ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች የሚገርመኝ ነገር መጀመሪያ ማሰባቸው ነው። መድኃኒት መሆኑ ከታወቀ በኋላማ ማንም ይጠቀመዋል። ግን ከቅጠሎች (ሥራሥሮች) ሁሉ ለይተው ይሄኛው መድኃኒት ሊሆን ይችላል ብለው ማሰባቸው እና ህመምተኞችን ማዳናቸው ትልቅ ብቃትን የሚጠይቅ ነው። ችግር ብልሃትን ይወልዳል መሆኑ ነው። የባህል መድኃኒት በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ነው።
በዓይን ከሚታየው ቁስል ጀምሮ ለብዙ ውስጣዊና ውጫዊ በሽታዎች ይጠቀሙታል። ለመሆኑ የባህል መድኃኒት ሲባም ምን ማለት ይሆን? ከተለያዩ ድርሳናትና የበይነ መረብ መረጃዎች ያገኘነውን እናካፍላችሁ። «ጉራጌና የባህል እሴቶቹ» በሚል ሰኔ 2004 ዓ.ም የታተመ ጽሑፍ እናስቀድም።
ከዚያ በፊት ግን አንድ ማሳሰቢያ። ይህ የባህል መድኃኒት ነው። ማሳየት የፈለግነውም የማህበረሰቡን ባህልና ጥበብ እንጂ የተጠቀሱት ነገሮች ፍቱን መድኃኒት ናቸው ማለት አይደለም። ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላል። የባህል ሐኪሞችን ወይም ዘመናዊ ሐኪሞችን ሳያማክሩ እንዳይጠቀሙት። አሁን ወደ ጽሑፉ። ባህላዊ መድኃኒት የሚባለው የአንድ ማህበረሰብ በውስጡ ለሚያጋጥሙት የተለያዩ ሕመሞች በባህላዊ መልኩ በማዘጋጀት በፈውስነት ሊጠቀምበት የሚችልበት መድኃኒት ማለት ነው።
ሕዝቦች ያላቸውን ሀገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅመው ቅጠል በመበጠስ፣ ስር በመማስ፤ የተመረጡ ምግቦችን በመመገብ፣ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን በማጀልና በማሸት፣ በመብጣትና በዋግምት በማከም የታመሙ ሰዎችን የሚያድኑበት መድኃኒት ናቸው። በኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻገረ በቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሷል። ህሙማንም ከበሽታቸው እንዲፈወሱና እንዲታደጉ አድርጓቸዋል። ኅብረተሰቡም ለባህላዊ መድኃኒቶችና ለዘርፉ ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ ኖሯል።
እየሰጡም ነው። ለዘመናዊ ሕክምና መስፋፋትም ተጠቃሹ ይኸው የባህልዊ መድኃኒት ነው። ለበርካታ በሽታዎች ፈውስ የሚሆኑ ባህላዊ መድኃኒቶች በየአካባቢው እንደሚገኝ ይታወቃል። ከባህላዊ መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች የባህላዊ ሕክምና አሰጣጥ ዘዴ አንዱ ነው። እንደ ቡድን ሆነው በባህላዊ መድኃኒት ሕክምና ተደራጅተው የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች ባይኖሩም በግል ግን ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ የሚሆን መድኃኒት በመቀመም ሕክምናውን የሚሰጡ ግለሰቦች ይገኛሉ።
