ለዩኒቨርሲቲዎች በጀት የሚመደበው በተማሪ ብዛት ሳይሆን ባስመዘገቡት ውጤት ልክ ሊሆን ነው

አዲስ አበባ፡- የዩኒቨርሲቲዎች በጀት ምደባ በተማሪና አስተማሪዎች ብዛት ሳይሆን ባስመዘገቡት ውጤት ልክ እንደሚሆን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴሩ 47 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውጤትን ማዕከል ያደረገ የአፈፃፀም ኮንትራት ስምምነት ትናንት ተፈራረመ ።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የዩኒቨርሲቲዎች የበጀት ምደባ የሚወሰነው ባላቸው የተማሪና መምህራን ብዛት ሳይሆን በሚሠሯቸው ችግር ፈቺ ምርምሮችና በሚያወጧቸው ብቁ ተማሪዎች ይሆናል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደብላቸው በጀት ባስመዘገቡት ውጤት ልክ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ እኩል በጀት የሚመደብበት አሠራር እንደሚቀር አመልክተዋል ።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመሠረታዊነት ለመቀየር የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራትና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ለማውጣት ጥራት ላይ መሥራት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

የትምህርት ዘርፉ ላይ የገጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ተግባራዊ እየተደረገ ለሚገኘው ሪፎርም አካል እንደሆነ በመግለጽ፣ በሀገር የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የዜጎችን ሕይወት እንዲቀይሩ ሁሉም ተቋም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የስምምነቱ ዓላማ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የትምህርት ጥራትን መፍጠር መሆኑን በመግለጽ፣ ተማሪ በተማረበት የትምህርት ዘርፍ እውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ ያለው ዜጋ መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮ ሀገርን ወደፊት ሊወስዱ የሚችሉ ጥራት ያላቸው ምርምሮች ማውጣትና ብቁ ተማሪዎችን ማፍራት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ለማሳካት ጥራት ያለው ትምህርት ለተማሪዎች ማቅረብ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ትስስርንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ተቋማቱ እንደ ሀገር መድረስ የሚፈለገውን እድገት እንዲያግዙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የምንሠራቸው ምርምሮችና የምናስተምራቸው ተማሪዎች የነገዋን ኢትዮጵያ የሚያስቀጥሉ መሆን አለባቸው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ስምምነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትክክለኛ መንገድ የሚሠሩና ተጠያቂነት ያለባቸው እንዲሆኑ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረገው ሪፎርም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፣ የትምህርት ዘርፉም ውጤት በሚያመጡ ሰዎች መመራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው፣ሥራን በውጤት የመለካት ስምምነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤት ላይ መሠረት ያደረገ አሠራርና ዕቅድ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ለትምህርት ጥራትና ምርምር በሚኖራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ የአፈፃፀም ኮንትራት ውል ሥራን ማዕከል ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ ተቋማቱ በኮንትራት ውሉ መሠረት ሥራዎችን እንዲፈጽሙና አፈጻጸማቸውን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ይሆናል ያሉት አቶ ኮራ፣ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚለካ መልኩ እንዲፈጽሙና ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኙ በማሰብ የተደረገ ስምምነት ነው ብለዋል፡፡

የስምምነቱ አተገባበር እቅድን፣ ውጤትና ግምገማን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውጤቱ በዓመት የሚገመገም ሲሆን በቁጥር የሚገለጽ የአፈጻጸም ውጤት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You