በትንኝ የሚተላለፈው ቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተ ነው

በአሜሪካ በትንኝ የሚተላለፈው እና መድኃኒት የሌለው ቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኤችአይቪ ቫይረስን በመታገል ነው ስማቸውን የተከሉት። ቀጥሎ ደግሞ በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ብዙ ጥረዋል፤ ግረዋል። አሜሪካዊው ዶክተር አንተኒ ፋውቺ። ነገር ግን አንተኒ ፋውቺን አዲስ በሽታ ለሆስፒታል አልጋ ዳርጓቸው እንደነበር ተነግሯል።

የ83 ዓመቱ ዶክተር ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እንዲሁም ድካም ይሰማቸው ጀመር። ለካ ዌስት ናይል የተባለው ቫይረስ ይዟቸው ኖሯል። ይህ ቫይረስ በትንኝ የሚተላለፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1930ዎቹ ኡጋንዳ ውስጥ የተገኘ በሽታ መሆኑ ታውቋል።

ነገር ግን ፋውቺ ቫይረሱ ያገኛቸው ወደ ምሥራቅ አፍሪካ መጥተው ሳይሆን ጓሮ አትክልት ሲኮተኩቱ ቫይረሱን ይዛ በምትንቀሳቀስ ትንኝ በመነደፋቸው ምክንያት ነው። የአሜሪካ የበሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል የሆነው ሲዲሲ ለቢቢሲ በላከው መረጃ መሠረት በየዓመቱ ከሁለት ሺህ በላይ አሜሪካውያን በዚህ ቫይረስ ይያዛሉ፤ 1200 የሚሆኑት ደግሞ ለሕይወት አስጊ ለሆነ በሽታ ይጋለጣል፤ 120 ሰዎች ይሞታሉ።

በአትላንታ፣ ጆርጂያ ኤሞሪ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የዌስት ናይል ቫይረስን ሲያጠኑ የቆዩት ክሪስቲ መሪ “ማንኛውም ሰው ሊያዝ ይችላል” ይላሉ።

“አንዲት ትንኝ ነደፈችን ማለት በበሽታው ልንያዝ እንችላለን ማለት ነው። ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ በጣም አደጋ ላይ የሚወድቁት በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቢሆኑም ወጣቶችም ይያዛሉ” ይላሉ። ዌስት ናይል ቫይረስ በአውሮፓውያኑ 1999 ነው ወደ ምዕራቡ ዓለም የገባው። ለመጀመሪያ ጊዜ ኒውዮርክ ከተማ የታየው ቫይረስ በወቅቱ 8200 ሰዎች በክሎ ነበር።

ቫይረሱ ለዘመናት በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በደቡባዊ አውሮፓ እና በሩሲያ ሲዛመት ነው የቆየው። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ግን አይታወቅም። ነገር ግን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ቫይረሱ ምናልባትም በአእዋፍ አማካኝነት ተዛምቶ ሊሆን ይችላል። ትንኞች ቫይረሱን ከታማሚ ወፍ ያገኙት እና ወደ ሰው ያስተላልፉታል።

በ1999 (እአአ) ከታየው የመጀመሪያው ወረርሽኝ ወዲህ 59 ሺህ ሰዎች ሲያዙ 2900 ገደማው ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል። አንዳንዶች ትክክለኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው። አሁን በሽታው እንደ አስጊ ያደረገው ምክንያት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቫይረሱ የመሠራጨት አቅሙ ሊጨምር ይችላል መባሉ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሞቃታማ የሚባሉ ሥፍራዎች ለትንኝ መራባት የተመቹ ናቸው። በስፔን ከ4 ዓመታት በፊት በሽታው በድንገት ተሰራጭቶ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በቫይረሱ ከተያዙ አምስት ሰዎች መካከል አንድ ሰው መካከለኛ የሚባል ምልክት ያሳያል። በሽታው በጣም ሲከፋ ለአካል ጉዳት ሊያጋልጥ ይችላል። ከ150 ሰዎች በአንድ ሰው ላይ ቫይረሱ ወደ ጭንቅላት ሊያመራ ይችላል፤ አልፎም የማዕከላዊ ነርቭ ሥርዓትን በመጉዳት ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ላይ የመጣል አቅም አለው ሲሉ አመልክተዋል።

በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ እና የመከላከል አቅማቸው የደከመ፤ አሊያም የስኳር ህመም እና የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች እጅግ ተጋላጭ ናቸው። በዌስት ናይል ቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለዓመታት ያጠኑት ፕሮፌሰር ክሪስቲ መሪ እንደሚሉት ቫይረሱ የጭንቅላት ጉዳትን ያስከትላል።

ምንም እንኳ በሽታው እንዲህ አስጊ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ክትባትም ሆነ በበሽታው የሚሰቃዩ ሰዎችን ለማከም የሚረዳ መድኃኒት የለውም። “በጣም የተረሳ በሽታ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሯ። እሳቸው እንደሚሉት በበሽታው የተያዙ ሰዎች አግኝተዋቸው “ምን ላድርግ?” ብለው ሲጠይቋቸው ምላሽ የላቸውም። ይህ ልባቸውን ይሰብረዋል ነው ያሉት።

በጣም የሚገርመው በዌስት ናይል ቫይረስ የተያዙ ፈረሶች የሚከተቡት ክትባት ከተመረተ 20 ዓመታት ያለፉት መሆኑ ነው። ከአውሮፓውያኑ 2004 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ዘጠኝ ክትባቶች ለክሊኒካዊ ሙከራ ቢበቁም አንዱም የመጨረሻው ሙከራ ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ይገለጻል።

ደረጃ 3 ክሊኒካል ሙከራ የሚባለው ክትባት ለገበያ ከመብቃቱ በፊት ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚለውን የሚመልስ ሙከራ ነው። ባለሙያዎች በሽታው እስካሁን ክትባት ያልተገኘለት ገበያ ላይ ቢቀርብ ትርፍ አያመጣም የሚል እሳቤ በመድኃኒት አምራቾች ዘንድ ስላለ ነው ይላሉ።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች ቢያንስ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ እና በቫይረሱ ከተጠቁ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ ሰዎች የሚወስዱት ክትባት መመረት አለበት ሲሉ ይከራከራሉ። ቫይረሱ እያደረሰ ያለው ጉዳት በተለይ ደግሞ በነርቭ ሥርዓት ላይ የሚያስከትለው ችግር ግልፅ ሆኖ ሳለ መፍትሔ አለመገኘቱ በርካታ ተመራማሪዎችን እያስገረመ ያለ ክስተት መሆኑ ተገልጿል።

አጥኚዎች የክትባት ሙከራው መደረግ ያለበት በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የቫይረሱ መነሻ በመሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ነው ብለው ያስባሉ። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት እና የግል ኩባንያዎች አብረው መሥራት ይኖርባቸዋል ተብሏል።

ክሪስቲ መሪ አሁን በፍጥነት የሚያስፈልገው ክትባት ሳይሆን በቫይረሱ ተይዘው ለሚሰቃዩ ሰዎች ማስታገሻ የሚሆን እንዲሁም ቫይረሱ ወደ ጭንቅላት እንዳይስፋፋ የሚያደርግ መድኃኒት ማቅረብ ነው። ዌስት ናይል ቫይረስን ለመግታት የትኛው መድኃኒት ነው አስፈላጊው የሚለውን ለማወቅ በርካታ ጥናቶች መሠራት አለባቸው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You