ሰሞኑን ሁለት የፈረንሳይ የሕክምና ተመራማሪዎች በፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተዘጋጀ የክርክር መድረክ ላይ ቀርበው በአውሮፓና በአውስትራሊያ ስለሚደረግ የክትባት ሙከራ ሲወያዩ «የኮቪድ-19 ክትባት በአፍሪካውያን ላይ መሞከር አለበት» የሚል ሃሳብ ሰነዘሩ፡፡ ይህ ንግግራቸው በሰው ልጆች እኩልነት በሚያምኑና እንደ ሰብዓዊ ፍጡር መልካምን ከሚያስቡ አካላት የመረረ ተቃውሞን አስከትሏል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም «አፍሪካ ለማንኛውም ክትባት መሞከሪያ አትሆንም፣ መሆንም የለባትም፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሳይንቲስት እንዲህ ዓይነት አስተያየት መስማት የተዋረደና አሳፋሪ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገርን በማንኛውም ሁኔታ እናወግዛለን። እናም የማረጋግጥላችሁ ነገር ይህ በጭራሽ አይሆንም» ብለዋል። ይህ የሐኪሞቹ አስተያየት ነቀፌታን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ አፍሪካውያንን «የቤተ ሙከራ መሞከሪያ» አድርጎ የማሰብ አካል እንደሆነም ተቆጥሯል።
የኮሮና ቫይረስ ከቻይና መነሳቱ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በጣሊያን፣ በስፔይን፣ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝና በአሜሪካ ከፍተኛ የሕዝብ እልቂትን አስከትሏል፡፡ ይህ ጽሑፍ እየተጻፈ ባለበት ወቅት እንኳ በአሜሪካ 8,358፣ በጣሊያን 15,889 በስፔይን 12,418፣ በፈረንሳይ 8,064፣ በእንግሊዝ 4,934፣ በኢራን 3,603፣ በጀርመን 1,434፣ በኢትዮጵያ 2 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
ታዲያ በዚህ የቁጥር መረጃ በብዛት እያጠቃቸው ያለው እነርሱን ሆኖ ሳለ የፈውስ መድኃኒቱን በአፍሪካውያን ላይ እንሞክር ከማለት በራሳቸው ቢሞክሩት ውጤቱን በቅርቡ ለማወቅ ይረዳቸው አልነበረምን። ተመራማሪዎቹ በአፍሪካውያን ላይ የሰነዘሩትን አስተያየት እንዲሁ በቀላሉ እንደ አፍ ወለምታ ወስዶ ማለፉ ብቻ ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ይህ ንግግራቸው የተወለደው ከዘረኝነት መርዝ ነውና። ንግግራቸው አሁን አሁን በተለይም በአውሮፓ እየተስፋፋ የመጣው ጥቁሮችን የማግለልና የመናቅ ነጸብራቅም ነው።
ዘረኝነት ቆሻሻ ተግባር ነውና ተጸየፉት እንደሚለው ሃይማኖታዊ ቃልም ይህ ተግባር ዘር እና ቀለም ሳይለይ በሁሉም የዓለም ሕዝቦች ዘንድ በጽኑ ሊወገዝ ይገባዋልም። ከዚህ በፊትም በተለይም በአውሮፓ የስፖርት መድረኮች በጥቁር ዜጎች ላይ ሲደረግ የነበረው የዘረኝነት ተግባር ምን ያህል የከፋ እንደነበር በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ጥቁርም ሆነ ነጭ የሰው ልጅ በሰውነቱ ሁሉም እኩል እና ክቡር ነው።
ይሁንና በጥላቻ የታወሩና አስተሳሰባቸው ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ እጅጉን በወረዱ ሰዎችና ቡድኖች ይህን መሰል የወረደ አስተሳሰብ ሲቀነቀን መታየቱ እጅጉን ያሳፍራል። የዘረኝነት ክፉ መርዝ ዓለማችንን ብዙ ዋጋ ከማሰከፈሉም በላይ በሕዝቦች መልካም ግንኙነት ላይ የሚያሳርፈው አሉታዊ አሻራ አብሮ በሰላም የመኖር እሴትን በእጅጉ ይሸረሽራል።
ከሰሞኑ እየታየ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ዘር እና ቀለም ሳይለይ ሁሉን እያጠቃ መሆኑም የሰው ልጆች በመከባበርና መፋቀር መርህ በአንድነት ካልቆሙ ህልውናቸው ፈተና ውስጥ መሆኑን ያመለክታል። ዓለም ሁሉ ያለምንም መከፋፈል እና ልዩነት በአንድነት ሆኖ የጋራ ጠላቱ የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ መመከት በሚገባው በዚህ ወቅት በሕክምና ተመራማሪዎቹ የተሰነዘረው ዘረኛ አመለካከት በዓለም ሕዝቦች ላይ የተቃጣ እጅግ አደገኛና ከፋፋይ አደጋ በመሆኑ ደግሞ ደጋግሞ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2012