ለአብነት ያህል በጉራጌ ወለኔ ወረዳ በግል የባህላዊ መድኃኒት ሕክምና የሚሰጡ ባለሞያዎች በቁጥር ከአራት በላይ ፈቃድ የጠየቁበት ሁኔታ ማስተዋል ይቻላል። ስለዚህ ባህላዊ መድኃኒቶቻችን በሳይንሳዊ መልክ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎ በስፋት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግ አለብን እያልን የጉራጌ ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸውን ባህላዊ መድኃኒቶችን ከነፈውሳቸው ለማየት እንሞክራለን።
- ጭራኩየ (ጫንየ) በአማርኛው ጤና አዳም ሲሆን ቅጠሉም ሆነ ፍሬው ለሆድ መታወክ፣ ለቁርጥማትና ለሌሎች መሰል ሕመሞች መድኃኒት ነው።
- ዳማ (በአማርኛው ዳማከሴ) ለጉንፋን፣ ለመተንፈሻ ቧንቧ ችግርና አጠቃላይ ለምች መድኃኒት ነው።
- የፉጋ አንክ (መርደድየ)፡- በአማርኛ ሬት ሲሆን ቅርፊቱ ተልጦ የሚገኘው የውስጡ ዝልግልግ የማር ወለላ የመሰለው ነገር ከሌላ ምግብ ጋር አዋህዶ በመምታት የከሱ ሕፃናት ቢመግቡት ወዲያውኑ ያፋፋቸዋል። ለቁስል ቢቀቡት ወዲያው የመፈወስ ኃይል አለው። የስኳር በሽተኞችና የደም ግፊት ችግር ያለባቸው ሰዎች አድርቀው ፈጭተው እንደ ሻይ አፍልተው ቢጠጡት የመፈወስ አቅም አለው።
- የጫት ቅርፊት፤ ስጋ በልቶ አልፈጭ ብሎት ሆዱ የታወከ ሰው ወቅጦ ቀቅሎ ቢጠጣው ይድናል።
- አቅምብየ፡- በአማርኛው አርማ ጉሳ አረንጓዴው ቅጠል በማድረቅ ወቅጠው እንደሻይ ለረጅም ጊዜ በመጠጣት የስኳር ህመምተኞች በደማቸው ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ፈጥኖ የማውረድና የመቀነስ አቅም አለው። ቅጠሉን ደግሞ በአረንጓዴነቱ ወቅጠው ጨምቀው ቢጠጡት ከቁርጥማት የመፈወስ ኃይልና የምግብ አፒታይት የመክፈት ኃይል አለው።
6.ቱማ/ነጭ-ሽንኩርት፡-ለደም ዝውውር፣ ለጨጓራ፣ ለውስጥ ካንሰር፣ ለመተንፈሻ አካል፣ ለወሲብ ማነቃቂያነት እና በሰውነት ውስጥ ምግብ እንዲንሸራሸር ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ አባቶች አብነት በመጥቀስ ይናገራሉ። - የኮክ ዛፍ ቅጠል፡- የጋማና የቀንድ ከብቶች በድንገት ሲታመሙም ሆነ ሰዎች በድንገተኛ በሽታ ሲያዙ ከጤና አዳም ጋር ተወቅጦና ተጨምቆ ሲጠጡት ከህመማቸው ይፈወሳሉ።
- አጓጅ በአማርኛ ግራዋ፡- ቀን ተመርጦ 7 ቅጠሉ ተቀንጥሶ በሰው እጅ መድኃኒት ለበላ ሰው ቢያጠጡት የመፈወስ ኃይል አለው።
