ክፍል ሁለት
አፍሪካና ኮሮና
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ
አሻም፣
ጤና ይስጥልኝ?
ከቤት ናችሁም አይደል? አደራ ከዚያው ሁኑ እንዳትወጡ። ከመጣብን መዓት እና የአምላክ ቁጣ ብቸኛው ፈውስ ከቤታችን ሁነን የፈጣሪን ምህረት መማፀን ነው። ግዴለም ይህም ያልፍና አንድ ቀን ስለዚህም እናወጋለን። ብቻ ፈጣሪ ይታረቀን። የታመሙትን በቶሎ ያሽርልን።
የሞቱትንም ነፍሳቸውን በአፀደ ገነቱ ያኑርልን። ባለፈው ሳምንት ኮሮናላይዜሽን በሚል ርዕስርዕስ ባዘጋጀሁት ፅሁፍ ክፍል አንዱን ማቅረቤ ይታወሳል። እነሆ ክፍል ሁለቱን በቀጣይ ይዤ ለመቅረብ ቃል በገባሁት መሰረት ለዛሬ በዋናነት ወረርሽኙ ከአህጉራችን አፍሪካ አንፃር ያለውን አንድምታ ከዚህም ከዚያም በመቃረም ያሰናዳሁትን እንደሚከተለው ከአዲስ ዘመን ገበታ አኑሬዋለሁ። ጠጋ ብላችሁ እንድትቋደሱ ደግሞ ግብዣዬ ነው።
ክልከላው በአካል ተጠጋግቶ ከአንድ ገበታ መብላቱ ላይ እንጂ የአዲስ ዘመን አገልግልን የሚመለከት አይደለም። እያነበባችሁ፣ በእጅ ስልክዎትም ሆነ ኮምፒዩተርዎን በመጠቀም ከማንበብዎ በፊትም በኋላም እጅዎን በሳሙና መታጠብን እንዳይዘነጉ አደራ አደራ ለማለት እንወዳለን። “
አፍሪካ ይህንን ወረርሽኝ በራሷ አቅም ብቻ ልትወጣው አትችልም። እናም ሳይረፍድ በጊዜው መሰናዳት ያሻል” ይለናል የእንግሊዙ “ዘ ጋርዲያን” ጋዜጣ አርታኢ ላሪ ኤሊዮት። አህጉሪቱ በወረርሽኙ ለመዋጥ ከአውሮጳ በኋላ የጥቂት ሳምንታት እድሜ ብቻ ነው ያላት። በቫይረሱ ክፉኛ እየተገረፉ ያሉት የበለፀጉት ሀገራት የቫይረሱን ሥርጭት አሁኑኑ ካላስቆሙት ሁላችንም ተያይዘን መጥፋታችን ነው። በአንድ መርከብ ላይ የተሳፈርን የህይወት ተጓዦች መሆናችንን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
ከዛሬ አስራ አምስት ዓመታት በፊት የተወሰኑ የሀብታም ሀገራት መሪዎችን ያካተተ ቡድን ለዓመታዊ ስብሰባቸው በስኮትላንድ ፐርዝሻየር ተሰባስበው ነበር። በጉባኤው ላይ በርከት ያሉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም በተጋባዥነት ታድመዋል። በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይም አንድ ስምምነት ላይ ተደረሰ። የስምምነቱ ጭብጥም የምዕራቡ ዓለም ኃያላን ለድሃ ሀገራት የብድር እዳ ስረዛ እና እርዳታ እንዲያደርጉ፤ አፍሪካውያን ደግሞ በምትኩ መልካም አስተዳደርን እንዲያረጋግጡ የሚያስገድድ ነበር።
ይህ የግሌንኢግልስ ስምምነት በራሱ የተዋጣለት ነው ባይባልም ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አንድ እርከን ከፍ ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል። ታዲያ ዛሬ ላይ ሆነን ትላልቆቹ የበለፀጉት ሃገራት የኮቪድ-19ን ዓለምአቀፋዊ ወረርሽኝ በጋራ ለመግታት እርስበርሳቸው እንኳ መስማማት ተስኗቸው ስናይ የግሌንኢግልሱ ስምምነት ከአንድ አስራ አመት ተኩል በላይም ብዙ የቆየ መስሎ ሊታየን ይችላል። በበለፀጉት ሀገራት ኢኮኖሚ ውስጥ እንደማነቃቂያ የተረጨውን የገንዘብ መጠንና ዝቀተኛ ገቢ ባላቸው የሰብ ሰሃራ አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው ንፅፅር የትየለሌ ነው። በቅርቡ የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ኮንግረስ የሁለት ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት ውሳኔ ማፅደቁን እናስታውሳለን።
ዩናይትድ ኪንግደምም ከሁለት ሳምንታት በፊት አራት ትላልቅ የበጀት አዋጆችን ማስተላለፉንም እንዲሁ አስታውቋል። የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ የፋይናንስ ማነቃቂያ የሚለውን ነገር ወዲያ በመጣል በምትኩ “ብቻ የሆነው ይሁን” የሚል አቀራረብ ለመከተል አቋም ወስዷል።
