በገብረክርስቶስ
የባልንጀራዬ ሰርግና የሥነ-ሥርዓቱ መሰረዝ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን! ባልንጀራዬ በመጪው ወርሃ-ሚያዚያ የሶስት ጉልቻን ኑሮ ሊጀምር፣ ጎጆ ሊቀልስ ደፋ ቀና ይል ይዟል። የጋብቻ ሥነ-ሥርዓቱንም በመዲናችን በሚገኝ አንድ ሆቴል “ድል ባለ ድግስ” ለማድረግ ነበር ያሰበው። በዚሁ መሰረት ታዲያ ከድግስና ከመስተንግዶ ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች በተመለከተ ከሆቴሉ ጋር ውል ካሰረ ሰነባብቷል። ቅድሚያ ክፍያም ለሆቴሉ ከፍሏል።
ታዲያ ምን ዋጋ አለው በዚህ መሃል መላውን የሰው ዘር ስጋት ውስጥ የጨመረው የኮሮና ቫይረስ አገራችንንም በከባድ ስጋት ውስጥ ጣላት። የበሽታውን መስፋፋት ተከትሎም መንግስት የሰዎችን ዝውውርና መሰባሰብን ከማገድ ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል ርምጃዎችን ወስዷል። ባልንጀራዬም ለሆቴሉ የጽሁፍ ማስታወቂያ ያደርሰዋል።
በማስታወቂያውም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መንግስት በወሰዳቸው የጥንቃቄ ርምጃዎች ምክንያት የሕዝብ ዝውውርም ሆነ መሰባሰብ በመከልከሉ ምክንያት ይህም የሰርጉ ሥነ-ሥርዓት እንደውሉ እንዳይፈጸም የሚያደርግ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት በመሆኑ የሰርጉን ሥነ-ሥርዓት በሆቴሉ ውስጥ እንደማያከናውንና የከፈለውንም ቅድሚያ ክፍያ እንዲመልስለት ነበር ለሆቴሉ ማስጠንቀቂያ የጻፈለት።
ይሁንና ሆቴሉ ችግሩ መንግስት ክልከላ በማስቀመጡ ምክንያት የተከሰተ እንጂ የእሱ ጥፋት እንዳልሆነ በመግለጽ ቅድሚያ ክፍያውን ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆኑን፤ እንዲያውም ኪሳራም እንደሚጠይቅ ይገልጻል። በዚህም በመካከላቸው የተወሰነ አለመግባባት ይፈጠራል። በመጨረሻም ሆቴሉ ከሕግ ባለሙያ ጋር መክሮ ውጤቱን እንደሚያስታውቅ፤ ለዚህም የተወሰነ ጊዜ እንደሚፈልግ በገለጸው መሰረት ግራ ቀኙ ተስማምተው ተለያይተዋል። በአሁኑ ወቅት በእኔ ባልንጀራና በሆቴሉ የውል ግንኙነት ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ በሌሎችም የውል ግንኙነቶች ውስጥ እንደሚከሰት ጥርጥር የለም። እናም ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገር አማን የተደረጉ ውሎች በአብዛኛው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አፈጻጸማቸው ስጋት ውስጥ ወድቋል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በተዋዋይ ወገኖች መካከል አለመግባባትን እንደሚፈጥር እሙን ነው። ባስ ሲልም በርካቶችን ወደ ሙግት መግፋቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም አለመግባባትን ለማስወገድና ሙግቶችን ለማስቀረት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የህግ ግንዛቤ ማስጨበጡ ወሳኝነት አለው። እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም በዚሁ የሕግ አምዳችን የጉዳት ኪሳራ አጠያየቅን አስመልክቶ ባሰናዳነው ጽሁፍ ጉዳዩን በተወሰነ መልኩ መመልከታችን ይታወሳል።
