የ ኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዕረቡ የኮሮና ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) እየተባባሰ መምጣቱን ምክንያት በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጁን አብስሯል። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልገናል?” በሚል በዚሁ ጋዜጣ ከሳምንታት በፊት ያቀረብኩት ሃሳብ እና ሌሎች ወገኖችም በማኀበራዊ ድረገጾች የወሰዱትን ተመሳሳይ አቋም መንግሥት ሰምቶ ተግባራዊ ማድረጉ በግሌ አስደስቶኛል።
ምንም እንኳን አዋጁ በይፋ ከመጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ የወጣ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ጀምሮ አንዳንድ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ነበሩ። እነዚህ መመሪያዎች አስገዳጅ ባለመሆናቸው የመተግበር አቅማቸው በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ የተናገረው ነው። ለአብነት ያህል በቤት ውስጥ የመቆየት ወይንም በተለያየ ምክንያት መሰባሰብ እንዲቀንስ የተሰጠው መመሪያ በአጥጋቢ መልኩ መተግበር አለመቻሉን መጥቀስ ይቻላል።
ጠ/ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ባሰፈሩት ማስታወሻ የሚከተለውን ብለው ነበር። “…የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሮና (ኮቪድ-19) የዓለም ሁለንተናዊ ችግር ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ደረጃ በደረጃ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ፣ የሕክምና ተቋማት እንዲዘጋጁ፣ የመከላከያና የሕክምና መሣሪያዎች ከውጭ እንዲገቡ፣ የማቆያ ሥፍራዎች እንዲዘጋጁ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፤ አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች በቤት እንዲወሰኑ፣ ብዙ ሕዝብ ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎታቸውን ሕዝብ ሊሰበሰብ በማይችልበት መንገድ እንዲከውኑ፣ በአብዛኛው ሥፍራዎች የሕዝብ ትራንስፖርት እንዲቋረጥ፣ ለአስቸጋሪ ጊዜ የሚሆን ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል።…
” የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ማምሻውን በሰጠው ማብራሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገበትን ሁኔታ አብራርቷል። አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተለመደው አሠራርና ሕገመንግሥታዊ ማዕቀፍ የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ በልዩ ሁኔታ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ የተወሰደ ዕርምጃ ነው። አዋጁ ለአምስት ወራት በሥራ ላይ እንደሚቆይ አስታውቋል።
የአዋጁ ፍሬ ነገር፣
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ክልከላዎችን ይዟል የሚለው ብዙዎች ሲጠይቁት የነበረና መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማብራሪያ ምላሽ ያገኛል ተብሎ የተጠበቀ ጥያቄ ነበር። በእርግጥም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምላሽ ሰጥተውበታል። የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችን በተመለከተ በአሁን ሰዓት በግልጽ ተለይቶ የተቀመጠ ነገር አለመኖሩንና በቀጣይ በሚኒስትሮች ም/ቤት በሚወጣ ደንብ የሚደነገግ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
“አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልጉ ክልከላዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተለዋዋጭነት ሊኖራቸው ስለሚችል፣ ይኸን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ በመገምገም እና ስለቫይረሱ ስርጭትም ሆነ ባህሪ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን፣ የህዝብ ጤና ባለሙያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት የመብት እገዳዎችና ዕርምጃዎች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝርዝርና ቋሚ የመብት እገዳዎችን ከመዘርዝር ይልቅ እንደአስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎችና ዕርምጃዎች እንዲደነገግ አዋጁ ሥልጣን ይሰጠዋል።” በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማብራሪያ መሠረት ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ለሚገኘው ፓርላማ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ በሚኒስትሮች ምክርቤት በሚወጣው ደንብ መሠረት ክልከላዎች በዝርዝር እንደሚታወቁ ፍንጭ ይሰጣል። ይኸን ጽሑፍ ሐሙስ ሚያዝያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እያዘጋጀሁ ባለሁበት ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤተ ለዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ተወያይቶ አዋጁን ለማጽደቅ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላትን ለመሰየም ልዩ ስብሰባ መጥራቱን በመገናኛ ብዙሃን ሰምቻለሁኝ።
እንግዲህ የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ የሚኒስትሮች ም/ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት ዝርዝር ክልከላዎቹ ተለይተው እንደሚታወቁ የሚጠበቅ ነው። በእኔ ግምት ደንቡ ምናልባትም የሚኒስትሮች ም/ቤት ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ ቀርቦ ሊያጸድቀው ይችላል። ያም ሆነ ይህ አዋጁን ተከትለው ሊወጡ የሚችሉ ክልከላዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ አሁንም በህብረተሰቡ ውስጥ እየተንሸራሸረ የሚገኝ ነው። መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ከአዋጁ በፊት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል የሃይማኖት እና የፖለቲካ ስብሰባዎችን፣ ግንኙነቶችን ማገድ ይገኝበታል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲህ ዓይነት መሰል ክልከላዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ለመሆናቸው የአስከአሁኑ ዕርምጃ ጠቋሚ ነው። መንግሥት ደጋግሞ እንደገለጸው በቤት ውስጥ መቀመጥ እና ርቀትን ከመጠበቅ አኳያ የተሰጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ አለመሆኑ አሳሳቢ ነው። በዚህም ምክንያት እነዚህን መብቶች የሚገድቡ ድንጋጌዎችን ሊያስቀምጥ የሚችልበት ዕድል ከግምት በላይ ነው።
ቻይና ውጤታማ ከሆነችባቸው መንገዶች አንዱ ዜጎች በቤታቸው እንዲቆዩ እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ መተግበር መቻሏ እንደሆነ ተደጋግሞ የሚጠቀስ ነው። ከዚህ አንጻር አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ጨርሶ የማይቻልባቸው ለአብነት ያህል ገበያዎች (በአዲስአበባ ከተማ እንደመርካቶ ያሉ የመገበያያ ቦታዎች) ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጉ ማድረግን ሊያካትት ይችላል።