በአንፃሩ ደግሞ አፍሪካ የታሪክ ጠባሳዋን የምትፍቅበት እድል እያገኘች ያለች ይመስላል። የዓለም ባንክ የአስራ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት፤ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ደግሞ ለደሃ ሀገራት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል የአስር ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን አስታውቀዋል።
የሁለቱ ዓለምአቀፍ ተቋማት መሪዎች አበዳሪ ሀገራት የብድሮቻቸው መክፈያ ጊዜንእንዲያራዝሙ እና ድሃዎቹ ሀገራት ደግሞ የፋይናንስ አቅሞቻቸውን ከወቅቱ ችግር አኳያ በይበልጥ በጤናው ዘርፍ ላይ እንዱያውሉት የማግባባት ዘመቻ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ነገር ግን ይህ እርምጃ የበለፀጉት ሀገራት በራሳቸው አጀንዳ ዙሪያ እያከናወኑ ካሉት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተራራቀ ነው።
ዓለም ባንክና አይኤምኤፍም አሁን እየወሰዱ ያሉት “የመፍትሔ ሃሳብ” በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2008 ዓ.ም ለደረሰባቸው የፋይናንስ ቀውስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ያ ደግሞ ለአሁናዊው በሽታ ፈፅሞ ማርከሻ መድኃኒት ሊሆን አይችልም። ይባሱኑ ለድሃዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ይህ የውሳኔ ማዕቀፍ እጅግ የከፋ አደጋ ይዞባቸው የሚመጣ ሌላ ወረርሽኝ ነው። በርግጥም አደጋው ለአፍሪካ ብቻም ሳይሆን ለበለፀገው ዓለምም ጭምር ነው። አሁን ባለንበት ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያለው ሥርጭት በአንፃራዊነት ሲታይ ዝቅተኛ ሊባል የሚችል እና አብዛኞቹ ሀገራት በሀገር ቤት ካለው ሥርጭት ይልቅ ከውጭ የሚገቡ የቫይረሱ ተጠቂ መረጃዎችን ብቻ ሪፖርት በማድረግ ላይ ነው ያተኮሩት። ይህ ደግሞ የተዳፈነ እሳት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ አደጋውን አቃሎ ወደ ማየት እየወሰደን ነው።
በተለምዶ አፍሪካ እጅግ ሞቃታማ የአየር ጠባይ ስላላት ቫይረሱ እንዳሻው ለመራባትም ሆነ ለመዛመት አስቸጋሪ ይሆንበታል። በዚያ ላይ ደግሞ አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ስለሆነ ልክ በጣሊያን እንደታየው አይነት በእድሜ የገፉ ሰዎች ያሉበት ሀገር የሞት ምጥጥን ሳይከሰት ወረርሽኙን ሊቋቋመው ይችላል የሚል ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው መላ ምትም በሰፊው እየተነገረ ይገኛል። ይሁንና ሁለቱም መከራከሪያ ሃሳቦች ውሃ የሚቋጥሩ አይሆኑም።
ሰሞኑን በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የተከሰተውን የቫይረሱ ተጠቂዎችን ያየነው እንደሆነ ኮቪድ-19 በሞቃታማ የአየር ንብረት ውስጥም መሰራጨት እንደሚችል በቂ ማሰረጃ ነው፤ በአፍሪካ ያለው የእድሜ ለጋነት በአውሮፓ እንዳለው የተሻለ የጤና ሁኔታ ጋር የሚስተካከል አይደለም።
የወባ በሽታ እና የምግብ እጥረት በእያንዳንዱ አፍሪካውያን ቤት በሽበሽ ነው። የኮሮና ቫይረስ ከሳምባ በሽታ ጋር ሲዛመድ በጣም ገዳይ ይሆናል። በኒሞኒያ ሳቢያ በየዓመቱ አራት መቶ ሺሕ ህፃናት ይሞታሉ። የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ ግልጽ ናቸው። በየእለቱ በቫይረሱ እየተጠቁ ያሉ አፍሪካውያን ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። ምናልባትም አፍሪካ ቀጣይዋ አውሮፓ እንደምትሆን መረዳት ይቻላል። መሰረታዊ የጤና አገልግሎት መሰረተ ልማትን ያየን እንደሆነ ደግሞ አደጋው ከአውሮፓም በእጅጉ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ለአብነት ያክል እንግሊዝ የኮቪድ 19ን በሽታ ከመግታት ረገድ 7000 ጽኑ ህሙማንን ማስተናገድ የሚችል አልጋ ስታዘጋጅ ከሰሃራ በታች ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት በአማካይ ለሃምሳ የጽኑ ህሙማን የሚውል አልጋ ቢኖራቸው ነው እንደ ሴቭ ዘ ቺልድረኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬሺን ዋትኪንስ።