ይሁንና አሁን ካለንበት ወቅት በመነሳት በኮሮና ምክንያት የአፈጻጸማቸው ነገር ስጋት ውስጥ የወደቁ ውሎችን ዕጣ ፋንታ አስመልክቶ ሰፊ የግንዛቤ ስንቅ ማስቋጠር ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው በዚህ ጽሁፋችን ከጉዳት ኪሳራ ጋር በተለይም ውልን ላለመፈጸም ከአቅም በላይ ናቸው ከሚሰኙ ሕጋዊ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ለማቅረብ የወደድነው።
የጉዳት ኪሳራ
የጉዳት ኪሳራ (Compensation for Damage) ከውልም ሆነ ከውል ውጭ በሚመጣ አላፊነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። ይኸውም በአንድ ሰው ጥቅም ላይ የሚደርስን በደል ለማካካስ ሲባል በጉዳት አድራሹ ትከሻ ላይ የሚጣል ግዴታ ነው። ኪሳራውም በተጎጂው ላይ የሚደርሰውን ቁሳዊ (የማቴሪያል) ወይም ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን የሕሊና (የሞራል) ጉዳትንም እንደሚያጠቃልል የፍትሐብሔር የሕገ-ፍልስፍና ልሂቃን ያስረዳሉ።
የጉዳት ኪሳራ ኪስንና ስሜትን ለሚጎዱት ቁሳዊም ሆነ ሞራላዊ ጉዳቶች ሊከፈል እንደሚገባው ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖቪች “The Ethiopian Law of Compensation for Damage” በተሰኘው ጽሁፋቸው የሰጡት ማብራሪያ ለዚህ ማሳያ ይሆናል። ውል በተዋዋዮች መካከል ሕግ ነውና ካልተፈጸመ የራሱ ውጤቶች አሉት።
አንዱ ተዋዋይ ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ የበኩሉን ግዴታ ለተወጣው ወይም ለመወጣት ዝግጁ ለሆነው ለሌላኛው ተዋዋይ ውሉን አስገድዶየማስፈጸም፤ ውሉን የመሰረዝ እንዲሁም ውሉ ባለመፈጸሙ ምክንያት ለሚደርሰው ጉዳት ኪሳራ የማስከፈል መብት ሕግ ያጎናጽፈዋል። ስለሆነም የጉዳት ኪሳራ የውል አለመፈጸም ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ ነው ማለት ነው።
እዚህ ላይ “የሚከፈለው ኪሳራ ምን ያክል ነው? መለኪያውስ ምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ኪሳራው ውሉ በተቀመጠው ጊዜና አኳኋን ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ተጎጂው ሊያገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም የሚያሟላና የሚያካክስም ሊሆን እንደሚገባው ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ “የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ-ሐሳቦች” በሚል ባሰናዱት መጽሃፋቸው የሰጡት ሐተታ ለጥያቄው አጥጋቢ ምላሽ ይሆናል።
