አስተናጋጆቻችንን በጨረፍታ

አንድ ወጣት አርሶ አደር እግር ጥሎት ወደ ከተማ መጣ፤ ለከተማው እንግዳ ለሰውም ባዳ ስለሆነ በከተማው ትርምስ እና በሰው ብዛት ተደመመ። ወዲህ ወዲያ ሲል ስለዋለ የሚቀማመስ ፈልጎ ከአላፊ አግዳሚው አንዱን ጠርቶ ጠየቀ። በአቅራቢያው ካሉ ምግብ ቤቶች አንዱን አሳዩት እና ወደዛው አቀና። እንደ ከተማው ሁሉ የሆቴሉ አጠቃላይ ነገር እንግዳ ሆነበት። በሆቴሉ የሚመገበው ሰው ብዛትም ሆነ ሁካታ አስደመመው።

ድንግርግር ማለቱን የተመለከቱ አሳላፊዎች ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ምን እንታዘዝ? ሲሉት ብንን አለ። ከፊቱ የቆሙት አስተናጋጆች በእድሜ የገፉ እና አንዳንዶቹም ሽበት የጎበኛቸው ናቸው። ወጣቱ አርሶ አደር ለከተማው እንግዳ ስለሆነ እና በአደገበት ባሕል ታናሽ እያለ ታላቅ ማስተናገድ ነውር ስለሆነ ነፍሱ ተጨነቀች። ልጅ እግር ካለ ብሎ የቤቱን አሳላፊዎች ማማተር ጀመረ፤ ሆኖም አብዛኞቹ አሳላፊዎች ከእሱ እድሜ የሚልቁ፤ ሰውነታቸው ጠና፣ ዕድሜያቸው ገፋ ያለ ነው።

አሁንም ከፊቱ የቆሙት አስተናጋጅ የምን ልታዘዝ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ሆኖም ወጣቱ አርሶ አደር ሴትዮዋን ማዘዝ ከብዶታል። ሁኔታው ቅጥ የለሽ (ሥርዓት አልባ) ሆነበት። አሳላፊዋ ደግማ ‹‹እኔ አመጣለሁ ንገረኝ›› እያለች ትነዘንዘዋለች። ወጣቱ አርሶ አደር ‹‹ግድ የለም ያለውን ንገሩኝና፤ እኔው ራሴን አስተናግዳለሁ፤ ነውርም አይደል ትልቅ ሰው ማዘዝ ?›› ሲል ቆፍጠን ብሎ ተናገረ።

አስተናጋጅዋ ትልቅ ሰው ማዘዝ ነውር ነው፤ የሚባለውን ንግግር ጆሮዋ ላይ ጭው ሲል እንደ ነውር ሰማችው። የዕድሜ ጉዳይ ስለተነሳባት ተናደደች። በቅጽበት ተስተናጋጁን ከአንቱታ ከፍታ ወደ አንተ ዝቅታ አወረደችው። ተበሳጭታም ‹‹ምን ይላል ይሄ ሞዛዛ! ፈዛዛ! ለዛ ቢስ! ዕድሜ ልትጠይቅ ነው የመጣኸው?›› ብላ ከፍ ዝቅ እያደረገች ‹ስድብ በያይነቱ› ጋበዘችው። ወጣቱ አርሶ አደርም ክው ብሎ ቀረ። እንደ ጤፍ አክብሮ የተመለከታት እንደ ገለባ ቀላ ሲያገኛት ተደናገጠ። ቀልቡ እንደተገፈፈም ሹልክ ብሎ ወጣ።

እንደ መግቢያ የወሰድነው ክስተት ስለ ሻይና ምግብ ቤት አስተናጋጆች ልናነሳ ሽተን ነው። የአስተናጋጅነት ሙያ ትልቅ ክብር የሚሰጠው እና ከሆቴል እና ከምግብ ቤት ገጽታ አልፎ የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ወይም የሚያፈርስ ሙያ ነው። አስተናጋጅነት በፈገግታ፤ በትሕትና እና በመልካም መስተንግዶ የሚገለጽ እና በተስተናጋጆች ላይም መልካም ስሜት የሚፈጥር ከፍተኛ ስብዕናን የሚጠይቅ ሙያ ነው።

