በፈተና ውስጥ አበረታች ለውጥ ያሳየው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ

የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው ኢንዱስትሪው ባለበት የእድገት ደረጃና ለኢንዱስትሪ ባለው ምቹ ሁኔታ ስለመሆኑ ይገለጻል። አንዳንድ ሀገሮች ያደጉ ሀገራት ተብለው የተለዩት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ልቀው በመገኘታቸውና ከራሳቸውም አልፈው የዓለምን ገበያ መቆጣጠር በመቻላቸው ነው።

ኢትዮጵያ የዚህን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ሚና በሚገባ ተገንዝባ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ መሥራት ከጀመረች ቆይታለች፡፡ ይህ ትኩረቷ ኢኮኖሚዋን ከግብር መር ወደ ኢንዱስትሪ እስከ ማሸጋገር ያዘለቀ ነው፡፡

ሀገሪቱ ይህን ያህል ትኩረት ሰጥታ መሥራት ውስጥ ስትገባም ብዙ ነገሮችን ታሳቢ አድርጋለች፡፡ ከእነዚህም መካከል ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ ካላቸው ሀገሮች አንዷ መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ የሰው ኃይል፣ ጥሬ እቃ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለባሕር በር ያላት ቅርበትና ሀገሪቱ በዘርፉ ለሚሰማሩ የፈጠረቻቸው የሕግና የመሳሰሉት ማሕቀፎች በኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶችና ሀገሮች ምቹ እንድትሆን የሚያደርጉ ናቸው።

ምቹ ሁኔታዎቹን ተከትሎ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እየተሠማሩ ይገኛሉ፡፡ ሀገሪቱ የውጭ ባለሀብቶች ይዘዋቸው የሚመጡት ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ካፒታል ይዘው ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ ለባለሀብቶቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠሯን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ይህን ተከትሎም በዘርፉ የሚሰማራው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ ይገኛል፡፡

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩም እንዲሁ በየጊዜው የተለያዩ ማበረታቻዎችን ስታደርግ ቆይታለች፤ ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ ክፍት ተደርገው የኖሩትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ክፍት አድርጋለች፡፡ ይህን ተከትሎም ባለሀብቶቹ ወደ ፓርኮቹ እየገቡ ናቸው፡፡

ሀገሪቱ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ግብርና መር የሆነውን ምጣኔ ሀብቷን ኢንዱስትሪ መር ለማድረግ ብትሠራም፣ ይህን የመዋቅር ሽግግር ማምጣት ደረጃ አልተደረሰም፡፡ ለኢንዱስትሪ ያላትን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ተጠቅማ የምትፈልገውን ለውጥ ላለማምጣቷ በምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የዘርፉ ችግሮች አሉ።

ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በቦታ አቅርቦት፣ እንደ ኤሌክትሪክ ያሉ መሠረተ ልማቶች አቅርቦት፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የሥራ ባሕል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር ዘርፉን ተብትበው የያዙ ችግሮች ሆነው ቆይተዋል። የውጭ ምንዛሬ፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ እጥረት፣ የጸጥታ ችግር፣ የገበያ እጦት የመሳሰሉትም ሌሎች የዘርፉ ችግሮች ናቸው፡፡

እነዚህ ችግሮች ኢንዱስትሪዎች በማምረት አቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የማህበረሰቡ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምትም ሌላው ተግዳሮት ነው ማለት ይቻላል፡፡

መንግሥት ቀደም ሲል አንስቶ አሁንም ድረስ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ ይገኛል፡፡ የቦታ፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችን መሠረተ ልማት ጭምር የተሟላላቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና መንደሮችን በመገንባት በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ምቹ አድርጓል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚሉትም ሌሎች ለዘርፉ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉም በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ በየዓመቱ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ዘርፉ በቀጣይም ውጤታማ እንደሚሆን እያመለከተ ይገኛል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ዓባይ እንደተናገሩት ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሻሻልና በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። ከዚህ ውስጥም የንቅናቄ፣ የሪፎርም ሥራዎች እና የፖሊሲና አሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች መደረጋቸውን በአብነት ይጠቅሳሉ።

እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፣ ለዘርፉ ማነቆ ከሆኑ ችግሮች መካከልም የሎጅስቲክስ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሰላም ችግርና የግብዓት አቅርቦት ውስንነት መኖራቸው ይታወቃል። የኤሌክትሪክ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስ፣ ከስም ንብረትና ከይዞታ፣ ከብድርና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን መንግሥት በዘርፉ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ትላልቅ ውሳኔዎች ማሳለፉን ተከትሎ በፈተና ውስጥ የሚገኘው ይህ ዘርፍ የስኬታማነት ምልክት ማሳየት የቻለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ እንደ ሀገር ከተላለፉት ትላልቅ ውሳኔዎች መካከልም የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የግብርና፣ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ይገኙበታል፡፡ ሌላው ለአምራች ዘርፉ አጋዥ የሆኑና ከዲጂታላይዜሽን ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች እንዲሁም፣ ለአምራች ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ያለው ከሎጅስቲክ ጋር ተያይዞ ያለው አገልግሎት የላቀ እንዲሆን ተደርጓል።

የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያስችል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ ማድረግ መጀመሩን አቶ ጥላሁን ጠቅሰው፣ በዚህም ዘርቱ ተቋማዊ አቅም እንዲኖረው የሚያስችል በስድስት ክላስተሮች የተደራጁ 35 ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ያቀፈ አደረጃጀት መፈጠሩን ይጠቁማሉ።

አቶ ጥላሁን እንዳብራሩት፣ በተለይም አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከዚህ በፊት ለወጪ ምርቶች ብቻ ይሰጥ የነበረው ትኩረት ለተኪ ምርቶች እንዲሰጥ ተደርጎ ተዘጋጀቷል። በዚህም በ2016 በጀት ዓመት በተኪ ምርት ሁለት ነጥብ 31 ቢሊዮን ዶላር ለማዳን ታቅዶ ሁለት ነጥብ 844 ቢሊዮን ዶላር በማዳን ውጤታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

ከዚህ ውስጥ እንደ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ አንድ ነጥብ 49 ቢሊዮን ዶላር የያዙት ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዙት ምርቶች ናቸው። በኬሚካል 832 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር፤ በማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ 96 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር፤ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች 320 ሚሊዮን ዶላር፤ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 104 ሚሊዮን ዶላር፤ በየደረጃቸው የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

በሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ እንደነበረው ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰው፣ የአምራች ኢንዱስትሪው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ በተሠሩ የለውጥ ሥራዎች የዘርፉ ዓመታዊ ዕድገት ወደ 10 ነጥብ አንድ በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለም አቶ ጥላሁን ይገልጻሉ። በቀጣይ 10 ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። አሁን ያለውን 59 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ ።

በተኪ ምርቶች እንቅስቃሴ ውጤት እንዲመዘገብ በመንግሥት በኩል የተወሰዱት ርምጃዎች ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙ አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ የሀገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም አኳያ ክፍተት በመኖሩ የመንግሥት ተቋማት ቅድሚያ የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል። በቀጣይ በአመለካከት ረገድ በግለሰብ ደረጃ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የዘርፉን ችግሮች መፍታት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሻሻልና በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ይገልጻሉ፤ የፖሊሲና አሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች ከእነዚህ ውስጥ እንደሚገኙበት ተናግረዋል። ለአምራች ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ያለው ከሎጀስቲክ ጋር የተያያዘው አገልግሎት የላቀ እንዲሆን መደረጉን አመልክተዋል።