አፍሪካ ውስጥ በጤና መሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድ ሳንባን የሚተካው የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንቲሌተር) ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መሠረታዊ የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ኦክስጅን ሳይቀር ከፍተኛ እጥረት አለ። አፍሪካ ለእንደዚህ አይነቱ የማህበረሰብ ጤና ቀውስ መቋቋም የሚያስችላት አቅም የላትም። ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አደጋውን ለመግታት ከጊዜ ጋር የምታደርገው ትንቅንቅ ደግሞ በእጅጉ አይሏል።
ብቻ የሆነው ሆኖ በቀጣይ አፍሪካ ውስጥ የሚከሰተው አደጋ ተወደደም ተጠላ በድፍን ዓለም ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ሀቅ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት በሽታው ከውጭ ሀገር ነው የመጣብን በሚል ደካማ ማላከኪያ ህዝቦቻቸውን በእሳት ለመማገድ ችግሩን ወደ ውጭ ከማሳበብ በዘለለ በተጨባጭ የየሀገራቸውን ውስጣዊ አደጋ ማዕከል ያደረገ የመከላከል ስራ በመሰራት ረገድ ያላቸው አፈፃፀም እጅግ ደካማ ነው። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ ደግሞ የምርመራ ተግባር በፍጥነት እና በስፋት ሊከናወን ግድ ይላል።
በአንፃራዊነት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው እስካሁን የተመዘገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎችን መለየትና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሌሎች ግለሰቦችንም የማጣራት ስራም አብሮ ሊሰራ ይገባል። በተቻለ ፍጥነት እና መጠን የምርመራ መሳሪያዎችን፣ የሰው ኃይል እና የኦክስጅን እጥረት ችግሮችን ከወዲሁ መቅረፍ አማራጭ የሌለው ነገር ነው። ይህን እንበል እንጂ የዓለማችን ድሃዋ ምድር የሆነችው ማማ አፍሪካ ይህንን ሁሉ በራሷ ልትፈጽም የምትችልበት እድል በጣም የጠበበ ነው።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ግዙፎቹ የዓለማችን የገበያ መዳረሻ የሆኑት ቻይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና ዩሮዞን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሶስቱም በተመሳሳይ በአንድ ጊዜ ለኢኮኖሚ ቀውስ መዳረጋቸውን ተከትሎ ኤክስፖርታቸው መውደቅ ጀምሯል። አብዛኞቻቸው ቀድሞውኑ በከፍተኛ እዳ እየተንገራገጩ ይገኛሉ። ይህ የሀብታም ሀገራትን የሚያስጨንቅ ችግር አይደለም።
ሌላው አሁን ለገጠማቸው ቀውስ የሚሆን ገንዘብ መበደር ቢፈልጉ እንኳ ለጤና ሴክተር ኢንቨስትመንትየሚውል ብድር የሚገኝበት እድል ዝግ ነው። በምዕራቡ ዓለም ሀገራት እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ የወለድ ምጣኔ መበደር የሚችሉበት እድል አላቸው። ለእንደኛ አይነቱ በውዝፍ እዳ ለተዘፈቀ አህጉር ግን ሰዎቹ ብድሩን በከፍተኛ የወለድ መጠን (አፍ አውጥተው አንሰጥም ላለማለት ስላለፈው ብድር መቀጣጫ በሚመስል እና በየጊዜው እየናረ በሚሄድ) ነው ሊያበድሩን የሚፈልጉት።