የመስተንግዶ ሙያ በውጭው ዓለም የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ቀደም ብሎ በብዙዎች ባሕል ሴቶች በምግብ ዝግጅትና መስተንግዶውን በመያዝ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። የመስተንግዶን ሙያ፤ ፈረንጆቹ ዌይተርስ ይሉታል። ለሙያውም ከፍ ያለ ክብር ይሰጡታል። ሙያው የሚጠይቀውን ሥነምግባር ማሟላት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። አንድ ግለሰብ ወደ ሙያው ለመግባት በቂ ትምህርት ከመውሰዱም ባሻገር በተፈጥሮ ሥነምግባርም ታዛዥ፤ በፈገግታ የተሞላ እና እንክብካቤ የተላበሰ መሆን አለበት።

አንድ ሰው የመስተንግዶ ሙያን ሲመርጥ ከሰዎች ጋር የመግባባት ባሕሪ ያለው እና ታዛዥ መሆን ይጠበቅበታል። እንደ እኛ ሀገር ፊትን እያኮሳተሩ መስተንግዶ መስጠት የሚታሰብ አይደለም። ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯችን እንግዳ ተቀባይ ብንሆንም ዘመናዊውን መስተንግዶ ሳይንስ በአግባቡ የተረዳን ባለመሆኑ ሙያውን ከፍ አድርገን ከራሳችን አልፈን ሀገራችንን መጠቀም አልቻልንም።

ምግብ ቤት መመገብ በሀገራችን ከተጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት ሆነው። ሥራው በሀገራችን በቀደሙት ዘመናት አስተናጋጅ አሳላፊ ይባል ነበር። ምግብ ቤት ባይኖርም፣ ከበርቴዎቹ ሕዝቡን ‹ግብር (ምግብ) ሲያበሉ› አሳላፊዎቹ ለማብላት የሚያስተናግዱ ናቸው። የደስታ ተክለወልድ አማርኛ መዝገበ ቃላት ‹አሳላፊ›ን፤ በድግስ ወይም በግብዣ ላይ የሚያስተናግድ ፣ ቋሚ በሚል ይፈታዋል። የምግብ ቤት የበዛውና፤ አሳላፊም እንጀራ የወጣለት፤ የምግብ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ሲጀምር ነው። ቤቱ ይመገብ የነበረው ውጭ መመገብ ሲጀምር ማለት ነው። ለዘመናትም ምግብ ቤት ገብቶ መመገብ እንደነውር የሚቆጠር እና አለፍ ሲልም እንደቦዘኔ የሚያስቆጥር ስለነበር ለዘርፉ አለማደግም የራሱ ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ወደ ዘመናችን ስንመጣ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች ከሆቴሎች እና ካፍቴሪያዎች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የመስተንግዶ ሙያም በርካታ መሻሻሎች እየታዩበት መጥቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ በዘመናችን የመስተንግዶ ሙያ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል። በሥልጠና ባይሆንም እንደ አንድ ክፍት የሥራ ቦታ በርካቶች ሙያውን እየተቀላቀሉት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በሥልጠና ያልተገራ በመሆኑ በርካታ ክፍተቶች እንዲስተዋሉበት አድርጓል።

በዚህም ምክንያት አሳላፊዎች ሲያስተናግዱ የተለያዩ ፀባይ ያሳያሉ። ተስተናጋጅ ካስተናገዱ በኋላ ገንዘብ (መልስ) ሰጥተው፤ መልሰው እጅ እጅ ማየት ይታይባቸዋል። አንዳንዶቹ ፀዓዳ ለብሰው የሰው እጅ ሲጠብቁ ስታዩ፤ ምፅዋት እየጠበቁ ይመስላሉ። አንዳንዴም ተስተናግደው ከፍለው መልስ ሲጠብቁ፤ ዝም ይላሉ። ‹‹ለትልቅ ሰው መልስ አይሰጥም›› የሚል ምግባር ይሆን ?