9.ጨለስ/አባርየ/ሁረታ/፡- የሚባል እንጨት በእርሻ፣ በአጥርና በቤት በር ቢያኖሩት አራሺ/ሰላቢ/ በንብረት ላይ ጥፋት የማድረስ አቅም ያሳጣዋል። - ነጭ አታንክርት(የነጭ ባህርዛፍ ቅጠሉ)፡- ተፈልቶ ቢታጠኑት የመተንፈሻ አካል ችግርም ሆነ የትኛውም የጉንፋን ዓይነት ፈውስ ያገኛል።
- ቀይ ሽንኩርት፡- ለአጠቃላይ ጤንነትና ለደም ዝውውር ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር የዘር ፈሳሽ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች በብዛት ለማመንጨት እንደሚያገለግል አባቶች ይናገራሉ።
12.ዞጓራጋጅ፡- የሚባል ቅጠል በእንጨት የሚጠመጠም ሆኖ እንደ አሚቾ ስር የሚያኮርት ሲሆን ይኸው ስሩ ትክትክ ለያዘቸው ሕፃናትና ወባ ለያዛቸው ሰዎች አገልግሎት እንደሚውል አባቶች ይናገራሉ። - የጣይበተረ/ኦምሮ፡- ሴቶች በወሊድ ወቅት የፈሰሳቸውን ደም ለመተካትና በወር አበባ ጊዜ ተቀቅሎ እንዲጠጡት ይደረጋል። ይህ መድኃኒት የቅጠላቅጠል ዝርያ ሲሆን ለወለደች ሴትና የወር አበባ ያየች ሴት ከአንድ ሣምንት ላላነሰ ጊዜ እየተቀቀለ እንዲጠጡት ይደረጋል። ምክንያቱም ቁርጠትን ይከላከላል፣ሆድ ያጥባል ተብሎ ስለሚታመን ነው። 14. እንስላል፡- ተቀቅሎ ሲጠጣ የተዘጋ የሽንት ትቦ ይከፍታል።
- የፉር ጌተረ፡- ሕፃናት ግግ ሲወጣባቸው ታሽቶ ሲቀባ ያጠፋዋል።
- የምድር እምቧይ ስሩ /አሚቾው/፡- ተወቅጦ የታመሙ ከብቶች እንዲጠጡት ሲደረግ ከብቶቹ ይድናሉ።
- መቅመቆ፡- የተባለ ተክል ስሩ ተወቅጦ እንዲደርቅ በማድረግ ዱቄቱ 2 ወይም 3 በሻይ ማንኪያ በውሃ በማፍላት እንዳሻይ ቢጠጣ የደም ግፊት ይቀንሳል።
- የእንጆሪ ቅጠል፡- በንፅህና ደርቆ ተወቅጦ በሻይ መልክ ተፈልቶ ቢጠጣ የስኳር ህመምን ይቀንሳል።
19.ሺፍ /ሽንፈ/፡- በአማርኛው ፌጦ ለድንገተኛ ህመምና ውጋት ተወቅጦና ተበጥብጦ በመጠጣት ከህመም መፈወስ ይቻላል።
20.ቀበርቾ /ቾሳ/፡- ከስራ ስር ክፍል የሚመደብ ሲሆን አገልግሎቱም ለድንገተኛ ህመም፣ ውጋት ወዘተ በማኘክ የሚወሰድ ፈዋሽ መድኃኒት ነው።
21.ጣዝማ ማር፡- ከመሬት ተቆፍሮ የሚገኝ የማር ዓይነት ሲሆን ከነጭ አዝሙድና ኮረሪማ ጋር በመቀላቀል በማንኪያ ጠዋት ጠዋት ሁለት በመውሰድ ከሳል፣ ከአስም፣ ከቁርጥማት ወዘተ ህመም መገላገል ይቻላል። ይህንን መድኃኒት የወሰደ አንድ ሰው መድኃኒቱ እንዲሠራ ቢያነስ ከአንድ ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ ድረስ ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዳይጠጣ ይመክራል።
22.ሎሚ፡- ለብዙ ዘመናት ከምግብ መመረዝና ተያያዥነት ካላቸው ሌሎች ምክንያቶች የሚከሰት የሆድ በሽታ ለመፈወስ ሲጠቀሙት የቆየ ባህላዊ መድኃኒት ነው።
23.ኑጨ/ልምጭ/፡- ከድንገተኛ ህመም ፈዋሽ ሲሆን የጥርስ መፋቂያ ዓይነትና ለብዙ በሽታዎች ፍቱን መድኃኒት ነው። ከበሽታዎቹም መካከል የአፍንጫ ነስርና ደም መፍሰስ ላለበት ሰው እና በክፉ መንፈስ ለተያዘ ሰው ይህንን ክፉ መንፈስ ለማባረርና ነስሩን ለማስቆም ቅጠሉን በመበጠስና በማሸት ቢያሸቱት ፍቱን መድኃኒት ነው። - እንቆቆና መስመስ፡- ለሆድ ትላትልና መሰል በሽታዎች ተፈጭቶና ተበጥብጦ ከኮሶ ጋር በመደባለቅና በመጠጣት ለኮሶ ትልና መሰል የሆድ ህመም መድኃኒት ነው።
- ቀይ ሽንኩርት፡- ኮረሪማና ቆንዶ በርበሬ፡- እነዚህ በአንድ ላይ ተቀምመው ለራስ ምዕታትና ለሆድ ቁርጠት ፍቱን መድኃኒት ናቸው።
- የጥቁር ገብስ አረቄ፡- የጥቁር ገብስ አረቄ ለአስም በሽታ ጠዋት ጠዋት ሁለት መለኪያ ቢወስዱት በሽታውን ማስታገስ ይቻላል።
27.አልግ፡- አልግ ቅጠሉን በመቀንጠስ /በመበጠስ/ ይወቀጥና በሰፊ ዕቃ በጥብጦ በማሳደር ጠዋት ሰው ሳይንቀሳቀስ እግሩ ያበጠበትና በልክፍት በሽታ የተያዘ ሰው ሲታጠብበት ፈዋሽ መድኃኒት ነው።
28.ሰንሰል፡- ሰንሰል ከሀገር በቀል መድኃኒት ውስጥ የሚካተት ሲሆን ቅጠሉን በመበጠስ ተወቅጦ በሻይ ብርጭቆ አንድ በባዶ ሆድ ሲጠጡበት በወፍ በሽታ ለተጠቃ ሰው ፍቱን መድኃኒት ነው።
29.አግብራ፡- አግብራ ቅጠሉ ተቀቅሎ አንድ የውሃ ብርጭቆ በባዶ ሆድ በመጠጣት በወፍ በሽታ ለተያዘ ሰው ፈዋሽ መድኃኒት ነው።
30.ደንቕንት(የእንሰት ዘር)፡- ከውስጥ አካሉ የሚገኘው ውሃ እና አሚቾው ተቀቅሎ ደጋግሞ መብላት ከወፍ በሽታ ይፈውሳል።
31.አስታራ (የእንሰት ዘር)፡- እንዲመግል የተፈለገ የተጎዳ የሰውነት አካልም ሆነ በሰውነት የወጣ ማንኛውም እባጭ መግል ሆኖ እንዲፈነዳ/እንዲወጣ የእንሰቱ አምቾ ተደጋግሞ ይበላል።
32.ቅብናር (የእንሰት ዘር)፡- የተሰበረ አጥንት በወጌሻ ማጀል ሲያስፈልግ የተሰበረው ቦታ ለማለዘብ (ለማለስለስ) አምቾውን በእርጎ እያማጉ ደጋግሞ መብላት ነው።
33.ጓርየ (የእንሰት ዘር)፡- አሚቾው በእርጎ ወይም በጠቦት ሾርባ ደጋግሞ መብላት የተሰበረን አጥንት ይጠግናል። 34.ደርየ(የእንሰት ዘር)፡- አሚቾው በእርጎ ወይም በጠቦት ሾርባ ደጋግሞ መብላት በመኪናም ሆነ በጦር ሜዳ ስጋው የተቦጨቀ ወይም አጥንቱ ላይ አደገኛ ስብራት ያጋጠመው ቁስሉ እንዲሽር(እንዲጠገን)
35.ኮሶ፡- የደረቀ የኮሶ ዛፍ አበባ ከእንቆቆና መስምስ ወቅጦ በብርጭቆ በመጠጣት የሆድ ውስጥ ጥገኛ ትላትልን ጠራርጎ ማስወጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2012
ዋለልኝ አየለ