በውል ግዴታ ውስጥ የጉዳት ኪሳራ የሚመዘነው የተጎጂው ኢኮኖሚያዊ አቅምና ውሉ በአግባቡ ቢፈጸም ኖሮ ሰውየው ሊገኝበት ይችል የነበረው ኢኖኮሚያዊ አቋም እየተገናዘበ ሊሆን ይገባዋል። እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ታዲያ ተጎጂው ማስረዳት የሚጠበቅበት የውሉን በአግባቡ አለመፈጸም ብቻ ሳይሆን በዚህም የተነሳ የደረሰበትንና በእርግጠኝነት ሊደርስበት የሚችለውን የጥቅም መቋረጥ ነው። የጉዳት ኪሳራ አጠያየቅን መሰረተ-ሃሳብ የሚያስቀምጠው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1790 እንደሚያመለክተው የኪሳራ ጥያቄ ከላይ ከዘረዘርናቸው የውል አለመፈጸም ውጤቶች (ማለትም ውሉ በግዴታ እንዲፈጸም ወይም እንዲሰረዝ) ጋር ተጣምሮ ሊቀርብ ይችላል።
ሕጉ ይህን መብት የሰጠው ተዋዋይ የኪሳራውን ጥያቄ ተዓማኒ ለማድረግ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን፤ ኪሳራውም የደረሰው በባለዕዳው ውል አለመፈጸም ምክንያት መሆኑን እንዲሁም ኪሳራውና የሌላኛው ወገን ውል አለመፈጸም ቅርብና ቀጥተኛ የሆነ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት እንዳላቸው ማስረዳት እንደሚገባው ነው ፕሮፌሰር ጥላሁን በተጠቀሰው መጽሃፋቸው የሚያብራሩት።
ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል
ባልንጀራዬና ሆቴሉ አለመግባባታቸውን በመስማማት ከቋጩት እሰየው። አይበለውና ግን ካልተስማሙ ውጤቱ ግልጽ ነው – የሰርግ ሥነ-ሥርዓቱ በሆቴሉ አይከናወንም። ምክንያቱም የኮሮና ስርጭት ከዕለት ዕለት አስከፊነቱ እየጨመረ ነው፤ መንግስትም በሽታውን ለመከላከል የሰዎችን ከቦታ ቦታ መዘዋወርና መሰባሰብ አግዷል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ሰርጉ አይከናወንም። ሰርጉ ካልተከናወነ እንደውሉ ባለመፈጸሙ ምክንያት በመካከላቸው የሚፈጠረው አለመግባባት ወደ ሙግት ማምራቱ አይቀርም። ሆቴሉ “እንደውሉ ባለመፈጸሙ ጉዳት ደርሶብኛል፤ ውሉ ቢፈጸም ኖሮ ላገኝ የምችለው ጥቅም ይከፈለኝ፤ ኪሳራም ይቆረጥልኝ” ይላል። ባልንጀራዬም የራሱን መሟገቻዎች ይደረድራል። የሆነው ሆኖ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በወደቁ ውሎች ተዋዋዮች ልብ ሊሏቸው የሚገቡ ሕጋዊ ነጥቦች አሉ።
የጉዳት ኪሳራ እንዲከፍል ክስ የቀረበበት ተዋዋይ ስለተከሰሰ ብቻ ይከፍላል ማለት አይደለም። ይልቁንም በተከሰሰ ጊዜ እሱም በፋንታው ሊያነሳቸው የሚገቡ መከራከሪያዎች እንዳሉት ልብ ይሏል። “ግዴታውን ፈጽሜያለሁ”፤ “ግዴታው አይመለከተኝም”፤ “የደረሰ ጉዳት የለም”፤ “ግዴታው እንዳይፈጸም ያደረገው ራሱ ከሳሹ ነው” አልያም “ጉዳት ቢደርስም ተጠያቂነት የለብኝም” ሲል ይከራከራል።
ከእነዚህ ውስጥ በፍርድ ቤቶችም ሆነ በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ዓይነተኛ ዓውደ-ክርክር የሚፈጥረው “ጉዳት ቢደርስም ተጠያቂነት የለብኝም” የሚለው መከራከሪያ ነው። ይህንን መከራከሪያ የሚያነሳ ሰው ውሉን በአግባቡ አለመፈጸሙን ያምናል። በከሳሹ ላይ ጉዳት መድረሱንም እንዲሁ።