አንዳንዴ ለተስተናጋጁ የሚሰጠውን መልስ የረሱ፣ የዘነጉ ወይም የሰጡ መስሎ መታየትም አለ። ገሚሶቹ ሆን ብሎ የሚሰጥን መልስን መዘንጋት ታዩባቸዋላችሁ። ከፊታችሁ ቀርበው መልስህ/ሽ ስንት ነው ብለው ጠይቀው ሲያበቁ፤ በፊታችሁ የተወሰነ ገንዘብ አውጥተው የቀረውን ጥቂት ብር እጃቸው ላይ የሌለ መስሎ መታየትና አቻዎቻቸውን አንዴ ብር ስጠ(ጪ)ኝ ብሎ መጠየቅ የተለመደ ነው። ለባልደረቦቻቸውም ብር እጅሽ ላይ ካለ አበድሪኝ ብሎ በተስተናጋጁ ፊት መጠየቅ በተመጋቢው አልያም በተገልጋዩ ብሩን (መልሱን)‹‹ በቃ ተይው/ተወው›› እንዲባሉ ማለት ነው። አስተናጋጅ እጅ እጅ ሲል ያልነውም በሚያበሳጭ መስተንግዶ ከበላተኛ ‹ቲፕ› ፍለጋ እጅ ማየት ስለሚያበዙ ነው። ምግቡ እጅ እጅ አለ ማለት ተበላሸ እንደሚባለው፤ አስተናጋጁ እጅ እጅ ሲል ስንል በሌላ ፍቺ አስተናጋጁ ያልተገባ ባሕሪ እያሳየ አሰልቺ ሆኗል ማለት ነው።

መልስ የረሱ መስለው መታየት የሚጥሩም ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል። ተስተናግደው መልስ ሲኖርዎት ብር አጉድለው መልሱን ሰጥተው፤ ሌላ ሰው ለማስተናገድ በሚመስል መልኩ ይሄዳሉ። እርስዎ መልሱን ሲቀበሉ ሲቆጥሩ የተወሰነ ብር እንደ እንደጎደለ ይረዳሉ። መልሱ ልክ አይደለም ብለው ሲጠይቁ፤ እንዴት ብለው ጠይቀው ያልተረዱ የተሳሳቱ በመምሰል፤ አዎ ይቅርታ ሊሉና ቀሪውን ብር ሊመልሱ ይችላሉ። በአንድ ምግብ ቤት ቁርስ በልቼ 200 ብር ሰጥቼ ቸኩዬ መልስ ስጠብቅ፤ 25 ብር መልስ ተሰጠኝ፤ ቆይቼ መልሱን ሳየው 125 ብር መሆን የሚገባው፤ 100 ብር ተቀንሶ ተሰጥቶኛል ያለኝ አንድ ወዳጄ ያወራኝ ትዝ አለኝ። ያው በወቅቱ ድፍን ሁለት መቶ ብርም ለሕዝቡ እንግዳ ስለነበር ብዙዎች ‹ይሸወዱ ›ነበረ።

እንደ ግሮሰሪ ባሉ መጠጥ ቤቶች አስተናጋጅ ሴት ጭንና ባት፣ ጡትና እምብርት ማሳየት ተጨማሪ ተልዕኮ ነው። የመጠጥ ቤቶቹ ተጨማሪ ገቢ ፍለጋ ነው። ራሳቸውን እየሸጡ በሚያስተናግዱት ቤት ከጠጪው ጋር የሚያድሩ ናቸው። በምሽት ቦታዎች የሚያስተናግዱ መቼም ቀጥታ ‹ሥራቸውም› ስለሆነ አንገረምም። በቀንም በእነዚህ ዓይነት ቤት የሚሠሩት ከተስተናጋጁ በየጊዜው የሚሰጣቸው ‹ቲፕ› ጉርሻ ሴትነታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ የሚገፋፉ ናቸው። ይህ ድርጊትም ቀስ በቀስም በምሽት እንደሚገቡት ሴቶች የመሆን ዕድላቸውን የሰፋ ያደርገዋል። እዚህ ላይ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተወሰደውን ሕጋዊ ርምጃ ሳልጠቅስ አላልፍም። በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተናጋጆቻቸውን ‹‹የተራቆተ›› ልብስ የሚያስለብሱ ከሆነ ጠበቅ ያለ ቅጣት የሚጠብቃቸው ይሆናል።