የፋይናንስ አቅርቦቱን በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ የለውጥ ሥራዎች በብሔራዊ ባንክ በኩል መሥራታቸውን ገልጸው፣ “ቀደም ሲል የማምረት አቅማችን ዝቅ ያለ ነበር። አሁን ላይ ከፍ ብሏል። በሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የነበረው የገበያ ድርሻ ዝቅ ያለ ነበር። ይህንንም ከፍ ለማድረግ ተችሏል። እነዚህ በሙሉ ተደምረው የአምራች ኢንዱስትሪዎች ዓመታዊ ዕድገት ወደ 10 ነጥብ አንድ በመቶ ከፍ እንዲል አስችለዋል” ሲሉም አብራርተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም በየጊዜው የሚታዩትን የዘርፉን ማነቆዎች በአፋጣኝ ለመፍታት መሠራቱን አቶ መላኩም ጠቅሰዋል፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በተቀናጀና በተናበበ መንገድ የዘርፉን ችግሮች በጥናት በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጠ የሚሠራ የአሠራር መዋቅር ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ አማራጭ ሆኖ ታይቷል ብለዋል። መንግሥት ይህን ታሳቢ በማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀው፣ በብሔራዊ አምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ በኩል በዘርፉ ችግሮች ላይ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የሚሠራበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ መላኩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በካውንስሉ መፈታት አለባቸው ተብለው የተቀመጡትና መፍትሔ እያገኙ የመጡ ጉዳዮች አሉ፤ የኤሌክትሪክ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስ፣ ከስም ንብረትና ከይዞታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ከብድርና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ተለይተዋል። በካውንስሉ በኩልም በችግሮቹ ላይ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ተደርጓል፤ ይህን ተከትሎም ችግሮች የቀነሱበት ሁኔታ ታይቷል። የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። አንዳንዶቹ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ምርታቸውን ከ20 በመቶ በላይ ማሳደግ ችለዋልም።

አቶ መላኩ፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም በየጊዜው የሚታዩትን የዘርፉን ማነቆዎች በአፋጣኝ ለመፍታት መንግሥት በቁርጠኝነት ይሠራል ሲሉ ገልጸው፣ ካውንስሉ የፋብሪካዎቹ አሠራር እንዲሻሻል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ በየትኛውም ሀገር የኢንዱስትሪውን እድገት ከሚወስኑት መካከል ለዘርፉ የተቀመጠው ፖሊሲ ውጤታማነት ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝ ይታወቃል። ኢትዮጵያም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ምን ማሳካት እንዳለበት በግልጽ በፖሊሲ አስቀምጣ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ሊያሠራ የሚችል ፖሊሲ በመቀመጡ በተግዳሮቶች ውስጥም እየታለፈ አበረታች ውጤት ለማስመዝገብ የተቻለው፡፡

ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ በዚህ ዓመት አስራ ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት ይጠበቃል። ከዚህም በየዘርፉ ስንመለከት ማኑፋክቸሪንግ አስራ ሁለት በመቶ እንዲሁም ከኮንስትራክሽን አስራ ሁለት ነጥብ ሶስት በመቶ እድገት ይጠበቃል። ኢንዱስትሪው በዚህ ዓመት ከፍተኛ እድገት እንደሚያመጣ የተጠበቀበት ዋነኛው ምክንያት ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመሩ ሥራዎች የሚጨበጥ ፍሬ እንደሚያመጡ የሚጠበቅ በመሆኑ ነው፡፡

በጥቅሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በፖሊሲ ደረጃ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ይታወቃል። ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ለዘመናት ተቀዛቅዞ የኖረውን የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማነቃቃት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ይነሳል። በዚህም በፈተና ውስጥ ሆኖ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ስኬት ፈክቶ መታየት ችሏል። ይህ እንደ ትልቅ ስኬት እንደሚታይ ጠቅሰው፤ አሁንም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ በአስተማማኝነት ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ ማስገንዘባቸው ይታወቃል።

በዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት የዘርፉን ችግሮች ማለትም የኤሌክትሪክ፣ የፋይናንስ የውጭ ምንዛሬ ችግሮችንና እና የግብዓት እጥረትን መፍታት ይገባል። ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ መቀጠል፤ ተኪ ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል:: ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሳብ እና ያሉትን በማጠናከር የሥራ እድል ፈጠራውን በሚጠበቀው ደረጃ የማሳደግና የአገልግሎት አሠጣጥን ማዘመን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል እንላለን።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You