ተቋሙ ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በ18ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሰብሎችን እያለማ ነው

– ለዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ ነው

አዲስ አበባ ፡- በድንገት የሚከሰቱ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲያስችለው በ18ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሰብሎችን እያለማ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ አስታወቀ:: ለዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለመስጠትም እየሠራ መሆኑን ገለጸ::

የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ሞገስ ኤዳኢ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ፤ ተቋሙ በክልሉ ለሚከሰቱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችለው በተለያዩ አካባቢዎች በ18ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሰብሎችን እያመረተ ይገኛል::

የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አጠቃላይ 43ሺ ሄክታር መሬት የማረስ እቅድ እንዳለው የገለጹት አቶ ሞገስ፤ ከዚህ ውስጥ 24 ሺህ ሄክታሩን የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ራሱን ችሎ ለማልማት እየተንቀሳቀሰ እንዳለና ቀሪው በወረዳ ደረጃ በሚገኙ የተቋሙ ቢሮዎች በኩል እንደሚለማ አስረድተዋል::

በዘንድሮው ዓመት አጠቃላይ በ18ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ እስከ አሁንም አምስት ሺህ ኩንታል ምርት እንደተሰበሰበ ፤ በቀጣይም የሚሰበሰቡ ምርቶች እንዳሉ ገልጸዋል::

እንደሀገር ከተያዘው አቅጣጫ አንጻር መርሃ-ግብሩን ከግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት የከተማ እና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት በጋራ የሚያካሂዱት እንደሆነም ተናግረዋል::

በሌላ በኩል የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ በዘንድሮው ዓመት በ15 ቢሊዮን ብር ዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አቶ ሞገስ ተናግረዋል፤ ከታረሰው መሬት 8 ሺህ ሄክታሩ ለተማሪዎች ምገባ የሚውል ስለመሆኑም አመላክተዋል::

እርሻው ዘግይቶ የተጀመረ መሆኑን ተከትሎ ምገባውን በእርሻ ገቢ ብቻ መሸፈን አይቻልም ያሉት አቶ ሞገስ ፤ ተቋሙ ተጨማሪ ሀብት በማሰባሰብ እቅዱን ለማሳካት እየጣረ ስለመሆኑ አስረድተዋል:: እስከ አሁንም የእቅዱን 50 በመቶ አሳክቷል ብለዋል::

የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ 26 ሚሊዮን አባላትን እንዳፈራ ተናግረው፤ ከአባላት መዋጮ እና ሀብት በማሰባሰብ ሂደት የሚገኘው ገንዘብ ለተቸገሩ ወገኖች የማድረስ፤ ተማሪዎችን የመመገብ እና ሕዝቡም እርስ በእርሱ እንዲደጋገፍ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል::

በአንዳንድ ወረዳዎች ትርፍ የእርሻ መሬት አለመኖር፣ የዝናብ እጥረት መከሰትና እና ግጭቶች መኖራቸው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ ለማልማት ተግዳሮት እንደሆኑባቸው ተናግረዋል::

አስቀድሞ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ፤ ትክክለኛ ተረጂዎችን በመለየት እና በዘንድሮው ምርት ላይ ግምገማ በማድረግ በክልሉ የተረጂዎችን ቁጥር ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወደ 580 መቀነስ እንደተቻለ አቶ ሞገስ አስረድተዋል:: የክልሉ አደጋ መከላከል ቡሳ ጎኖፋ በሚል ስያሜ እንደሚጠራ ይታወቃል::

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You