በኤጀንሲው ከተመዘገበው ልደት 80 በመቶ የጊዜ ገደብ ያለፈባቸው ናቸው

አዲስ አበባ፡- በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ሶስት ወራት ከመዘገበው ከ113 ሺህ በላይ የልደት ምዝገባ 80 በመቶ የሚሆኑት የጊዜ ገደብ ያለፈባቸው ምዝገባ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ጀሚላ ረዲ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ወሳኝ ኩነትን በወቅቱ በማስመዝገብ ረገድ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ከፍተኛ ክፍተት ይታያል። አብዛኛው ሕብረተሰብ ኩነቶቹን በወቅቱ እያስመዘገበ አይደለም ፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞትና ጉዲፈቻ ባጋጠመ በ30 ቀናት ውስጥ ምዝገባው ሲከናወን ወቅታዊ ምዝገባ ይባላል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ሁለት ሺህ 471 ጋብቻ፣ 291 ፍቺ፣ አንድ ሺህ 291 ሞትና 10 ጉዲፈቻ በወቅቱ ተመዝግቧል፡፡

ልደት ህጻኑ ከተወለደ እስከ 90 ቀን ምዝገባው ከተከናወነ ወቅታዊ ምዝገባ ይባላል ያሉት ወይዘሮ ጀሚላ፤ በሩብ ዓመቱ 18 ሺህ 330 ልደት በወቅቱ ምዝገባቸው መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ ከሌሎች አገልግሎቶች አንጻር የልደት ተመዝጋቢ ቁጥሩ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ሆኖ ከተመዘገቡት 16 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ወቅቱን የጠበቀ ምዝገባ ማካሄዳቸውን አመልክተዋል፡፡ ምንም እንኳን ሕብረተሰቡ በሆስፒታሎች አገልግሎቱን ማግኘት የሚችል ቢሆንም፤ በወቅቱ ልደትን ከማስመዝገብ አንጻር ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል፡፡

እንደ ዳሬክተሯ ገለጻ ፤ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞትና ጉዲፈቻ ኩነቱ ካጋጠመ ከ31 ቀን አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ምዝገባው ሲከናወን የዘገየ ምዝገባ ይባላል፡፡ የልደት ምዝገባ ውልደቱ ከ91 ቀን እስከ ዓመት ባለው ጊዜ ሲከናወን የዘገየ ምዝገባ ይሆናል፡፡

እንደ ወይዘሮ ጀሚላ ማብራሪያ፤ ሁሉም ሁነቶች ካጋጠሙ ከዓመት በኋላ ሲመዘገቡ ነባር፤ የጊዜ ገደብ ያለፈበት ምዝገባ ነው፡፡

ኤጀንሲው በሩብ ዓመቱ ከመዘገባቸው ምዝገባዎች ውስጥ 78 በመቶ የጊዜ ገደብ ያለፈበት ምዝገባ ናቸው፡፡

ወቅቱን የጠበቀ ምዝገባ ከማከናወን አንጻር የልደት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ82 በመቶ ብልጫ ሲኖረው፤ የሞትም በተመሳሳይ የ57 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡

ኩነቶችን በወቅቱ ማስመዝገብ ጥቅሙ ለግለሰብም፤ ለሀገርም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ኩነቶችን በወቅቱ ማስመዝገብ ሕብረተሰቡ ካለው ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያግዝ በመሆኑ፤ ሕብረተሰቡ በወቅቱ ኩነቶችን እንዲያስመዘግብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቤዛ እሸቱ

 

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You