ነገር ግን ለጉዳቱ እሱ ተጠያቂነት እንደሌለበት ነው ሽንጡን ገትሮ የሚሞግተው። እነዚህን እርስ በእርስ የሚጣረሱ መከራከሪያዎች ማቅረብ ሕጋዊ ድጋፍ አለው። ከሕጉ ቁጥር 1791 እንደምንረዳው የተከሳሹ አንደኛው የመሟገቻ ነጥብ የውል ግዴታውን ያልፈጸመበት በቂ ምክንያት ያለው መሆኑን መግለጽ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህ ምክንያትም ከአቅሙ በላይ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።
እነዚህን ሁለት መከራከሪያዎች በአግባቡ ካቀረበ ውሉን አለመፈጸሙ ከሚያመጣበት የኪሳራ አላፊነት ይድናል። እዚህ ክርክር ውስጥ መሰረታዊው ጉዳይ “ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል” የሚለው ነው (የፈረንሳይን ሕግ አርዓያ አድርጎየተቀረጸው የእኛው ሕግ “Force Majeure” ይለዋል)።
ይህ መከራከሪያ በተለያዩ አገራት ሕጎች የተለያየ መለኪያዎች የተቀመጡለት ሲሆን፤ በሕግ ልሂቃን ዘንድም እንዲሁ የአመለካከት ልዩነት የሚስተናገድበት አከራካሪ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። የአገራችን ሕግ “የተፈጠረው ችግር ከባለዕዳው (ከተከሳሹ) ተግባር ጋር ከማይዛመድ ባዕድ ከሆነ ምክንያት የመነጨ እንዲሁም ችግሩ እጅግ ከባድና በባለዕዳው አቅም በምንም አኳኋን ሊመለስ የማይሞከር መሆኑ” ከሚለው የ‹‹ሲቪል ሎው›› አመክንዮ እና “ከፈጣሪ ሥራ ጋር ይዛመዳል” ከሚሉት የ‹‹ኮመን ሎው›› አስተምህሮዎች በተጨለፈ መልኩ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይልን ደንግጎት እናነባለን።
በሕጉ አነጋገር ተከሳሹን ከኪሳራ ከፋይነት ነጻ የሚያደርግ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል አጋጥሟል የሚባለው “ባላሰበው ነገር ድንገት ደራሽ ሆኖበት ግዴታውን እንዳይፈጽም ፍጹም መሰናክል በሆነ ዓይነት የሚያግደው ነገር ባጋጠመው ጊዜ ነው።” ከዚህ የምንረዳው ከአቅም በላይ የሆነውና ሊመልሱት የማይቻል ነው የሚባለው ባለዕዳው ያላሰበው ነገር ነው።
ይህም ድንገት ደርሶበት የተከሰተና የውል ግዴታውንም እንዳይፈጽም ፍጹም መሰናክል የፈጠረበት ነው። በዚህም መነሻ ተከሳሹ “እርግጥ ነው እንደውሉ አልፈጸምኩም፤ በከሳሼ ላይም ጉዳት ደርሶበታል። ይሁንና ተጠያቂነት የለብኝም። ምክንያቱም እንዲህ እንዲህ ያለ ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ስላጋጠመኝ ነው።” በማለት እንዲሟገት ሕጉ መከራከሪያውን አስቀምጦለታል።
ከአቅም በላይ ኃይል አጋጥሟል የሚያሰኙ ምክንያቶች
ከአቅም በላይ ኃይል አጋጥሟል የሚያሰኙ ምክንያቶችን መዘርዘር አስቸጋሪ ቢሆንም ሕጋችን ዓይነተኛ ናቸው የሚላቸውን በጥቂቱ ለመዘርዘር ሞክሯል። የመጀመሪያው ባለዕዳው አላፊ የማይሆንበት ያልታሰበና በሌላ ሰው ላይም የሚመጣ ድንገት ደራሽ ነገር (ለምሳሌ ዝርፊያ) ነው።
ውሉ እንዳይፈጸም ከመንግስት የሚደረግ ክልከላ (ለምሳሌ ኮሮናን ለመከላከል መንግስት የወሰደው እርምጃ፤ ዕቃ ከውጭ እዳይገባ ከታገደ) ሁለተኛው ምክንያት ነው። እንደ መሬት መናወጽ፣ መብረቅ፣ ማዕበልና ይህን የመሰለ ፍጥረታዊ መቅሰፍት፤ ጦርነት እንዲሁም የባለዕዳው መሞት ወይም ባልታሰበ ሁኔታ የሚደርስበት ከባድ አደጋ ወይም ጽኑ ሕመም ከአቅም በላይ ኃይል አጋጥሟል ያሰኛሉ።
