይ የተከፈተው የሴራ ዘመቻ የተነሳ ልጆቻቸውን የሚያስከትቡ ወላጆች መቀነስ እንዲሁም አለማቀፍ የሰዎች እንቅስቃሴ መጨመር ለወረርሽኙ በፍጥነት መዛመት አስተዋፆ እንዳለው ይተነትናል።ይህ ማብራራት ጋዜጠኝነት ከእነ ሙሉ ማዕቀፉ የሚገለጥ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከሀገራችንም ከላይ የተገለፁትን የማብራራት ጋዜጠኝነት አላባውያንን ያሟሉ ዘገባዎችን አልፎ አልፎ አጋጥመውኛል። ፋና ቴሌቪዥን በዚያ ሰሞን ስለፒራሚድ ንግድ፤ ፍ – ት – ሕ መፅሔት ከወራት በፊት ስለ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድና ዝውውር የዘገቡትን እንደ አብነት ማውሳት ይቻላል።
የምርመራ ጋዜጠኝነት በውስጣቸው ያቀፉ ቢሆንም ለማብራራት ጋዜጠኝነት በማሳያነትልንጠቀምባቸው እንችላለን።የማብራራት ጋዜጠኝነት የዜናዎችን ትክክለኛ መሆን አለመሆን ከማጣራት ባሻገር በየደቂቃው የሚዥጎደጎደውን ዜና ከተዘገበበት አውድ አንፃር አንባቢ፣ አድማጭ ተመልካችና ተከታይ በቀላሉ እንዲደርሰውና እንዲገነዘበው በማረቂያነት ያግዛል።
በተጨባጭ መረጃና በአሐዝ የበለፀገ የጋዜጠኝነት አይነት ቢሆንም ለእውነት ወግኖ ከመሞገት ወደኋላ እንደማይል፤ ፖሊሲዎችን ከታሪካዊ አውዳቸውና ከአሐዛዊ መረጃዎች ጋር በማዋሐድ እንደሚያፍታታም ይገልፃል፡፡ የኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው (ሲ ጄ አር) ጋዜጠኛ አሌክሳንድሪያ ኔሰን ” In a pandemic, what is essential journalism? ” በሚለው ጽሑፏ፣ የማብራራት ጋዜጠኝነት አሁን እንደምንገኝበት አይነት ክፉ ቀን ሲመጣ ጋዜጠኞች ጠቃሚ መረጃን በማሰራጨት ብቻ ሳይወሰኑ መመሪያ ሰጭ በመሆን ወደ ጋዜጠኝነት ጥንተ መሰረታቸው ይመለሳሉ።አድማጭ ተመልካቹ፣ አንባቢውና የማህበራዊ ድረ ገጾቻቸው ተከታይን፤ ምን ማድረግ ? ምን ማድረግ እንደሌለበት ? መረጃ ዕርዳታ ሲፈልግ ማን ዘንድ መደወል እንዳለበት፣ ምን እንደሚፈልግ፣ የት መሔድ እንዳለበት፣ አቅጣጫ ያመላክታል።በግል፣ በድርጅትና በመንግሥት ሚዲያዎች ስለኮሮና ቫይረስ የሚዘገቡ ዜናዎች ምን ያህል የሚያብራሩ እንደሆነ በእነዚህ አላባውያን አማካኝነት መመዘን እንችላለን፡፡
እንደ መውጫ
በሁሉም የሀገራችን ብዙኃን መገናኛዎችም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች ስለ ኮቪድ 19 እየቀረቡ ያሉ መረጃዎች ወረርሽኙን ለመከላከል በተወሰነ ደረጃ አስተዋጾ እያደረጉ ቢሆንም በሕዝቡ ዘንድ በሚፈለገው ደረጃ ግንዛቤ በመፍጠር የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ላይ ግን ብዙ ይቀራቸዋል ማለት ይቻላል። ስለ ወረርሽኙ የሚቀርቡ መልዕክቶች፣ መረጃዎች ከውጭ ሚዲያዎች እንዳለ ተገልብጠው የሚቀርቡ እና ሾላ በድፍን ስለሆኑ ሕዝቡ በቅጡ እየተረዳቸው አይደለም። መረጃዎች ይበልጥ ግልፅና ቀላል በሆነ ቋንቋ ለአብዛኛው ሕዝብ ተደራሽ መሆን አለባቸው። እያንዳንዷ የመረጃ ቅንጣት ከአድማጭ ተመልካችና አንባቢ የመገንዘብ አቅም አንፃር መቃኘት አለበት።
ደግሞ ደጋግሞ የወረርሽኙን ምንነት፣ የመተላለፊያ መንገድ፣ የመከላከያ ዘዴውን ኢትዮጵያዊ አውድ ሰጥቶ ማብራራት ይጠይቃል። በቅጡ መከላከል ካልተቻለ ወደ ለየለት የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የህልውና ቀውስ ሊከተን እንደሚችል ከተለያየ ማዕዘን አንፃር መብራራት አለበት። አኃዞች ተስፋ መቁረጥንና ሽብርን እንዳያስከትሉ በጥልቀትና በስፋት መተርጎም መተንተን አለባቸው። መረጃዎችን ከአንድ ብሔራዊ ቋት መውጣት ቢቻል መጣረስን፣ መምታታትንና ውዥንብርን መቀነስ ያስችላል። የማብራራት ጋዜጠኝነትን መከተል ፍቱን መድሃኒት የሚሆነው ለዚህ ነው። ከወረርሽኙ ባሻገርም ይህን የጋዜጠኝነት ዘርፍ ከሀገራችን አውድ አኳያ ቃኝተን በቀጣይ ብንጠቀምበት ብዙ እናተርፍበታለን፡፡ ፈጣሪ ሕዝባችንን ከዚህ ወረርሽኝ ይጠብቅልን! አሜን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
” ኮቪድ 19 የሚጠይቀው ጋዜጠኝነት … ! ? “