በተጨማሪም እንደሠርግ፣ ተዝካር የመሳሰሉ ማህበራዊ መሰባሰቦች እንዲሁም መጠጥ ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች… እንዲሁ በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ ሊከለከሉ ይችላሉ። ሩቅ ሳንሄድ ቀደም ሲል ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በመጋቢት ወር አጋማሽ ትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበሩ የሚታወቅ ነው። የክልሉ መንግሥት ባወጣው በዚሁ የጊዜ አስቸኳይ አዋጅ፤ በትግራይ ክልል ከገጠር ወደ ከተማ፤ ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከከተማ ወደ ከተማ የሚደረጉ ዝውውሮች ከልክሏል።
ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው የገበያ ማዕከላት፣ ሠርግ፣ ተዝካርና መሰል ማኅበራዊ ክንውኖችና የእግር ኳስ ጨዋታዎች ማከናወን ተከልክለዋል። በተጨማሪም የንግድ ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጫት ቤቶች፣የምሽት መዝናኛ ክለቦች እና ሌሎችን ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል። የመንግሥት ሠራተኞችን በተመለከተም ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ ዕድሜያቸው ለጡረታ የተቃረቡ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ተወስኗል።
መንግሥታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎችና ጽሕፈት ቤቶችን በተመለከተ በሚወጡ መርሐ ግብሮች ሥራቸውን የሚያከናውኑ መሆናቸውን በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ወስኗል። በተጨማሪም የቤት አከራዮች የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ፤ተከራዮችንም በግዳጅ ማስወጣት ተከልክለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ባለው አንድ ወር ውስጥ የቤት ኪራይ ዋጋ በግማሽ እንዲቀንስ ተወስኗል። የፌዴራል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ የሚካተቱ ክልከላዎች ይኸ ጹሑፍ እስከተጠናቀረበት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ድረስ ባይታወቅም የትግራይ ክልል ካወጣቸው ክልከላዎች አንዳንዶቹን ሊያካትት እንደሚችል መገመት ስህተት አይሆንም። በተመሳሳይ ሁኔታ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት እንዲሁም ዋሽንግተን እና ፍሎሪዳ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው የሚታወስ ነው። አዋጁ በሕንድም ተተግብሯል። በሕንድ አዋጁን ተከትሎ የባቡር፣ የታክሲ፣ የአየር በረራ አገልግሎቶችን በማገድ በሯን ጥርቅም አድርጋ ዘግታለች። ወሳኝ ከሆኑ ክሊኒኮች፣ ሆስፒታሎች፣መድሃኒት ቤቶች..በስተቀር የንግድ ተቋሞች እንዲዘጉ የወሰነችው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት ነው።
ከአምስት ወራት በኋላስ?
ትልቁና አሳሳቢው ጉዳይ የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ ከአምስት ወራት በኋላ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። ወረርሽኑ መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ሁኔታዎች የሚስተካከሉ ከሆነ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለምንም ተጨማሪ ጊዜ ሊያበቃ ይችላል። ችግሩ ግን መቆጣጠር ሳይቻል በተቃራኒው የመባባስ ሁኔታ ከተከሰተ ምን ይሆናል የሚለው ነው። አሁን የተደነገገው አዋጅ የሚቆየው ለአምስት ወራት ነው ተብሏል።
በዚህ ስሌት መሰረት እስከ መጪው ሐምሌ መጨረሻ ድረስ በሥራ ላይ ይቆያል ማለት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል። ነገርግን አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ፓርላማ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ የአምስት ዓመት የምርጫ ዘመን ቆይታውን ጨርሶ ይበተናል። እናም አዋጁን ማራዘም ቢፈለግ ምን ሊደረግ ይችላል የሚለው አለመታወቁ ያሳስባል።
እንደመቋጫ
ሕገ-መንግሥቱ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲህ ይላል። ሀ/ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው።
ለ/ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ። ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገመንግሥቶች ይወሰናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛው ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ብቻ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል። ሀ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሰረት የሀገርን ሠላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል።
ለ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው። ሐ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገመንግሥት አንቀጽ 1፣ 18፣ 25፣ እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም። (አንቀፅ 93 (4) (ሐ) ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢሆን የማይገደቡ መብቶች የጠቀሰ ሲሆን እነዚህም አንቀፅ 1 (የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ)፣ አንቀፅ 18 (ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ)፣ አንቀፅ 25 (የእኩልነት መብት) እና አንቀፅ 39 (1) (2) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት) ናቸው።
በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ መቋቋም በአዋጁ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦችን ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ የማድረግ ሥልጣንና ተግባር የሚኖረው ነው።
በተጨማሪም በማናቸውም ሁኔታ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ኢ- ሰብዓዊ እንዳይሆኑ የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣንም ይኖረዋል። ማናቸውም ኢ-ሰብዓዊ ዕርምጃ መኖሩን ቦርዱ ሲያምን ለጠ/ሚኒስትሩ፣ ለሚኒስትሮች ም/ቤት እና ለአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ዕርምጃውን እንዲያስተካክል ሃሳብ ይሰጣል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስታከው ኢ- ሰብዓዊ ዕርምጃዎች የሚወስዱ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ መርማሪ ቦርዱ ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ፣ የማሳሰብ መብትም አለው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2012
ፍሬው አበበ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንደምታ