ወረርሽኝ ከበሽታው ባልተናነሰ ከበስተጀርባው አስከትሎት የመጣው የሴራ መላምት በዓለም ሀገራት መካከል ዘመናትን የሚሻገር ቁርሾ እና የቀዝቃዛው ጦርነት ነጋሪትን የሚጎስሙ ፕሮፓጋንዳዎችንም ጭምር ነው። ይህ የቃላት ጦርነት ከበይነ-መረቡ አውታርም ተሻግሮ ወደ መደበኛው የመገናኛ ብዙኃን በስፋት ሲሰራጭ እንደነበር ግልጽ ነው።
የአልጀዚራው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሪቻርድ ጊዝበርት ይህንን አስመልክቶ በሳምንታዊው «ዘ ሊስትኒንግ ፖስት» የተሰኘው ፕሮግራሙ የዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያሰራጩትን ዘገባዎች እና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ተዋናይ የነበሩ መንግሥታት በዋናነትም ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በትሩን በእጃቸው የያዙት ኃያላን በየፊናቸው የሚያስተጋቡትን አቋም በመዳሰስ አንድ ግንዛቤ እንድንይዝ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፎ ነበር። ሁለቱን የምድራችን ጉልበተኞች አሜሪካን እና ቻይናን ዋናዎቹ ገፀባህሪያት በማድረግ ትንተናውን ይጀምራል ጋዜጠኛ ሪቻርድ ጊዝበርት።
የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ቻይና የመጀመሪያዋን የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ሪፖርት ካደረገችበት ዕለት ጀምሮ የተቀሰቀሰው እና ለምድራችንም አዲስ ክስተት የሆነው አስከፊው ወረርሽኝ የዓለማችን የዜና አርዕስት መሆኑን ቀጥሏል። ይህ ጽሑፍ እስከተሰናዳበት ሰዓት ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ207 ሀገራት በላይ ያዳረሰው ወረርሽኝ ከሰባ አራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከበሽታው ፈጣን ሥርጭት ጋር በየማህበራዊ ሚዲያው እና በመደበኛው የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት እየተዛመተ ያለው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ወረርሽኝ በቫይረሱ ትክክለኛ ምንጭና አመጣጥ ዙሪያ የተሳሳተ መረጃ በመልቀቅ እና ቀጥሎም ቫይረሱን ለማከም የሚያስችሉ ዕድሎችን የማጨለም ዘመቻዎች ከወረርሽኙ እኩል እንዲዛመቱ የማድረጉ የሴራ ኅልዮት በስፋት ሲስተጋባ ነበር።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተዘጋጀ እና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ይፋ የተደረገው አንድ ጥናት እንዳመለከተው በግርድፉ ሁለት ሚሊዮን ያህል የትዊተር ዘገባዎች በሽታው በሀገረ ቻይና መቀስቀሱ እንደተሰማ ቀጥለው ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት «በሥነሕይወታዊ የጦር መሣሪያ (ባዮሎጂካል ዌፐን አማካይነት የተቀሰቀሰ ነው» ከሚለው ጀምሮ ስለ ቫይረሱ የሚነዙ የሴራ ኅልዮቶች ከአሜሪካ ውጭ ባለው ዓለም በሰፊው ሲራገቡ ቆይተዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶከተር ቴድሮስ አድኃኖም በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ሁለተኛው ወር መግቢያ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት «እኛ እንደ የዓለም የጤና ድርጅት እየተዋጋን ያለነው ከቫይረሱ ጋር ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ የተዛባ መረጃን የሚነዙ የሴራ ኅልዮተኞችንና ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት የሚያደናቅፉ ኢሰብዓውያንን ጭምር ነው» ብለዋል።
ፍርሃት ፣ አሉባልታ እና ጭፍን ጥላቻ ከዓለም የጤና ድርጅት መግለጫ ጋር በተያያዘ አሜሪካን፣ ማሌዥያ እና አውስትራሊያን ጨምሮ ከስምንት አገራት የተውጣጡ ሃያ ሰባት አባላትን ያቀፈ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን በየካቲት ወር ለደብሊው ኤች ኦ በፃፉት ይፋዊ ደብዳቤ እንዳስታወቁት ኮቪድ-19 ተፈጥሯዊ ክስተት ሳይሆን ሰው ሰራሽ የላቦራቶሪ ግኝት ነው…ወዘተረፈ በማለት በቫይረሱ ዙሪያ የሚያሰራጩት የተሳሳተ መረጃ «ይህንን ቫይረስ ለመዋጋት እያደረግን ያለውን ዓለምአቀፍ ትብብር አደጋ ላይ የሚጥል ፍርሃት፣ አሉባልታ እና ጭፍን ጥላቻን ከመፍጠር በስተቀር አንዳች ጥቅም የላቸውም» በማለት ከዚህ አንፃር የሚረጩ የሴራ ፅንሰ-ሀሳባዊ ህፀፆችን በግልጽ አውግዘዋል።
ከዚህ ተነስተን እውነታውን ለማሰላሰል ብንሞክር እንኳ በአንድ በኩል ይኸ ረቂቅ ቫይረስ አዲስና ከዚህ ቀደም በሰው ልጅ የእውቀት ልኬት መሠረት እንግዳ ነገር በአንድ አፍ እየተስማማንበት በፍጥነት ለመዛመቱም ዋነኛው መንስኤ ይኸው አዲስነቱ ነው ማለት በራሱ የሚጣረስ እና የለየለት ቅጥፈት መሆኑን ለመለየት ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም። መሠረታቸውን በደቡብ አፍሪካ እስቴለንቦሽ ያደረጉት ከፍተኛ የሥነሳይንስ ተግባቦት ሊቅና ተመራማሪ ማሪና ጆቤርት እንደሚሉት «እንደዚህ ያለ ወረርሽኝ በሚቀሰቀስበት ወቅት ብዙ እንቆቅልሾች ይፈጠራሉ፤ በተለይም ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው በቂ መልስ ከሌላቸው፣ እና ሳይንቲስቶችም ለተከታዮቻቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ምላሽ እና ማረጋገጫ መስጠት ካልቻሉ ወደ ራሳቸው መላምት ሊገቡ ይችላሉ» ብለዋል ።
«እንዲሁም በጆሮ ገብ የመረዳት አቅማችን ተነስተን ስናየው ሰዎች አካባቢያቸው ለመሰል አደጋ ሲጋለጥ በፍርሃት ስሜት መዋጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነው።
ከወትሮው በተለየ መልኩ ሰዎች የፊት ጭምብል አጥልቀው ሲመለከቱ፤ ከተሞች እና ትላልቅ ጎዳናዎች ወፍ እንኳ ዝር የማይልባቸው ዱር ሲሆኑባቸው ለከባድ ጭንቀት መዳረጋቸው ግድ ነው። ይህ የሰው ልጅ ባህሪ ነው» በማለት ወረርሽኙን ለመግታት በበርካታ የቻይና እና የኢጣሊያን ከተሞች እየታየ ያለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ያክላሉ። በተመሳሳይ በአሜሪካ የምሥራቅ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሬ ካታ የተባሉ ምሁር በበኩላቸው በ COVID-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የሚነሱት የተንኮል ቲዎሪዎች «የትርክት አቀራረብ» ከዚህ ቀደም በታሪክ ካጋጠመን ወረርሽኝ ጋር ተመሳሳይ ናቸው ብለዋል። እንደርሳቸው ትንተና ባሳለፍነው ምዕተ-ዓመት ካጋጠሙን እንደ ኤች.አይ.ቪ ወይም ኤች.ዋን.ኤን.ዋን ያሉ ወረርሽኞች ዙሪያም በባዮኢንጂኒየሪንግ፣ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማጥፋት ከሚሸረብ ሴራ አልያም ከአመጋገብ እና ከንፅህና አጠባበቅ ልማድ ጋር የተገናኘ ነው ከሚል የሻጥር ፖለቲካ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሴራ ያላቸው ንድፎች ነበሩ ብለዋል፡፡
አንዲት ቻይናዊ እንስት ከሌሊት ወፍ የተዘጋጀን ሾርባ ስትመገብ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በሰፊው ሲሰራጭ እና በኋላም ንብረትነቱ የራሺያ መንግሥት የሆነው እንደ አር.ቲ. እንዲሁም የእንግሊዙ ዴይሊ ሜይል ያሉ የሜይንስትሪም ሚዲያዎች ጭምር ተቀባብለው በስፋት ሽፋን መስጠታቸውን ተከትሎ የተሰራጨው የሻጥር ፅንሰሀሳብ የቫይረሱን አመጣጥ በቀጥታ ከቪዲዮው ጋር አገናኘ። ነገርግን ይህ የቪዲዮ ክሊፕ በኋላ ላይ ሲጣራ ወቅቱም ከአራት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. በ2016 በኢንዶኔዥያ ውስጥ ተመሳሳይ ሾርባ የሚመገብ ሌላ ታዋቂ ቻይናዊ ቪሎገርን የሚያሳይ እንጂ እንደተባለው ከኮቪድ ጋር በምንም የሚገናኝ አለመሆኑ ተረጋገጠ። ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሌሊት ወፎች የአዲሱ ቫይረስ ተሸካሚ እንደሆኑ ያምናሉ። ቫይረሱ በሌላ እንስሳ ተሸካሚነት አማካኝነት ወደ ሰዎች ሊተላለፍ እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
እንግዲህ የሌሊት ወፏ ሾርባ ጉዳይ ወረርሽኙን በቀጥታ ከቻይናውያን ባህላዊ አመጋገብ ጋር ለማያያዝ ከተረጩት የሴራ ዘገባዎች መካከል አንዱና የሰዎችን ማህበራዊ ማንነት መሠረት አድርጎ የዘረኝነት ጥላቻን ለመስበክ የተዘራ ሀሜት ነው። ከተከሰቱት አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች መካከል ቻይናውያን ‘ቆሻሻ’ እና ያልተለመዱ ነገሮችን የሚመገቡ ሕዝቦች ናቸው የሚለው ነው። እኛ የሰው ልጅ የምንባል ፍጡራን በአንድ ጉዳይ ዙሪያ የምንፈልገውን በቂ መረጃ ሳናገኝ ስንቀር ወደ ግምታዊ ስሌት ለመግባት እንገፋፋለን። ነገርግን እንደ አለመታደል ሆኖ የእኛ ዘረኝነት እና የአድልዎ ካንሰራችንም የሚጀምረው ከዚሁ በመነሳት ነው። ወደ ጨዋታ መጫወት ይጀምራል።
ይህንን የምናደርገው የተሻለ ደህንነት እንዲሰማን ከማሰብ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእውነቱ ከሆነ የዚህ ዓይነት አካሄድ በመሠረታዊነት ችግር ያለበት እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ይህን የመሰሉ ወቀሳዎች እና የአሽሙር አካሄዶች አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና እንደ ጣሊያን እና ዩክሬን ባሉ ሀገራት በቻይናውያን ዜጎች እና በእስያ ተወላጆች ላይ ከሚሰነዘሩ ጥቃትና መድልዎ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎችን እያስጨነቃቸው ያለው ነገር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ ያለው የተሳሳተ መረጃና የሴራ ትርክት ብቻ ሳይሆን ይኸው ውንጀላ ወደ ዋናው ሚዲያም ቀስበቀስ እየተዛመተ መምጣቱ ነው።
በዚህ ረገድ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሩሲያ እና አሜሪካን በአብነት የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህንኑ ሃሳብ ይበልጥ ማጠናከር ያስችለን ዘንድ በበሽታው ወረርሽኝ የመጀመሪያ ቀናት አካባቢ አል-ወጠን በተሰኘው ታዋቂው የሳዑዲ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ በየካቲት 2 እንደገለጹት አዲሱ ኮሮናቫይረስ በምዕራባውያን የመድኃኒት ኩባንያዎች ለቫይረሱ የሚውሉ ክትባቶችን በመሸጥ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አካል ነው ብለው ነበር። ሌላኛው የሶሪያ አል-ሰውራ ዕለታዊ ጋዜጣ አምደኛ ደግሞ በየካቲት 3 2020 እንደፃፉት ቫይረሱ የአሜሪካ መንግሥት በቻይና ላይ የከፈተው ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ጦርነት አካል እንደሆነ ያትታል። ተመሳሳይ የውንጀላ ዘገባዎች እንዲሁ የሩሲያ መንግሥት ንብረት በሆነው ቻናል ዋን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ተላልፏል።
በተጨማሪም በየካቲት 5/2020 ዕለት በዚሁ ጣቢያ ላይ በተላለፈ ዘገባ አንድ የዜና አቅራቢ መወገዝ ያለበት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነው። ምክንያቱም ኮሮና የሚለውን ቃልና ትርጉሙም በራሺይኛ ቋንቋ ዘውድ ማለት ሆኖ ሳለ እርሳቸው ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በማያያዝ ለወረርሽኙ ሩሲያን ጥፋተኛ በማድረግ የሴራ ፕሮፓጋንዳ ከፍቶብናል በማለት ጠቁሟል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ወግ አጥባቂ የቀኝ ክንፍ ሚዲያዎች የየራሳቸውን የሴራ ፅንሰ-ሀሳቦችን ሰርተዋል። ለምሳሌ ያክል ዋሽንግተን ታይምስ የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 24 እትሙ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ከቻይናው «ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያ ፕሮግራም» ጋር በተገናኘ ላብራቶሪ የተፈበረከ ሊሆን ይችላል በማለት አስነብቧል።
በኋላም ይህንኑ ፅንሰ-ሃሳብ በመደገፍ የሪፑብሊካኑ ሴኔተር ቶም ኮተንም አስተጋብተውታል። ሩሽ ሊምቦ የተባለው ሌላኛው ወግ አጥባቂ የሬዲዮ አዘጋጅም በበኩሉ «ኮሮናቫይረስ ፕሬዚዳንት ትራምፕን እንደገና ከሥልጣን ለማውረድ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ሌላኛው መሣሪያ ነው» ብሏል፡፡ አንዳንድ ተንታኞች እንዳሉትም ጂኦፖሊቲክስ በተስራጨው የተሳሳተ የመረጃ ዓይነት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የታይላንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና ባንኮክ የሚገኘው የሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ቲቲናን ፓንሻሺሻክ የተባሉ የታይ የፖለቲካ ሳይንቲስት እና የሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ደህንነት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ቲታኒን ፖንግሱዲራክ በበኩላቸው «ቫይረሱ በጣም ትልቅ ባልሆነ ሀገር ውስጥ የተገኘ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ይህን ያህል ባልተራገበ ፣ባልተካበደ ነበር» ብለዋል። ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ተቀናቃኝነት እና የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶችን ጨምሮ ከብዙ ሀገራት ጋር በበርካታ ጉዳዮች ትገኛለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተሰሚነት አላት። በተጨማሪ የቻይና ቱሪስቶች ለበርካታ የኤሺያ ሀገራት ቁጥር አንድ የገቢ ምንጭ ናቸው።
ይህ ሁሉ ግን ወረርሽኙ በሚዘገብበት አግባብ ላይ የራሱ የሆነ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡
የሌሊት ወፍ ሾርባ እና የባዮኢንጂኒየሪንግ ሥራ’ ቀደም ሲል በኮቪድ ዙሪያ ያለውን የሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የዓለም ጤና ድርጅት «የመረጃ ወረርሽኝ» ብሎ ከገለጸው በኋላ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ዩቲዩብ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች የCOVID-19 ወረርሽኝን በተመለከተ የሚራገቡ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመዋጋት የተወሰኑ እርምጃዎችን ወስደዋል። እነዚህ ድርጅቶች ስለ ኮሮና ቫይረስ መረጃ ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎችን እንደ ደብሊው.ኤች.ኦ. ወዳሉ ተዓማኒ የመረጃ ምንጮች የሚመሯቸው እርምጃዎችን እንዳወጁ አስታውቀዋል።
ነገር ግን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የበለጠ መሥራት አለባቸው ሲሉ በዩናይትድ ስቴትስ የማሳቹሴትስ አምሃርስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዲጂታል ሚዲያ ባልደረባ ፕሮፌሰር ዮናታን ኮርፖስ ኦንግ ተናግረዋል። እኛ ከዚህ ቀደም በዓለማችን ከተከሰቱ እንደ ‹SARS› ወይም «ስዋይን ፍሉ (የአሳማ ጉንፋን)» ካሉ ወረርሽኞች በተለየ ጊዜ ውስጥ ሆነን ከዚህኛው ወረርሽኝ ጋር እየታገልን ነን ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የተዛቡ የጤና መረጃዎች እና አጋጋይ የሆኑ ስውር ዜናዎች በበይነመረብ አውታሮች ዙሪያ በሰፊው እያደጉ መምጣት ችለዋል። ብዙ ወሬ በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት ይህ ወረርሽኝ አጋጥሞናል።
በተጨማሪም ብዙ የተለያዩ ምርቶችን ለማስተዋወቅ እየሞከሩ ያሉ ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዎች አሉ። ይህን ለመጋፈጥ እና ለመዋጋት በጣም ከባድ ነው።
የሴራ ፕሮፓጋንዳን ለመዋጋት ከተፈለገ በቅድሚያ እነዚሁ ቅጥፈቶች የባሰ እሳት ለማቀጣጠላቸው በፊት ከአውታሮቹ እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ስለ የሌሊት ወፏ ሾርባ እና ባዮኢንጂነሪንግ ዙሪያ የቀረበው የሀሰት መከራከሪያ አሁንም ድረስ በየማህበራዊ ሚዲያው ፕላትፎርም እየተሰራጩ ይገኛሉ። እንዲሁም ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የምንጣጣረውን ያክል ሀሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ከአውታሮቹ ማውረድ ላይ በቂ ትኩረት አልተደረገም፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ሐሚልተን አብዱልአዚዝ