በከተማዋ የባሕል፤ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀው ይኸው ሕግ አስተናጋጆች ሰውነታቸውን የሚያጋልጥ ልብስ እንዳይለብሱ፤ በሚታይ የሰውነት አካል ላይ ንቅሳት እንዳይኖራቸው እንዲሁም ወንዶች ጆሮ ጌጥ አድርገው እንዳያስተናግዱ የሚከለክል ነው። በተለይም እንደሥጋ ቤቶች ባሉ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ባልተገባ መልኩ የነበረውን አለባበስ ያስቀራል ተብሎ የሚታመንበት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለመዝናናት ወጣ ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩትም ሰዎች እየጠጡ ሲሄዱ እና ሞቅ ያላቸው ሲመስል ለአስተናጋጆች ሠርግ እና ምላሽ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፋ ነው። በዚህ ወቅት ያልተጠቀሙበትን ሂሳብ መጠየቅ እና ማወናበድ የተለመደ ነው። ስለዚህም አስተናጋጆች ሙያቸውን ላልተገባ ነገር በመጠቀም የተገልጋዩን ገንዘብ ወደ ኪሳቸው የሚያስገቡባቸው አጋጣሚዎች የሰፋ ነው።

በየትም ቦታ በተስተናጋጅ መስተንግዶ የረካ ሰው ጉርሻ የሚባለውን ቲፕ ይሰጣል። አንዳንድ አስተናጋጆች በጭቅጭቅ በብስጭት ጭምር አስተናግዷችሁ ከእናንተ ጉርሻ የሚጠብቅ አለ። ጉርሻ የሚሰጠው ሰው በመስተንግዶው መርካቱን ለመግለጽ እና አስተናጋጁን ለማበረታታት ነው። አንዳንዱ በጭቅጭቅ ውሃ ስላመጣላችሁ ብቻ ቲፕ ይፈልጋል። አንዳንዱ አስተናጋጅ አዛችሁት ስትጠብቁ ሲቆይባችሁና ስታስታውሱት መታዘዙን እንደረሳው አውቃችሁ ድጋሚ ታዛላችሁ። አንዳንዱ መጠጥ ምግቡን አምጥቶ፤ ድጋሚ ልታዙት ስትፈልጉት ታጡታላችሁ። በሚሰጣችሁ ምላሽ (ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃላት) እያዘዛችሁ ሊመስላችሁ ይችላል።

ተስተናጋጅ በክፍያና በሒሳብ ለመታለል የማይችሉት በብዛት የሚጠቀሙትን መጠጥና ምግብ በተጨማሪ ዕሴት ታክስ መሠረት የሚከፍሉ ሲሆን ነው። አስተናጋጆቹ ያልበሉበትንም ያልጠጡበትንም ጨምሮ ለማስከፈል አይፈልግም፤ ቢፈልግም አይችልም። ገንዘቡ ለመጠጥ/ምግብ ቤቱ ከሆነ የማጭበርበር ፍላጎቱ አናሳ ነው። አንዳንድ ምግብና መጠጥ ቤቶች ደግሞ ተገልጋዩን ከነተጨማሪ ዕሴት ታክስ አስከፍለው ደረሰኝ የማይሰጡ አሉ። በዚህ ላይ ክትትል እየተደረገ እርምጃ ቢወሰድ ሸጋ ነው።

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You