ሕጉ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል አለመኖሩን የማያሳዩ ሁኔታዎችንም አስቀምጧል። እነዚህም የተዋዋዮቹ ሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ፤ የተዋዋዮቹ ፋብሪካ ወይም መስሪያ ቤት መዘጋት፤ የዕቃዎች ዋጋ መወደድ ወይም መርከስ እንዲሁም የባለዕዳውን ግዴታ የሚያከብድ አዲስ ሕግ መውጣት ናቸው። እነዚህን ምክንያቶች አንስቶ መከራከር ከኪሳራ ከፋይነት አያድንም።
ይሁንና ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ሊሆኑ አይችሉም በሚል ሕጉ እነዚህን ሁኔታዎች ቢያስቀምጥም ተዋዋዮቹ ግና እነዚህ ምክንያቶች ቢያጋጥሙ ባለዕዳው ኪሳራ የመክፈል ግዴታ እንደማይኖርበት በውላቸው ውስጥ ማስፈር ይችላሉ። “ግልጽ የሆነ ተቃራኒ የውል ቃል ከሌለ በቀር” የሚለው የሕጉ አነጋገርም ከላይ የተዘረዘሩትን ምክንያቶች ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ብሎ መሰየም የተዋዋዮች መብት መሆኑን ያመላክታል። “ሰራተኞች አድማ መትተው ምርት ማምረት ባይቻል ሌላኛው ወገን ኪሳራ ላይጠይቅ ተስማምቷል” የሚል የውል ቃል መጨመር ይችላሉ። ካላሰፈሩ ግን ተከሳሽ ጥፋት ኖረውም አልኖረውም ኪሳራ ከፋይ ነው።
የተከሳሽን ጥፋት
የማሳየት ግዴታ ከላይ እንዳብራራሁት በውል ውስጥ በግልጽ ካልሰፈረ በቀር በሕጉ ከአቅም በላይ ያልሆኑት ምክንያቶች (ስራ ማቆም፣ መዘጋት፣ የዋጋ መለዋወጥ…) ቢከሰቱም እንኳ ተከሳሽ ጥፋት ኖረበትም አልኖረበትም ኪሳራ ይከፍላል። ይሁንና በአንዳንድ ሁኔታዎች ከሳሹ የተከሳሹን ጥፋት የማሳየት ግዴታ ተጥሎበታል።
ሕጉ “ጥፋት” ለሚለው መለኪያ/ትርጓሜ አላስቀመጠለትም። ይህንንም ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖቪች “Formation and Effects of Contracts in Ethiopian Law” በተሰኘው መጽሃፋቸው ተችተውታል። በተለይ “ጥፋት” ከውል ውጭ በሆነ ተጠያቂነት ረገድ በሕጉትርጉም ተሰጥቶት ለውል ተጠያቂነት ግን አለመተርጎሙ እንደሚያስነቅፈው ነው የሚገልጹት። የሆነው ሆኖ ኪሳራ ለማስከፈል ጥፋትን ማሳየት የግድ ከሚሉ ሁኔታዎች የመጀመሪያው የተረጋገጠ ውጤት እንዲገኝ ተገቢ ጥረት ከማድረግ ጋር የተያያዙ ውሎችን ይመለከለታል።
የማድረግ ግዴታን የተመለከቱ ውሎች በአንድ በኩል አንድን የተረጋገጠ ውጤት ለማስገኘት አልያም ውጤቱ እንዲገኝ ተገቢውን ጥረት ለማድረግ እንደሚቀረጹ ከሕጉ ቁጥር 1712 መረዳት እንችላለን።
ኪሳራ ለማስከፈል የተከሳሹን ጥፋት ማሳየት ግዴታ የሚሆንባቸው ውሎች ታዲያ ውጤት ለማስገኘት የሚደረጉት ሳይሆኑ ውጤቱ እንዲገኝ ጥረት ከማድረግ ጋር የተያያዙት ናቸው። በእነዚህ ውሎች ኪሳራ ለመጠየቅ ወሳኙ ጉዳይ የውጤቱ አለመገኘት ሳይሆን ተከሳሹ የሚጠበቅበትን ጥረት ባለማድረግ ጥፋት መፈጸሙን ማሳየት ነው። ሐኪሙ ሙያው የሚጠይቀውን ትጋት ሁሉ አድርጎ ሕመምተኛውን ለማዳን ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ታካሚው ባይድን ወይም ቢሞት አልያም ጠበቃው የሚፈለግበትን ሁሉ አድርጎ ሙግቱን ባይረታ እነዚህ ሁለቱም ባለሙያዎች የገቡት የውል ግዴታ ውጤት ለማስገኘት የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ስለሆነ ውጤቱ አልተገኘምና ኪሳራ ክፈሉ ሊባሉ አይገባም። የሚፈለግባቸውን ባለማድረግ ጥፋት ከፈጸሙና ይህንንም ማሳየት ከተቻለ ግን ኪሳራ ከፋዮች ናቸው።