ስለዚህ ምንድን ነው የሚበጀን? አንደኛ ነገር እኒህ ከበርቴ ሀገራት ይህ አግጦ የመጣው የአፍሪካ ቀውስ ሳይውል ሳያድር ለእነርሱም የሚተርፍ አደጋ እንደሆነ ያለምንም ማቅማማት ማመን አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ እንዳሁኑ አይነት ከችግሩ ምንጭ ጋር ያልተጣጣመ የግብር ይውጣ አይነት የፈንድ ቃል መግባቶች ሳይሆን የተቀናጀ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ረገድ የዓለም የጤና ድርጅት አፍሪካ ያሉባትን ክፍተቶች በመለየት እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ሊደግፉን የሚችሉበትን ቴክኒካል ሃሳብ እና የአሰራር ማእቀፍ በመቅረጽ ሊያቀርብላቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ድጋፉና ድጋፍ የፈለግንበት ዘርፍም ይገናኛሉ። አለበለዚያ ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው። ልክ ሀገሬው እንደሚለው ከጉልበቱ የተሰበረን ሰው ትከሻውን እንደማሸት ማለት ነው። ይህ አፍሪካውያን መሪዎች ቆራጥ አቋም እና ያልተቋረጠ ጥረት እንዲያደርጉ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አፍሪካን ወክለው የእዳ ስረዛ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሳላደንቅ አላልፍም። እንዲህ አይነት ድምፆች ናቸው የሚያስፈልገን።
እስካሁን ያለው የድጋፍ መንፈስ የሚበረታታ ሆኖ ነገር ግን ከችግሩ ጥልቀትና አሳሳቢነት አኳያ ገና ብዙ መሰራት እንዳለበት ያሳያል። የዓለም ባንክ ቃል የገባውን እርዳታ ለማቅረብ በቅድሚያ ለስላሳ ብድሮችን እና እርዳታዎችን መለገስ ይጠበቅበታል። አይኤምኤፍም በበኩሉ ይህንን ከታዳጊ ሀገራት የሚነሳውን ከፍተኛ የካፒታል ፍሰት በሚገባ ምላሽ ለመስጠት ከዚሁ ጋር የሚጣጣም አዳዲስ የተጠቃሚነት ማዕቀፎችንም አብሮ መቀየስ ይኖርበታል። ይህም በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የካፒታል መጠን በማሳደግ እና ለአባል ሀገራት ደግሞ ካልተጠበቀ አደጋ መከላከል የሚያስችል ተቀማጭ ሀብት መፍጠሪያ መንገድም ጭምር ማለት ነው።
እናም የዓለም ባንክና አይኤምኤፍም በየሳምንቱ ይፋ ከሚደረግ ውሱን የብድር ፓኬጅ ሳይሆን የጋራ የሆነ አጠቃላይ የእዳ እፎይታ እቅድ ሊኖራቸው ይገባል። ይህም ለቻይና ዕዳ የተሰበሰበውን ከፍተኛ ገንዘብ ጨምሮ ለሁሉም መንግስታት ዕዳዎችን እና ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ የተቀበሉትን ገንዘብ መመለስን ያካትታል። እንዲሁም የግል ባለሀብቶች ከፍተኛ ብድር ያለባቸውን አገራት እያፈላለጉ እንዳያድኗቸው ለመከላከልም ጭምር እርምጃዎች ያስፈልጋሉ።
የሆነው ሆኖ ዋናው ነገር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን አሁን ለተከሰተው ለጤና ቀውስ ለማዘጋጀት አነስተኛውን የዕድል መስኮት መጠቀም ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር የበጀት ምላሹ የጤና ሥርዓቶችን ማጠናከርና በጥሬ ገንዘብ ለሚፈልጓቸው ሀብቶች ላይ ማነጣጠርን ያካትታል። አሁን ላይ አፍሪካ በሄሊኮፕተር ከሚወረወርላት የገንዘብ ፍርፋሪ በላይ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በድጋሚ እንዲረጋገጥ ትፈልጋለች።
እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ነገር ቢኖር የገንዘብ እርዳታው በፍጥነት አሁኑኑ መድረስ አለበት የሚለው ነው። ያለበለዚያ ዓለም ወደ ጥፋት እያመራች መሆኗ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ውድ አንባቢያን ዛሬም አልጨረስኩም። የኮሮና ጉዳይ መች እንዲህ እንደዋዛ ይላቀቀንና! ክፍል ሶስትን እና ቫይረሱ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ምን አንድምታ ይኖረዋል የሚለውን ደግሞ በክፍል ሶስት ይዤ ለመቅረብ ዳግም ቃል እየገባሁ እለያችኋለው። ችርቻሮ ሰንብቱልኝማ የተለመደውን አስተያየታችሁን ደግሞ እጃችሁን ታጥባችሁ በሰም በታሸገ ኤንቨሎፕ ከግርጌው ባኖርኩት አድራሻዬ ትሰዱልኝ ዘንድ እማጠናለሁ!
ስልክ: +251 964 113111
ኢሜይል : hamileekoo@gmail.com
ሐሚልተን አብዱልአዚዝ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2012