ኪሳራ ለማስከፈል ጥፋትን ማስረዳት የግድ ነው የሚባልበት ሁለተኛው ሁኔታ በሕጉ ቁጥር 1796 የተመለከተው ነው። ይኸውም ተነጻጻሪ ግዴታ በሌለባቸው ውሎች (መብት ለአንደኛው፣ ግዴታን ለሌላው የሚሰጡ እንደ አደራ ዓይነት ውሎች) ሊከሰት የሚችል አጋጣሚ ነው።
ውሉ ባልተፈጸመ ጊዜ ተከሳሽ ኪሳራ ሊከፍል የሚገባው ከባድ ጥፋት ፈጽሞ ከሆነ ነው። በአደራ የተቀበለው ዕቃ ቢበላሽ የአደራውን ውል ባለመፈጸሙ ኪሳራ ሊከፍል አይገደድም። ይልቁንም ከሳሽ የአደራ ተቀባዩን ከባድ ጥፋት ማሳየት አለበት፡ “ከባድ ጥፋት ምንድን ነው?” የሚለው በሕጉ የተመለከተ ባይሆንም ለዳኞች ሕሊና የተተወ ነው።
ማስታወቂያ መስጠት ብልህነት ነው
ከአቅም በላይ ኃይል አጋጥሞኛል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርብ ተከሳሽ ከአቅም በላይ የሆነውን ሁኔታ ወዲያውኑ (ችግሩ እንደደረሰ) ለሌላው ተዋዋይ የማስታወቅ ግዴታ አለበት። ይህንን በማድረግም ግዴታውን እንዳይፈጽም የሚከለክለውን ምክንያት ሌላው ተዋዋይ እንዲያውቅለት ያደርጋል ማለት ነው። የዚህ ግዴታ መሰረታዊ አመክንዮ ደግሞ ተዋዋዩ ስለችግሩ በጊዜው ማስታወቂያ ሲደርሰው ጉዳት እንዳይደርስበት ከወዲሁ የራሱን ጥረት ያደርጋል የሚል ስለመሆኑ የፍትሐብሔር ሕጋችን ያመላክታል።
የእኔም ባልንጀራ ያደረገውም ይህንኑ ነው። በአጠቃላይ ከኮሮና ጋር ተያይዞ በውሎች አፈጻጸም ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ ወይም ውሎቹ ባለመፈጸማቸው ምክንያት የሚፈጠረውን ከባድ ኪሳራ ለመቀነስ ተዋዋዮች አንድም በመስማማት ውሉን ማሻሻል አልያም ውልን ቀሪ በማድረግ ተነጻጻሪ ግዴታዎቻቸውን ማስቀረት ይጠበቅባቸዋል።
ካልተስማሙ ግን የኪሳራ ክርክርና “ከአቅም በላይ ምክንያት” የሚባለው ክርክር መነሳቱ አይቀርም። ውሉን ቀሪ ለማድረግ ከተስማሙ ውሉ በተደረገበትና ቀሪ በሆነበት ጊዜ መካከል ሁሉ የተከናወኑትን ተግባራት እንደማይነኳቸው ማወቅ ይገባቸዋል።
ይልቁንም ውል ቀሪ ሲደረግ እንደ ፈራሽ ወይም ዋጋ አልባ ውሎች ከቶውንም እንዳልተደረገ አይቆጠርም። የተከናወኑትን ተግባራት አጽንቶ የግራ ቀኙን የወደፊት ግዴታዎች የማስቀረት ውጤት አለው እንጂ። ከዚህ ሌላ ውሉ ቀሪ ሲሆን የሶስተኛ ወገኖችን መብት መንካት የለበትም። ሶስተኛ ወገኖች ውሉ ከተደረገ በኋላ በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመግባት መብት አግኝተው ሊሆን ይችላል።
ወይም የውሉ ባህርይ ከተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ በተጨማሪ ሌሎች ወገኖችንም መብት ጠያቂና ግዴታ ፈጻሚ ሊያደረግጋቸው ይችላል። ስለሆነም ተዋዋዮች ውላቸውን ቀሪ በሚያደርጉበት ወቅት የሶስተኛ ወገኖችንም መብት ከግምት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል። በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 302012
በገብረክርስቶስ